Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ፓርቲና መንግሥት ምንና ምን ናቸው?
ፓርቲና መንግሥት ምንና ምን ናቸው? Print E-mail
Wednesday, 20 February 2008
በከበደ አለማየሁ

አንድ አገር ከሚለካባቸው መሠረታዊ መርሆዎች መካከል ለምሳሌ አንድ በፓርቲ እና በተለይም በገዢው ፓርቲና በመንግሥት መካከል የታወቀ፣ የለየለት፣ የማያሻማና የማያደናግር ልዩነት ያለ መሆኑ ነው፡፡ ፓርቲ እና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን በፓርቲ እና በመንግሥት መካከል በጽኑ መሠረት ላይ የቆመ ይህንንም ጽኑ መሠረት በህግ የበላይነት ላይ የገነባ አጥር ወይም ግንብ ያለመሆኑ ነው፡፡
በአንድ ዲሞክራሲያዊ ህገመንግሥት መሠረት የተመሠረተና የተገነባ ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲ ከሚታወቅባቸው ሁለንተናዊ    (ዩኒቨርሳል) ባህሪዎች መካከል አንዱ ይህ የተባለው በፓርቲና በመንግሥት መካከል ያለው በጥሩ፣ በመልካምና ጤናማ ..ጉርብትና.. ላይ የተመሠረተ፣ ጽኑ መሠረት ባለው አጥር የተለየ ግንኙነት ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ጭምር አባል የሆነችበትና ከሌሎች 129 አገሮች ጋር በጋራ በመሆን በዓለም ፓርላማዎች ህብረት ምክር ቤት እ.ኤ.አ ማርች 26 ቀን 1994 ዓ.ም. ፓሪስ ላይ የፀደቀው “የነፃ እና ትክክለኛ ምርጫዎች መመዘኛዎች ድንጋጌ” በየአንዳንዱ አገር ዲሞክራሰያዊ ምርጫ መካሄድ ይቻል ዘንድ አስቀድሞ ሊኖሩ/ሊሟሉ ከሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ለምሳሌ አንዳንዶቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለማቋቋምና በነፃነት ስለሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ የመደንገግ አስፈላጊነት እንዲሁም የፓርቲ፣ የመንግሥትን ልዩነት የማረጋገጥ ግዴታ ይገኝበታል፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ፣ አጠቃላይ ምንነቱ እንደሚያመለክተውና በአገራችንም የፖለቲካ ፓርቲዎች (ምዝገባ) ህግ በትርጉም ድንጋጌው እንደሚወስነው ከህብረተሰቡ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎችን በማሰባሰብ የራሱን የፖለቲካ እምነትና ዓላማ የሚያንፀባርቅበት ኘሮግራም በማውጣት በሀገር አቀፍ ወይም በክልል የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ በህግ መሠረት የተደራጀ ማህበራዊ ተቋም ነው፡፡ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ (ወይም ማቋቋሚያ) የህግ ማዕቀፍ በተለያዩ ዘርፎች ያለበት ውስንነት፣ በተለይም ከዚህ የምዝገባ ህግም ሆነ ከሌሎች ተመሳሳይና ተዛማጅ የህግ ማእቀፎች አኳያ የፓርቲና የመንግሥትን ልዩነት ማረጋገጥን በተመለከተ የሚያቋቁሙትና የሚያስተጋቡት ይህ ነው የሚባል መርህ አለመኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የፓርቲዎች ዓላማ የፖለቲካ ሥልጣን በህጋዊ መንገድ መያዝ ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የፖለቲካ ሥልጣን ሲይዝ የፓርቲና የመንግሥትን ልዩነት ማረጋገጥ የሚያስፈልገውም፣ አስፈላጊነቱም ግዴታ የአንድ ዲሞክራሰያዊ ሥርዓት ምትክ የለሽና የማይታለፍ ቅድመ ሁኔታ የሆነውም በዚሁ ውስጥ ነው፡፡

የፓርቲና በመንግሥት መካከል ይህን በመሰለ ድንበርና የወሰን መስመር የሌለው ወይም ሊበጅለት የማይችል በሚመስለው ግንኙነት ውስጥ የፓርቲንና የመንግሥትን ልዩነት የማረጋገጥ ግዴታ ከፍ ሲል የጠቀስነው ዓለማቀፋዊ የዓለም ፓርላማዎች ህብረት በሚያተኩርበት የምርጫው ዘርፍ እና የምርጫ ወቅት ብቻ እንደክት ልብስ ብቅ ብሎ የሚጠፋ ወይም ለይምሰል በመደበኛው የዘወትር ልብስ ላይ ጣል አድርገው ለእይታ ብቻ የሚያስመዘግቡት አይደለም፡፡ በቅርቡ መላው የዓለም ህዝብ የመሰከረው የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ (የኤ.ኤንስ) የፓርቲ አመራር አካላትና አባላት ምርጫ ላይ እንደተመለከትነው የፓርቲ እና የመንግሥትን ልዩነት የማረጋገጥ ግዴታ በገዢው ፓርቲ እና በመንግሥት መካከል መኖር ያለበትን ልዩነት በማረጋገጥ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በገዢው ፓርቲ የመንግሥት አመራር አባላትና በገዢው ፓርቲ በራሱ የፓርቲ አመራር አባላት መካከልም ያለው ወይም መኖር ያለበት ልዩነት ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ የ1990ዎቹ የመጀመሪያዎቹ አንድና ሁለት ዓመታት ውስጥ የነበረውን ግጭትና ጦርነት እንዲሁም የ1992ቱን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርጫ ተከትሎ በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ (በተለይም በሕወሓት) ውስጥ የተከሰተው መጠነ ሰፊ እና አደገኛ ልዩነት የገዢው ፓርቲ ትግር ብቻ ሆኖ በዚያው ውስጥ መወሰን ሳይችል ቀርቶ የመንግሥትና የአገር ስጋትና አደጋ የሆነው ውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሰያችንን ጨምሮ ዴሞክራሲያችን ለእንግዲህ ያለ ልዩነት እና ..መጠበቂያ.. እንሰዶና ባዶ ስለሆነ ነው፡፡

አገራችን ውስጥ እንኳንስ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ የተደረገው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ ፓርቲ ምርጫ ያሳየን ዓይነት (በጆሴፍ ዙማ እና ቦታ በእምባኪ መካከል) ልዩነት ቀርቶ ሌላው አገርና ዲሞክራሲ ውስጥ ተራም መሠረታዊም የሚባለው ማብራሪያ ሳያስፈልገው ስሙ ወይም ምንነቱ ሲጠራ፣ ሲጠቀስ ብቻ የሚታወቀው (ሳይታለም የፈታው) የገዢው ፓርቲ እና የመንግሥት ልዩነት በጭራሽ ስለመኖሩ፣ መኖር ያለበት ስለመሆኑም የሚታወቅ አይደለም፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ዝግጅትና ሂደት ውስጥ በራሱ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እና የቦርዱ አማካሪ በሆነው አይሪስ በተባለ የምርጫ ድርጅት አዘጋጅነት የቀረበው የፓርቲዎች የጋራ መድረክ ማቋቋሚያ ሰነድ እና የምርጫ ቅስቀሳና ዘመቻ አካሄድ ላይ ማስረዳት ያዳገተው መርዳት ያቃተው ከፍተኛ “እንቆቅልሽ” ቢኖር ይኸው የፓርቲ እና የመንግሥት (ለዚያውም በምርጫ ወቅት) ልዩነት ነው፡፡

“በምርጫ ወቅት” ማለት ላይ አፅንኦት ማድረግ ያስፈለገው በፓርቲ እና በመንግሥት መካከል መኖር ያለበትን ልዩነት የማረጋገጥ ግዴታ፣ ከዚያም በፊት የዚህን ልዩነት ልክና መልክ በህግ በዝርዝርና በነቂስ ለይቶና ለቆም የማስቀመጥ ግዴታ እንደ የምርጫ ወቅት ባለ ችግሩ ገፍቶና ከፍቶ በሚወጣበት ጊዜ ብቻ ባለመሆኑ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም.ቱ ምርጫ ዝግጅትና ሂደት ውስጥ ለዚያውም በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች አነሳሽነት ጥረትና ትጋት እንዲሁም በገዢው ፓርቲ ተመሳሳይ እርምጃ፣ ፍላጐትና ፈቃድ ላይ ሳይሆን ይልቁንም በተቃራኒው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካሪ ሆኖ ይሰራ በነበረው ተቋም አፍላቂነት የተነሳውና ለውይይት የቀረበው ይህ የፓርቲና የመንግሥት ልዩነት በሁለቱም ወገኖች በኩል ለ”ውይይት” ያስቸገረው ለምርጫ ቦርድ ለራሱም ቢሆን ሚና ለይቶ በመነሻ (ሚኒመም) ሁኔታዎች ላይ አቋም መውሰድ እንዳይችል ያደረገው (ከሌሎች መካከል) በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት በዚያን ወቅት በውጭ አገር የለጋሽ መንግሥታትና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ውጭ የኢትዮጵያን የምርጫ ቦርድ እንዲያማክር የተቀጠረው ድርጅት የፓርላሜንታዊ ሥርዓት ተከታይ አገሮችን ከነዚህም መካከል የዚህ ዓይነቱ ሥርዓት “እናት አገር” የምትባለዋን የእንግሊዝን በህግ እና ከህግ ይልቅ ደግሞ መላው አገር ሕዝብና ማንም ሰው በተቀበለው ወግና ባህል የተቋቋመውን የአሰራር “ሚኒማ” መንግሥትም ሌሎች ፓርቲዎችም እንዲያሟሉ ሲጠይቁ በሁለቱም ወገኖች በኩል ይቀርብ የነበረው ለገላጋይ ያስቸገረ መከራከሪያ የሚደንቅና የሚያስደነግጥ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ለምሳሌ ገዢው ፓርቲ የመንግሥት ሀብት (ሪሶርስ) ለፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ማዋል የለበትም፤ በእንግሊዝ አገር (በወቅቱ በሚያዚያ ወር 1997 ወይም አኘሪል 2ዐዐ5 እንደሆነው) ለምርጫ ዝግጅት ፓርላማው የፓርቲን እና የመንግሥትን ልዩነት የሚያከብረው (የገቨርንመንትንና የስቴትን ልዩነት የሚያውቀው) ሲቪል ሰርቫንት ብቻ የቀረውና የመንግሥቱን ሥራ እሱ ብቻ የሚያከናውነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ቶኒ ብሌር ለምሳሌ በዚህ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩን መኪና እና አውሮኘላን አይጠቀሙም፤ ለፀጥታና ለደንነት ሲባል የመንግሥት መጓጓዣና የመንግሥትን ሀብት የግድ መጠቀም ካለባቸውም የዚህን ውጭ ፓርቲያቸው ይተካል የሚል ምሳሌና “ትምህርት” ይቀርብ ነበር፡፡

የገዢው ፓርቲና የመንግሥት፣ ባለሥልጣናት ይህ ምሳሌና ትምህርት የሚያቋቁመውን የህግና የአሠራር መርህ ሲሰሙና ሲነገራቸው ያቀረቡት መከራከሪያ የማናቸውም ፓርቲ ዓላማ በምርጫ ሥልጣን መያዝ ነው፡፡ ሥልጣን ሀብት (ሪሶርስ) ነው፡፡ ሥልጣን ይዞ በዚህም ሆነ በሌላው ሪሶርስ አልጠቀምም ማለት እርስ በርሱ የሚያቃርን የማይገባና የማይቻል ጉዳይ ነው የሚል ነወ፡፡ በአንፃሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለዚህ ያቀረቡት የመርህ መከራከሪያና ተቃውሞ ሳይሆን እኛ ሥልጣን ስንይዝ በመንግሥት ሀብት (ሪሶርስ) የመጠቀሙ ..መብት.. እና የወር ተራ ይቅርብን አንፈልግም፣ ስለዚህ እናንተም ይቅርባችሁ በዚህ “እነስማማ” የሚል ዓይነት ለአዲስ የውል ስምምነት ጥሪ የሚያደርግ እንጂ በዲሞክራሲያዊ መርህ ላይ የተመሰረተ አቋም ይዘው አልነበረም፡፡

የ1997 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ እስከ የምርጫው፣ የድምፅ መስጫው ዕለት (ግንቦት 7/97) ይዘት የበረውና የደገሰው ዓይነት ህዝባዊ እንቅስቃሴና መነቃነቅ ስለመኖሩ በጣም አጠራጣሪ ነው እንጂ ለሚያዚያው የ2ዐዐዐ ምርጫ ከወደሁ የሚደረገው በተለይም ወደፊት የሚደረገው የቅስቀሳ ዘመቻ እንቅስቃሴ ይህንኑ ተመሳሳይ ጥያቄ አነሰም በዛም በምርጫው ተሳታፊ ፓርቲዎች መካከል ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ከነዚህም መካከል ሌሎች ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር ከሚጋጩበት (ከማይግባቡት) ጉዳዮች ውስጥ ለምሳሌ አንዱ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ነው፡፡

የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃንን አጠቃቀም የሚመለከተው ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የወጣው አዲሱ የምርጫ ህግ ድንጋጌ “የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ስርዓት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ከቦርዱ ጋር በመሆን በሚያወጣው ድልድል መሠረት ይከናወናል” ሲል የሚደነግገው በተመሳሳይ አንቀጽ በሌላ ንዑስ አንቀጽ ነው፡፡ በ1987 ዓ.ም. ወጥቶ ከተወሰኑ ማሻሻያዎች ጋር በ1997 ዓ.ም. ተሻሽሎ ከጥር 1ዐ ቀን ጀምሮ የፀና ሆኖ የተሰራበት የምርጫ ህግ በተመሳሳይ ሁኔታ ስለመገናኛ ብዙሃን የምርጫ ወቅት አጠቃቀም የማስታወቂያ ሚኒስቴርን የጉዳዩ ባለበት የሚያደርገው በወቅቱ (በ1987 ዓ.ም.) የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን በማስታወቂያ ሚኒስቴር ቁጥጥር ሥር የነበሩ በመሆኑ ነበር፡፡ የምርጫ ህጉን መውጣት ተከትሎ ወዲያውኑ የወጡት የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን እንደገና ማቋቋሚያ ህጐች እና ከህገ መንግሥቱ ሥራ ላይ መዋል በኋላ የወጣው የአስፈፃሚውን አካል ሥልጣንና ተግባር (በተለይም የማስታወቂያ ሚኒስቴርን) ለመወሰን የታወጀው ህግ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን የመንግሥት ቃል አቀባይ ብቻ ከማድረግ ይህንን ሥልጣኑን ቀሪ አድርገው፡፡ በዚህ ብቻ የምርጫው ህግ (በግልጽ ሳይነገር) መሻሻሉን ለሁሉም ግልጽ የሆነና የማያከራክር ጉዳይ መሆን ነበረበት፡፡ የምርጫ ቦርዱም ጉዳይ ፍርድ ቤት መቅረብ ሳያስፈልገው ይህንን ነገር ራሱ የሚቆርጠው አድርጐ መውሰድ ነበረበት፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በተከታታይ በተሻሻሉት የምርጫ ህግ ድንጋጌዎችም ከወዲሁ ይህንን የማስታወቂያ ሚኒስቴርን ሥልጣን አከራካሪነት፣ ምናልባትም ወደፊትም ቢሆን ህጋዊና ህገ መንግሥታዊ አይደለም የሚል ተቃውሞ ጭምር ለማስቀረት በህግ “እንዲፀድቅለት” ተደረገ፡፡

በየጊዜው በሚደረግ ምርጫ የሚለዋወጠውን መንግሥት ወይም በምርጫው  ውጤት መሠረት የሚቀየረውን “የመንግሥትን አቋም የሚያንፀባርቀውን” ወቅታዊ “ርዕሰ አንቀጽ” የሚስተጋባው የማስታወቂያ ሚኒስቴር በምርጫ የሚፋለመው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ሥርዓት “ከቦርዱ ጋር በመሆን” በሚያወጣው ድልድል መሠረት ይከናወናል ማለት አለ የሚባለውን የቦርዱን ነፃነት ጭምር የሚፃረር ነው፡፡

አዲስ እየተረቀቀ ባለው የፓርቲዎች ረቂቅ ህግ ውስጥ መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ስለሚያደርገው የገንዘብ ድጐማ የሚወስኑ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በዚህ ረቂቅ መሠረት የገንዘብን ድልደላ የሚመለከተው ሥልጣን የተሰጠው በረቂቁ መሠረት ለገንዘብ ማኒስቴር ሳይሆን ለምርጫ ቦርድ ነው፡፡ የቦርዱ ተጠሪነት ቢያንስ ቢያንስ በህግ ለተወካዮች ምክር ቤት የሆነው፣ እንደማስታወቂያ ሚኒስቴርም ሆነ እንደገንዘብ ማኒስቴር ለሚኒስትሮች ምክር ቤትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልሆነው “ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኛነት እንዲካሄድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል” የሚል ህገመንግሥታዊ ድንጋጌ የመቅረጽ አስፈላጊነት እውን የሆነው ከሌሎች መካከል ይህንን የፓርቲ ተፅእኖ ለመከላከል ነው፡፡

በመንግሥትና በፓርቲ መካከል ሊኖር የሚገባውን ልዩነት የማረጋገጥ ግዴታ ግን የሚነሳው ወቅት እየጠበቁ በምርጫ ጊዜና በምርጫ ቅስቀሳና ዘመቻ ወቅት ብቻ እንዲሁም ከመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሞላ ጐደል ከ1983 ዓ.ም. በተለይም ከ1987 ዓ.ም. ወዲህ የፖለቲካ ሥልጣን በክልልም ሆነ በማዕከላዊ መንግሥት ደረጃ የያዘው የኢሕአዴግና የዚህ ግንባር አባል ፓርቲዎች በየወቅቱ የምስረታ በዓላቸውን ሲያከብሩ፣ ወይም ከዚህ በተለየ ሁኔታ መደበኛ ሥራቸውን ሲሰሩ ወይም ከነዚህ ፓርቲዎች ጋር ፓለቲካዊ ዝምድና አላቸው፤ የሚባሉት የልማት ድርጅቶች (አልማ፣ ትልማ፣ ኦልማ፣ ደህልማ) ሲንቀሳቀሱና እንደ ቴሌቶን ያለ የገንዘብ ማሰባሰብ ዝግጅት ሲያካሂዱ የሚያገኙት ተራ የሚዲያ ሽፋን ለሌሎች ፓርቲዎች የሚታሰብና የሚገመት አይደለም፡፡

የፓርቲ አካላት ባልሆኑ፣ ወይም አይደለም በሚባሉ ድርጅቶች ለምሳሌ በወጣቶችና በሴቶች ማህበራት፣ በፎረሞች እንዲሁም በህዝባዊ ድርጅቶችና በሙያ ማህበራት ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በትምህርት ቤቶች በመንግሥት የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ የፓርቲዎችን (የሁሉንም ፓርቲዎች) ሥራና እንቅስቃሴ ህግም ሆነ የተቋቋመ አሠራር ገደብ ያበጅለት በእኩልነት የሚያየው ነው ወይ? ለሚሉት ጥያቄዎች ተገቢውንና የፓርቲንና የመንግሥትን ልዩነት ማረጋገጥ ግዴታ የሚያደርገውን ምላሽ ማግኘት ቀርቶ ጥያቄውን ራሱን ያለ ስጋትና በክፉ አይን ሳይታዩ ማንሳት በሚያስችል ጤናማ ከባቢ አየር ውስጥ አለን ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡

በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግስት የተከሰተው የ193 ሲቪሎችን የስድስት ፖሊሶችን ህይወት የቀሳፊው በንብረት በሀብትና እንዲሁም በህዝብ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ስሜት ውስጥ ከፍተኛ መሸማቀቅን የፈጠረውን ችግር ከሌሎች መካከል መከላከል ማስቀረት ማድረግ ይቻል የነበረው ወደፊትም እንዳይደገም ማድረግ የሚቻለው በፓርቲ እና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባውን ልዩነት ጥረት አድርጐና በዝርዝር በመወሰን ይህንንም በተግባር በማረጋገጥ ነው፡፡
 
< Prev   Next >