| ድንጋይ ሸጦ ማደር |
|
|
| Wednesday, 20 February 2008 | |
|
ኘላዛ ሆቴል ፊት ለፊት፣ መንገዱን ተሻግሮ ከሚገኘው አጐዛ ገበያ መንገድ ዳር ብዛት ያላቸው ጥቁር ድንጋዮች፣ በነጭ ድንጋይ የተሞሉ ማዳበሪያዎችና የተለያዩ ቅርፃ ቅርፅ ያላቸው ነጭ የወንዝ ድንጋዮች ተክበው በመመልከታችን በአቅራቢያው የነበረን አንድ ወጣት አነጋገርን፡፡
አቶ አበራ አንጃ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነው፡፡ ድንጋዮቹ የእሱና የሌሎች አምስት ጓደኞቹ እንደሆኑና የሚያወጧቸውም ከቀበና ወንዝ መሆኑን ገልፆልናል፡፡ ትላልቆቹ ጥቁር ድንጋዮች እያንዳንዳቸው በሀያ ሳንቲም፣ ትንንሾቹ ደግሞ በአሥር ሳንቲም ይሸጣሉ፡፡ ነጫጮቹ የወንዝ ድንጋዮች ተከስክሰውና በማዳበሪያ ተሞልተው ሲሸጡ በአንድ ማዳበሪያ አራት ብር ያወጣሉ፡፡ አበራን በማነጋገር ላይ እያለን ጓደኞቹም መጥተው ተቀላቀሉን፡፡ ከገለፃቸው እንደተረዳነው ሁሉንም ዓይነት ድንጋዮች የሚያወጡት ከወንዝ ቢሆንም ነጫጮቹ ድንጋዮች በብዛት የሚገኙት በክረምት ነው፡፡ ትላልቆቹ ጥቁር ድንጋዮች በክረምትም ሆነ በበጋ የሚገኙ ሲሆን ድንጋዮቹን ተሸክሞ ከወንዝ ማውጣት አድካሚ እንደሆነ አቶ አበራ ገልፆልናል፡፡ ትንንሾቹ የወንዝ ድንጋዮች (ጠጠሮች) ቀላል ቢሆኑም ወንዝ ውስጥ ጠልቀው ስለሚገኙ በቀላሉ አይወጡም፡፡ አቶ አበራና ጓደኞቹ ሁሉንም ዓይነት ድንጋዮች የማውጣቱን ተግባር በግልና በህብረት እንደሚያከናውኑ ለመረዳት ችለናል፡፡ በግል የመስራት ተራ የደረሰው ሰው ድንጋይ በማውጣት ድንጋዮቹ ሊሸጡ የሚቀርቡበት ቦታ ላይ የመካብ ኃላፊነት ሲኖርበት በሳምንት ሁለትና ሦስት ቀን በህብረት ይሰራል፡፡ ድንጋዮቹን እንዴት ነው የምትሸጧቸው? ስንል ጠየቅን፡፡ “ከወንዙ ድንጋዮቹ እስከሚሸጡበት ቦታ ያለው ርቀት፣ የተወሰኑት ድንጋዮች በቀላሉ አለመገኘት እንዲሁም የጥቁሮቹ ድንጋዮች ክብደት ድንጋዮችን በማንኛውም ጊዜ ለማውጣት ስለማያስችል አብዛኛውን ጊዜ ድንጋይ ለማውጣት ወደ ወንዝ የምንወርደው ገዢ መጥቶ የሚፈልገውን ዓይነት ድንጋይ በመምረጥ ቀብድ ሲከፍል ነው” በማለት ከወጣቶቹ አንዱ መልሶልናል፡፡ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩት ወጣቶች በዚያው አካባቢ እንደሚኖሩ ሲገልፁልን ይህን ሥራ በትኩረት መሥራት ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ ነገር ግን ሠዎች በተለያየ አጋጣሚ የወንዝ ድንጋይ ሲፈልጉ ወንዝ ወርዶ የተፈለገውን ዓይነት ድንጋይ አውጥቶ መሸጥ በፊትም የተለመደ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ድንጋዮቹን ከወንዝ ማውጣትና ማጓጓዝ አድካሚ ከመሆኑ አኳያ የሚሸጡበት ዋጋ አነስተኛ መሆኑን፣ የድንጋዮቹ በአነስተኛ ዋጋ መሸጥ የድንጋዮች ዓይነትና የገዢዎች ፍላጐት ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ድንጋዮችን በብዛት ከወንዝ አውጥተው ሳይሸጡ ሁለት ወርና ከዚያም በላይ የሚቆዩ ሲሆን የእለት ከእለት ኑሯቸውን ለመምራት እዚያው አካባቢ የሚያጋጥሟቸውን ማናቸውም የጉልበት ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ለድንጋይ መሸጥ ይልቅ እንዲያውም የተሻለ ሣንቲም የሚያገኙት ከተባራሪ የጉልበት ሥራዎች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ድንጋዮቹ ብዙም ስለማይፈለጉ በህብረት ከወንዝ አውጥቶ በብዛት ከመሸጥ ይልቅ በአጋጣሚ ድንጋይ ሊገዛ ከመጣ ሰው ጋር በግል ተስማምቶ ለመሥራት ተገድደዋል፡፡ ገዢ በሄደበት ወቅት በቦታው ላይ የተገኘ ሰው ከገዢው ጋር በመስማማት ለብቻው ወንዝ ገብቶ ድንጋዮችን በማወጣት መሸጥ ይችላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ድንጋዮችን ለማውጣት የሚመረጠው ማታና ጠዋት ነው፡፡ ትልልቅ ጥቁር የወንዝ ድንጋዮች በቀላሉ ተከስክሰው ለተለያዩ ሥራዎች ስለማይውሉ ብዙም ተፈላጊ አይሉም፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ ለአትክልት ሥፍራ መሥመር ማስያዣነት የሚውሉበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀውልናል፡፡ ወጣቶቹ እንደገለፁት፣ እንደነሱ ከወንዝ ድንጋዮች አውጥተው የሚሸጡ ግለሰቦች በቦሌና እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ አሉ፡፡ ነገር ግን በአቅራቢያው የእነዚህ ግለሰቦች መገኘት በእነሱ ሥራ ላይ ብዙም አሉታዊ ተፅእኖ የለውም፡፡ እንደ ወጣቶቹ ገለፃ ጥቁር ድንጋዮች በቀላሉ አይከሰከሱም፣ ነጫጮቹን ድንጋዮች ወለል ሊሾ ለማድረግ መጠቀም የመስመጥ ባህሪ ስላላቸው ችግር ይፈጥራሉ ተብሎ በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ሰዎች የሚሰጥ አስተያየት አለ፡፡ ለድንጋዮቹ በብዛት አለመሸጥ ዋነኛው ምክንያትም ይህ ነው፡፡ ምናልባትም የድንጋዮቹ የተለየ ጠቀሜታና በምን መልኩ አገልግሎት ላይ ሊውሉ ይችላሉ የሚለው ሁኔታ አለመታወቅ እንጂ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ወጣቶቹ እንደሚሉት ገዢዎች የድንጋይ ዓይነት ከመምረጥ ባሻገር ነጫጭ የወንዝ ድንጋዮች በሚፈልጉት መጠን እንዲከሰከሱላቸው የሚጠይቁ ሲሆን በደቃቁ የተከሰከሰ ድንጋይ በማዳበሪያ ውስጥ ሲከተት የመጠቅጠቅ ፀባይ ስለሚኖረው መከስከሱ አድካሚ ከመሆኑ በተጨማሪ ትርፋማ አይደለም ብለዋል፡፡ ድንጋዮቹ የሚወጡበትን ሁኔታ ለማየት ወደ ወንዝ ሄድን፡፡ በርከት ያሉ አዛውንቶች እንዲሁም ጐልማሶች ሰውነታቸውን ሲታጠቡና ልብሶቻቸውን ሲያጥቡ ተመለከትን፡፡ ብዙም ወደ ወንዙ ሳንገባ ዳር ላይ ስንቆም ከወጣቶቹ አንዱ ወደ መሀል በመሄድ ትልቅ ጥቁር ድንጋይ አውጥቶ በማምጣት ድንጋዮቹን የሚያወጡት በዚያ መልኩ መሆኑን አሳየን፡፡ በጣም ትላልቅ የሆኑት ድንጋዮችን ለማውጣት እጅን ወደ ወንዙ ውሀ መክተት ግድ ባይሆንም ትናንሾቹን የወንዝ ድንጋዮች ለማውጣት እጅን ወደ ውሀው ሥር መክተት ግዴታ ነው፡፡ ትናንሽ ድንጋዮችን ለማግኘት በሚደረገው ፍለጋ በተለያዩ ስለቶች መቆረጥና መወጋት የተለመደ ነው፡፡ ክረምት ላይ ድንጋይ ማውጣት ጐርፍ የሚያመጣቸውን የድንጋይ ዓይነቶች (ነጭ) በማግኘት በኩል ጠቀሜታ ቢኖረውም ድንጋይ በሚወጣበት ጠዋትና ማታ ላይ የሚኖረው ቅዝቃዜ፣ ድንጋዮቹን ጭቃ በሆነ መንገድ ተጉዞ የሚካቡበት ቦታ ማድረስ ፈተና መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በምህረት አስቻለው |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |