| አዋሽ ባንክ 98 ላኪዎችን ሸለመ |
|
|
| Wednesday, 20 February 2008 | |
የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ለሁለተኛ ጊዜ ባከበረው አመታዊ ዝግጅት ከባንኩ ጋር ለሚሰሩ 98 ላኪዎች የምስክር ወረቀት የሰጠ ሲሆን ብልጫ ላሳዩ 31 ላኪዎች የዋንጫ ሽልማት አበርክቷል፡፡ በእለቱ የዋንጫና የሽልማት ወረቀት ያገኙ ላኪዎች እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም በወጪ ንግድ 150 ሚሊየን ዶላር ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ያስገኙ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አመታዊ የላኪዎች ቀንን ትናንት የካቲት 11 ቀን 2000 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ለሁለተኛ ጊዜ ባከበረበት ወቅት ለ98 ላኪዎች ሽልማት ሰጥቷል፡፡ ከተሸለሙት ባለሃብቶች በአብዛኛው የተሰማሩት በአትክልት፣ በቡና፣ በአበባ፣ በጫት፣ በጥጥ፣ በጥራጥሬ፣ በቅባት እህልና በተለያዩ የእርሻ ምርት ውጤቶች መሆኑም ተገልጿል፡፡ የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ለይኩን ብርሃኑ በስነስርዓቱ ላይ እንደገለፁት ባንኩ ላኪዎች እያበረከቱ ላለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለውን አድናቆት በዚህ ዓመትም እየገለፀ መሆኑን ተናግረው ከባንኩ ጋር እየሰሩ ያሉ ላኪዎች ለባንኩ እድገት የበኩላቸውን ማበርከታቸውንና እነዚህ ላኪዎች ባለፈው ዓመት ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለአገራቸው ማስገኘታቸውን ገልፀዋል፡፡ ባንኩ ለውጭ ንግድ ምቹ የሆኑ ልዩ ልዩ የብድር አይነቶች በማዘጋጀት ላኪዎችን እያበረታታ ሲሆን በብሔራዊ ባንክ የኤክስፖርት ብድር ዋስትና አሰራር መሠረት ለኤክስፖርተሮች በማበደር የራሱን ሚና ማበርከቱን ገልፀዋል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ በቀለ ነዲ በበኩላቸው እንደተናገሩት ባንኩ ላለፉት 13 ዓመታት ባደረገው እንቅስቃሴ የባለአክስዮኖች ቁጥር 486 ወደ 2451 ከፍ ብሏል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታልም ከ24 ሚሊዮን ወደ 283 ሚሊዮን ብር አድጓል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ሃብትም 6.8 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቁመው በአሁኑ ጊዜ የተቀማጭ ሂሳብ ደንበኞች ቁጥር 337,045፣ የተቀማጭ ሂሳብ መጠን 3.5 ሚሊዮን ብር መድረሱን ገልፀዋል፡፡ ሰብሳቢው አያይዘውም የተበዳሪ ደንበኞች ቁጥር ከ3500 በላይ መድረሱንና ባንኩም የሰጠው ብድር ወደ 2.7 ቢሊየን ብር መድረሱን ገልፀው ባንኩ 46 ቅርንጫፎች ሲኖሩት በአዲስ አበባ ያሉ ቅርንጫፎቹን ሙሉ በሙሉ በኔትወርክ ማገናኘቱን ጠቁመዋል፡፡ በመላኩ ደምሴ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |