Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow መሠረት መሆን የሚችሉ እንቅስቃሴዎች
መሠረት መሆን የሚችሉ እንቅስቃሴዎች Print E-mail
Wednesday, 20 February 2008
Image
አቶ እሸቱ ጐሳዬ
ወጣቶች በተለያየ መስክ በመሳተፍና የራሳቸውን አስተዋፅኦ በማድረግ በአገር ግንባታ ሂደት ያላቸውን ሚና የሚያመላክት፣ ሕብረተሰቡ ለወጣቶች ያለውን አመለካከት መሻሻልንና መንግሥት በወጣቶች ላይ ያደረገውን ትኩረት ለማሳየት የሚረዳ አገር አቀፍ ፌስቲቫል በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እሸቱ ጐሳዬ ገልፀዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተለያዩ የክልል ቢሮዎች ጋር በመሆን ተግባራዊ እያደረገ ያለው የኢትዮጵያ ወጣቶች የእድገት ፓኬጅ በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን በመጥቀስ አገር አቀፉ የወጣቶች ፌስቲቫል እንዲካሄድ የተፈለገው በመልካም ሥነ ምግባርና ውጤታማነት ለሌሎች ወጣቶች አርአያ የሚሆኑ ወጣቶችንን ለማበረታታት፣ ወጣቱ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለመዋጋት ቃል የሚገባበትን መድረክ ለመፍጠር ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ስለታመነበት መሆኑን አቶ እሸቱ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚደረገው ፌስቲቫል የተለያዩ የውይይት መድረኮችን ጨምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆዩ ሌሎች ተጨማሪ ፕሮግራሞች ይኖሩታል፡፡ በፌስቲቫሉ ሦስት ሺህ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ ወጣቶቹ ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ሲሆን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የክልል ቢሮዎች ክልሎችን ወክለው በፌስቲቫሉ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን በተለያየ መመዘኛ መርጠው እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡   

የወጣቶችን ጉዳይ የሚመለከቱ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተቋቁመዋል፡፡ ወጣቱን በሚመለከት በርካታ መድረኮች ተዘጋጅተው ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ እነዚህ ሂደቶች የወጣቱን ችግር በመቅረፍ ረገድ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ “የወጣቶችን ችግር ለመፍታት በመንግሥትም ሆነ ወጣቶች ላይ በሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ውጤታማ ነበሩ ለማለት አይቻልም፡፡ በወጣቱ ላይ ያሉ ማሕበራዊ፣ አኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በአንድ ጀንበር የተከሰቱ ባለመሆናቸው በአንድ ጊዜ ሊፈቱ አይችሉም፡፡ ነገር ግን እየተደረጉ ያሉት እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጪ፣ አበረታችና መሠረት የሚሆኑ ናቸው” በማለት ወጣቶች ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚንቀሳቀሱ መስሪያ ቤቶች መቋቋም፣ ወጣቶች ያለባቸውን ችግር በመመልከት ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የሚወያዩበት መድረክ መዘጋጀት ቀደም ሲል ለወጣቶች ይሰጥ ከነበረው ትኩረት ጋር ሲነፃፀር በአሁኑ ወቅት ለወጣቶች በመንግሥትና በሕብረተሰቡ እየተሰጠ ያለው ትኩረት ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረገው ፌስቲቫልም ይህንኑ ትኩረት የሚያመላክት እንደሆነ የገለፁት አቶ እሸቱ ፌስቲቫሉ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ወጣቶች የሚሳተፉበት መሆኑ ወጣቶች በከተማና በገጠር ልማት እንዲሁም በአቅም ግንባታ ሂደት ያበረከቱትን ተሳትፎ የማሳየት ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

አቶ እሸቱ አክለውም “ወጣቶች የተለያዩ ችግሮች አለባቸው፡፡ የወጣቶች ጉዳይ የወቅቱ የመንግሥት ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡ የተለያዩ የመንግሥት ፖሊሲዎች ወጣት ተኮር ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የወጣቶችን ችግር በመፍታት ሂደት ጥሩ መሠረት ለመፍጠር ወሳኝ እርምጃ ነው” ብለዋል፡፡

የወጣቶችን ችግር ለመፍታት በሕብረተሰቡ፣ በመንግሥትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች ቢሆንም ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ በማሳሰብ ወጣቶች ደግሞ መደራጀት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል፡፡

አቶ እሸቱ እንደገለፁት፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች የእድገት ፓኬጅ ወቅታዊ አፈፃፀምን በሚመለከት በክልል ደረጃ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ እየተሰራ ሲሆን መረጃው ተሰባስቦ እንዳለቀ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከክልል ቢሮዎች ጋር በተከናወኑ ተግባራትና ቀጣይ ሂደቶች ላይ ይወያያል፡፡    

የወጣቶች አገራዊ ፌስቲቫልን በሚመለከት ከሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የማኔጅመንት አካላት፣ በሌሎች አጋር ተቋማት እንዲሁም ከወጣት ማህበራት የተውጣጡ ግለሰቦች የተካተቱበትና በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ በመግለፅ በዚህ እንቅስቃሴ ወጣቶች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በምሕረት አስቻለው
 
< Prev   Next >