Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow ለቆዳ ኢንዱስትሪዎች ብድር...
ለቆዳ ኢንዱስትሪዎች ብድር... Print E-mail
Wednesday, 20 February 2008
ለቆዳ ኢንዱስትሪዎች ብድር የእፎይታና የመመለሻ ጊዜ እንዲራዘም ተጠየቀ

ፋብሪካዎች የመበደር አቅም ውሱንነት አለባቸው


የኢትዮጵያ ቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር ሊቀመንበርና የባህር ዳር ቆዳ ፋብሪካ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይግዛው አሰፋ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ የቆዳ ፋብሪካዎችን ለማስፋፋትም ሆነ አዳዲስ ለመገንባት ብድር በሚፈለገው ወቅትና ጊዜ የማግኘት ችግር አለባቸው፡፡
በወጪ ንግድ ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የባንክ ወለዱ ከሌሎች ባነሰ 7.5 በመቶ የእፎይታ ጊዜው 3 ዓመትና ክፍያው በ10 ዓመት እንዲጠናቀቅ ቢደረግም ለማስፋፋት በሚደረገው ሂደት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ተመቻችተው ስለማይገኙ የእፎይታ ጊዜውን መጨመር አስፈላጊ እንደሆነ አቶ ይግዛው ተናግረዋል፡፡

በተበዳሪ ኢንዱስትሪዎች የመበደር አቅም ውሱኑነት እንዳለ የገለፁት አቶ ይግዛው ለማስፋፊያ ሥራ ከሚፈለገው ገንዘብ 30 በመቶ ድርጅቶች ማዋጣት ስለሚጠበቅባቸው ይህን ካፒታል የማግኘት ችግር በማስፋፋት ሥራ ውስጥ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፋብሪካዎችን አቅም ለማስፋፋት በተለየ ትኩረት የብድር አገልግሎት የሚሰጠው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብቻ ሲሆን በመንግሥት በኩል የገንዘብ አቅርቦት ችግር እንደሌለ ቢገለፅም ብድር በማግኘት ሂደት አሰራሩ ቀልጣፋ እንዲሆን ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም የማህበሩ ሊቀመንበር ገልፀዋል፡፡

በዘርፉ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚያስፈልጋቸው የጥራት፣ የግብይት፣ የካፒታልና የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግሮች እንዳሉ አቶ ይግዛው ገልፀው እነኚህን ለማስተካከል የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም በቂ እንዳልሆኑና ተጨማሪ ጥረት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከውጪ ንግድ 50.4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱንና  ባለፈው አመት ከተገኘው 40.3 ሚሊዮን ዶላር የ25 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም አቶ ይግዛው ገልፀዋል፡፡ ክረስትንና ያለቀላቸው ቆዳ የቆዳና ውጤቶች ወጪ ንግድ 18.1 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ይህ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 13.2 ጋር ሲነፃፀር በ37፤ በመቶ ማደጉንም የማህበሩ ሊቀመንበር ተናግረዋል፡፡

የጥራትና የግብይት ችግር በአጭር ጊዜ የሚፈታ ስላልሆነ በአገር ደረጃ ለውጥ ለማምጣት ሰፊ አቅምና ጊዜ እንዲሁም የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ሲገልፁ ግብይቱ አብዛኛው ሰው የሚሳተፍበት መሆኑና የጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይት በአንድ ቦታ አለመሰባሰቡ በአስተዳደር ላይ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ ከብቶች በበሽታ መጠቃታቸው በተለይ የእከክ በሽታ በቆዳ ጥራት ላይ ችግር መፍጠሩም አቶ ይግዛው ገልፀዋል፡፡

በዘርፉ ማግኘት የሚገባንን ገቢ እንዲገኝ ሰፊ ሥራ እንደሚያስፈልግም ተገል"ል፡፡ የሰለጠነ የሰው ኃይልን በተመለከተ በአገር አቀፍ ደረጃ እያሰለጠነ የሚያወጣው የማሰልጠኛ ተቋም በቅርብ ጊዜ በመቋቋሙ እንዲያድግ መምህራንና አስፈላጊ ቁሳቁሶች ሊሟሉ እንደሚገባና ይህ ሲሆን ብቻ ከፍተኛ ባለሙያዎችን ሊያፈራ እንደሚችል አቶ ይግዛው ጠቅሰዋል፡፡

 ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳ ወደ ውጪ መላክ የተከለከለ ቢሆንም የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን መታየት ካለባቸው ሕግጋት ማንኛውም አገር ያለውን ምርት አለመላክ በጎ አመራር አለመሆኑ በመታወቁ ጥሬ ቆዳ መላክ በፓርላማ ፀድቋል፡፡ ይህ ሁኔታ በቆዳ ፋብሪካዎች ላይ ተፅዕኖ አይፈጥርም ወይ ብለን ለጠየቅናቸው አቶ ይግዛው ሲመልሱ ጥሬ ቆዳን 150 በመቶ ታክስ ከፍሎ እንዲላክ መደረጉ የጥሬ ዕቃ እጥረት ያጋጥማል የሚል ሥጋት እንደማይፈጥር፣ የታክሱ ከፍተኛነት በፊት ከነበረው የአሰራር ለውጥ ቢያመጣ እንጂ ውጤቱ ተመሳሳይ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በቆዳ ፋብሪካዎች ተሠርቶ ሲላክ የነበረው ፒክል፣ ዌት ብሉ (የፍየል ሌጦና) በበሬ ቆዳ ላይ በእያንዳንዳቸው የ10 በመቶ፣ የ5 በመቶና የ20 በመቶ ታክስ በመክፈል ወደ ውጪ እንዲላክ መወሰኑን በተመለከተ የታክሱ አላማ ወደ ውጪ ሲላክ የነበረው በከፊል የተለፋ ሌጦ በመሆኑ ካለው የእንስሳት ኃብት ማግኘት የሚገባንን የውጭ ምንዛሪ ባለማግኘታችን የመጣ መሆኑን የገለፁት አቶ ይግዛው ክረስትና ያለቀላቸው የቆዳ ምርቶችን ለማሳደግ ያልተዘጋጀ ቆዳ በሚልኩ ምርቶች ለመሸጋገር ለማበረታታት አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ገልፀዋል፡፡

በወጪ ንግድ ላይ ተጨማሪ እሴት ያላቸውን ምርቶች ለማበረታታት በጥሬ ዕቃ እጥረት ማስገኘት የሚገባቸውን ምርቶች አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ በጎ ተፅዕኖ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ በተለይ ቆዳ ፋብሪካዎች የአሰራር ለውጥ እያደረጉ ሲሆን ወደ ክረስትና ያለቀለት ቆዳ ለማሸጋገር መሳሪያ በመግዛት፣ ሠራተኛ በማሰልጠንና በአለም አቀፍ ገበያ ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ገልፀው በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመፍታት በኩል ትኩረት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የምርት ቅብብሎሽን በሚመለከት ሁሉም ፋብሪካዎች በአንድ ጊዜ ያለቀለት ምርት የማምረት ሁኔታን መፍጠር አስቸጋሪ እንደሆነ አቶ ይግዛው ገልፀው ተጨማሪ እሴት ወዳላቸው ለመሸጋገር በተለያዩ የምርት ደረጃ የሚገኙ ምርቶችን የመቀባበል ሂደቱ አናሳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዘርፉ ወደፊት እየተጠናከረ መሄዱ በአንዳንድ ማምረቻዎች ላይ ያለውን ርብርብ እንዲቀንስና የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር እንደሚስችልም ተናግረዋል፡፡ ሂደቱ በቅርቡ በመጀመሩ ጥሬ ቆዳ የማምረትና ያለቀለትን ቆዳ የማምረት ሂደትና ጊዜ ለማጥበብ እንደሚያስችል ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል፡፡

ለመንግሥትና ለግል ፋብሪካዎች የሚሰጠው እገዛ እንደሚለያይ ለተነሳላቸው ጥያቄም፣ በመንግሥት እጅ ያሉ ፋብሪካዎች ቁጥር አናሳ መሆኑንና የጋራ አገልግሎቶችን ገበያ በሚመለከት ለመንግሥት ፋብሪካዎች በተለየ የሚደረግ የጎላ ነገር አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ልታገኘው የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ያለቀላቸው ቆዳ ምርቶች ድርሻ ማደግ እንዳለበትና ለዚህም አዳዲስ ምርቶቻችን በአለም አቀፍ ገበያ ታዋቂነት አግኝተው ጥሩ ገበያ እንዲያገኙ በተለያዩ የአውሮፓ እስያ በንግድ ትርዒቶች ላይ ተሣታፊ በመሆን ምርቶችን ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን በአለም አቀፍ ባዛርና ኤግዚቢሽን ለማቅረብ የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ መሆን እንቅፋት ሆኖባቸው መቆየቱን ገልፀው ከመንግሥት አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት የሚያስፈልገውን ወጪ መንግሥት ለመጋራት ፈቃደኛ መሆኑ መልካም ጅምር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ በተካሄደው የመላው አፍሪካ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የንግድ ትርዒት በርካታ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን አበረታች መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ያለቀለት ምርት ድርሻ እያደገ ሲሄድ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ገበያ አስፈላጊነት አዳዲስ ጫማ ፋብሪካዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸው ከውጪም ኢንቨስት ለማድረግ እንቅስቃሴ የጀመሩ ፋብሪካዎች መኖራቸው ተወዳዳሪ አቅም ለመገንባት ሰፊ ሥራ እንደሚያስፈልግ አመላካች መሆኑን አቶ ይግዛው ተናግረዋል፡፡

በጥሬ ቆዳ ጥራትና የግብይት ሁኔታ በማስተካከል የጥራቱ ችግር ለመፍታት ያለው እንቅስቃሴ በጅምር ላይ መሆኑንና በመንግሥትም ሆነ በሴክተሩ ኃይሎች ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

ተወዳዳሪነት በአገር ውስጥ ከሚቋቋሙት ብቻ ጋር ሳይሆን ውጭም ከሚቋቋሙት ጋር እንዲሆን በጥራት፣ በአቅርቦትና በዋጋ ተወዳዳሪ ለመሆን የሰው ኃይል ብቃትን የመሳሪያ አቅርቦትን አቅምን በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግና የማሰልጠኛ ተቋሙ አቅሙ እንዲያድግ ለማብቃት ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ተወዳዳሪ አቅም ለመገንባት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችንም በመለየት መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊነት ተናግረዋል፡፡

በቤዛዊት ሥዩም
 
< Prev   Next >