Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የተለያዩ አገራት (እንግሊዝ፣ ሆላንድ..... የከበረ
የተለያዩ አገራት (እንግሊዝ፣ ሆላንድ..... የከበረ E-mail
Sunday, 06 January 2008

አቶ ጁነዲን ሣዶ፣
የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር

አቶ ጁነዲን ሣዶን የዛሬው ቆይታ ገጽ እንግዳችን አድርገናቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በድርጅትዎ ውስጥ የተካሄደው ሪፎርም በአግባቡ ተካሂዷል?

አቶ ጁነዲን፡- ጥሩ ሪፎርም ነው፡፡ ጥሩ አካሄድ ተከትሏል፡፡ የተዝረከረኩ አሰራሮችን  ለማስተካከልና ቅልጥፍና ለማምጣት በተቻለ መጠን አምስት መሥሪያ ቤቶች ላይ አካሄደናል፡፡ ከሰኔ ወር 1999 ዓ.ም ጀምሮ በየጊዜው የትግበራ አድማሱ ከፍ እያለ ሄዷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ ሂደት እየገባን ነው፡፡ አንዳንድ ያልተሟሉ መሣሪያዎችም አሉ፡፡ በተለይም በመንገድ ትራንስፖርት መሠረታዊና ጠንካራ ]ö`U ›"H>Å“M TKƒ ÁeÅõ^M::

ሪፖርተር፡- በመንገድ ትራንስፖርት በተለይ ተሰራ የሚሉት ምንድነው? ጉቦ ጠፍቷል?

አቶ ጁነዲን፡- ለሙስና የሚያጋልጡ አሰራሮች የተወገዱበት ነው ብለን እናስባለን፡፡ የመንጃ ፍቃድ አሰጣጥ ለሙስና በጣም የተጋለጠና ክፍት የነበረ፣ መንጃ ፍቃድ ወሳጁንም ሲያንከራትት የነበረ፣ ለሦስተኛ ወገኖችም አስቸጋሪ የሆነ ወደ መንገድ የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ አሰጣጥም ሕገወጥነት የበዛበት ነበር፡፡ የትራፊክ ማኔጅመንቱም ከፍተኛ ችግር ያለበትና ሥርዓት ያልያዘ ነው፡፡ የደረቅ ጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርትም ቢሆን ተጠንቶ የተሣፋሪንና የእቃ አጓጓዦችን ምሬት የማያስከብር እንግልት የበዛበት ነበር፡፡ እነዚህንና ሌሎችን ከመሰረቱ ይቀይራሉ ብለን ያሰብናቸው አሰራሮች ናቸው፡፡ የሚያበረታታ ውጤት አግኝተናል፡፡ የሌላውንም ዓለም የትራንስፖርት ሥርዓት ለመፍጠር የምንሄድበት አሰራር ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ከዘጠኝ የማያንሱ ሕጎች፣ አዋጆችና ደንቦች ላይ ከፍተኛ ውይይት ተደርጎባቸው ለሚኒስትሮች ምክር ቤትና ለተወካዮች ምክር ቤት ደረጃ በደረጃ እየቀረቡ የሚሄዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡  

ሪፖርተር፡- ሕጉ ምን ላይ ያተኩራል?

አቶ ጁነዲን፡- የትራንስፖርት ሥርዓቱን የሚያስተካክል ሕግ ነው፡፡ ስለአሽከርካሪ፣ ተሽከርካሪ፣ ስለትራፊክ፣ ስለአደጋዎች፣ ስለሕዝብ ማመላለሻ ሊሆን ይችላል፡፡ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ዘጠኝ የሚሆኑ ሕጎች ተቀርፀው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው ለመንግሥት እየቀረቡ ነው፡፡ በፌዴራል ደረጃ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ ብቻ ሳይወሰን ወደ ክልሎችም መሄድ እንደሚገባው በመጀመሪያ ደረጃ አዋሳ ላይ በነሐሴ ወር ውስጥ ከባለሙያዎች ጋር ባደረግነው ስብሰባ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በመቀጠልም የአራት ክልሎች ፕሬዚዳንቶች የየክልሎቹ የቢፒአርና ቢሮ ኃላፊዎች የተገኙበት ጠንከር ያለ ስብሰባ በማድረግ በተለይም የአሽከርካሪ ብቃትና የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋጫ የሥራ ሂደቶች በማቅረብ ወሳኞቹ ሥራዎች እነዚህ ስለሆኑ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ትግበራ ለመግባት፣ ክልሎችም ከሦስት አስራ ስድስት ወራት ውስጥ ወደ ትግበራ የሚገባበት ሥርጭት ፈጥረን በየወሩ በጋራ እየገመገምን እያጠናከርን የምንሄድበትን አካሄድ ተስማምተን ተለያይተናል፡፡ ይህ የሚያበረታታና ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ሪፎርም እንደሚሆን አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሪፎርሙ ለውጥ እንደሚያመጣ ቢታመንም ትግበራው ላይ ግን ችግር አለበት፡፡ ቂም መበቀያ ሆኗል የሚሉ አሉ፡፡

አቶ ጁነዲን፡- አቤቱታዎች በተለያየ ደረጃ ቀርበዋል፡፡ የሪፎርሙ መዋቅር ከተሰራ በኋላ የሰራተኞች ምደባ አካሂደናል፡፡ ይህ የተካሄደበት አግባብ አለው፡፡ ሦስት ሰራተኞች ቢ.ፒ.አር ካጠኑ የኮሚቴ አባላት፣ ከሰራተኞች ደግሞ አምስት ከየመሥሪያ ቤቱ ተመርጠው ምደባውን እንዲሠሩ አድርገናል፡፡ የምደባ አካሄድ ግልጽ የሆነ መስፈርት ተቀምጦለት ሰራተኛው (በአምስቱ መስፈርት) እንዲወያይ ተደርጓል፡፡ አስተያየት ተሰጥቶበት ተቀባይነት ያገኘ ሰነድ ነው፡፡ ምደባው አልቆ ይፋ ሲሆን ሰራተኛው ቅሬታ ሊኖረው ይችላል ተብሎ ስለሚታመን የቅሬታ ኮሚቴ በየመሥሪያ ቤቱ ተቋቁሞ ሦስት ከሰራተኛ፣ ሁለት ሰው ከየመሥሪያ ቤቱ ማኔጅመንት፣ የሰራተኞች ቁጥር ብዛት እንዲኖረው ተደርጎ አምስት ሰዎች ቅሬታ ሰሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ቅሬታ ሰሚዎችም ችግር እንዳለባቸው ይነገራል፤ በተለይ ፖስታ ድርጅት፣ አቪዬሽን...

አቶ ጁነዲን፡- በየመሥሪያ ቤቱ ቅሬታ ተሰምቷል፡፡ ችግር አለ በሚሉት ላይ ፋይሎችን የመፈተሽ እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡ አንዳንዶቹ ላይ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ መግባባት ያልተደረሰባቸውና ቅሬታቸው በቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ተቀባይነት ያላገኙ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በተለይም በመኮድ በትራንስፖርትና ሲቪል አቪዬሽን በኩል የየመስሪያ ቤቱ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች ካዳመጡ በኋላ አሁንም ቅሬታ አለ ብለው በተለይም የመንገድ ትራንስፖርት እኔ ጋር መጥተው አወያይቻቸዋለሁ፡፡ ሚኒስትር ዲኤታዎች፣ የመሥሪያ ቤቱ አመራሮች በተገኙበት ተወያይተናል፡፡ ምደባው ትክክል አይደለም፣ በዘመድ አዝማድ ነው የተካሄደው፣ ሙስና አለበት የሚሉ ቅሬታዎችን አቅርበዋል፡፡ እነሱ ቅሬታ ላይ ተመርኩዘን መሥሪያ ቤቱ የሚመራው ሌላ ኮሚቴ አቋቁመን ሰፊ ጥናት አጠናን፡፡ ጥቆማ እንዲሰጡ የቢ.ፒ.አር ኮሚቴ ላይ፣ የመሥሪያ ቤቱ ማኔጅመንት ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ያቀረቡት ቅሬታ ብዙም ሚዛን የደፋ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ አራት ሰዎች ያለአግባብ ከምደባ ውጭ ሆነዋል የሚል ቅሬታ ነበር፡፡ እሱን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሄደው ኮሚቴ መረመረና አራቱ ሰዎች ተመልሰው ወደ ምደባ እንዲገቡ አድርገናል፡፡ ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ የሥነ ምግባር ጉድለት ያለባቸው የኋላ ታሪካቸው ጥሩ አይደለም ተብሎ የታመነ፣ ወይም በፊት ከነበሩበት መምሪያ ችግር አለባቸው የተባሉ ከሀላፊነት ቦታ እንዲነሱ አድርገናል፡፡ ሌቦች አሉ ከተባለ እነሱን ለፖሊስ አሳልፈን የመስጠት ፍላጎት አለን፡፡ መንገድ ትራንስፖርት ውስጥ ችግር እንደነበር እናውቃለን፡፡ ለውጡ የመጣው ይህን ሥርዓት ለማስተካከልና ለሚመጡ አስቸጋሪና እንቅፋት የሆኑትን አሰራሮች አስተካክለን ሌቦቹን ዛሬ በግልፅ ማግኘት ባንችልም ከዚህ በኋላ የሚኖረው ምዕራፍ ለሌብነት የተመቸ እንዳይሆን ለማድረግ ነው፡፡ ሌብነት አይኖርም ማለት ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን ለሌብነት የሚመች ሲስተም መኖር የለበትም በሚል ሙከራ አድርገናል፡፡

ሌቦች እንደሚኖሩ ቢገመትም እርምጃ ለመውሰድ የሚከብዱ አሰራርና የመንግስት ሕግች ስላሉ ሁኔታው ከዚህ አንፃር መታየት ይገባዋል፡፡ በተረፈ ከምደባ ውጭ የሆኑት ሰራተኞች ራሳቸው ምደባው ውስጥ በነበሩበት ወቅት ይህን ለማጋለጥ ጥረት አድርገዋል ወይስ አላደረጉም የሚለው ሌላ ታሪክ ሆኖ አሁን ችግር አለ ብለው ቅሬታ እስካቀረቡ ድረስ በኛ በኩል ጉዳዩን ለመመልከትና ለማስተካከል ዝግጁ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ሪፎርሙ ሰራተኞችን ለመቀነስ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው በማለት የሚወቅሱ አሉ፤

አቶ ጁነዲን፡- ሪፎርሙ የተዘጋጀው ሰራተኞችን ለመቀነስ አይደለም፡፡ ሰራተኞችን ለመቀነስ ሁለት ዓመት የሚፈጅ ሪፎርም አያስፈልግም፡፡ የሪፎርሙ አላማ ብልሹ አሰራሮችን፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ ለተገልጋይ የማይመቹ ልማዳዊ አሰራሮችን ለማስተካከልና ለማረም ነው ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ያለነው፡፡ መነሻችን ሰራተኛ መቀነስ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለብልሹ አሰራር ምክንያት ሰራተኛው አይደለም፡፡ ነገር ግን በተዘረጋው መዋቅር አጥፊ ሰራተኛ የለም ለማለት አይደለም፡፡ እንኳን በመሥሪያ ቤት በቤት ውስጥም አጥፊ ሊኖር ይችላል፡፡ አጥፊዎቹም ባይኖሩ ያለው አሰራር ለተገልጋይ፣ ለእድገትና ለሕዝብ የሚያመች ነው፡፡ እዚህ አሰራር ላይ ነው ትኩረት አድርገን የተንቀሳቀስነው፡፡ ይህን ስናደርግ እንደማንኛውም ስራ የተወሰነ ችግር ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ቢ.ፒ.አሩን ከሰራን በኋላ አሰራሮች አውቶሜትድ መሆን አለባቸው፡፡ በኮምፒውተር የተዘረጋ አሰራር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መሥሪያ ቤቶች በሙሉ ሕዝቡን በተቻለ ቅልፍጥናና ጥራት ለማገልገል ሲባል፡፡ ይህን በምናደርግበት ጊዜ የኮምፒውተር እውቀት ያለውና የትምህርት ደረጃውም ከፍ ያለ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ በፊት በአምስት መምሪያዎች የሚሰራውን ሥራ አሁን በአንድ መምሪያ እንዲሰራ ማስቻል ነው፡፡ ይህን ስናደርግ ስራዎቹ በቢሮክራሲያዊ ሰንሰለቶች ሲንዛዙ እንዳይከርሙና በተወሰነ ደረጃ ላይ ደንበኞች አገልግሎት እንዲያገኙ ነው የምናደርገው፡፡

ሪፖርተር፡- የተቀነሱት ሰራተኞች አልበዙም? ቀደም ሲል ሰራተኛ አይቀነስም በማለት በዚሁ ጋዜጣ ተናግረው ነበር፡፡

አቶ ጁነዲን፡- በአምስቱ መሥሪያ ቤቶች ከሁለት ሺህ በላይ ሰራተኞች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አምስት መቶ ሰራተኞች ያልተመደቡበት ሁኔታ አለ፡፡ ምደባው በተቻለ መጠን ሰራተኞችን በተለይም የፖስታ አገልግሎት ድርጅትን እንዳይጎዳ ጥረት ተደርጓል፡፡ ብዙ ሰራተኞች ከምደባ ውጭ ይሆኑ ነበር፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ማኔጅመንት ቡድን አይቶ የሰራተኛው ምደባ በተቻለ አቅም ብዙ ሰራተኛ እንዲያቅፍ ሆኖ ተሰርቷል፡፡ በማንኛውም ሀገር በመንግሥት ተቋማት ለውጥ ሲካሄድ የተወሰነ ችግር ይደርሳል፡፡ ይህ የማይቀር በመሆኑ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ከዚህ በፊት ለሪፖርተር ጋዜጣ ሰራተኛ አይቀነስም ብዬ ያልኩት አነጋገር እዚህ ጋ ነው ነጥቡ ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- 500 ሰራተኞችን አለመመደብ ከመቀነስ ውጪ ምን ሊባል ይችላል?

አቶ ጁነዲን፡- ሰራተኛ አይቀነስም ስንል ሰራተኞች የስራ ፀባያቸውና የስራ ቦታቸው ተቀየረ እንጂ ከሥራ አልተወገዱም ነው የኛ አቋም፡፡ አማራጭ የሥራ ዕድል ማንም ሳያስገድደን ፈጥረናል፡፡ ለሌሎች መስሪያ ቤቶች ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ በዓመት ከአንድ እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር ትርፍ ሊያመጡ የሚችሉ ቢዝነሶችን ፈጠርን፡፡ ከዚህ በፊት በጨረታ ስንሰጥ የነበውን የመኪና ማቆሚያ ያለምንም ጨረታ እነዚህን ሰራተኞች ለመደገፍ ሰጥተናል፡፡ የብድር አገልግሎት አመቻችተናል፡፡ መኖሪያ በየመናኸሪያው ያሉ መዝናኛ ክበቦችን ያለ ቤት ኪራይ ሰጠናቸው፡፡ ጥሩ ገቢ ያለው ነው፡፡ እነሱ ግን ለኢንቨስትመንት ይሰጥ እንጂ ለእኛ አያስፈልግም ያሉት በደንብ ስላላሰቡበት ይሆናል፡፡ ይህ የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ አካሄድ ነው የዘረጋነው፡፡ ይህ ሪፎረሙ ሳይጠናቀቅ ከመጋቢት 1999 እንዲህ አይነት ሁኔታ ቢከሰት ሰራተኛውን በምንም መልኩ ከስራ ውጭ ማድረግ የለብንም ብለን ነው፡፡ የስራ ዘርፍ ቀይሩ፣ አትርፉ ነግዱ ማለት ከስራ ማባረር ነው ከተባለ ያስቸግራል፡፡   

ሪፖርተር፡- ወደኋላ ልመልስዎትና የአሰራር ጥናት ማሻሻያ የሚሰራ (የሚመራ) በስነ ምግባር አርአያ የሆነ፣ ከሙስና የፀዳ መሆን የለበትም?

አቶ ጁነዲን፡- ይህ ገና በ1997 ዓ.ም የደመደምነው ጉዳይ ነው፡፡ ቢ.ፒ.አር ውስጥ የሚገባና ለውጡን የሚመራ ሰው ታታሪ መሆን አለበት፡፡ ለሕዝብ ተቆርቋሪ የሆነና ከስነ ምግባር ብልሹነት የፀዳ መሆን አለበት፡፡ ይህ ግልፅ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ዳይሬክተሮቹን አወያይተን ዳይሬክተሮቹ ሰራተኞችን በዚህ መሰረት እንዲመርጡ ተደርጓል፡፡ እኛ ባለን ሪፖርት  እስከ 1999 ታህሳስ ወር በቢ.ፒ.አር ውስጥ የተሳተፉ ሰራተኞች ዘጠና አምስት በመቶ ጥሩ ሰራተኞች እንደሆኑ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ሒደት ላይ ሦስት ሶስት ሰው ነው የተቀመጠው፡፡ ከዚህ ውስጥ ዘጠና አምስት በመቶ ጥሩ የሰው ሀይል ያፈራንበት ነው፡፡ አምስት በመቶ ያህል ጥሩ ያልሆኑ ሰዎች ገብተው ይሆናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ያጠኑት ሂደቱን ነው፡፡ ግጭቱ ያለው ደግሞ ምደባ ላይ ነው፡፡ ሂደቱ ሲቀርብ እዚህ እኔ ከምመራው ኮሚቴ ጋር ገምገመን የሚያስኬደን አሰራር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላ አማራጭ የስራ እድል ለመፍጠር አልታሰበም?

አቶ ጁነዲን፡- አንቀበልም ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ነው፡፡ ከዲፕሎማ ደረጃ በታች የሆኑ ሰራተኞች እንዳይጎዱ ሆደ ሰፊ ሆነን ማድረግ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ አማራጭ የሥራ እድሎች ካሉ አሰልጥነን ክፍት ቦታ ቢኖረን እየሞላን እንሄዳለን፡፡ ደሞዛቸው አይነካም፡፡ ከዲፕሎማ በላይ ሆኖ ፍላጎት ካለው ቢዝነስ ውስጥ የመግባት መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ በተረፈ ግን አማራጭ የሥራ እድል እንፈጥርላቸዋለን፡፡ ይህን እያየን ነው፡፡ ሌላ ኮሚቴ አቋቁመን በሁለት ሣምንት ውስጥ ለይተን እነዚህን ወጎኖች ለማካተት እንሞክራለን፡፡

ሪፖርተር፡- በተለይ በፖስታ ድርጅት የተካሄደው ጥናትና ምደባ ከፍተኛ ቅሬታ ቀርቦበታል፤

አቶ ጁነዲን፡- የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ስራውም የተለየ በመሆኑ ለየት ያለ ችግር አለው፡፡  ከአንድ መቶ አመት በላይ የቆየ ድርጅት በመሆኑ አሰራሩም በጣም ያረጀ ነው፡፡ ያለለውጥ ብዙ ዓመታት የቆየ ድርጅት ነው፡፡ አገልግሎቱም በሰባትና ስምንት መቶ ፖስታ ቤቶች አገልግሎት ለመስጠት እየሞከረ ያለ ድርጅት ነው፡፡ የመገናኛ አገልግሎቶች በመስፋፋታቸው ሥራ ተነጠቅኩ ብሎ የሚያስብ፣ እይታ የሌለው ድርጅት በመሆኑ ለውጡ ይህንን ለመግፈፍ ነው፡፡ ፖስታ አገልግሎት በቀላሉ በዝቅተኛ ሰራተኛ ሊሰጥ ይችላል በሚለው ያረጀ አስተሳሰብ የተተበተበ፣ የወደፊት ራዕይ የሌለው በመሆኑ መቀየር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ለውጡ ሲጀመር ችግር ነበር፡፡ ለምሳሌ ዋናው ሥራ አስኪያጅ ሰራተኞቹን ሰብስበው ያሉትና የሆነው የተለያየ ነው፡፡ እርስዎም ይህንን እንደሚያውቁ በስብሰባ ላይ ገልፀዋል ይባላል፡፡

አቶ ጁነዲን፡- እንደ አጋጣሚ ሀላፊው ለጡረታ የተዘጋጁ ስለነበሩ እድል አልነበረንም፡፡ ቢ.ፒ.አሩን ስናጠናቅቅ ጡረታ ወጥተዋል፡፡ የተጀመረው ሥራ እስከነ ችግሩ ወደ ትግበራ ሳንደርስ የበፊቱ ሥራ አስኪያጅ ጡረታ መውጣታቸው ክፍተት ፈጥሯል፡፡ ይህ ክፍተት ለመሙላት ከሚኒስትር መስሪያ ቤቱ አንድ ኃላፊ መድበናል፡፡ በፊት የነበረው ማኔጅመንት አልተበተነም፡፡ አሁንም አለ፡፡ በፍላጎት ሳይሆን ይህን ያደረግነው የሽግግር ወቅቱ ያመጣው ነው፡፡ ጊዜያዊና ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጁ በሽግግር ወቅት የሚመሩት ሥራ ነው ተብሎ መታሰብ አለበት፡፡ የቀድሞ ሥራ አስኪያጁ ጡረታ መውጣትን ተከትሎ ሰራተኛው ለውጡ ትክክል አይደለም ብሎ እንዲያምን የመቀስቀስ አዝማሚያዎች ሁሉ በፖስታ ድርጅት ታይቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በፖስታ አገልግሎት ድርጅት የተደረገው ሪፎርም አግባብ አይደለም፡፡ ሚኒስትሩም በቂ መረጃ የላቸውም እየተባለ ነው፤

አቶ ጁነዲን፡- ስህተት ነው፡፡ የፖስታ አገልግሎት ሪፎርም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ልክ እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ በአዲስ ይገነባል፡፡ የመንግሥት ድርጅት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ይህን አይገነዘቡም፡፡ መንግሥት የፖስታ ድርጅት ዘመናዊ እንዲሆንና ብዙ ደንበኞች እንዲኖሩት ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ተግባራዊነት አመራሩን አስተካከለን ተጀምሮ የነበረውን የለውጥ ሂደት ገምግመንና አስተካክለን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ድርጅቱ ያሉበትን ችግሮች አውቀናል፡፡ በፊት ከነበሩት ሥራ አስኪያጅ ጋር በቢ.ፒ.አር ማንዋል አመራር መሰረት አምስትና ስድስት ጊዜ ሠራተኛው ተወያይቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ዋሽተውናል ስብሰባ አድርገን የሆነውና የተወያየንበት ሌላ ነው በማለት ሠራተኞች ያማርራሉ፤

አቶ ጁነዲን፡- የበፊት አመራር በአዲሱ ሲተካ ክፍተት ነበር፡፡ ሠራተኛው በሚወያይበት ነጥብ ላይ ዛሬም እንወያያለን፡፡ በሩ ክፍት ነው፡፡ አዲሱ ሥራ አስኪያጅ ለሠራተኛው እንደገለፁት የአሰራር ጥናት ማሻሻያው ራሱ ትክክል አይደለም በሚል ስህተቶቹን ለማሳየት ሃሳብ ካቀረባችሁ ትበረታታላችሁ ቢሉም የቀረበ ሃሳብ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የአመራሩ ችግር ሠራተኛው በድርጅቱ ላይ እምነት እንዳይጥል አድርጐታል ይባላል፤

አቶ ጁነዲን፡- አመራሩ ችግር ሊኖርበት ይችላል፡፡ አመራሩ ውስጥ በፀረ ሙስና የሚፈለጉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሌቦችን መያዝ እንፈልጋለን፡፡ መረጃ ካለ ፖሊስም ሆነ ፀረ ሙስና እርምጃ ለመውሰድ ከፈለጉ ፈቃደኛ ነን፡፡ ፖስታ ይቀደዳል፣ ፐርሲድ ይሰረቃል፣ በሕገወጥ መንገድ የፖስታ ሳጥኖች ይከፈታሉ ወዘተ.፡፡ ሠራተኛው፣ የሠራተኛው ማህበር የእውነተኛ ተቋርቋሪነታቸው ማረጋገጫ ድርጅቱን ለማዳን ሌቦችን ለማጋለጥ ርብርብ ሲያደርጉ ነው፡፡ ሌባን የሚያጋልጥ ማህበርና አመራርን ማየት እንፈልጋለን፡፡ የደንበኞችና የግለሰቦች ንብረት ወደ አሜሪካ ሳይላክ እዚህ ይቆያል፣ የሚቀበለው አጥቶ ሲመለስ ለባለቤቱ ቶሎ አይደርስም፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር ሲሸፋፈን ቆይቷል፡፡ እያካሄድን ባለው ሽግግር አጥፊዎቹ ተጠቁመዋል፡፡ አመራሩን ለማስተካከልና ለማጠናከር የሰው ኃይሉን እያጠናን ነው፡፡ ይህን አስተካክለን ሪፎርሙን ከመተግበር ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ሪፎርሙ ሌብነት የሚቀንስ እንጂ የሚጋብዝ አለመሆኑን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፖስታ አገልግሎት ሪፎርም ከሌሎች የተለየ የሆነበት ምክንያት ይህ ነው?

አቶ ጁነዲን፡- በዓለም በተለያዩ አገራት እንግሊዝ፣ ሆላንድ የከበረ እቃ ወደ ኢትዮጵያ አትላኩ ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት ውስጥ ሌብነት እንደሚፈጸም አውቀዋል፡፡ ይህ የሀገር ገፅታና ሞራል የሚያበላሽ አሰራር ነው፡፡ የተላከው እቃ እንዳልደረሰው ተረካቢው ሪፖርት ሲያደርግ ችግሩ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ይነገራል፡፡ ፖስታ አገልግሎት ከቴሌ ያልተናነሰ ብዙ ካፒታል ሊያንቀሳቅስ፣ የፖስታ ባንኪንግ ሊፈጥር የሚችል አቅም ያለው ድርጅት ነው፡፡ በትራንስፖርት የቤት ለቤት እደላ ለመጀመር የሚያስችል ዘመናዊ የመገናኛ አውታር ነው፡፡ ወደ ዘመናዊነት ለመሸጋገር ከሰራተኛው ብዙ ይጠበቃል፡፡ ሰራተኛው ሥነ ምግባር የሌላቸውን የሚታገል ከሆነ መንግሥት ከጎኑ ይቆማል፡፡ ሌባን በመደበቅ ድርጅቱ እዲጎድፍና እንዲደክም የሚፈልግ ያለ አይመስለኝም፡፡ ካለም አዲሱ አሰራር ያስወግደዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ሲቪል አቪየሽን የአሰራር ለውጥ ምን ይላሉ?

አቶ ጁነዲን፡- ሲቪል አቪየሽን ቴክኒካል መስሪያ ቤት ነው፡፡ እዚያ ያልተመደቡ ሠራተኞች ደመወዛቸው ከሌሎች አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ነው፡፡ የክፍያ ሥርዓቱም የተለየ ነው፡፡ ስራ እንፍጠርላችሁ ሲባሉ አንፈልግም ብለዋል፡፡ መልሰን አሰልጥነን ተመልሰው መስራት የሚችሉ ከሆነ አጠቃላይ አቅጣጫው ለእነርሱም ይሰራል፡፡ የተለየ አመለካከት የለንም፡፡ አሰራሩን ስናስተካክል ግን ሰራተኞች ከምደባ ውጪ ሆነዋል፡፡ ደመወዛቸው እንደቀጠለ ነው፡፡ ከሌላው የሚለየው የመስሪያ ቤቱ የስራ ባህርይ ሌላ ቦታ የሌለ መሆኑ ነው፡፡ የአስተዳደርና ፋይናንስ፣ የጠቅላላ አገልግሎት ሰራተኞችና ባለሙያዎችን ሌላ ቦታ መመደብ አይቻልም፡፡ ስልጠናው ለሲቪል አቪየሽን የሚሆን መሆን አለበት፡፡ ምን ዓይነት ስልጠና ሰጥተን እንመድባቸው የሚለውን የሰዎቹን ካሪኩለም ቪቴ በማየት የምናጠናው ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ቴሌን ለማሻሻል የተወሰዱት እርምጃዎች ቴሌን አሻሽለውታል?

አቶ ጁነዲን፡- የቴሌኮሙኒኬሽን ሪፎርም አላለቀም፡፡ ቴሌን የምናሻሽለው በሁለት መልክ ነው፡፡ ለውጡ የሁለቱ ድምር ውጤት ይሆናል፡፡ አንዱ የሪፎርም ሥራ ነው፡፡ ሁለተኛው የመሠረተ ልማትንና የአውታሩን ሥራ መቀየር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ቴሌ አሁን ካለበት ሁኔታ እንዲለወጥ ያደርጋል፡፡ ሪፎርሙ የሚያነጣጥርበት ሶፍትዌር በድርጅቱ አመራርና ብቃት ላይ ነው፡፡ ሪፎርሙ ቴሌ ምን አይነት ቢዝነስ ድርጅት ይሁን? ምን አይነት የደንበኛ ፖሊሲ ይኑረው? ቴሌ ዘመናዊ ሆኖ ሲቀረፅ ዘመናዊ ኔትወርክ /ኒው ጄኔሬሽን ኔትዎርክ/ የሚቀጥለው ትውልድ ይረከባል፡፡

ሪፖርተር፡- ቴሌ አዲስ ቴክኖሎጂ እያስፋፋ ያለው ከቻይናው ዜድቲኢ ከተባለ ኩባንያ ጋር በቬንደር ፋይናንስ ነው፡፡ ግን ንብረት እየተዝረከረከ ነው፡፡ ጥራት የለም ይባላል፡፡ በተለይ ሰበታ፣ ናዝሬት፣ አዋሳ፣ መቀሌ፣ አዲስ አበባ የስልክ ጥራት የለም፤

አቶ ጁነዲን፡- የጥራት ችግር በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በመቀሌ፣ በባህርዳር፣ በድሬዳዋ፣ በአዋሳ፣ በጅማ፣ በደሴ አለ፡፡ የደንበኛ ፍላጎትና የተከልነው ኔትወርክ ባለመመጣጠኑ የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ በአዋሳ እኛ ያለን ኔትወርክ የመሸከም አቅሙ 80ሺህ ነው፡፡ ነገር ግን ሞባይል ያላቸው ደንበኞች 97 ሺህ ናቸው፡፡ መስመሮች ስለሚጨናነቁ ጥሪዎች ይወድቃሉ፣ በቶሎ አይገኙም፡፡ ይህንን ችግር መደበቅ አይቻልም፡፡ ኔትወርኩ የቀድሞ እንጂ ዜድቲኢ የተከለው አይደለም፡፡ ዜድቲኢ ከሚሌኒየሙ ጋር አያይዞ የ1.2 ሚሊዮን የሞባይል መስመር አቅም ብቻ ጨምሯል፡፡ ይህ ለአደስ አበባ የጥራት ችግር የነበረው የኖኪያና ዜድቲኢ አንዱ በአንዱ ላይ ስታክ የሚባለው በኔትወርክ አርክቴክቸር እየተሠራ ነው፡፡ የኖኪያ 1800 ኤምኤች ፍሪኩየንሲ፣ የዜድቲኢ 900 ኤምኤች ላይ ነው፡፡ በኔትወርክ መካከል አለመጣጣም አለ፡፡ ኦብቲማይዜሽን የሚሰራበት የአሰራር ችግር አለ፡፡ ቴሌ ይህንን የመቆጣጠር፣ ኔትወርኩን በማጣጣም መጓዝ እንዲችል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የኔትወርኩ አለመጣጣም በፈጠረው ችግር የጥሪ መዘግየት፣ መውደቅና ያለአድራሻው የመሄድ ሁኔታ ተከስቷል፡፡ ችግሩ ታውቆ የሁለቱም ኔትወርክ ባለሙያዎች የማስተካከል ስራ ለመስራት በርብርብ ላይ ናቸው፡፡ በክልል ከተሞች የተፈጠሩት ችግሮች የመስመር ጥበት ያመጣው ነው፡፡ በሁሉም ክልሎች ከፍተኛ የሞባይል ፍላጎት አለ፡፡ የዓለም የቴሌኮም ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የሚቋምጡት ለዚህ ነው፡፡ የዜድቲኢ ኔትወርክ የማስፋፋት ሥራ እስከ አሁን በድርድር ላይ ነው፡፡ ከሚሌኒየም ሞባይል በስተቀር ይሄ ነው የሚባል ትልቅ ሥራ አልተሰራም፡፡ /ሲዲኤምኤ/ ሽቦ አልባ ቴክኖሎጂ ላይ የተወሰኑ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከሐምሌ ጀምሮ እስከ አሁን እልህ አስጨራሽ የሆነ ዝርዝር ድርድር የዜድቲኢና የቴሌኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችና አማካሪ መሐንዲሶች ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አሁን እየተጠናቀቀ ነው፡፡ የተፈረሙ አሉ፡፡ በፈረንጆቹ 2008 ሰፊ እንቅስቃሴ ይጀመራል፡፡ በዋናነት በክልል ከተሞች የተፈጠረውን መጨናነቅ የማስተንፈስ ስራ ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- ገንዘቡ እዳ ነው፡፡ እዳው ደግሞ ከፍተኛ ነው፡፡ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል፡፡ ጥንቃቄ አያስፈልግም?

አቶ ጁነዲን፡- እዳው ወደ ሌላ አይተላለፍም፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን በአስር ዓመት ውስጥ ራሱ ይከፍለዋል፡፡ ከቴሌ ጋር የሚወዳደር ሌላ ድርጅት የለም፡፡ በጣም ከፍተኛ ገንዘብ ያገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ 1.7 ቢሊዮን ብር አግኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ካሉት ኩባንያዎች በሐብትም ሆነ በትርፍ ከአየር መንገድ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ይበልጣል፡፡ ይህ ገቢ አገር ሙሉ ባላዳረሰ ኔትወርክ፣ ውሱን ከተሞችና መንገዶችን ተከትሎ በሚሄድ የተገኘ ነው፡፡ አሁን የምንዘረጋው ኔትወርክ የአገሪቱን 90 በመቶ ያዳርሳል፡፡ ገበያው ስላለ እዳው ቢከፈልም ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ በኩል ስራውን የመመርመር፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ስራ የሚሰራው ቴሌ ስለሆነ ኃላፊነት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንተርኔት እያማረረ ነው፡፡ እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል?

አቶ ጁነዲን፡- አሁን ኢንተርኔት አለን ማለት አያስደፍርም ሙሉ በሙሉ የሚቀየርና ከፍተኛ ፍጥነትና ኮኔክቲቪቲ ያለው ለመገንባት ድርድሩን ጨርሰናል፡፡ የቻይና ኩባንያዎች ገንዘብና ቴክኖሎጂ ይዘው መምጣታቸው የሚያስመሰግን ነው፡፡ እያንዳንዱ ዕቃ ሲመጣ ተቀባይነት እንዳለው ተረጋግጦ ብቻ ነው ወደ ሳይት የሚላከው፡፡ ያመጡትና የተተከለው እቃ ችግር ቢያስከትል ለ10 ዓመት አብረውን ስለሚሰሩ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ውለታ አስፍረናል፡፡ ችግር ቢፈጠር በራሳቸው ወጪ ያስተካክላሉ፡፡ የአገራችንን የወደፊት እድል ከሚወስኑት አንዱ መገናኛ ነው፡፡ ባለሀብቶች ከሌላ አገር መጥተው መሥራት ሲፈልጉ ምን አይነት የቴሌኮም አገልግሎት እንዳለ ያጠናሉ፡፡ ዓለም ወደ ስሪጂ (3ጂ) እየገሰገሰ ነው፡፡ የስሪጂ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባት ያስደስታል፡፡ ትናንት ስንዴ ሲሰጣት ነበር የምትባል አገር የ3ጂ ተጠቃሚ መሆኗ የሚገርማቸው አሉ፡፡ አገልግሎቱን ለሚፈልጉት የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ብናቀርብም አብዛኛው ሰው የሚፈልገው የድምጽ ስልክ ነው፡፡ ሁሉም 3ጂ ያገኛል ማለት አይደለም፡፡ በሦስት አመት ውስጥ የምንፈጥረው ከ10-15 ሚሊዮን ይሆናል ብለን እናስባለን፡፡ ከዚህ ውስጥ ስሪጂ የሚፈቀደው ከ1 በመቶ በታች ነው፡፡ ቀስ በቀስ የገቢ ምንጩ ካደገ መጨመር ይቻላል፡፡ አሁን የምንሰጠው አገልግሎት ቱጂ (2ጂ) 95 በመቶ የሚሆነውን ይይዛል፡፡ 2.5 የሚባለው ጂፒአርኤስ፤ ኤስኤምኤስጂ አገልግሎት የምንጠቀምበት 2.75 ኤጂኢ የሚባል አለ በአገልግሎቱ የተመረጡ ደንበኞች ተጠቃሚ ናቸው፡፡

 
< Prev   Next >