| ለትምህርት ወደውጭ የሚሄዱ... |
|
|
| Wednesday, 20 February 2008 | |
|
ለትምህርት ወደውጭ የሚሄዱ ተማሪዎች ላልተጠቀሙበት ጉዞ ይከፍላሉ
ለትምህርት ወደ ውጭ ሃገር የሚሄዱ ተማሪዎች ላይመለሱ ይችላሉ፤ በሚል ግምት የደርሶ መልስ ክፍያ እንደሚከፍሉና በትምህርት ላይ መሆናቸውን ማረጋገጫ ቢያቀርቡም ገንዘባቸው እንደማይመለስላቸው ወላጆች ገለፁ፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦች እንደሚሉት ለትምህርት ወደ ውጭ የሚሄዱ ተማሪዎች ክፍያቸው የአንድ ጉዞ ቲኬት መሆን ሲገባው ፣ኢትዮጵያውያን ከሄዱ አይመለሱም፣ በሚል ግምት የደርሶ መልስ እንዲከፍሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ በትምህርት ላይ መሆናቸውን ማረጋገጫ ካመጡ ይመለሳል ቢባልም ማረጋገጫው ሲመጣ ሰበብ እየፈጠሩ ገንዘቡን እንደሚያስቀሩ ተናግረዋል፡፡ ይኸ በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ አሰራር ህጋዊ እንደማይሆን የሚገልፁት ወላጆች አንዳንድ የጉዞ ወኪሎች በዚህ "ህገወጥ" በሚሉት አሠራር መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ተማሪ አማኑኤል አካሉ ለትምህርት ወደ ዩክሬይን ሲሄድ ትኬቱን የገዛበት ታይኮን ትራቭል ኤጀንሲ፤ ኢትዮጵያዊያን ከሄዱ አይመለሱም በሚል ጥርጣሬ የደርሶ መልስ ዋጋ እንዳስከፈሏቸው ቤተሰቦቹ ተናግረዋል፡፡ ታይኮን ትራቭል ሙሉ ትኬቱን ከአስከፈለ በኋላ ወደ ዩክሬን የሄደው ልጃቸው ከሚማርበት ዩኒቨርሲቲ ማረጋገጫ ሲልክ፣ በእጥፍ የተከፈለው ገንዘብ እንዲመለስላቸው ሲጠይቁ ገንዘቡን ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን በቅሬታ ጠቅሰዋል፡፡ በኦገስት 7/2006 15"080 ብር በታይኮን ትራቭል ኤጀንሲ በኩል በተቆረጠ ትኬት ወደ ዩክሬን ከሄደ በኋላ ማረጋገጫውን አቅርበው ገንዘቡ እንዲመለስ ታይኮንን ሲጠይቁ፣ በኢትዮጵያ የዩክሬን ኤምባሲን ሄደው እንዲያነጋግሩ መላካቸውን የሚገልፁት የተማሪ አማኑኤል ቤተሰቦች ኤምባሲው በበኩሉ ስለትኬት ጉዳይ እንደማያገባው ገልፆ እንደመለሳቸው አስረድተዋል፡፡ ቤተሰቦቹ እንደሚሉት ከዩክሬን የኤዱኬሽንና ሳይንስ ሚኒስተር ለትራቭል ኤጀንሲው በቁጥር 132/07፣ የተፃፈ ማረጋገጫ ደብዳቤ አቅርበዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በፃፈው ደብዳቤ ላይ ኪሩቭይ ሮግ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆኖ እየተከታተለ መሆኑን ያመለክታል፡፡ "ነገር ግን" ይላሉ ወላጆቹ፤ "ነገር ግን እኛን ወደ ኤምባሲና በቀነ ቀጠሮ እያዘገዩ ካጓተቱን ከአንድ ዓመት በኋላ ጊዜ ያለፈበት ነው ብለው እንደማይመለስ ነገሩን . . . " "ታይኮን ትራቭል ለኮሚሽን የተከፈለው ተመላሽ እንዳይሆንበት ሲል ከ5,000 ብር በላይ የሚሆን የግለሰቦችን ገንዘብ አለአግባብ እንዲቃጠል በማድረግ በደል ፈፅሞብናል" ሲሉ ወላጆቹ ገልፀዋል፡፡ "ኤጀንቶች በደንበኛውና በአየር መንገዶች መካከል ድልድይ ሆነው ማገልገል ሲገባቸው ጉዞ ያልተደረገበት ክፍያ ያስፈፅማሉ፤ ኢትዮጵያኖች ከሄዱ አይመለሱም የሚል የንቀት ስሜት አላቸው . . . " ይላሉ፡፡ የታይኮን ትራቭል ኤጀንሲ በበኩሉ ሙሉ ጉዞ የሚከፈለው ኢትዮጵያኖች ከሄዱ አይመለሱም ተብሎ መሆኑን ያምናል፡፡ ነገር ግን ማረጋገጫ ከቀረበ ከተከፈለው የደርሶ መልስ ትኬቱ የመመለሻው ለባለቤቱ እንደሚመለስ ይገልፃል፡፡ የታይኮን ትራቭል ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደሚሉት፣ ተማሪዎች በትምህርት ላይ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ከተፃፈ ገንዘቡን እንደሚያስመልሱ ይናገሩና የተማሪ አማኑኤልን ጉዳይ በተመለከተ ማመልከቻው የቀረበላቸው ባለፈው ታህሳስ መሆኑን፣ ይኸም የትኬት ጊዜው ከሚቃጠልበት ነሐሴ ወዲህ በመሆኑ ያልተጠቀመበት ከ5,000 ብር በላይ ሊመለስ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ሥራ እንደሚበዛባቸው በተደጋጋሚ የሚገልፁት የታይኮን ዋና ሥራ አስኪያጅ የአማኑኤል ቤተሰቦች ከነሐሴ በፊት መምጣታቸውንና፣ ኤምባሲው ጠይቁ፣ መባላቸውን እንደማያውቁ ገልፀዋል፡፡ ታይኮን፣ ከዩኩራይን ኤምባሲ ጋር በትኬት ጉዳይ ስምምነት እንዳለው አምነው ይኸም የራሳቸው አሠራር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ኤምባሲና የጉዞ ኤጀንሲው በትኬት ሽያጭ ጉዳይ ስምምነት ማድረግ ለምን እንዳስፈለገ የስምምነቱን ዝርዝር አልገለፁም፡፡ "ገንዘቡ ለደንበኛው ባይመለስ እኛ የምንጠቀመው ነገር የለም፤ ስለዚህ የምንፈልገው ደምበኛችን ገንዘቡ እንዲመለስለት ነው" ይላሉ ሥራ አስኪያጁ፡፡ ከጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |