| የካቲት11ን ስናከብር "የሰማዕታት"ን አደራ እንዘክ |
|
|
| Wednesday, 20 February 2008 | |
|
33ኛው የህወሓት ምስረታ ቀን ትናንት የካቲት 11 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በሽሬ እንደስላሴ ተከብሯል፡፡ ውሏል፡፡ የዘንድሮው የካቲት 11 ከሌላው ጊዜ ለየት የሚለው ህወሓት ፀረ ደርግ ትግሉን በጀመረባት "ደደቢት" ላይ መከበሩ ነው፡፡
የካቲት 11ና ደደቢት በህወሓት ብቻ ሳይሆን በመላው የትግራይና የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩ ስፍራ ይይዛሉ፡፡ ደርግን የተደመሰሰው በዚች ቀንና በዚህ ስፍራ በተወለደው ትግል ነበር፡፡ ደርግን ማሸነፍ "ተራራን በገመድ እንደመጐተት" ተደርጎ ይታሰብ በነበረውና ሌሎች በርካታ ሕብረ ብሔርና በብሔር ላይ የተመሰረቱ የትጥቅ ትግሎች ተስፋ ያስቆረጠ ወታደራዊ ኃይል ባለቤት የነበረው "ደርግ" በዚሁ ስፍራ በተጠነሰሰው የ17 ዓመት ትግል ሊወገድ ችሏል፡፡ ይህ ሲባል 17 ዓመት ሙሉ የተከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም፡፡ በአስራ ሰባቱ ዓመት ትግል ውስጥ የወደመው ንብረትና የጠፋው የሰው "ሕይወት በርካታ ታጋዮች አልፈዋል፡፡ በርካታ ታጋዮች አካለ ጎደሎ ሆነዋል፡፡ የዚህ ፅሑፉ ዓላማ የየካቲት 11ን ለመግለፅ አይደለም፡፡ ለመግቢያ ተጠቀምኩበት እንጂ መፃፍ የፈለግኩት ሌላ ነው፡፡ በዚህች ቅድስት ዕለትና ስፍራ የተቀመጡ ዓላማዎች ምን ነበሩ? አሁንስ ምን ደረጃ ላይ እንገኛለን? አሁን ያለው እውነታ ምን ይመስላል? ብለን መጠየቁ ተገቢ ነው፡፡ የዛሬ 33 ዓመት ገደማ ህወሓት በዚች "ደደቢት" በተባለች ስፍራ ሲመሠረት አንግቧቸው ከተነሳ ዓላማዎች መካከል እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ ነፃነትና ፍትህ ይገኙበታል፡፡ የደርግን መደምሰሱ ብቻ የመጨረሻው ግብ አይደለም፡፡ ደርግን ከመደምሰስ ባሻገር ቀደምት ታጋዮች (በህይወት የሌሉና በህይወት ያሉት) እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት እንቅፋት የሆነው ደርግ ማጥፋት በእርግጥ ቅድሚያ የሰጡት ዓላማ ነበር፡፡ ከዚያ ባሻገርስ? በዓሉን አስመልክተው ከትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ በርካታ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡ በተለይ ከተሃድሶ በፊትና ከተሃድሶ ወዲህ የነበረውን ችግርና የተገኘውን ለውጥ አነፃፅረዋል፡፡ መንግሥት እስከ አሁን በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከተሃድሶው ወዲህ በገጠሩና በከተማው አካባቢ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች የተሳኩ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ ድርጅታቸው ባደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ለውጥ ማስመዝገቡንም ይፋ አድርገዋል፡፡ አቶ መለስ ከተሃድሶ ወዲህ ድርጅታቸው ባደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ከፍ ያለ ቁጥር ያለው አባል ማፍራታቸውም ገልፀዋል፡፡ እንደ እሳቸው አባባል 36ሺህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ 80 በመቶ የሚሆኑ መምህራንና 4 ሚሊዮን አርሶ አደሮች የኢሕአዴግ አባል ሆነው ተመልምለዋል፡፡ ከተሃድሶ በፊት ድርጅቱ ከ700 ሺህ በላይ ያልሆነ አባል የነበረው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ይህን ያህል አባል ማፍራቱ በሁለት መንገድ ሊታይ ይችላል፡፡ በአንድ ወገን አንድ የፖለቲካ ድርጅት አባላት የማፍራት መብቱ የተጠበቀና ማድረግ ያለበት ቢሆንም ቅሉ በሌላ በኩል አባላት የመለመለበትን መንገድ ማየትን የግድ ይላል፡፡ ድርጅቱ 80 በመቶ መምህራንና 36 ሺህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አባል ማድረጉ በራሱ አወንታዊ ለውጥ ሊሆን አይችልም፡፡ ሲጀመር በመምህራንና በተማሪዎች ያለውን ግንኙነት የትምህርት ግንኙነት መሆኑ ቀርቶ የፖለቲካ ግንኙነት እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት የሚስፋፋባቸው መሆኑን ቀርቶ የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም የሚስፋፋባቸው የፖለቲካ ማዕከል ይሆናሉ፡፡ አባል በሆኑና ባልሆኑ መካከል አለመተማመን፣ የእርስ በርስ ጥርጣሬና መጠቋቋምን ያስከትላል፡፡ መምህራን በተቻለ መጠን ከፖለቲካ ነፃና ገለልተኛ ሆነው በተማሪዎቻቸው ላይ የፖለቲካ ተፅዕኖ ሳያሳድሩ ቢያስተምሩ ይመረጣል፡፡ አባል በሆኑና ባልሆኑት ተማሪዎች መካከል የሚፈጠር ግጭት ቀላል አይደለም፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያለው አጠቃላይ የተማሪ ቁጥር ባላውቅም 36 ሺህ ተማሪዎች የአንድ የፖለቲካ ድርጅት አባል ከሆኑ በግምት ከአራትና ከአምስት ተማሪዎች መካከል አንዱ የኢሕአዴግ አባል ሆኗል ማለት ነው፡፡ የአባል ምልመላ ሂደቱ የትምህርቱን ሂደትና የአካዳሚክ ነፃነት በሚጋፋ መልኩ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢሕአዴግ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች አባል ሲያደርግ ሌሎች ሕጋዊ ተቃዋሚዎች አባል የመመልመል እኩል ነፃነት አላቸው ወይ? የተመለመሉ አባላትስ ዲሲፕሊናቸው ምን ያህል ነው? ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል፡፡ ሌላ ጎን ለጎን መነሳት ያለበት ጥያቄ እነዚህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አባል የሆኑት የድርጅቱን ርእዮተ ዓለም አምነውበትና በፍላጎታቸው ነው? የሚለውን ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ እንዳነሳ የገፋፋኝ ከሁለት ዓመት በፊት በመቀሌ ከተማ በትግራይ ክልል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተሰብሰበው ከህወሓት ባለስልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ ሁሉም አባል እንዲሆኑ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር አባል ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ተማሪዎቹ አባል የሆኑበት ዋናው ምክንያት ሥራ እንዳያጡ በመፍራት እንዲሁም አባል ለመሆን ፈቃደኛ ያልሆኑ ተማሪዎች "በቅንጅትነት" ወይም "በአንጃነት" የመፈረጅ ስጋት ስላደረባቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ በአንዳንድ አካባቢዎች በሹመት፣ በውጭ ዕድልና ዕድገት፣ የሥራ ቅጥር ላይ የአባልነት "ግሪን ካርድን" የሚሰራበት ሁኔታ እየታየ ስለሆነ አቅጣጫው ጥሩ አይሆንም፡፡ ይህ በፍፁም መወገድ ያለበትና ከየካቲት 11 ዓላማዎች ጋር የማይጣጣም ነው፡፡ በወቅቱ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ተማሪው ሁለት አማራጮች ብቻ እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ የመጀመሪያው አብዮታዊ ዴሞክራሲና ብቸኛው ዴሞክራሲያዊ መስመር መከተል ሲሆን በተቃራኒው የተቃዋሚዎች መስመር እሳቸው ፀረ-ዴሞክራሲ ያሉትን ነው፡፡ ተማሪው ይህንን "አባል ወይም ጠላት ሁን" የሚለው አስተሳሰብ መቃወምና መከራከር የነበረበት ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥትን ወክለው ይህንን ማለታቸው ግን አግባብ አልነበረም፡፡ በተማሪው ዘንድ "አባል ያልሆንክ ቦታ የለህም" ዓይነት መልእክት ያዘለ በመሆኑ በዚህ መንገድ አባል የሆነው በተፅዕኖ በመሆኑ አካሄዱ በማንኛውም መንገድ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ሶስተኛ አማራጭ፣ ገለልተኛ መሆንም የማይፈቅድ መንገድ ነው፡፡ ይህንን አስተሳሰብና አመለካከት እንደእኔ "ተሃድሶ" ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ሂደት በተማሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በአርሶ አደሮችም ላይ ተመሳሳይ ስሜት ፈጥሯል፡፡ አንድ ሰው አባል በመሆኑ በዕርዳታ፣ በብድርና በሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ቅድሚያ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዳለ ከአርሶ አደሮቹ መገንዘብ ይቻላል፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ንግግር ከሆነ በገጠሮች አካባቢ ያለውን ልማትና መልካም አስተዳደር ከከተማው በሁለት እጥፍ በልጧል፡፡ በገጠሩ አካባቢ ያሉት የልማት እንቅስቃሴዎች አበረታች መሆናቸው አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል መልካም አስተዳደርና ፍትህ አለ ማለታቸው በቂና ትክክለኛ መረጃ ደርሷቸዋል ወይ እጠራጠራለሁ፡፡ ባለፈው ዓመት ከተለያዩ ክልሎች (ከትግራይ፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያና ከደቡብ) የተውጣጡ ያሉበት ቡድን ወደ ትግራይ ክልል ጉዞ አድርጎ ነበር፡፡ ቡድኑ ከትግራይ ተራ አርሶ አደሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የተወያየ ሲሆን አርሦ አደሮቹን ጠይቆ ያገኛቸውን መልሶች ግንቦት 1999 ዓ.ም በታተመው ወይን መጽሔት ላይ እንመልከት፡፡ በወረዳ ክልተወላዕሎው ቀበሌ አዲቅሳንዳድ ነዋሪ የሆኑ "የልማት አርበኛ ተብለው ለተሸለሙ" አርሶ አደር ቡድኑ ያቀረበላቸው ጥያቄ "እውነት ልማት አለ ወይ?" የሚል ነበር፡፡ የልማት ችግር እንደሌለ ገልፀው "ግን አንድ ችግር አለ" ማለታቸው የቡድኑን ቀልብ መሳቡን መጽሔቱ ያትታል፡፡ "ግን አንድ ችግር አለ" ያሉት አርሶ አደሩ "ፍትህ የለም፣ መልካም አስተዳደር የሚባል የለም፡፡ ፣ውድብና፣ (ድርጅታችን) ዛፍ ስር ሆኖ ፍርድ ሲሰጥ፣ ፍትህ ያኔ ቀረ፡፡ ልጆቻችን ወደ ህንፃ ከገቡ ጀምሮ ፍትህ እምቢ ብሏቸዋል"". ማለታቸው ቀላል ንግግር አይደለም፡፡ ድሮ የነበረው የፍትህ አሰጣጥ፣ ሃቀኝነት፣ ቅልጥፍና፣ ግልፅነት አሁን ካለው ጋር አነፃፅረው ማብራራታቸው በገጠራማ የአገራችን ክፍል የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት ለመበራከቱ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ ቡድኑ ጉብኝቱን በመቀጠል ወረዳ እንዳሞኸኒ ደርሷል፡፡ መጽሔቱ እንደዘገበው ተጠያቂዎቹ "ቅሬታችንን፣ ብሶታችንን የሚሰማ አካል የለም" ብለዋል፡፡ አድሎ፣ መደለል፣ ማጓተት". የመሳሰሉ ችግሮች መኖራቸው ተጠያቂዎች ያለአንዳች ልዩነት መናገራቸው ቡድኑን አስደንቋል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ አርሶ አደሮቹ ፊታቸው ላይ ብሶት እንዳለባቸው እየተነበበ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ሌላ ችግር እንዳያስከትልባቸውና የፓርቲው አባላት እንዳይሰሟቸው በመስጋት በድፍኑ "ምንም ችግር የለብንም" ብለዋቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ለመናገር ምክንያታቸው ሲገልፁ፣ "ተናግረን ምን እናመጣለን፣ እነ እገሌ ሌቦች፣ ሙሰኞች ናቸው ብለን ተናግረን ስናበቃ ተመልሰው በመሾማቸው እየተበቀሉን ነው፡፡ ዝምታ ይሻላል" ብለዋል፡፡ በርካታ አርሶ አደሮች ከላይ እስከታች ካሉት ሹማምንት/አስተዳደሮች በዝምድና የተሳሰሩ በመሆናቸው እርስ በርሳቸው እንደሚጠባበቁ ገልፀውላቸዋል፡፡ ሕዝብ እነዚህ ጉበኞችና ብልሹ አስተዳዳሪዎችን ሊያጋልጥበት የሚችል መድረክ (ገምጋም) ከማጣቱም ባሻገር የሆነ አጋጣሚ ተጠቅመው የሚገመግሙ አርሶ አደሮች በአስተዳዳሪዎች "አቃጣሪዎች"፣ "ቡድነኞች" "ፀረ-ልማት" ወዘተ. የሚል ስም ስለሚለጠፉባቸው አንገታቸው እንዲደፉ ተደርገዋል፡፡ በተለየ አንድ ወጣት አርሶ አደር "".ፍትህ ጠምቶናል፡፡ ከዚህ በላይ ምንም ማለት አንችልም" በማለት በአጭሩ "በሉ ደህና ሁኑ"". ብሎ ከጐብኚዎቹ ሸሽቷል፡፡ ይህ አርሶ አደሮቹ ፍትህ ማጣታቸው ብቻ ሳይሆን ችግር አለ ብለው በተናገሩ ሰዎች ላይ የሚወሰድ እርምጃ ቀላል እንዳልሆነ የሚያሳይ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ በልማት እንቅስቃሴዎችም ሕዝቡ እንደ ውኃ ማቆርና ሌሎች ሥራዎች እንዲሰራ የሚደረገው የአካባቢው አስተዳዳሪዎች አርሶ አደርን አሳምነውት ሳይሆን በማስፈራራትና በማስገደድ መሆኑን ለቡድኑ ገልፀውለታል፡፡ የትግራይ ሕዝብ የሚወዳቸው ልጆቹን ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህና ለእኩልነት". ገብሮ እንዲህ መልካም አስተዳደር፣ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትና ዴሞክራሲ ሲስተጓጎሉበት ምን ማለት ይቻላል? የሌሎች ክልሎች ሁኔታም ከዚህ እንደማይለይ በመገመት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገጠራማ አካባቢ መልካም አስተዳደር ሰፍኗል ማለታቸው በገጠሩ የሚኖር ሕዝብ ለሚዲያ ቅርበት ስለሌለው አልሰማቸው እንደሆነ እንጂ ይታዘባቸው ነበር፡፡ እንዲሁም ከአዲስ ተቃዋሚ ፓርቲ መምጣት ጋር ተያይዞ ህወሓት ስጋት ስላደረበት በሁሉም ቢሮዎች የሚገኙ ሠራተኞች አባል እንዲሆኑ ማስገደድ፣ የፓርቲው አባል ያልሆኑትን ማስፈራራት፣ ማጥላላት ለዴሞክራሲ ማስፈን 17 ዓመት በትጥቅ ትግል፣ 17 ዓመት በስልጣን ከቆየው ፓርቲ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ በቅርቡ ከአቶ ፀጋይ በርሀ የተሰጠው መግለጫ አዲሱ ፓርቲ የማጥላላት ዘመቻና በየደረጃው የህወሓት አባላት እየተወያዩበት የሚገኘው ከህውሓት ጽ/ቤት የወጣው ተመሳሳይ ዓላማ ያለው መመሪያ የየካቲት 11 መርሆዎችን የሚፃረር ነው፡፡ ይህ "እንዴት እንዋጋቸው" የሚል መምሪያ በምንም መልኩ ጤነኛ አስተሳሰብ ሊሆን አይችልም፡፡ መቃወም የዴሞክራሲ መርህን ፈለግ እንጂ ፀረ ዴሞክራሲነት አይደለም፡፡ የተቃዋሚ ኃይል መኖር የመድብለ ፖለቲካ ግንባታ መሠረት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የሃሳብ ልዩነት በማይከበርበት ሁኔታ ዴሞክራሲ አለ ማለት ቅዠት ነው፡፡ ህወሓት የካቲት 11 ሲያከብር በዚች ቀን ቃል የገባቸውን የዴሞክራሲ መርሆዎች ካላከበረ በዓሉ ከጭፈራና ከፈንጠዝያ በላይ አይዘልም፡፡ በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ቢያንስ እየተሞከሩ ያሉት የዴሞክራሲ መርሆዎች የትግራይ ሕዝብም ሊቋደሳቸው ይገባል፡፡ የካቲት 11 ስናከብር ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ ፀረ ደርግ በተካሄደው የትጥቅ ትግል ቆይተው በመጨረሻ በተለያዩ ምክንያት ተቀናሽ የሆኑት ተጋዮችና አካለ ጎደሎ የሆኑ ጀግኖች በአሁኑ ወቅት የተረሱ ይመስላል፡፡ በተለይ ለብሔር ስብጥር ከውትድርና ዓለም እንዲሰናበቱ የተደረጉ ታጋዮች ምንም የመልሶ ማቋቋሚያ እገዛ ስላልተደረገላቸው ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀው ይገኛሉ፡፡ አካላቸው በመጉደሉ መሥራት የማይችሉ የትናንትናው ጀግና ታጋዮችም በሕብረተሰቡና በመንግሥት በቂ ትኩረት አግኝተዋል ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ ደግሞ የሴት ታጋዮች የወጣት ዕድሜያቸው በትግል የጨረሱት በመሆኑ በተለይ አንዳንዶቹ ኑሮአቸውን ለማሸነፍ አቅቷቸው እንደሚገኝ በርካታ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ እነዚህን ወገኖች መርሳት ያለፈውን ታሪክ እንደመርሳት መሆኑ ታውቆ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የትግራይ ሕዝብ እንደተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ሃሳብ የመያዝ መብቱ፣ አማራጭ የማግኘት፣ ሙሰኞችን ወደ ፍርድ የማቅረብ፣ የመፃፍ፣ የመደራጀትና ሃሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብቱ ሊከበርለት ይገባል፡፡ "ክብርና ሞገስ ለሰማዕታት" ስንል የተሰው ታጋዮችን አደራ እንዘክር፡፡ በየማነ ናግሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |