Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow "ተመድ እንዲህ አይነት ውርደት ደርሶበት አያውቅም"
"ተመድ እንዲህ አይነት ውርደት ደርሶበት አያውቅም" Print E-mail
Wednesday, 20 February 2008
አቶ ዋህድ በላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ

ከኤርትራ ድንበር ወጥቶ በኢትዮጵያ እንዳይሰፍር የተከለከለው የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮ ኤርትራ ሰላም አስከባሪ ጦር (አንሚ) ከፍተኛ ውርደት የደረሰበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ዋህድ በላይ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለጹ፡፡
"በአለም ታሪክ ተመድ እንደዚህ አይነት ውርደት ደርሶበት አያውቅም" ያሉት አቶ ዋህድ ድርጅቱ ቀደም ሲል በኤርትራ ላይ እርምጃ ቢወስድ ኖሮ ይህ ውርደት ሊከሰት እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ቃል አቀባዩ እንደሚሉት የአልጀርሱን ስምምነት በመጣስ የአንሚን እንቅስቃሴ ስትገታ የቆየችው ኤርትራ እርምጃ ስላልተወሰደባት የተመድን ክብር የሚነካ ድርጊት ፈፅማለች፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ምክር ሰምቶ በኤርትራ ላይ እርምጃ ቢወስድ ኖሮ ሁኔታው አሁን ካለበት አስከፊ ደረጃ ላይ እንደማይደርስ የገለጹት ቃል አቀባዩ "በሕግ የማያምን የጫካ መንግሥት" አንድን ትልቅ የሰላም ጠባቂ ሀይል ማገቱ የሚያሳዝን መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አያይዘውም "ለኤርትራ መንግሥት የልብ ልብ ሰጥቶ እዚህ ያደረሰው የፀጥታው ምክር ቤት በመሆኑ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ለማለት አንደፍርም" ብለዋል፡፡

የአልጀርሱን ስምምነት በሚጥስ ወገን ላይ የቅጣት እርምጃ እንደሚወሰድበት በግልጽ መቀመጡን የጠቆሙት አቶ ዋህድ በስምምነቱ መሰረት በኤርትራ ላይ ቅጣት ሊተላለፍ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የተመድ ዋና ጸሀፊ ባን ኪሙን በኢትዮ ኤርትራ በሰፈረው የሰላም አስከባሪ ጦር ላይ ኤርትራ የምትፈጽመው ድርጊት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል፡፡

የነዳጅና የምግብ አቅርቦት ያጣው የአንሚ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመሄድ በጊዜያዊነት ለመቆየት ያደረገው ሙከራ በኤርትራ መንግሥት እገታ ከሽፏል፡፡ የአንሚ መኪና በኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ተይዘው ድንበሩን እንዳይሻገሩ ተከልክለዋል፡፡ የካቲት 6 ቀን 2000 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ለመሻገር የሞከሩ የተመድ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች መሳሪያዎቻቸው በኤርትራ ሰራዊት የተወሰዱባቸው ሲሆን ዛቻም ደርሶባቸዋል፡፡

ለሰላም አስከባሪው ሀይል አስደንጋጭ የሆነበት ዜና ግን ለአንሚ የተለያዩ ምግቦችን ሲያቀርብ የቆየው የኤርትራ የንግድ ኩባንያ ከእንግዲህ በኋላ የተዋዋለውን የኮንትራት ግዴታ ማሟላት እንደማይችል መግለጹ ነው፡፡ ከሰላም አስከባሪው ሀይል የተገኙት ምንጮች እንደሚያመለክቱት ጦሩ በአሁኑ ሰዓት ያለው መጠባበቂያ ምግብ ለጥቂት ቀናት የሚሆን ብቻ ነው፡፡

ከፀጥታው ምክር ቤትና ለኢትዮ ኤርትራ ድንበር የሰላም አስከባሪ ጦር ወታደር ካዋጡት አገሮች ጋር እየተነጋገሩ የሚገኙት የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን የኤርትራ መንግሥት በአንሚ ላይ እየወሰደው ያለውን ተቀባይነት የሌለው እርምጃ እንዲያቆም ጠይቀዋል፡፡

ከኤርትራ ድንበር ወጥቶ በኢትዮጵያ የሚሰፍረው የሰላም አስከባሪ ኃይል በኢትዮጵያ የሚቆየው ለጥቂት ጊዜ መሆኑን ያመለከተው ተመድ ኤርትራ ይህንን አለማቀፋዊ ግዴታ ማሟላት እንዳለባት አሳስቧል፡፡

በኃይሌ ሙሉ
 
< Prev   Next >