Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow ሰዎች የስሜት የጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ!
ሰዎች የስሜት የጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ! Print E-mail
Sunday, 17 February 2008
በአቤል ደስታ

ከአንድ ዓመት በፊት ልክ በዚህ በበጋው ወራት (ከታህሳስ 26 እስከ መጋቢት 25 ቀን ድረስ ያለውና ፀሐይና ድርቅ የሚበዛበት የሚባለው ወቅት በጋ ይባላል) በወይዘሪት ካሚላት መኸዲን ላይ የደረሰው አሰቃቂ አደጋ ዜናውን የሰማው ሕዝብ ሁሉ አስደንጋጭ መርዶና መራር ሀዘን ነበር፡፡
 ብርቱ ቁጭት ያስከተለ ብሔራዊ ሐዘን መሆን የቻለ አደጋም ነበር፡፡ ታህሳስ 28 ቀን 1999 ዓ.ም የደረሰው ይህ አሰቃቂ አደጋ የግል ተበዳይዋ ወይም የወንጀሉ ድርጊት ሰለባዋ ወደ ፈረንሳይ አገር ለሕክምና ከሄደች በኋላም ጭምር ባለው ጊዜ ውስጥ የሰው መነጋገሪያ የአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም የዜና አገልግሎት ድርጅቶችና ጋዜጦች ሌሎችም የመገናኛ ብዙሃን ልዩ የዜናና የዘገባ ርዕሰ ጉዳይ ነበር፡፡

ከዥንዋ እስከ ሮይተርስ ከዋሽንግተን ፖስት እስከ ቢቢሲ ወርልድ ያሉ ልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙሃን ዜናውን የዘገቡትና በመላው ዓለም ያስተጋቡት ካሚላት ላይ የደረሰውን ድንጋጤ ጭምር በመግለጽ ነበር፡፡ አገራችን ውስጥ ጉዳዩ ምን ያህል እንደተዘገበ የቱን ያህል ዜና እንደነበር ማሳየት ይቻል ከሆነ በዚህ ጉዳይ አንደኛ ተከሳሽ ሆኖ ፍርድ ቤት ቀርቦ እስካለፈው ጥር 21 ቀን 2000 ዓ.ም ድረስ ክሱ ሲታይ የቆየው ደምሰው ዘሪሁን የመከላከያ (የሰነድ) ማስረጃ አድርጎ ያቀረባቸው ስድስቱ (ከሰባት ውስጥ) ከመጋቢት እስከ ነሐሴ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የወጡ የተለያዩ መጽሄቶችን ነው፡፡

ይህ ጉዳይ ምን ያህል ወሬውን የሰማውን የእያንዳንዱን ግለሰብ ቤተሰብ ስሜት እንዳሸበረ እንደሚገባውና እንደሆነው መግለጽ በጣም ያዳግታል፡፡ እንዲያውም በደፈናውና እንደተለመደው “ቃላት ያጥሩኛል” ብሎ ማለፍን ያልወደድኩትና ያልፈለግሁት ይህ የተለመደ፣ ሁሉም ያለ “ኮፒ ራይት” እና ያለ “የደረጃዎች መለኪያ” የሚጠቀምበት አባባል በውስጤ የሚተናነቀኝን ነገር ግን በቃላት እገልፀው ዘንድ ያልተቻለኝን ስሜት ይበልጥ ተራ ያደርግብኛል፣ ያዳፍንብኛል ከሚል ፍርሃትና ስጋት የተነሳ ነው፡፡

ስለዚህም እንደማንኛውም የተቸገረ ሰው ስሜቴን የእኔን ብቻ ሳይሆን የሌላውንና የሁሉንም ስሜት ይገልጽልን ከሆነ እንደ “ገጠመኝ”ም እንደ ምሳሌም ሊያገለግል የሚችል አንድ ጉዳይ ላንሳ፡፡ ሼኽ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስምና ዝና የማያውቅ የለም፡፡ ያንኑ ያህል ችሮታቸውን ልግስናቸውን አባመስጠትነታቸውን አላውቅም የሚል ተፈልጎ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም ሰውየው ይበልጥ የሚታወቁት ከሁሉም በላይ በዚሁ ነው፡፡ አዝማሪው የሚመርቅበት፣ ባለመንዙማው በተመሳሳይ ለሰውም ለራሱም “ዱዓ” የሚያደርግበት ግጥም ሳይቀር የሰውየውን አባመስጠትነት የህዝብ የእምነት ድጋፍ እንዲያገኝ ያደረገ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሰውየው እንደሰሚ ታቦት እና ወይም እንደ “ለይለታል ቀድር” በየቤቱ በየግለሰቡ ምኞት ውስጥ ድረሱልኝ ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡

የሰውየውን የህይወት ታሪክ በተለይም ልግስና የሚያሳየውን ዶክመንተሪ ፊልም አይቼዋለሁ፡፡ በዚያ ውስጥ የተካተቱትን አላሙዲ ለክፉ ቀን የደረሱላቸውንና ከዚህም ለየት ባለ ደግሞ ድንገትም ሆነ ባጋጣሚ የዋሉላቸውን ልዩ ልዩ መልክና ገጽታ ያላቸውን የሰዎች ዝርዝር አይቻለሁ፡፡ በጥር ወር 1999 ዓ.ም አንድ ቅዳሜ ምሽት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የታየውና የተነበበው ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ከውጭ አገር ሆነው አገር ውስጥ በሚገኝ ተወካያቸው አማካኝነት የላኩት ደብዳቤ፣ በደብዳቤውም አማካኝነት የገቡት ውለታን ግን የሚመስልና የሚወዳደር የለም፡፡ በእኔ እምነት ምናልባት አንጀቴና አዕምሮዬ ቢጣሉ ተጣልተውም እኔጋ ለዳኝነት ቢቀርቡ አዕምሮዬ ምንም “ዕቃ” የለውም ብዬ የምፈርድበት አንድ የማይቀየር የማይለወጥ አንድ የማምንበት ከልብ የመነጨ ጉዳይ አለ፡፡ ይህም አላሙዲ ካሚላትን አሳክማለሁ ያሉበትን ቃልና በዚህም መሰረት እየፈፀሙ ያሉትን ተግባር የሚመስል፡፡ ከዚህም በፊት የቀደመ ከዚህም በኋላ የሚከተል ምንም አይነት ችሮታ ውለታ ልግስናና እርዳታ የለም ባይ ነኝ፡፡

ይህንን ሁሉም ቢያንስ ቢያንስ አብዛኛው ይጋራዋል ያምንበታል ብዬ የምወራረድበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ይህንንስ ስሜት ምን አመጣው? ብለን እንጠይቅ፡፡ የካሚላትን ከሌላውም የትኛውም እያንዳንዱና በድምር ደግሞ ከሁሉም ይበልጥ ሆኖ የተሰማኝ የበለጠብኝና እንደ ማንኛውም ዜናውን የሰማው ሰው ለገዛ ራሴ ለራሴ ቤተሰብ ለማውቀው፣ ለምወደውና ለምዛመደው ሰው እንደተደረገ ውለታ አድርጌ የቆጠርኩበት ምክንያት ምንድን ነው? የገንዘቡ መጠን አይደለም፡፡ ይህን የመሰለ ልግስና በዓይነቱ የመጀመሪያው ስለሆነ አይደለም፡፡ በጭራሽ የመጀመሪያውም አይደለም፡፡ እውነቱን ለመናገር እጅግ በጣም ብዙዎቻችን ካሚላት ያገኘችውን ዕድል የሼሁ የመጀመሪያ ደንበኛና ትክክለኛ ምስጋናው፣ ወረታው እግዜር ደጅ የሚደርስ ስለመሆኑ “ሰማያዊ ኢንሹራንስ”ና ዋስትና ያለው ውለታ ብለነዋል፡፡

በካሚላት መኸዲን ላይ የደረሰውን አደጋ ጣሯን ስቃይዋን የወደፊት የህክምናና የህይወት እጣፈንታዋን የገዛ ራሳችን አድርገን የወሰድነው፣ ይህን በመሰለ ወቅት ውስጥ የሚነገርለትና አለ የሚባል ደስታ ካለ በሼሁ ፈጥኖ ደራሽነት ላይ ሲበዛ የተደሰትነው እራሷን ካሚላትንና ቤተሰቦቿን ሆነን ነው፡፡

ለምንድነው ግን እንዲህ የሆንነው? የካሚላት መኸዲን ጉዳት በ1999 ዓ.ም የሔርሜላ ወሰንየለህ ነገር በ1993 ዓ.ም ወሬውን የሰማውንና ያወቀው ሰው ሁሉ ጉዳይና ጥቃት የሆነው ለምንድ ነው? ብቸኛዎቹ ሰዎች ስለሆኑ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታገሰው፣ ያጋጥማል ብሎ ከሚጠብቀው በላይ ይህን የመሰለ ግፍ ጥቃት ሰቆቃና መከራ ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው በመሆኑ አይደለም የእያንዳንዱ የፖሊስ ጣቢያ የዕለት ሁኔታ መዝገብ የሚያውቀው እያንዳንዱ ቤት የሚቆጠረው ከዚህ የባሰ፣ ወይም ከዚህ እኩል የሚዘገንን አለዚያም በጭራሽ የማይተናነስ ጥቃት ለአገራችን አዲስና እንግዳ ባዳና የተለየ ገጠመኝ ሆኖ አይደለም፡፡ የፖሊስ የዕለት ሁኔታ መዝገብ የሚያውቃቸው ብቻ ሳይሆኑ የማያውቃቸው (በተለይ የካሚላት ጉዳይ ተጨማሪ ግንጥል ዘርፍ ሆኖ፣ ጎድን ተብሎ ተንቆ ተደባብሶ እየቀረ እንጂ) አላውቅም የሚላቸው በህዝብ ህይወት ድቅድቅ ጨለማ (ዳርክ ፊገር) አሀዝ ውስጥ ተውጠው የቀሩ የኢትዮጵያን የወንጀል ድርጊት ጥቃት ሰለባዎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ናቸው፡፡ የካሚላትን ጉዳይ ልዩ ያደረገው ካሚላት በተሻለ አንፃራዊ ሁኔታ እንደ ሔርሜላ “የታደለች” የተሻለች የወንጀል ድርጊት ሰለባና የግል ተበዳይ በመሆኗ ነው፡፡ ይህንን “እድል” ታገኝ ዘንድ ካሚላት እና ሔርሜላ ከኢትዮጵያም ሆነ ከአዲስ አበባ ሰፊ ተጠቂ ህዝብ መካከል “እጣው ወጥቶላት” ከቤተሰብና ከወዳጅ ዘመድ የሆድ ውስጥ ሙሾና የብቸኝነት ሀዘን ወጥታ የጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ እንድትገባ ጥቃቱም ብሔራዊ ጥቃት እንዲሆን ብዙ ጉዳዩች አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ሚዲያው ጉዳዬ ያለው መሆኑ አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያም “መንግሥት” በተለያየ ቅርጽና መልኩ ፊቱን ያላዞረበት መሆኑ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ የካሚላትን ጉዳይ አደባባይ ያወጣው የመጀመሪያው ሚዲያ ከአዲስ አበባ ክልል ወጥቶ ሌላ ቦታ የማይሰማው የአዲስ አበባ መስተዳድር ቴሌቪዥን መሆኑ የመደበኛውን የኢትዮጵያ የዜና አገልግሎት ድርጅቶችና የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን የዜና ማዕረግ ለማግኘት አነሰም በዛም ጊዜ የወሰደ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

የሔርሜላ ጉዳይ ደግሞ ከዚህ የተለየ “መስተንግዶ” አጋጥሞት የነበረ ስለመሆኑ ለብዙው ሰው የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡ አለዚያም ከጊዜ ጋር ተረስቷል ተዘንግቷል፡፡ የፍትህ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን ነሐሴ 17 ቀን 1993 ዓ.ም ላይ ያገደው ማህበሩ ከተመዘገበበትና ከተቋቋመበት ዓላማ ውጭ ወጥቶ ያለስራው ገብቶ ተንቀሳቅሷል ብሎ መግለጫ ያወጣበት በሔርሜላ ጉዳይ ምክንያት ነው፡፡ እስከ ጥቅምት 7 ቀን 1994 ዓ.ም ለዘለቀው እገዳ፣ ከላይ ለተጠቀሰው የፍትህ ሚኒስቴር ክስና ወቀሳ መነሻና ምክንያቱ ደግሞ ማህበሩ ፍትህ ሚኒስቴር (እንደ አቃቤ ህግነቱ በዚህ ጉዳይ ሥራውን አልሰራም ወዘተ.) በማለቱ ነው፡፡

የካሚላትና የሔርሜላ ጉዳይ ነገሩን በደሉን ጥቃቱን የሰማው ህዝብ በገዛ ራሱ ጉዳይ እንደሆነ ያደረገው ሌላም ከዚህ ቀደም ሲል ከተጠቀሰው ሰፋ እና ከፍ ያለ ምክንያት አለ፡፡ ይህም በመንግሥት አገር የመንግስት መሰረታዊና የጥንት የጠዋቱ ዋነኛ ተግባርና ግዴታ ወንጀል መከላከል መሆኑ የት ቦታና በየትኛውም የመንግሥት አይነት ቁልፍ ጉዳይ በሆነበት ሁኔታ ሌላው ቢቀር “ውሎ መግባት እንኳን ጤና ላይሆን ነው ወይ?..” የሚለው የህዝብ ስሜት ነው፡፡ ይህን ስሜት እንደሌላው ስሜት፣ የካሚላትንና የሔርሜላን ጥቃትና ህመም እንደገዛ ራሱ ህመም አብሮ ታሞ፣ አብሮ እንደመግለጽ ህዝቡ ግልጽ አድርጎ ማውጣት ማስተጋባት ያልቻለበት፣ ያላወቀበት፣ ያልሆነበት ምክንያት አለ፡፡ ባህሉ አላደረገውም፤ ባህሉ እንዲያደርገው የሚያበረታታው አድርጎት ቢገኝ አበጀህ ብሎ ዋስትና የሚሰጠው የተቋምና የህግ ከለላ የለውም፡፡

ይልቁንም በካሚላት እና በሔርሜላም ጉዳይ እንዳየነው አጋጣሚው ያለወትሮውና ያለፍጥርጥሩ አደባባይ እንዲወጣ ህዝብ ውስጥ ገብቶ እንደነገሩም ቢሆን ኃይልና አቅም ያገኘው ይህ የህዝብ ስሜት በሌላ አካል፣ በሌላ ኃይል ይጠለፋል፣ ይማረካል፡፡ ቁጣውና መራር ሀዘኑ ዓላማውን ይስትና በአንድ ጊዜ (ዜጋም ባልሆነ ሰብዓዊ ፍጡር) ላይ የደረሰ የሰብዓዊ መብት ረገጣንና ገፈፋን ለማረምና ለመታደግ የሚወሰድ እርምጃ በሌላ ሰብዓዊ መብትና ነፃነት ላይ (ያልታሰበም፣ ያልታቀደም ሊሆን ይችላል) ሌላ ተመሳሳይ አደጋ ያደርሳል፡፡

የአርሲዋ የአበራሽ በቀለ ጉዳይ በ1990 ዓ.ም አካባቢ የሔርሜላ ወሰንየለህ እና የካሚላት መኸዲን ነገር በ1993 አና በ1999 ዓ.ም ያረጋገጠው ይህንኑ ነው፡፡ በአበራሽ በቀለ ላይ የደረሰው አሰቃቂ አስገድዶ የመድፈር ወንጀል፣ በሔርሜላ ወሰንየለህ ላይ በተደጋጋሚ የደረሰው ጥቃትና ማለቂያ ማብቂያ የሌለው ሆኖ የዘለቀው፣ ከዓመት በፊት ደግሞ በካሚላት መኸዲን ላይ “ድጋሚ” ደርሶ አገርን እንደብራ መብረቅ ያስደነገጠው ጥቃት አስቀድመው የሚከላከሉት የአገር የወንጀል መከላከል መሰረታዊ ግዴታ አለመሆኑ የመጀመሪያው ጥፋት የመጀመሪያው በደል ነው፡፡ የወንጀል ድርጊት የጥቃት ሰላባዎች መብታቸው አለመጠበቁ (ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ) የሚታደጋቸው ህግና ስርዓት የተዋጣለት ሆኖ ሊሰራና ሊያሰራ አለመቻሉ ያንኑ ያህል ሌላው ጥፋት፣ ሁለተኛው ጥቃት ነው፡፡ የካሚላት ጉዳይ ይፋ በሆነበት በመጀመሪያው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሮግራም ስለ ካሚላት ብቻ ሳይሆን ካሚላትን፣ ሔርሜላን በመሰሉ ሌሎች ሚዲያ ውስጥ ባልገቡ ለአደጋ የተጋለጡ መከረኛ ተበዳዮች አንደበት የሰማነው ፖሊስ እነ ካሚላት እንደዚያ እስከሆኑ ድረስ ምናልባትም እንደዚያ ካልሆኑ በስተቀር አቤቱታቸውን የማይሰማ መሆኑን ነው፡፡  ስለሌሎች ጉዳዮች እንድናወራ ሲፈቀድልን የምንነጋገርበት ጉዳይ፣ ክስና ወቀሳ እንደተጠበቀ ሆኖ ለምሳሌ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ሴቶች ማህበር ከተመዘገበበትና ከተቋቋመበት ዓላማ ውጭ ሰራ ተብሎ የተወቀሰበትና የታገደበት የባንክ ሂሳብም እንዳይንቀሳቀስ የተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው? የሔርሜላ ጉዳይ ያንን በመሰለ ሁኔታ ይፋ ከወጣም በኋላ ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ ስራቸውን መስራት አልቻሉም፡፡ የዳኝነቱና የፍትህ ስርዓቱ የግል ተበዳይና የተከሳሽ መብቶችን አጠባበቅ ህግ በሚፈቅደው ሕገመንግስታዊ ስርዓቱ ባመቻቸው አግባብ ሊያስተናግዱት አልቻሉም፣ በመባላቸው ነው፡፡ የዚህ ምላሽ ከ “እሽ አትበሉን የሹም ዶሮ” በላይ ልክና ገደብ አጣ፡፡ የግል ተበዳይን የወንጀል ድርጊት የጥቃት ሰለባን መብት ለማስከበር በሌላው የተከሳሽ መሰረታዊ መብት ላይ ጦር ማወጅና መዝመት እውነትም ትክክለኛው ዘዴና መፍትሄ አይደለም፡፡ እየሆነ ያለው አለዚያም ሆነ እየተባለ ክስ ሲቀርብበት ወቀሳ ሲነሳበት የህዝብ እምነት “ሲሸፍትበት” የምናየው ከዚህ መነሻነት ነው፡፡

የአበራሽ በቀለ ጉዳይ ከእነ ሔርሜላና ከእና ካሚላት ትንሽ ለየት የሚልበት ምክንያት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈፀመባትን ሰው እራሷ የገደለችው መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በስተቀር አበራሽም (በአገር ውስጥ ካልሆነ በስተቀር) የውጭም ሚዲያ ቦግ አድርጎ ያሳዩትና ያስተዋወቁት ቢቢሲ ልዩ ፕሮግራም ልዩ የዶክሜንታሪ ፊልም የሰራባት ናት፡፡ ካሚላትና ሔርሜላም የሚያስቀና አይደለም፣ በእርግጠኝነት ደግሞ በደላቸውን የሚታደጋቸው ባጠቃላይ ምንም አይነት ተገቢ ነገር አላገኙም እንጂ በተመሳሳይ ሁኔታ ፊልም የሚሰራባቸው የሚሰራላቸው ሆነዋል፡፡

በሔርሜላ ላይ የደረሰው ጥቃትና ግፍ ባለታሪክ የሆነው ግለሰብ ልክ በአበራሽ በቀለ እጅ ሕይወቱ እንዳለፈው ሰው ሞቷል፣ ተገድሏል፡፡ የሞተው ሳይፈረድበት በመንግስት ቁጥጥር ስር እያለና እስረኛ ሆኖ ፍርድ ቤት በቀረበበት አንድ የቀጠሮ ቀን ሊሸሽ ሲል ተገደለ ተብሎ ነው፡፡ ከዚህ በላይ የሚታወቅ ሰውም ሚዲያውም አፍ ውስጥ የገባ ታሪክ የለውም፡፡ የካሚላት ጉዳይ ከመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔና የሞት ቅጣት ፍርድ ገና ብዙ የተጓዘ አይደለም፡፡ እንደ ሁኔታው ወደፊት የምንመለስበት ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ፍትህ በሚገባ ይበየን ዘንድ ግን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድምጽ መስማት ያለበት ሰዎች የወንጀል ድርጊት የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ብቻ ሳይሆን ከዚህ የተነሳም የወንጀል ድርጊት ተከሳሽ (ተጠርጣሪዎች) የህዝብም ስሜት ጭምር ሰለባ እንዳይሆኑ ጭምር ነው፡፡       
 
< Prev   Next >