Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow አትላንቲስ ወደ ምድር ትመለሳለች
አትላንቲስ ወደ ምድር ትመለሳለች Print E-mail
Wednesday, 20 February 2008
"አትላንቲስ" የተሰኘችው መንኩራኩር ተልዕኮዋን አጠናቃ ወደ ምድር የመልስ ጉዞዋን ለመጀመር ከዓለም አቀፉ የህዋ ጣቢያ ተላቃለች፡፡
የአትላንቲስ ጠፈርተኞች በህዋ የቆዩበትን ተልዕኮ በተለይም የኮለምበስ ሳይንስ ላብራቶርን በጠፈር ጣቢያው የመግጠም ዓላማ አሳክተዋል፡፡ የላብራቶሩ መተከል የአውሮፓ በጠፈር ድርጅት በኩል አውሮፓ ለሳይንስ ያበረከተችው ትልቅ አስተዋፅኦ መሆኑን የገለፀው የቢቢሲ ዘገባ የጠፈር ጣቢያውን ግማሽ አካል በጀርመን ከሚገኝ ጣቢያ ሆኖ መቆጣጠር እንደሚቻል አትቷል፡፡

1.3 ቢሊዮን ዩሮ የፈጀው ላብራቶር ተግባር ከመሬት በላይ 340 ኪ.ሜ ርቆ የሚገኙ ክብደት አልባ ነገሮችንና ክስተቶችን በተመለከተ ተከታታይና ሰፊ ጥናቶችን ማድረግ ነው፡፡

አትላንቲስን ያመጠቁት ፈረንሳዊው ጠፈርተኛ ሊኦፖልድ አያሃርትስ የኮለምበስ ላብራቶርን የሙከራ ሥራዎች አጀማመር ለማገዝ በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ይቆያሉ ተብሏል፡፡ ጠፈርተኛው ለሚቀጥሉት ሳምንታት በላብራቶሩ የሚደረጉ የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያንቀሳቅሱ እንደሚቆዩ ዘገባው አመልክቷል፡፡

አትላንቲስ ከጣቢያው ከመላቀቋ በፊት የጠፈር ጣቢያውን ከፍታ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ማሳደግ የቻለች ሲሆን ይኸውም ከ2ዐዐ2 በኋላ የመጀመሪያው ዕድገት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ የሚቀጥለውን መንኩራኩር የመላክ ዕቅድ በመሥራት ላይ ሲሆን የዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያን ግንባታ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ 11 መንኩራኩሮችን የመላክ ሥራ እንደሚጠይቅ ተመልክቷል፡፡

ከ20 ዓመት በኋላ ማሽኖች ከሰው ብቃት እኩል ይሆናሉ

ሰው ሰራሽ ማሽኖች እ.ኤ.አ በ2029 ከሰው ልጆች እኩል የማሰብ ብቃት ሊኖራቸው ይችላል ሲል ታዋቂ የአሜሪካ ማሽን ኢንጅነር መተንበዩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ሬይ ኩዝዌይል የተባለው ባለሙያ እንደሚለው ትናንሽ ሮቦቶች በሰው አእምሮ ውስጥ ተቀብረው ሰዎች የበለጠ ብልህ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያግዙበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

ኢንጅነሩ እንደሚያምነው በሚቀጥሉት ዓመታት ማሽንና የሰው ልጅ ጭንቅላት ተባብረው የሰውን የአስተሳሰብ ብቃትና ጤንነት ያሻሽላሉ፡፡

እንደ ባለሙያው ይህ ክስተት ማሽኖች በሰዎች ላይ የሚያደርጉት ወረራ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት ሰዎች ያከናውኗቸው የነበሩ በርካታ ተግባራት በማሽኖች ተግባር ተተክተዋል፡፡ ማሽኖቹ በሰዎች የአእምሮ ብቃት ልክ አልያም በተሻለ ደረጃ ተግባራቱን ሲያከናውኑም ቆይተዋል፡፡

“በሰውና ማሽን ጥምር ሥልጣኔ ዘመን ውስጥ ገብተናል፡፡ አእምሮአዊና አካላዊ ችሎታችንን ለማስፋፋት ቴክኖሎጂን እየተጠቀምን ነው፡፡ የማሽን ችሎታ የሰውን አእምሮ መተካቱ ወይም ለማገዝ መስራቱም የዚሁ ቀጣይ አካል ነው” ብሏል ኢንጅነሩ፡፡

ይኸው አዲስ ትንበያ የቀረበው “የአሜሪካ የሳይንስ አድቫንስመንት ማህበር” ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ሲሆን በዚሁ ስብሰባ በዘርፉ ታዋቂነት ያተረፉ 18 ተመራማሪዎች በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሰው ልጅ ላይ የሚያጋጥሙ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች ቀርበዋል፡፡

አራት ቋንቋዎችን የሚተረጉም የኮምፒውተር ኘሮግራም

የአውሮፓ አንድ ኘሮጀክት ደች፣ ጀርመን፣ ግሪክና ስፓኒሽ ቋንቋዎችን ወደ እንግሊዝኛ ሊተረጉም የሚችል ቀላልና ርካሽ ኘሮጀክት በሙከራ ላይ እንደሆነ ፊዚኦርግ ዶት ኮም የተሰኘው የሳይንስ ድረ-ገፅ ዘገባ ያሳያል፡፡

እንደዘገባው ኘሮጀክቱ 23 የሥራ ቋንቋዎች ላሉት አውሮፓ ህብረት ሥራ ጠቃሚ ሊሆን የሚችል ነው፡፡

በኮምፒውተር የቋንቋ ትርጉሞችን የመስጠቱ ቴክኖሎጂ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለ ቢሆንም በውጤቱ አሁንም በሰዎች ከሚደረጉ የትርጉም ሥራዎች ሊወዳደር እንደማይችል ዘገባው ጠቅሷል፡፡

አውሮፓ ህብረት በዘርፉ የሚደረጉ ምርምሮችን በተለይም በ198ዐዎቹ ከተካሄደው ፣ዩሮትራ፣ ኘሮጀክት አንስቶ ሲደግፍ ቆይቷል፡፡ የዩሮትራ ኘሮጀክት ሥራ ለኮምፒውተሩ የሰዋሰው ሥርዓትን በማስተማር ፅሁፎችን ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ለመተርጐም የሚቻልበትን መንገድ የተከተለ ነው፡፡

ሆኖም ከ199ዐዎቹ ወዲህ ስታስቲካዊ ትርጉሞችን የመጠቀሙ አዝማሚያ ያየለ ሲሆን ይህ አሠራር የቃላትን ትርጉም በሙሉ ያካተተ ፣ኮርፐስ፣ እየተባለ የሚጠራን ቴክስት ይከተላል፡፡

አዲሱ በአራት ቋንቋ መተርጐም የሚችል ኘሮግራም በእነዚህ ተከታታይ ኘሮጀክቶች አማካኝነት የተከናወነ ነው፡፡
 
< Prev   Next >