| ለመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት... |
|
|
| Sunday, 24 February 2008 | |
|
ለመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ደመወዝ ለመጨመር ጥናቱ እየተጠናቀቀ ነው
መንግሥት ማንም አስገድዶትና ገፋፍቶት ሳይሆን የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት አቅም፣ የሰራተኛውን ሁኔታ፣ ያለው የኑሮ ውድነትና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በመመርመር በአሁኑ ጊዜ 11ሺ ለሚሆኑ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ሰራተኞች ደሞዝ ለመጨመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡ ማህበሩ አቋሙን መቀየሩን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ለባንክ ኃላፊዎችም ይሁን ለሠራተኛ ያልተደበቀ እውነት ሆኖ ሳለ ሰሞኑን የንግድ ባንክ ሠራተኞች ማህበር መንግሥት "ደሞዝ ካልጨመረ ርምጃ እንወስዳለን" የሚል ወረቀት በመገናኛ ብዙሃን ማሰራጨታቸው መንግሥት የያዘውን እቅድ ያራዝመዋል እንጂ አያቀላጥፈውም ሲሉ ባለስልጣኑ ተናግረዋል ፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሥልጣኑ "ይህ ጉዳይ እጅግ አስቂኝና አሳፋሪ ተግባር ነወ፡፡ እኛ ባወጣነው መግለጫ ምክንያት መንግሥት ደሞዝ ይጨምራል ብሎ ማሰብ ተረት ተረትና ቅዥት ነው፡፡" ሲሉም የማህበሩን አመራሮች እንቅስቃሴ አጣጥለዋል፡፡ መንግሥት ደሞዝ ለመጨመር በዝግጅት ላይ መሆኑ እየታወቀ "ደሞዝ የተጨመረው በእኛ ምክንያት ነው" ለማለት የማህበሩ አመራሮች የፈፀሙት ቅንነት የጐደለው ተግባር ነው፡፡ የሠራተኛ ማህበሩ ጫና በማድረግም ሆነ ርምጃ በመውሰድ የሚያስጨምረው አንድም ዓይነት የደመወዝ ጭማሪ እንደማይኖርም ባለስልጣኑ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ደመወዝ ለመጨመር እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ያለውን የኑሮ ውድነት፣ የሰራተኛውንና የባንኩን አቅም በማገናዘብ ስላመነበት እንጂ "አንድ ቀን ወረቀት ይበተናል"፣ ከሚል ስጋት እንዳልሆነ የገለፁት ባለስልጣኑ "እንቅስቃሴው የማህበሩ ብልጣ ብልጥ አመራሮች አጀንዳ እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም" ብለዋል፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ አባባል እነዚህ ኃላፊነት የጐደላቸው አመራሮች በህልማቸው የውሸት ትግልና ድል የሚታያቸው ናቸው፡፡ መንግሥት የሠራተኛውን ኑሮ ለማሻሻል የያዘውን እቅድ ተግባር ላይ ለማዋል ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ይህንን ወረቀት ለምን እንደበተኑ እስኪጣራ ድረስ የደሞዝ ጭማሪውን ያዘገየዋል እንጂ አያፋጥነውም፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች መሠረታዊ ማህበር የአዲስ አበባ ምክር ቤት ለዝግጅት ክፍሉ በላከው ደብዳቤ ቀደም ሲል ያስቀመጠውን ቀነ ገደብ ማንሳቱን ገል"ል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች መሠረታዊ ማህበር የአዲስ አበባ ምክር ቤት የካቲት 4 ቀን 2000 ዓ.ም የጊዜውን የኑሮ ውድነት አስመልክቶ አድርጎት በነበረው አስቸኳይ ስብሰባ ጠቅላላ ጉባኤውን ለመጥራት የ15 የሥራ ቀናት የጊዜ ገደብ አስቀምጦ እንደነበር ያስታወሰው ደብዳቤ፡፡ "ይሁንና ይኸው ምክር ቤት የካቲት 13 ቀን 2000 ዓ.ም በድጋሜ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ከባንኩ የበላይ አመራር ጋር ባደረገው ውይይት መግባባት ላይ ስለደረሰ ጠቅላላ ጉባኤውን ለመጥራት አስቀምጦት የነበረውን የ15 የሥራ ቀናት ጊዜ ገደብ አንስቷል" ይላል፡፡ የማህበሩን አቋም መቀየር በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን የማህበህሩን አቋም መቀየር "አስገራሚ" ሲሉ ገልፀውታል፡፡ "መንግሥት በድርድርም ሆነ በወረቀት መበተን ማስፈራሪያ አንድም ነገር አያደርግም፡፡ ሊያደርግም አይችልም" ያሉት ባለሥልጣኑ "በማህበሩ ጥያቄ ቢሆንማ የጥያቄው ምንጭና አካሄዱ እስኪጠና የሚወስደው ጊዜ ደመወዝ ሳይጨመር ከቆየበትን ጊዜ በላይ ይፈጅ ነበር" ብለዋል፡፡ አያይዘውም የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪ መንግሥት የወቅቱን የገበያ ውድድር፤ የኑሮ ውድነትና የተቋማቱን የመክፈል አቅም አገናዝቦ በእቅድ ሲያከናውነው የቆየና አሁን ተግባራዊ ሊያደርገው በዝግጅት ላይ ያለ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |