Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow "ቂምና ቁርሾ ይዞ ፖለቲካ ውስጥ...
"ቂምና ቁርሾ ይዞ ፖለቲካ ውስጥ... Print E-mail
Wednesday, 20 February 2008
Image"ቂምና ቁርሾ ይዞ ፖለቲካ ውስጥ መንቀሳቀስ የሚቻልበት ዕድል አለ ብለን አናምንም"
አቶ ሙሼ ሰሙ

አቶ ሙሼ ሰሙ የኢዴአፓ መድህን ዋና ፀሐፊ ናቸው፡፡ ስለ ፓርቲያቸውና በቅርቡ በሚደረገው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ዝግጅታቸው ዙሪያ ሰለሞን ጐሹ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለአካባቢና ማሟያ ምርጫ ኢዴአፓ መድህን ተዘጋጅቷል?

አቶ ሙሼ፡-
ፓርቲያችን በሚያዚያ ወር በሚካሄደው የማሟያ፣ የወረዳና የክፍለ ከተማ ምርጫዎች ላይ ከመርህ ተነስቶ በተሳትፎ ደረጃ ውድድር እንደሚያደርግ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲናገር ቆይቷል፡፡ ቢያንስ በ5 ክልሎች ላይ እጩዎችን የምናቀርብ ሲሆን በተጨማሪም ሁለት ወይም ሦስት ክልሎችን  በተራዘመው ጊዜ ውስጥ አካትተን እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በአዲስ አበባ ላይ ክፍት በነበሩት ወይም በማሟያነት በተያዙት በሁሉም የተወካዮች ምክር ቤት ቦታዎች ላይ እንሳተፋለን፡፡ በክፍለ ከተማና በቀበሌ ደረጃ ተሳትፎአችን እንደተጠበቀ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭም በ5ቱ ክልሎችና መስተዳድሮች ተሳትፎአችን እየተጠናከረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከምርጫ 97 ወዲህ የሕዝቡ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደቀነሰ ይነገራል፡፡ በእናንተ በኩል ደጋፊዎቻችሁ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት?

አቶ ሙሼ፡-
ከምርጫ 97 በኋላ በተፈጠረው የፖለቲካ አለመግባባትና ግጭት በሕዝቡ ዘንድ ተስፋ የመቁረጥ ወይም ደግሞ ከዚህ በኋላ በምርጫ ውጤት ሊመጣ አይችልም የሚል መንፈስ አልፎ ተርፎም በተቃዋሚውና በገዥው ፓርቲ እምነት የማጣት ነገር ተንፀባርቋል፡፡ ይሄ ሁሉንም የኢትዮጵያ ቆዳ ስፋት ያካልላል ብለን ለማመን ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን ጉዳቱ ደርሷል፡፡ ይሄ ሊካድ አይችልም፡፡ ይህም ሆኖ ኢዴአፓ መድህን ከዚህ አለመረጋጋትና ፖለቲካዊ ግጭት በኋላ ራሱን አጠናክሮ ለመስራት ጊዜ ወስዶ ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህም መሠረት አመርቂ የሆነ ከተሳትፎም ዘለል ያለ እንቅስቃሴ የማድረግ እድል ገጥሞታል፡፡ ከ5ቱ ክልሎች በተጨማሪ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ አስተዳደሮች እጩዎች ማቅረብ ችለናል፡፡ ከምርጫ ቦርድ በሰማነው መረጃ መሠረት ወደ 29 ሚሊዮን የሚጠጋ መራጭ እንደተመዘገበ ነው፡፡ ይህ 29 ሚሊዮን ተመዝጋቢ ከምርጫ 97 ተመዝጋቢ በቁጥር ከፍ ይላል፡፡ ይህም ሆኖ ግን በአሁኑ ወቅት ካርድ የወሰደ ሰው በሙሉ መንፈሱ በምርጫው ላይ ተሳትፎ ካርዱን ይጠቀምበታል የሚለው ነገር የሚታየው ከአሁን በኋላ በሚኖሩት የመድረክ ውይይቶች ላይ በቂ እድል የሚሰጥ፤ ተቃዋሚዎችም ሆነ ገዥው ፓርቲ በቂ ተሳትፎ የምናደርግበት እድል የተፈጠረ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ሕዝቡ በውስጡ የያዘው ስሜት እንዳለ ሆኖ እንደተለመደው የምርጫ ካርድ አለመውሰድ መሠረታዊ የሆነ የመንግሥት አገልግሎቶችን የሚያሳጣ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት ስላለው ከዚያም ተነስቶ ሊሆን ይችላል የወሰደው፡፡ ከዚያ ዓይነት የስነ ልቦና ቀውስ አውጥተነው በምርጫው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ካርዱን እንዲጠቀምበት ለማድረግ በእኛም በገዥው ፓርቲ በኩልም መድረኮች በሰፊው ተዘጋጅተው የምንሳተፍበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ ህጋዊ ግዴታ አለበት፡፡ ይህ እየተደረገ ነው?

አቶ ሙሼ፡-
ድጋፉ እስከአሁን አልተለቀቀልንም፡፡ ድጋፉ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንደኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች በየቀኑ ለሚያደርጉት የፖለቲካ እንቅስቃሴአቸው የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ምርጫን አስመልክቶ በተለይ ምርጫውን ውጤታማ ለማድረግ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ምርጫውን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማምጣት የሚደረግ ድጋፍ ነው፡፡ ሁለቱ የተለያዩ ዓይነት ድጋፎች ናቸው፡፡ በመጀመሪያው ድጋፍ ዙሪያ በእኛ በኩል አሁንም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ የማጠናቀቅ አዝማሚያ ቢያሳይም ወደ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ሊያስወስን አልቻለም፡፡ ይሄ ለእኛ ከፍተኛ የሆነ ጉዳይን የማጓተት አካሄድ ነው ብለን ነው የታዘብነው፡፡ ለዚህ ትዝብታችን ምክንያቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ስንነጋገር ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ አልፏል፡፡ ይህ አጀንዳ በቅድሚያ ቀርቦ ለምርጫው ተሳትፎአችንም ቢሆን ሕብረተሰቡን ከነበረበት የፖለቲካ ቀውስ አውጥተን የተሻለ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲያመጣ ለማድረግ የሚያግዙ እድሎችን ለመፍጠር የገንዘብ ድጋፍ ቅድሚያ እንዲሰጠው ደጋግመን ወትውተናል ጠይቀናል፡፡ አጀንዳው በተለያየ መንገድ ሲቀርብ ከመሸሽ ይልቅ ውስጥ ገብተን ለመሳተፍ ስለመረጥን በዚያ ጉዳይ ላይ እንቅስቃሴ አድርገናል፡፡ ከቋሚ ኮሚቴ ባለፈ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ልዩነቶች ቢኖሩም ፀድቆ ወደ ተግባራዊነት ለመለወጥ እስከአሁን አልቻለም፡፡ በእኛ በኩል ምክንያቱን አናውቅም፡፡ በመንግሥት በኩልም የቀረበልን ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ ይሄ ነገር ምናልባት ስንፍና ነው ብንለው ነው የሚሻለው፡፡ ጉዳዩን ለማስፈፀምም ካለመፈለግ ባለፈ ገዥው ፓርቲ በዚህ ነገር ተጠቂ ስለማይሆንና የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄው በአብዛኛው የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመሆኑ አንገብጋቢ ጥያቄው አይደለም፡፡ የራሱ አንገብጋቢ አጀንዳዎችን በ24 ሰዓትም የሚያጠናቅቅበት ሁኔታ ነበር፡፡ ሕዝቡ ንቁ የሆነ የምርጫ ተሳትፎ አንዲያደርግ መንግሥት ከወዲሁ አስቦበት ውሳኔ እንዲያሳልፍ እንጠይቃለን፡፡ በምርጫ 97 ምርጫ ቦርድ የሰጠን ድጋፍ በቁሳቁስ ነበር፡፡ አሁን እንዴት እንደሚሆን መረጃ የለንም፡፡ አሁን ፖለቲካ ፓርቲዎች ስለተዳከሙ የገንዘብ ድጋፍ አስፈላጊ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ይህን እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- በምርጫ ሕጉ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የጋራ መድረክ (ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ) እንደሚያዘጋጅ ይጠበቃል፡፡ በዚህ በኩል ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርባችኋል?

አቶ ሙሼ፡-
ምርጫ ቦርድ እስከአሁን ድረስ የጋራ መድረክን አስመልክቶ ያደረገው እንቅስቃሴ የለም፡፡ ግን ምርጫውን በሚመለከት ባደረግናቸው እንቅስቃሴዎች ዙሪያ በየጣቢያዎቹ ከሚገኙ መዝጋቢዎችና ከጣቢያ ኃላፊዎች ጋር ስልክ በመደዋወል የተፈጠሩብንን ችግሮች መፍታት የቻልንበት ሁኔታ ስላለ በምርጫ ቦርድ ደረጃ ወጥተን ጉዳዩ እንዲታይልን የሚያደርግ ሁኔታ አልገጠመንም፡፡ ይሄ ማለት ግን ጠቅላላ ዝርዝሩ የምርጫ እንቅስቃሴአችን ዘገባ ተጠናቆ ገብቷል ማለት አይደለም፡፡ በየአካባቢው የላክናቸው የፓርቲያችን አባሎች በዚሁ ሥራ ላይ ነው የሚገኙት፡፡ የተመዘገቡ እጩዎችም ቁጥር ተጠቃሎ አልመጣልንም፡፡ የደረሱ ችግሮችም ተጠቃሎ አልደረሰንም፡፡ ሲደርሱ ከምርጫ ቦርድም ጋር የምንገናኝበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ እስከአሁን ድረስ ባለው ሁኔታ ግን በተለያየ መንገድ ከአፈፃፀም፣ ከግንዛቤ እጥረት፣ ሕጎቹን በደንብ መተርጎም ካለመቻል እና ከመሳሰሉት የተነሱ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህን በስልክ በመነጋገር ፈተናቸዋል፡፡ ካለፈው በመማር በሰነድ ላይ ተደግፈን ቀኑን፣ ስሞችን፣ ምስክሮችን ሌላም ነገር ያካተተ ዘገባ ይዘን ነው መቅረብ የምንፈልገው፡፡

ሪፖርተር፡- በፓርላማ የተቃዋሚዎች ቀን ላይ ብዙ ጊዜ ውይይት የማይካሄደው ተቃዋሚዎቹ አጀንዳ ስለሌላቸው ነው ብለዋል አፈጉባኤው፡፡ አጀንዳ የላችሁም?

አቶ ሙሼ፡-
አፈጉባኤው እንዲህ ማለታቸውን አይቻለሁ፡፡ ለእኔ ይሄ ትርጉም አልሰጠኝም፡፡ ምክንያቱም የማሳጣትና ጉዳዩን የፕሮፖጋንዳ አጀንዳ ከማድረግ ያለፈ ትርጉም አላየሁበትም፡፡ አሁን በቅርብ ቀን እንኳን አዲስ አበባን በሚመለከት ኢዴአፓ መድህን ያለውን አቋም አስመልክቶ አጀንዳ እንዲያዝልን ጠይቀን ውድቅ ሆኗል፡፡ ከዚህ በፊትም በሁለት አጋጣሚዎች አጀንዳ አቅርበናል፡፡ ፓርላማውም ተወያይቷል፡፡ አጀንዳ የላቸውም ብሎ በዚህ ደረጃ መናገሩ አግባብ አይመስለኝም፡፡  በተደጋጋሚም አጀንዳዎች እየቀረቡ የወደቁበት ሁኔታ አለ፡፡ ገዥው ፓርቲ አብላጫ ድምፅ ስላለው ውድቅ ያደርጋል፡፡ ይሄ አባባል ወደ ኋላ የሚወስደን ነው የመሰለኝ፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በምክንያትና በመረጃ ተደግፈን ውይይት የምናደርግባቸው ቀኖች ከፊታችን እየመጡ ነው በምንልበት ጊዜ ፕሮፖጋንዳ በመሰለ መልኩ አጀንዳና ሀሳብ የላቸውም ብሎ ማቅረቡ ጠቃሚ ጎን አለው ብዬ አላምንም፡፡ አጀንዳዎች አሉን፡፡ ኢሕአዴግ አጀንዳ እየተቀረፀለት ስለሚቀርብ ራሱን የተለየ አካል አድርጎ ቆጥሮ ከሆነ ይሄ ስህተት ነው፡፡ ኢሕአዴግ የራሱን አጀንዳ ቀርፆ ይዞ የመጣበትን ቀን እኔ አላውቅም፡፡ የመንግሥት አጀንዳዎችን በተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ይዞ አምጥቶ ስላፀደቀ ይሄ ከሌሎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለ የሚያደርገው አይደለም፡፡ በራሱ አጀንዳ ቀርፆ አምጥቶ ይሄ ጉዳይ የተወካዮች ምክር ቤት ላይ ተቃዋሚዎቹንም ጭምር አወያይቶ መወሰን አለበት ያለውን አጀንዳ ስለማላስታውስ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ የብድርና የእርዳታ ስምምነቶች በብዛት እንደሚፀድቁ አውቃለሁ፡፡ ከመንግሥት ተቋማት ውጭ በኢሕአዴግ በራሱ ተጠንቶ የቀረበና ያወያየንን ሰነድ አላስታውስም፡፡ ኢደአፓ መድህን በኢኮኖሚ ላይ የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ የአቅም ውስንነትና ችግር ቢኖርበትም የራሱን ጥናት እንደ አጀንዳ አቅርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዴአፓ መድህን ከምርጫ 97 ፖሊሲውና ስትራቴጂው ለዚህ ምርጫ ምን የተለየ ነገር አለው?

አቶ ሙሼ፡
- ፓርቲው ከምርጫ 97 በኋላ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዶ ያለፉትን የስምንት ዓመታት የትግል ዘመኑን ገምግሟል፡፡ በዚህም ደካማና ጠንካራ ጐኖቹን አንጥሮ ማወቅ ችሏል፡፡ ከዚህም በመነሳት ፖሊሲዎቹን ለመፈፀም የሚያግዙትን የአሰራርና የአካሄድ ስልቶች የነደፈበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይሄም ሦስተኛው አማራጭ ብለን የቀረፅነው አሠራር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንቅስቃሴ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅፋት የፈጠረ በተቃዋሚና በገዥው ፓርቲ፣ በገዥው ፓርቲና በውስጡ ባሉት የተለያዩ ድርጅቶች መካከል አልፎ ተርፎም በተቃዋሚዎቹም መካከል እርስ በርሳቸው ከፍተኛ የሆነ አለመግባባት መንስኤ የነበረን አሰራር የሚቀርፍ አካሄድ ነው ብለን ያመንበትን ነገር ለሕዝቡ ይፋ አድርገናል፡፡ በምክንያት መደገፍና መቃወምን ከስሜት የወጣ በመረጃ ላይ ተደግፎ መመስገን የሚገባውን እያመሰገኑ መነቀፍ የሚገባውን እየነቀፉ አልፎ ተርፎም አቅም በፈቀደው አማራጭ ሀሳቦችን እያመነጩ መንቀሳቀስ ትክክለኛው የፖለቲካ ስልት ነው ብለን ነድፈናል፡፡ ይሄንን አሠራር ወደ ሕዝብ አስርፀን ሕዝቡም በዚህ የፖለቲካ አቅጣጫ እየተመራ ተስፋ ሰጭ የሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴና የልማት የእድገት እድል እንዲፈጥር ነው አቅደን የተነሳነው፡፡ ከዚያ በተረፈ የነበሩንን የፖሊሲ አማራጮች እና አቅጣጫዎች የለወጥንበት ሁኔታ የለም፡፡ ፖሊሲዎቹን ለመለወጥ የሚገፋፋን ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ቅንጅቱ በምርጫ 97 የተጠቀመበት የምርጫ ማኒፌስቶ የኢዴአፓ መድህን ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ የኢኮኖሚ እድገቱ፣ የማህበረሰቡ ቁጥር መጨመር፣ የዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታዎች መቀየርን ግምት ውስጥ ያስገባ ተከታታይ የሆነ ማኒፌስቶ ነው መዘጋጀት ያለበት፡፡ አዳዲስ መልካም ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ የማናውቃቸውም ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ ይሄም ሰነዶቹን ለማዳበር ይጠቅማል፡፡ እኛም ሰነዶቹን የምንከልሰው ከ2 ዓመት በኋላ ለሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ነው፡፡ ይሄንን ምርጫ የምንወስደው ገዥው ፓርቲ የሚከተላቸው ፖሊሲዎች ትክክል እንዳልሆኑ የሕዝብን ጥቅም በሚፈለገው ደረጃና መጠን እንደማያስከብሩ የማሳያ ሰነዶቹንም እየፈተሽን ለሚቀጥለው ዝግጅት የማድረጊያ ጊዜ አድርገን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሌሎቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ያላችሁ ግንኙነት በአሁኑ ጊዜ ምን መልክ አለው?

አቶ ሙሼ፡-
ከሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ያለን ግንኙነት ሁልጊዜ እኛ ከመርሀችን በመነጨ ነው የሚነሳው፡፡ መጀመሪያ ጥያቄው ከመብት ነው የሚመነጨው፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በሚያምንበት አስተሳሰብ የሚያምነውን ነገር የማራመድ መብት ስላለው ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ተከባብረን መንቀሳቀስን ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡ ከዚያ በተረፈ በተለያየ መንገድ አጀንዳዎቻችን አንድ ሆነው አብረን ለመሥራት የሚያስችለን እድል ሲፈጠር አብሮ በመሥራት ዙሪያ አጀንዳዎቻችንን በማሳደግ በማጎልበትና በማጠናከር ዙሪያ ለመወያየት ኢዴአፓ መድህን ክፍት ነው መድረኩ፡፡ በጠላትነት የመፈራረጅን አጀንዳ ከምርጫ 97 በኋላ የተዘጋ አጀንዳ ነው፡፡ ቂምና ቁርሾ ይዞ ፖለቲካ ውስጥ መንቀሳቀስ የሚቻልበት እድል አለ ብለን አናምንም፡፡ በተለይ በሰላማዊ ትግል ውስጥ፡፡ ሰላማዊ ትግል የሚያሳየው ወይም ደግሞ የሚመራን በመቻቻልና በመከባበር ነው፡፡ ልዩነቶችም ካሉ ልዩነቶችን ባሉበት የማስተናገድ መርህ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አኳያ ይቅር የመባባል ጉዳይ ሳይሆን ልዩነቶቻችን አሉ ነገር ግን የጋራ ከሚያደርገን አንድ አጀንዳ አለ ሀገራችን ኢትዮጵያና ሕዝቧ፡፡ ይሄን ሕዝብ የጋራ የሚያደርግና ተጠቃሚ የሚያደርገው ጋር በጋራ ለመሥራትና በመወያየት ችግሮችን ለመፍታት ተቀራርቦ ሀሳቦችን የበለጠ ለማዳበርና ሕዝቡ የሚጠቀምበትን እድል ለመፍጠር ሁልገዜም ኢዴአፓ መድህን ዝግጁ ነው፡፡ ማህበረሰቡም እኛን ተከትሎ የማይጋጭበትና እርስ በርሱ የማይሻኮትበት ሁኔታ የማመቻቸት ኃላፊነት አለብን፡፡ ሕብረተሰቡ ሀገሪቷን ከማልማት ይልቅ ልዩነቱን እያጎላ አውጥቶ በልዩነቶቹ ምክንያት ልማቶችን የመርሳት ኃላፊነቱን የመወጣትን ጉዳይ ችላ ሲል ቆይቷል፡፡ ይሄ እንዲቀር እንፈልጋለን፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሀገርን የማልማት ጉዳይ ላይ ልዩነት የለንም፡፡ ልዩነት ካለም የመንገድ ነው፡፡ የእኛ ፓርቲ ከጥምረትና ውህደት ጋር በተገናኘ ያለው ታሪክ መራር ነው፡፡ ፓርቲ ይፈጠራል፣ ይለመልማል ወይም ይከስማል፡፡ ሕዝብ ግን  ለዘለዓለም ይኖራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስንመለከት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ከገዥው ፓርቲ ባለፈ ጨዋነትና ጠንካራ የመቻቻል ባህል አለው፡፡ ይሄ ባህል እንዳይሸረሸር ጥንቃቄ አድርገን መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ለዚህም ምሳሌ መሆን አለብን፡፡   

ሪፖርተር፡- ኢዴአፓ መድህን ካለፈው የጥምረትና ውህደት ታሪኩ መጥፎ ጠባሳ በመነሳት ዳግም ለጥምረትና ውህደት እድል ላለመስጠት ወስኗል ማለት እንችላለን፡፡ ከዚህ አንፃር ገዥውን ፓርቲ በተናጠል መወዳደር ትችላላችሁ?

አቶ ሙሼ፡-
በዚህ ጉዳይ ላይ የምንነሳው ከፓርቲያችን ደንብና ፕሮግራም ነው፡፡ የፓርቲያችን ፕሮግራም የሚያስተላልፈው መልዕክት በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ በሚያደርጉን የፖለቲካ አጀንዳዎች ካሏቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ከመስራት ጀምሮ እስከ ውህደት መሄድ እንደሚቻል ይገልፃል፡፡ ይሄ መርሁ ነው፡፡ መርሁ ወደ መሬት ሲወርድና ሲተነተን የየራሱ ተጨባጭ ሁኔታዎች ስላሉ እንደተጨባጩ ሁኔታ ነው የምናየው፡፡ ግን መራሩ ልምዳችን ወደኋላ ያደርገናል ብዬ አላምንም፡፡ ብዙ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እጅግ የመረረ ከባድ መስዋዕትነት ያስከፈለ ልዩነት ፈጥረው መጥተው በኋላ አንድ ሆነው ተቻችለውና ተከባብረው የሰሩበት እድል አለ፡፡ ይሄ ዓለም ያየው ተጨባጭ ሁኔታ ነው፡፡ በተለያየ ግንባር ላይ ተሰልፈው በጥይት ሲጠዛጠዙ የነበሩ ሁለት ወንድማማች ዜጎች ከዚህ መራር ልምዳቸው ተመልሰው በአንድነት አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ልማትን፣ እድገትንና ብልፅግናን ያመጡበት ተጨባጭ ሁኔታ በዓለም ላይ አለ፡፡ ይሄ ልምድ ለእኛ ትምህርት ነው፡ ይህን ልምድ እንጋራዋለን፡፡ በመርህ፣ በደንብ፣ በስርዓት፣ በሕግ ላይ የተመሰረተና ጠንካራ የሆነ ግንኙነትን የመፍጠር ነገሩ ሁሌም ጠቃሚ ነው፡፡

የኢሕአዴግን መጠናከር በተመለከተ መጠናከር በብዙ መልኩ ይገለፃል፡፡ ማግበስበስም መጠናከር ነው፡፡ ኢሕአዴግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባሎች አሉኝ እያለ የሚናገርበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ማሰባሰብ የጥንካሬ ምልክት ነው ብዬ አላምንም፡፡ በመልክ በቅርፅ በይዘት የማያውቃቸውን አባሎች በተለያየ መንገድ በማስገደድ፣ በማስፈራራት፣ በጥቅም". ሊያሰባስብ ይችላል፡፡ ይሄ ጠቃሚ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስትወስደው ወደ ማዕከል ያተኮረ ሀይል ወደ አምባገነንነት የማምራት እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በጥቂት ሂደቶች ውስጥ "ከእኔ በላይ አማራጭ የለም፣ ልሸነፍ የምችል ፓርቲ አይደለሁም" የሚል ግብዝነትን ሊያመጣበት ይችላል ብዬ እፈራለሁ፡፡ ሰዎች በጥቅም ስለተሰባሰቡ በብድርና በእርዳታ ስርዓቶችና ሕጎች አማካይነት ራሱን፣ ቁመቱንና መጠኑን ስላሰፋ እውነት ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ከሚገባው በላይ መወጣጠር መፈንዳትን ያመጣል፡፡ ይሄ አሠራር ለዴሞክራሲያዊ አሠራር ጠቃሚ አይደለም፡፡ በእውነት በርዕዮተ ዓለሙ ተስበው በአስተሳሰቡ ተገዝተው በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባሎች ኢሕአዴግ መልምሎ ከሆነ ድንቅ ነው፡፡ ይህንን ልንቃወም የምንችልበት ምክንያት የለንም፡፡ ነገር ግን እጅግ ድህነት በተንሰራፋበት የሰው ልጅ ህልውናው የሞት የሽረት በሆነበት ሀገር ላይ በተለያዩ ጥቅሞች በዙሪያው የሚሰባሰቡ ሀይሎችን እንደ ጡንቻ ማፈርጠም በፖለቲካ አግባብ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ኢሕአዴግ ጃፓንና ሌሎች የምስራቅ ኤስያ ሀገሮችን እየጠቀሰ 40 እና 50 ዓመት የመግዛት ፍላጎት እንዳለው የጠቋቆመበት ሁኔታ አለ፡፡ ያ ወደ አምባገነንነት እንዳያመራ ነው ስጋታችን፡፡ አምባገነንነት በራሱ ጊዜ የሚሟሽሽ ነገር በመሆኑ ያን ለማፍረስ እኛ ምንም አንሰራም፡፡ እኛ በሕዝቡ ውስጥ መሠረት ጥለን መራጭ ሀይል እያበረከትን በ10 እና 20 ሺህ የሚቆጠሩ ጠንካራና ጥቂት ካድሬዎችን ይዘን ፖለቲካችንን መስራትን ነው አጠንክረን የምንቀጥለው፡፡
 
< Prev   Next >