| ክቡር ሚኒስትር |
|
|
| Wednesday, 20 February 2008 | |
|
(መንግሥት ሕዝቡን በየክፍለ ከተማው እየሰበሰበ ማነጋገር ተያይዞታል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩም በዚሁ ፕሮግራም የሕዝብ ብሶት ለመስማት በአንዱ ክፍለ ከተማ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋላ ጥያቄ እየቀረበላቸው ይመልሳሉ)
- የሕዝብ ብሶት እንሰማለን ስንል ሰምተን ዝም ለማለት አይደለም፡፡ አጥጋቢና አስቸኳይ መፍትሔ ለመስጠት ነው፡፡ የንግግሬ ማጠቃለያም ይኸው ነው፡፡ (ተጨበጨበ) - ቢኒያም እባላለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡ እጅግ በጣም ደስ የሚል ንግግር ነው ያደረጉት፡፡ እውነት ግን ሥራ ላይ ይውላል? - እንዴት አይውልም? ይውላል እንጂ፡፡ ኢሕአዴግ የማያደርገውን አደርገዋለሁ አይልም፡፡ ሳይናገር የሚያደርገው ሊኖር ይችላል? ተናግሮ የማያደርገው ግን የለም፡፡ - ክቡር ሚኒስትር መልካም አስተዳደር አሰፍናለሁ ብሎ ነበር እኮ፤ - ይኸው እየሰፈነ አይደል፡፡ - ክቡር ሚኒስትር መልካም አስተዳደር ማስፈን ማለትኮ ጉቦኛውንና ቀማኛውን ማጥፋት ማለት ነው፡፡ - ገባኝ፡፡ እሱንም እያደረግን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ እሑድ እሑድ የፖሊስ ፕሮግራም የምትከታተሉ ከሆነ በየሰፈሩ ያለ ሌባ፣ ቦዘኔ፣ በርበሬና አፈር ደባልቆ የሚሸጥ ቀማኛና አጭበርባሪ እየተከታተልን እያደንን መሆናችን ታረጋግጣላችሁ፡፡ ገባህ አቶ ቢኒያም? - ክቡር ሚኒስትር ከእንዲህ ዓይነት ወንጀለኞች በላይ ሥልጣን ላይ ያሉ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ መልካም አስተዳደር ማስፈን ማለትኮ በእነሱ ላይ እርምጃ ወስዶ ማፅዳት ማለት ነው፡፡ በርበሬና አሸዋ የደባለቁ ላይ ብቻ መገታት ምን ዋጋ አለው ክቡር ሚኒስትር? - እሱማ ምን ጥያቄ አለው፡፡ ይህ መንግሥትኮ ከጫካ ጀምረው አብረው የታገሉትንም ያሳሰረና ያስፈረደ ነው፡፡ ምን ጥያቄ አለው፡፡ - አይደለም፣ አይደለም ክቡር ሚኒስትር... ይቅርታ ሳይፈቀደልኝ ተናገርኩ፡፡ ተናድጄ ነው፡፡ እሌኒ እባላለሁ፡፡ - ግድ የለም ቀጥይ ያናደደሽን ተናገሪ፡፡ - ክቡር ሚኒስትር እኛ በጋዜጣ ነው የምናነበው፡፡ በአገር ወርቅ እኮ እየተቀለደ ነው፤ - የወርቅ ማዕድን ለማስፋፋት ፕሮጀክት እየተቀረጸ ነው፤ - ክቡር ሚኒስትር የወርቅ ማዕድን ማስፋፋቱ ጥሩ ነው፡፡ እኔ የምለው ግን ወርቅ ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ እየተጭበረበረ አገርና ሕዝብ ከሚጠቀምበት ይልቅ አገርና ሕዝብ መሳቂያ መሳለቂያ ሆኗል ነው፡፡ - እኮ.. ወርቅ የአገር መኩሪያ ይሁን ብሎ ኢሕአዴግ ተነስቷል፡፡ - ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር ራሄል እባላለሁ፡፡ ነገሩን የተረዱት አይመስለኝም፡፡ በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር የአገር ወርቅ ወደ ውጭ ሄዶ ተሸጦ አገርን እንዲያሳድግ ሲጠበቅ ባሌስትራ ሆኖ ተገኘ፡፡ አትራፊ ከመሆን ይልቅ በሕዝብም አክሳሪ፣ በታሪክም አሳፋሪ እየሆነ ነው ማለትዋ ነው እሌኒ፡፡ መንግሥት ምን እያደረገ ነው? - አጭበርባሪን እያሳደደ ነው፡፡ ራሄል ገባሽ? - እኔ ገብቶኛል፣ እርስዎ ግን የገባዎት አይመስለኝም? - ገብቶኛል፡፡ አጭበርባሪ ያመልጣል ብለሽ አታስቢ፡፡ ከገባበት ገብተን እናወጣዋለን፡፡ - በሚገባ የተገነዘቡት አይመስለኝም፡፡ - እንዴት? - ክቡር ሚኒስትር በአሁኑ ጊዜ እጮኛዬ የሚሰጠኝ የጋብቻ ቀለበትም አላምነውም፡፡ - እንዴት አታምኝውም? - ባሌስትራ እንዳይሆን ነዋ (ቤቱ ሳቀ) - በእኔ ይሁንብሽ አጭበርባሪ ይያዛል፡፡ የመንግሥት ትኩረት በግልፅ ልንገራችሁ ወርቅ ላይ አይደለም እንጀራ ላይ ነው፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ወደ እንጀራ መቀየር የነበረበት ወርቅ ተሰረቀ ነው እኮ የምንለው፡፡ - እኔም የሰረቀ ይያዛል ነው ያልኩት፡፡ አሁን የሻይ እረፍት እናድርግና እንቀጥላለን፡፡ (በሻይ እረፍት ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ይነጋገራሉ) - ስብሰባውን እንዴት አየኸው? እኛ ስለ እንጀራ እያወራን ሰዉ ግን ስለ ወርቅ ያወራል፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ያልገባዎት ነገር አለ፡፡ - ምንድን ነው ያልገባኝ? - ሰው ስለወርቅ ያንገበገበው ነገር አለ፡፡ - ምንድነው ያንገበገበው? ወርቅ እኮ የጥቂቶች እንጂ የሕብረተሰቡ አጀንዳ አይደለም፡፡ - አልገባዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እስቲ ያልገባኝን አስረዳኝ፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ሰው ስለወርቅ የሚያነሳው ባለፈው ጊዜ በወርቅ ምክንያት ኢትዮጵያ 200 ሚሊዮን ብር ከሰረች ተባለ፡፡ ቀጥሎ 65 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ወርቅ ድንበር ሲያሻግር ተያዘ፡፡ 41 ኪሎ የሚመዝን ባንክ የገባ ብረት ወርቅ ነው ተባለ፡፡ ወደ ውጭ የሚላከው ወርቅ ሲከፈት ባሌስትራ ሆኖ ተገኘ ተባለ፡፡ ይህ ሁሉ የሕብረተሰቡ መነጋገሪያ ሆኗልኮ፡፡ - መቼ ነው እንዲህ የሆነው? - ክቡር ሚኒስትር የከተማው ወሬ ሁሉ እኮ እሱ ሆኗል፡፡ - እንዴት አልነገርከኝም? - ነግሬዎት ነበር፡፡ - ምን ብለህ? - መንግሥት የራሱን መስሪያ ቤት ይፈትሽ፡፡ ብሄራዊ ባንክን ይፈትሽ እያለ ነው ብዬ፡፡ - በሌላ ቦታም ስለወርቁ ሰው ያወራል ማለት ነው? - አዎን ከአርሰናልና ከማንቸስተር በላይ ስለወርቅና ስለባሌስትራ የሚያወራ በእጅጉ በዝቷል፡፡ - ወደ ማንቸስተር ወርቅ ልከናል እንዴ? - ከእግር ኳስ በላይ ስለወርቅ ይወራል ማለቴ ነው፡፡ - እ... የጋብቻ ቀለበትም ባሌስትራ እንዳይሆን ፈራሁ ብላኮ ቀለደች፡፡ - ቀልዷን አይደለም፡፡ እርሶም የወርቅ እስክርቢቶ ነው ብሎ ያ ነጋዴ የሰጠዎትን ስጦታ ባሌስትራ እንዳይሆን ያስመርምሩት፡፡ - በል፣ በል ጣጣ ውስጥ አስገባኛ፡፡ - የምን ጣጣ? - ሳስመረምር ደግሞ ወርቅ ጉቦ ተቀብለሃል ይበሉኝ እንዴ? - ሰውየው ወርቅ ቢለኝም የውሸት ወርቅ ነው ብዬ ነው እንደተራ እስክርቢቶ የተቀበልኩት ብለው ይከራከራሉ ችግር የለም፡፡ (ስብሰባውን ጨርሰው ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ አንድ ነገር አጋጠማቸው) - ጤና ይስጥልኝ ጋሼ ዮሐንስ ባነጋግርዎት አልሰሙኝም፡፡ - ሰምቻለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እና ሰምተው ነው ዝም ያሉት? - ልክ እንደእናንተ፤ - እንዴት ልክ እንደእናንተ? - እናንተ ሰምታችሁ ዝም እንደምትሉት፣ እኔም ሰምቼ ዝም አልኩ፡፡ - ለምን? - አዝኜ ነዋ፡፡ - ምን ሆኑ? - ክቡር ሚኒስትር በቴሌ ሙስና ብላችሁኮ ልጄን አሰራችሁት፡፡ - ታዲያ ምን ችግር አለ? ንፁህ ከሆነኮ ነገ ይወጣል፡፡ - መቼ ወንጀለኛ ያዛችሁና ነው ንፁህን የምትለቁት፡፡ - ሽርደዳው ወይም አሽሙሩ አልገባኝም? - የምን ሽርደዳ ክቡር ሚኒስትር አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀውና ሁሉም የሚያወራውኮ ነው፡፡ - ምኑ? - ዘመድ ያላቸው፣ የባለሥልጣን ድጋፍ ያላቸው ኃላፊዎች ሳይነኩ፣ ሳይታሰሩ ከእነሱ በታች ያሉትን አሰራችሁ.. ልጄን፡፡ - አልገባኝም ግልፅ ያድርጉልኝ፡፡ - ዋናውን ሌባ ትታችሁ ሌላውን ታስራላችሁ ማለቴ ነው፡፡ - ይቅርታ እኔ መኪና ውስጥ ሆኜ በመስኮት ከማነጋግርዎት ሌላ ጊዜ በስፋት እናወራለን፡፡ - እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡ (ሾፌራቸውን ይጠይቃሉ) - ምንድነው እስከዚህ ምርር ያደረጋቸው? - እንዴ ክቡር ሚኒስትር ሰውዬው አገር ሁሉ እየሳቀበትና እየተናደደበት ያለ ጉዳይኮ ነው ያነሱት፡፡ - ምንድነው ነገሩ? - ራሱ የቴሌ የውጭ ኦዲተር ያወጣው በቢሊዮን ተጭበረበረ ያለው የቴሌ ጉዳይ ዋናው አዛዥና ሥራ አስኪያጁ የነበሩት ሳይያዙ እየተንፈላሰሱና ወደ ውጭ እየተመላለሱ ሌሎች መታሰራቸው ጉድ አሰኝቷል፡፡ - ለምን አልነገርከኝም? - ነግሬዎታለሁ ክቡር ሚኒስትር ይህ አካሄድ አደገኛ ነው፡፡ ሕዝቡ ዘመድ ያለው አልታሰረም ሌላው ነው የታሰረው እያለ ነው ብዬ፡፡ - እና እኔ ምን አልኩህ? - “የምቀኝነት ባህል አልለቅ ብሎ እየተጠናወተን ነው” አሉኝ፡፡ - ዘርዘር ግልጥልጥ አድርገህ አልነገርከኝማ! - ኧረ ዘርዘር አድርጌ ነው የተናገርኩት፡፡ - ሥራ በዝቶ አልሰማሁህም ማለት ነው፡፡ በል ዛሬ አድካሚ ቀን ስለነበር ቤቴ ገብቼ አረፍ ልበል፡፡ (ቤት ገብተው ተጣጥበው እራት በልተው ከባለቤታቸው ጋር ሳሎን ተቀምጠዋል) - ምን ነው ዘጋሽ? - የእናንተ ሥራ ነዋ! - የእናንተ ስትይ? - እህቴ መጥታ አብዳ አብዳ ነው የሄደችው፡፡ እኔም ራሴን አሞኛል፡፡ - ምን ሆንኩ አለች? - የልማት ባንክ ጉዳይ ነዋ! - ልማት ባንክ ምን ሆነ? - 32 ሚሊዮን ብር አተረፍኩ ብሎ ሪፖርት ሲያቀርብ ብሄራዊ ባንክ አትዋሽ እንኳን ልታተርፍ ኪሣራህ 700 ሚሊዮን ብር ደርሷል ብሎ መለሰለት፡፡ - ትቀልጃለሽ፡፡ - እንዲውም ኪሳራው አንድ ቢሊዮን ብር ይደርሳል ተብሏል፡፡ ይህ እህቴን አሳብዷታል፡፡ - ለምን ከሰራችሁ እንባላለን ብላ ነው? ልማት ባንክ ነው የምትሰራው አይደል፡፡ - ለምን ከሰራችሁ ተባልን አይደለም? - ታዲያ ምን ሆና ነው? - ይህ ችግር እንዳለ በተደጋጋሚ ተናግሬ የሚሰማኝ አጣሁ፡፡ አሁን ግን በከፋ መልኩ ጉዱ ወጣ ብላ አብዳለች፡፡ - ለምን አስቀድማ አልተናገረችም? - ተናግራለች፡፡ በተደጋጋሚ ነግራሃለች፡፡ - ምን ብላ? - በልማት ባንክ ችግር አለ ብላ፡፡ መያዣ የለ፣ ብድር አይሰበሰብ፣ ግምት የውሸት ነው፡፡ ኦዲት አይደረግም ወዘተ. ብላ፡፡ - እና እኔ ምን አልኳት? - ፀረ ልማት ሃይሎች የሚያወሩት የሃሰት ወሬ ነው አልካት፡፡ አትሰሙማ፡፡ - ግልፅ አድርጋ ብትነግረኝ ኖሮኮ ችግሩ በተፈታ ነበር፡፡ - ችግሩ ከአነጋገርዋ አይደለም፡፡ ችግሩ ከሌላው ነው፡፡ - ለምን? - ጆሯችሁ? አያዳምጥም ወይም ጥሪ አይቀበልም የሚል ነው፡፡ (አቋርጠው ክቡር ሚኒስትሩ ለተመሳሳይ ሥራ ሌላ ክፍለ ከተማ ሊያነጋግሩ ደወሉ) - ስብሰባው እንዴት ነበር? - ክቡር ሚኒስትር ያልጠበቅኩት ነገር ነው የነበረው፡፡ - ምን አጋጠመህ? - የሕዝቡ ቁጣ ነዋ! - የምን ቁጣ? - ግማሹ የወርቁ ነገር አናዶታል የባሌስትራው ማለት ነው፡፡ በቴሌ ያልተናደደ የለም፡፡ አሁን ደግሞ በልማት ባንክ ተበሳጭቷል፡፡ - አመፅ ነበር በለኛ፡፡ - አመፅ አይደለም ክቡር ሚኒስትር ምክር ነው፡፡ - ምን ብሎ መከረ? - ራሳችሁን ፈትሹ! |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |