| የሚሌኒየሙ "ወርቅ" ቅሌት! |
|
|
| Sunday, 24 February 2008 | |
ኢትዮጵያ ማዕከላዊ ባንክ አላት? የሚሌኒየም በዓልን በደመቀ ሁኔታ እናከብራለን ብለን እንደ ሕዝብ በገባነው ቃል መሰረት አነሰም በዛም በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል ማለት ይቻላል፡፡ የፈጠረው መንፈስም ጥሩ ነው፡፡ አዲስ ስሜት ፈጥሯል፡፡ ሆኖም ግን የሚሌኒየሙ ደስታ የሚሌኒየሙንም ቅሌት ፈጥሯል፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አሳፋሪና አሳዛኝ ቅሌት ነው፡፡ ለአጭበርባሪዎቹና ለዘራፊዎቹ ግን ዕቃውም ወርቅ ነው፣ ቅሌቱም ወርቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው በእነሱ ቋንቋና በእኛ የቁጭት አገላለጽ የሚሌኒየሙ "ወርቅ" ቅሌት ያልነው፡፡ ስለወርቅ ማጭበርበር ሁሉም እያወራ ነው፡፡ ስለ ባሌስትራና ወርቅ ማውራት የወቅቱ አጀንዳ ሆኗል፡፡ የጋብቻ ቀለበትም ባሌስትራ እንዳይሆን መጠርጠር የተጀመረበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ነገር ግን፣". ነገር ግን ወርቅ ስንልና ስለተጭበረበረ ወርቅ ስናወራ ስለተመሳሳይ ጉዳይ እያወራን ነው ወይ የሚል ሥጋት አለን፡፡ ለምን? ወርቅ ወርቅ ማለት አይደለም ወይ የሚል ጥያቄም ሊነሳ እንደሚችል እንገምታለን፡፡ መልሳችን ግልፅና ግልፅ ነው፡፡ ወርቅ ማለት ወርቅ ማለት አይደለም፡፡ ፒያሳ አካባቢ፣ ብሄራዊ ቲያትር አካባቢ፣ በትላልቅ ሆቴሎችና በሌሎች ከተሞች ወርቅ ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህ ወርቅ ቤቶች ለጌጣጌጥ የሚሆኑ ወርቆችን ይሸጣሉ፡፡ ሙሽሮች ወርቅ ይገዛሉ፡፡ ስጦታ መስጠት የሚፈልጉም እንደዚሁ ወርቅ ይገዛሉ፡፡ ይህ ወርቅ ነው፡፡ በብሄራዊ ባንክ የሚገኝ ወርቅ ግን የወርቆች ሁሉ የበላይና ልዩ ወርቅ ነው፡፡ ምክንያቱም የፒያሳው አይነት ለጌጣ ጌጥ ተብሎ የሚሸጥ ወርቅ ሳይሆን የአገር ሃብትን ወክሎ የሚቀመጥ "ሪዘርቭ" ማለትም መጠባበቂያ ወይም የዋስትና መያዣ ሃብት ነው፡፡ አንዲት አገር ምን ያህል "ሪዘርቭ" አላት ሲባል የመጠባበቂያው መለኪያ ወርቅ ነው፡፡ ስለሆነም የብሄራዊ ባንክ ወርቅ ተጭበረበረ፣ ባሌስትራ ሆኖ ተገኘ ሲባል ለጉትቻ የሚሆን ወርቅ ጠፋ ማለት ሳይሆን የአገር የመጠባበቂያ የዋስትናና የመያዣ ሃብት ጎደለ ጠፋ ማለት ነው፡፡ በአገር ልማትና በአገር ሃብት ላይ የተደረገ ወንጀል ነው፡፡ በምድር ብቻም ሳይሆን በሰማይም ወንጀል ነው ለማለት አቅሙ የለንም እንጂ በምድር ላይ የተፈጠረው ቅሌት ግን በአገር ሃብትና በአገር መጠባበቂያ ላይ የደረሰ ውድቀት ነው፡፡ በአገራችን ላይ ጠላት ቢነሳ፣ ጦርነት ቢቀሰቀስ ለሚያስፈልገን ሁሉ የምንገለገልበት ሃብት ይህ መጠባበቂያ ነው፡፡ ይህ በወርቅ መልክ የተቀመጠ ሃብት ነው፡፡ እየተቀለደ ያለው በዚህ ላይ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ፓርላማ ቀርበው ጥያቄና መልስ ሲያካሂዱ ስለ ኤች አር 2003 ተጠይቀው ነበር፡፡ በልማት ላይ ይህ ውሳኔ ቢፀድቅ ሊያደርሰው የሚችል ጉዳት በሚመለከት ልማታችን በጭራሽ አይደናቀፍም በማለት የሰጡት መልስ "ያገኘናትን ሳንቲም አጠረቃቅመን ለልማት እንነሳለን እንጂ ልማታችን አይቆምም" የሚል ነበር፡፡ በመንግሥት አመራር ደረጃ ያገኘናትን ሳንቲም አጠረቃቅመን ለልማት እናውላለን ሲባል ከዚህም በላይ የሆነ የአገር ሃብት መጠቀሚያ የልማት አስተማማኝ ሃብት ግን የአጭበርባሪ ነጋዴና ቢሮክራት መቀለጃ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ሌቦች አይታለች፡፡ ፓርላማውን የግላቸው ቤት አስመስለው ለመሸጥ የሞከሩ አጭበርባሪዎች እንዳሉም ይነገራል፡፡ በአገር መጠባበቂያ ሃብት ቀልዶ አገርን ለአደጋ የሚዳርግ ግን ለየት ያለ ቅሌት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ወደ አንድ ሌላ ትልቅ ጥያቄ ያመራናል፡፡ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ባንክ አላትን የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ ምክንያቱም የማዕከላዊ ወይም ብሄራዊ ባንክ አንዱና ዋነኛው ሥራው መጠባበቂያ ሃብትን መያዝና ለዚሁ የሚሆን ወርቅን መቆጣጠር ነው፡፡ ወርቅ ነው ብሎ ሳይሆን "ወርቅ መሳይ" እያለ በሰነዱ የሚረከበው ነገር እውነትም ወርቅ ያልሆነ ወርቅ መሳይ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ይህ ባንኩ ብቃት እንደሌለው ያረጋግጣል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ብቃት እንደሌለው የሚያረጋግጠው ልማት ባንክ ሰባት መቶ ሚሊዮን ብር ከስሯል ብሎ ብሄራዊ ባንክ ሪፖርት ቢያቀርብ በሌላ አነጋገር ልማት ባንክ ሰባት መቶ ሚሊዮን ብር ሲከስር የሚቆጣጠርና የሚያግዝ፣ ተው የሚል ማዕከላዊ ባንክ አልነበረም፣ የለም ማለት ነው፡፡ የልማት ባንክ እንዲህ ሆኖ መታየትም የብሄራዊ ባንክ ደካማነት ማሳያ ተጨማሪ ትልቅ ማረጋገጫ ነው፡፡ ለነገሩ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ብር ማቃጠል እንደ ትልቅ ሥራ የወሰደው ብሄራዊ ባንክ ተቃጠለ ያለው ብር ሳይቃጠል እንደሚቀርና ወደ ገበያ እንደሚገባም ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚፈጭ ማሽን እያለ እያቃጠለ የሚውል መሆኑንም ስለ ተግባራዊነቱ ያጠያይቃል፡፡ ለአበባ የሚሰጠው ገንዘብና በአበባ የሚገባው ገቢ ያልተመጣጠነ መሆኑን አይቶ ለምን ብሎ አልጠየቀም፣ ሌላው ደካማነቱን የሚያሳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ የብሄራዊ ባንክን የአስራ አምስት ዓመታት ጉዞ ብናይ ስራውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ሲሰራለት ስለሚውል ድክመቱን ሲሸፋፍንለት ቆይቷል እንጂ አቅምም ራዕይም የሌለው ነው፡፡ በተለይ አሁን እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታያል እንጂ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ኤጀንሲ ለሶስት ዓመት ተዘግቶ መክረሙም በደካማው ብሄራዊ ባንክ ላይ ተጨማሪ ጆሮ ደግፎ ተፈጥሮበት ከርሟል፡፡ መደረግ ያለበት ግልፅና አስቸኳይ እርምጃ አለ፡፡ ብሄራዊ ባንክ መገምገም አለበት፡፡ አለኝ የሚለው ወርቅ መፈተሽ አለበት፡፡ ፖሊሲውና አወቃቀሩ መጠናከር አለበት፡፡ ከሁሉም በፊት ግን ያሉት የባንክ ገዢዎች፣ ኃላፊዎች ከቦታቸው ይነሱ፡፡ የሚመረጠው፣ "ራሳቸው ባንኩ መቀለጃ ስላደረግነው ወርቁን ባለመቆጣጠራችን በአገር መጠባበቂያ ሃብት በመቀለዳችን፣ የመንግሥት የግል ባንኮችን መምራት ስላልቻልን፣ እንደዋነኛው ሥራ አድርገን የወሰድነው የብር ማቃጠል ሥራና ኃላፊነትም በአግባቡ ስላልተወጣን ያቃጠልነውም ቢሆን ኋላ ቀር በሆነ አሰራር እንጂ ዘመናዊ ማድረግ ስላልቻልን ደካሞች ነንና ሥራችንን በፈቃዳችን ለቀናል" ቢሉ ነበር፡፡ የማይሉ ከሆነ ግን በትዕዛዝ ሊነሱ ይገባል፡፡ መንግሥት ጠንካራ ብሄራዊ ባንክ ይፍጠር፡፡ የሚሌኒየሙ የወርቅ ቅሌት እንዳይደገም እንዳይደጋገም! |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |