| "በገንዘብ ሊቆጠር የማይችል የዓለማችን... |
|
|
| Wednesday, 20 February 2008 | |
"በገንዘብ ሊቆጠር የማይችል የዓለማችን ከፍተኛ የጄኔቲክ ወይም በረሃ ላይ ያለ ሃብት የአርብቶ አደሮች ነው"አቶ ተዘራ ጌታሁን (የፓስቶራሊስት ፎረም ከኢትዮጵያ ኤክሲኪዩቲቭ ዳይሬክተር) “ፓስቶራሊስት ፎረም ኢትዮጵያ” በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እየተገናኙ ስለአርብቶ አደሩ ጉዳዮች ሃሳብ እንዲለዋወጡ ለማድረግ እ.ኤ.አ በ1999 የተቋቋመ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ የፓስቶራሊስት ፎረም ኢትዮጵያ ኤክሲኪዩቲቭ ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ተዘራ ጌታሁንን የድርጅቱን እንቅስቃሴ በተመለተ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ፓስቶራሊስት ፎረም ኢትዮጵያ የተቋቋመበት ዋነኛ አላማው ምንድነው? አቶ ተዘራ፡- ፎረሙ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ የአርብቶ አደሩን ድምፅ ከፍ ብሎ የሚሰማበትና ትኩረት እንዲሻ የሚያደርግ ሥራ ለመሥራት ነው፡፡ ትልቁ ነገር በሁለተኛ ደረጃ ፓስቶራሊስት ፎረም ኢትዮጵያ እናት ድርጅት ነው፡፡ ይሄ ድርጅት በስሩ ያሉ አባል ድርጅቶችን ድምፅ ከፍ ተብሎ የሚሰማበትና የጋራ መልክቶቻቸውን የሚያስተላልፉበት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በስሩ ምን ያህል ድርጅቶች አሉ? አቶ ተዘራ፡- 27 የሚሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሥሩ አሉ፡፡ ሪፖርተር፡- ሁሉም በአርብቶ አደሩ አካባቢ ይሠራሉ? አቶ ተዘራ፡- ሁሉም በአርብቶ አደሩ ዙሪያ የሚሠሩ ናቸው፡፡ የእኛ ትልቁ ሥራ አርብቶ አደሩን የሚመለከት ስለሆነ በአብዛኛው አባሎቻችንም በዚያ ላይ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ሪፖርተር፡- እነዚህ ድርጅቶች በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚሠሩ ናቸው ስንል ሁሉም ተመሳሳይ ሥራ ነው ወይስ የተለያየ? አቶ ተዘራ፡- የተለያየ ሥራ ነው የሚሠሩት፡፡ ለምሳሌ ውሃ፣ ጤና፣ ትምህርት የመሳሰሉት አሉ፡፡ በቦረና አካባቢ የሚሠሩ የአርብቶ አደሩ አጋር ድርጅቶች ውሃ ጤና ትምህርት ላይ ይሠራሉ፡፡ በአፋርም አካባቢ እንደዚሁ ሊሠሩ የሚችሉ አሉ፡፡ በሶማሌ በጋምቤላ በደቡብም እንዲሁ፡፡ የኢኮኖሚ ሥራ የሚሠሩ አለ፡፡ በመንግሥት ሊሠሩ የሚችሉ ትላልቅ መሠረተ ልማቶችና የመሳሰሉት ካልሆነ በስተቀር በማኀበራዊውም ሆነ በኢኮኖሚው ዘርፍ ቀላል የማይባሉ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ያሉ አርብቶ አደሮች ቁጥር ምን ያህል ይሆናል? ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት አንፃር ምን ያህሉን ይሸፍናሉ? አቶ ተዘራ፡- አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በርካታ አርብቶ አደሮች ይገኙባቸዋል ከሚባሉት አገሮች ውስጥ አንዱዋ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የአርብቶ አደር ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን እንደሚደርስ የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ወረቀት ያሳያል፡፡ አርብቶ አደሮች 61 በመቶ ድረስ ያለውን የአገሪቷን የቆዳ ስፋት ይዘው ነው የሚገኙት፡፡ በአብዛኛው የቆላውን አካባቢ በአርብቶ አደሮች የተያዘ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ስለአርብቶ አደሮች ሲነሳ በብዙ ቦታዎች ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ኑሯቸው አስቸጋሪ እንደሆነም አይተናል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ፎረማችሁ ምን አድርጓል? አቶ ተዘራ፡- አንድ የማልግባባበት ነገር አለ፡፡ እኔ እዚህ ሙያ ላይ ከአስራ ሰባት ዓመታት በላይ ቆይቻለሁ፡፡ አርብቶ አደሮች ሁሉ ደሃ ናቸው የሚባለውን አልቀበልም፡፡ በግምት ስለምንናገር ነው እንጂ የተሻሉ ብዙ አርብቶ አደሮች አሉ፡፡ ብዙ ሃብት ያላቸው አሉ፡፡ እንደውም በገንዘብ ሊቆጠር የማይችል የዓለማችን ከፍተኛ የጄኔቲክ ወይም በረሃ ላይ ያለ ሃብት የአርብቶ አደሮች ነው፡፡ በገንዘብ መተመን ይከብዳል እንጂ ከፍተኛ የሆነ ሃብትነው ያላቸው፡፡ ይህንን ድሃ ስለሆኑ መረዳት አለባቸው የሚለውን አልቀበልም፡፡ ሪፖርተር፡- ደሃ ናቸው ደሃ አይደሉም ለማለት አይደለም፡፡ በአካባቢው ችግሮች አሉ፡፡ ያየናቸው አንዳንድ የአርብቶ አደሮች አካባቢዎች ይህንን ይመሰክራሉ፡፡ ለምሳሌ የውሃ ችግርን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ስለዚህ በእንዲህ ዓይነቱ የአርብቶ አደሩ ችግሮች ሠራችሁ? አቶ ተዘራ፡- ለአርብቶ አደሮች ልማት ዋናውና ትልቁ ነገር የተፈጥሮ ሐብቱን እንዴት ይጠቀማሉ የሚለውና ለዚህ አቅጣጫ ማስያዝ ነው፡፡ ይሄ ከፖሊሲ ጋር የሚገናኝ ማለት ነው፡፡ ለአርብቶ አደሩ የሚሆን ፖሊሲ ያስፈልገዋል፡፡ መዘዋወሩ እንደሃጢአት ሳይታይበት ማለት ነው፡፡ አርብቶ አደርነት የኑሮ ዘይቤና መሠረት ነው ብለን ከተነሳን ለእሱ የሚሆነውን ጉዳይ በጋራ እየተወያየን እሱን ማዕከል ያደረገ የፖሊሲ አቅጣጫን ማስቀመጥ የሚቻልበት ጉዳይ አለ፡፡ ድሮ ለአርብቶ አደሩ ልማት መፍትሄው አርብቶ አደሩን በአንድ ቦታ ማስፈር መቻልነው የሚል ነበር፡፡ አሁን ይሻላላ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የሚል ሃረግ አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች አርብቶ አደርነት የህይወት ዘይቤያቸው ነው ስንል ከሁሉም ነገር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ የአመለካከት ለውጥ መምጣት አለበት፡፡ አርብቶ አደሮች የተገፉበት ነገር መስተካከል አለበት፡፡ ለረዥም ዘመናት የቆዩት መንግሥት ደግሞ ቆለኛ ናቸው ብሎ ከዚህ ወደዚያ መልዕክቶችን ሕጎችን ማውረድ እንጂ እስኪ ምንድናቸው? ምንድነው የምትፈልጉት እንዴት ብናለማ ይሻላል በሚል በምክክር ላይ የተመሠረተ ተሰርቶ አይታወቅም፡፡ ሪፖርተር፡- ከቀድሞው ተለወጠ ብላችሁ የምታቀርቡት ምንድነው? አቶ ተዘራ፡- አሁን የተሻለ ነገር አለ፡፡ ሪፖርተር፡- የተሻለ ምን? አቶ ተዘራ፡- በራሳቸው ጉዳይ ላይ በየምክር ቤቶቻቸው የመወሰን ስልጣን አላቸው፡፡ አርብቶ አደር ስለሆንክ ያለብህ ችግር በአንድ ጊዜ ይፈታልሃል ማለት አይደለም፡፡ ከሀገሪቷ እድገት ጋር ነው ጉዳዩ ሊታይ የሚችለው፡፡ አሁን አርብቶ አደር ናችሁ ተብለው ተሸልመዋል፡፡ ጀግና አርብቶ አደር ናችሁ፣ አልሚ ናችሁ ተብለው መሸለማቸው በራሱ አንዱ ገፅታ ነው፡፡ አርብቶ አደርነታቸው ታውቆላቸዋል ማለት ነው፡፡ ፖሊሲና ስትራቴጂ የምትቀርፀው በመንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አካባቢ በምንመለከትበት ጊዜ በአፋር ክልላዊ መንግሥት በቅርቡ በሚዲያ ከ15ዐ ሚሊዮን ብር በላይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውጪ አድርገው የተለያየ ሥራ መስራታቸው ተገልጿል፡፡ በኦሮሚያና በሌሎች የአርብቶ አደሮች አካባቢ በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ ወጥቶ እየተሠራ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በልማት ሥራው የመጣው ለወጥ ሊነግሩኝ ይችላሉ? አቶ ተዘራ፡- ልማቱ ያመጣውን ለውጥ ለማወቅ ትልቅ ሰርቬይ መሠራት አለበት፡፡ የውሃ ሽፋኑም ቢሆን በጋራ በተሠራ ሥራ ነው፡፡ ከሆነ ደረጃ ወደ ሆነ ደረጃ መጣ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ከሰባት ዓመት በፊት በሶማሌና በአፋር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰባትና ስምንት ብቻ ነበሩ፡፡ ዛሬ ከ4ዐ በላይ ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር ትልቅ አመላካች ነው፡፡ ብዙ ሃብት ይዘው ነው የሚሄዱት፡፡ አርብቶ አደርነትን ተቀብለው አርብቶ አደርን ለመርዳት ነው፡፡ ቀደም ብሎ ትኩረት አልነበረም፡፡ አሁን ግን አርብቶ አደርነት ብሔራዊ አጀንዳ እየሆነ ስላመጣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና መንግሥትም ከፍተኛ ትኩረት እየሰጡት ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ አለ የሚባለው ችግር ምን ያህል ይሰፋ እንደነበር መገመት እንችላለን፡፡ ሪፖርተር፡- በአርብቶ አደሩ ዙሪያ የሚሠሩ ይህን ያህል ድርጅቶች ካሉ በተግባር የተሠራውን ቢጠቅሱልኝ፡፡ እየተሠራ ነው ከማለት ይልቅ ቢዘረዝሩልኝ፤ አቶ ተዘራ፡- በተግባር የታየው አርብቶ አደሮች ኢምፓወር የሆኑበትን ነገር ነው እኛ የምናስበው፡፡ ለምሳሌ ፎረሙ የሚሠራው የእነዚህ ሰዎች ድምፅ ከፍ ብሎ እንዲሰማ ማድረግ ነው፡፡ በመጀመሪያው የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ወረቀት ላይ እና በአሁኑ ስለአርብቶ አደሩ የተጠቀሰው ልዩነት አለው፡፡ ከዚህ በፊት አልተካተተም፡፡ አሁን ተካቷል፡፡ እኛ የምናስበው እዚያ ጋር አስራ ስድስት ትምህርት ቤት ተሠራ፣ ሦስት ተሠራ የሚለው አይደለም፡፡ አጠቃላይ የልማቱ ፍሬም ወርክ ነው መታየት ያለበት፡፡ ተቀባይነት አግኝተዋል ወይ? ተቀባይነት ሲገኝ ነው ልማቱ የሚገኘው፡፡ ትልቁ ነገር አርብቶ አደሮችን የሚመጥናቸው አካሄድ ይህንን ይመስላል ብሎ በአዲሱ ስትራቴጂ ላይ ሰባት ገፅ አለ፡፡ የመጀመሪያው የድህነት ቅነሳው ስትራቴጂ በሚሠራበት ጊዜ ስለአርብቶ አደር የሚያወራ አንድ አረፍተ ነገር ብቻ ነው፡፡ ይህም “አርብቶ አደር ኮምኘሬክስ ሲስተም ስለሆነ በዝርዝር የሚታይ ነው” የሚል ዓይነት ነበር ያለው፡፡ የአገር የልማት አጀንዳ በሚቀረፅበት ሁኔታ ውስጥ አንድ አረፍተነገር 12ና 15 ሚሊዮን ለሚሆን ሕዝብ ተካቶ የነበረው ዛሬ ግን ሰባት ገፅ መድረሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የአርብቶ አደሩ ያለውን ሐብት እንዲጠቀም ገበያ በማመቻቸቱ ረገድ የተሠራ ሥራ ምንድነው? በዚህ አካባቢ ተደጋግሞ የሚነሳ ችግር አለ፡፡ ለምሳሌ የቆዳ ላኪዎች የሚቀርብልን ቆዳ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፤ ቆዳው በበሽታ የተጠቃ ነው እያሉ ያማርራሉ፤ አቶ ተዘራ፡- ልማቶችን በተለያየ ደረጃ ልናይ እንችላለን፡፡ አሁን እነዚህ ሩቲን የልማት ሥራዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተለያየ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ የላይቭ ስቶክ ዴቨሎኘመንት ብለው የሚሠሩት ይሆናል፡፡ ይህንን ያህል ሰዎች ይህንን ያህል ቆዳው የተበላሸባቸው ቆዳን በጥራት እንዲያመርቱ ሰርቬይ መሠራት አለበት፡፡ ሪፖርቶች ተጠናክረው መቅረብ መደረግ አለባቸው፡፡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተሠራ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እዚያ አካባቢ ሪፖርት የሚደረጉት የበለጠ በመንግሥት ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ የአርብቶ አደሮች ቀን ላይ የቀረቡትን ሪፖርቶች ስንመለከት በኤን.ጂ.ኦዎቹ ይህንን ያህል ተሠራ ተብሎ ተቀናብሮ የቀረበ ነገር የለም፡፡ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ ነው የኤን.ጂ.ኦዎቹን ሥራ የሚቆጣጠረው፡፡ በዚያ በኩል ተቀናብሮ መምጣት አለበት፡፡ ምክንያቱም ከ80 በላይ የሚሆኑ ኤን.ጂ.ኦዎች በሁለት ክልል የማሠሩትን ሥራ ሪፖርት ሠርቶ በአንዴ እዚህ ለማምጣት ያስቸግራል፡፡ በእኛ በኩል ይህንን ለመሥራት እቅድ አለን፡፡ ሪፖርተር፡- ለአርብቶ አደሩ ትምህርት በመስጠት ብቻ የሚሠሩ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ያስገኙት ውጤት መጥቀስ ይቻላል? አቶ ተዘራ፡- ትምህርት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች አሉ፡፡ ”ይህንን ያህል ትምህርት ቤት ተሠርቷል፤ ይህን ያህል ተማሪዎች ከዚህ አካባቢ ወጥተዋል ለማለት በሙሉ ግን መረጃ መሠብሰብ ያስፈልጋል፡፡ በእኛ ድርጅት አቅም ቀርቶ የብሔራዊ ስታስቲክስ ባለሥልጣን ስለአርብቶ አደር አካባቢ በየዓመቱ ከሚያወጣቸውን ዘገባዎች ብንመለከት “ከአርብቶ አደር አካባቢ ውጪ ነው” በሚል የሚካተት መረጃ እንጂ ሙሉ መረጃ አታገኝም፡፡ ስለዚህ ይህ መረጃ የለም፡፡ አርብቶ አደር መባል ከጀመረ ገና አሥር ዓመት አልሞላውም፡፡ ስለአርብቶ አደር ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የሚያወጣውን እናያለን፡፡ በየክልሉ ያሉ መረጃዎች ሲሰሩ መረጃው መጨረሻ ላይ አርብቶ “አደሮች አካባቢ ውጭ” የሚል ተካቶ መውጣቱ ራሱ ችግሩን ያሳየናል፡፡ የአገሪቱን መረጃ የሚሰጠው የብሔራዊ ስታስቴክስ ባለሥልጣን ነው፡፡ እኛ ብናሠራና ብናወጣ የእኛ ሥልጣን አይደለም፡፡ በአዋጅ የተቀመጠ ሥልጣን የተሰጠው ለብሔራዊ ስታስቲክስ ባለሥልጣን ነው፡፡ በእኛ አገር ህግ መሠረት መጠቀስ ያለበት መረጃ የባለሥልጣኑን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- አርብቶ አደሩ ገበያ የሚያገኝበትን አጋጣሚ ፈጥራችኋል? አቶ ተዘራ፡- በዚህ ረገድ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ “አርብቶ አደሮች ከእንስሳት ሃብታቸው ተመጣጣኝ ገቢ ይሻሉ” የሚለውን ዘመቻ አዘጋጅተናል፡፡ ከእኛ አጋር ድርጅቶች ውስጥም “ኤሲቪ ቮካ” የተባለው ድርጅት የእንስሳት የገበያ ቦታዎችን በማሠራት፣ የገበያ ጥናቶችን በማድረግ ምን ያህል እንስሳ ከአርብቶ አደሩ አካባቢ ወደ ከተማ ይመጣል? እዚያ አካባቢ ስንት ነው ዋጋው? በሚል በየወሩ መረጃ ያወጣሉ፡፡ አንድ በሬ ቦረና ገበያ ላይ ሁለት ሺህ ብር ነው ብለን ብናስብና መካከል ላይ ደግሞ አራት ሺህ ብር ቢያወጣና ከዚያ እዚህ ሲገባ ስድስት ሺህ ብር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሽያጭ አርብቶ አደሩ ምን ያህል ገቢ ነው ያገኘው? ተጠቃሚ ሆነዋል ወይ? የሚለው ሁሉ እየታየ ነው፡፡ ለቡና የተሰጠው ትኩረት ለእንስሳትም መሠጠት አለበት፡፡ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ኪሎ ስጋ 6ዐ ብር ገብቷል፡፡ በዚህ ዋጋ ማነው የሚገዛው? ሪፖርተር፡- ፈጠር አለበት ብላችሁ የምታምኑት የገበያ ስርዓት ይህንን የዋጋ ውድነት ሊቀንሰው ይችላል? አቶ ተዘራ፡- ለምሳሌ የቡና ዋጋ በየጊዜው ይነገራል፡፡ ለእንስሳት ገበያም መረጃ የመስጠት ሥራ የጀመሩ ድርጅቶች አሉ፡፡ ይህንን ያህል መጠን ያለው በሬ በዚህ ዋጋ ተሸጠ የሚለውን መረጃ ካገኘ አርብቶ አደሩ ነገ የሚሸጥበትን ዋጋ ሊያውቅ ይችላል፡፡ ይህ ገበያውን ይለውጣል፤ ሳይቋረጥ መቀጠልም አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- ፎርማችሁ ከዚህ በኋላ ለመሥራት ያቀደውስ ምንድነው? መለወጥ አለበት የምትሉትና መንግሥትም ማድረግ ይገባዋል የምትሉት ምንድነው? አቶ ተዘራ፡- የእኛ የሥልጣንና ኃላፊነት በበለጠ በፖሊሲ አቅጣጫ ላይ መሥራት ነው፡፡ የአርብቶ አደር የእውቀት ዘርፍ በደንብ ተደርጐ መሠራት አለበት ባይ ነው፡፡ በብዙ ቦታዎች አርብቶ አደሩን በተመለከተ ያለው እውቀት በጣም አናሳ ነው፡፡ በአምስት ዓመት ዕቅዳችን ላይ እንደተቀመጠው ሊሆን የምንፈልገው የእውቀት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ሥራ መስራት ነው፡፡ የእውቀት ሥራዎች ውስጥም በአርብቶ አደሩ አካባቢ የተሠሩ ሥራዎችን መፈተሽን ያጠቃልላል፡፡ የመሬት አጠቃቀምና የመሬት ይዞታን በተመለከተም እንሠራለን፡፡ በህገ መንግሥቱ ላይ አርብቶ አደሩ ከፍላጐቱ ውጭ ከመሬቱ መነሳት የለበትም የሚል ነገር አለ፡፡ ዝርዝር ህጉ ግን ወደፊት ይወጣል ተብሎ ቢገለፅም እስካሁን አልወጣም፡፡ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይም እንሠራለን፡፡ “የአርብቶ አደሩ አስተሳሰብ ይህ ነው፤ የሚፈልገው ይህንን ነው” ብለን የተሻለ ነገር እንዲመጣ ለማድረግ እንጥራለን፡፡ ሪፖርተር፡- በአርብቶ አደሩ አካባቢ አሉ ከሚባሉ ችግሮች አንዱ የግጦሽ ቦታ እያጣ መምጣቱ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ምን አስተያየት አለዎት? አቶ ተዘራ፡- የግጦሽ ቦታ ችግር በግጭትም ሊመጣ ይችላል፡፡ ሁለት ተቀናቃኝ ጐሣዎች የሚጋጩበት ከሆነ ያንን ግጭት ፍራቻ ላይጠቀሙባት ይችላል፡፡ አንዱ ይህ ነው፡፡ ሌሎችም ምክንያቶች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |