| ኢትዮጵያ መኪና ለአውሮፓ ገበያ... |
|
|
| Sunday, 24 February 2008 | |
|
ኢትዮጵያ መኪና ለአውሮፓ ገበያ ለማቅረብ ተስማማች
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቤት አውቶሞቢል መገጣጠሚያ ፋብሪካ በመሆን የሚታወቀው ሆላንድ ካር ኃ.የተ.የግል. ማህበር በ2000 ዓ.ም ማምረት የጀመረውን መኪና ወደ አውሮፓ ለመላክ ከሆላንድ ኩባንያ ጋር ተስማማ፡፡ ሆላንድ ካር ይህንን ስምምነት ያደረገው ዘዲን ኢንቨስትመንት ከሚባለው የሆላንድ ኩባንያ ጋር ሲሆን መኪናዋ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚያስችላትን የጥራት ደረጃ ለማግኘት በሰባት ሺህ ዩሮ የተሸጠችው የመጀመሪያዋ መኪና በሁለት ሳምንታት ውስጥ ትላካለች፡፡ መኪና ለውጪ ገበያ በማቅረብ ኢትዮጵያ ስምምነት ያደረገችበት የመጀመሪያው ታሪክ እንደሆነ የተነገረለት ይህ ክስተት፣ አዲስ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘቱ በተጨማሪ ኢትዮጵያን በሌላው ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገል"ል፡፡ መኪኖቹን በሆላንድና በሌሎች የአውሮፓ አገራት ለመሸጥ የሚያስችለው ስምምነት ከትናንት በስቲያ ምሽት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በተፈረመበት ወቅት እንደተገለፀውም ከዚህ በኋላ በየዓመቱ ቢያንስ 3000 ያህል ተሽከርካሪዎችን ኢትየጵያ ለአውሮፓ ገበያ ታቀርባለች፡፡ የሆላንድ ካር ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ ለሪፖርተር እንደገለፁት መኪናዋ በኔዘርላንድ መንግሥት ተቀባይነት እንደሚኖራት አረጋግጠው "ማረጋገጫው ከተገኘ በኋላ ምርታችንን በማሳደግ በሌሎች አገራትም ተጨማሪ ገበያ ለማግኘት እንድንጥር ያደርገናል" ብለዋል፡፡ መኪኖቹን ተረክቦ ለኔዘርላንድና ለአውሮፓ ገበያ ለማቅረብ ከሆላንድ ካር ጋር ስምምነት ያደረገው ዘዲን ኢንቨስትመንት የተባለው ኩባንያ ተወካይ ሚ/ር ካርሎ ሔል "አባይ" ደረጃዋን የጠበቀች ተሽከርካሪ መሆኗን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም "መኪናዋን በመላ አውሮፓ ለመሸጥም ተዘጋጅተናል፡፡ አሁን የምንጠብቀው ማረጋገጫውን ነው፡፡ ማረጋገጫውንም እንደምታገኝ አልጠራጠርም" ብለዋል፡፡ ኢንጂነር ታደሰ ጨምረው እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት 2000 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ፋብሪካው የሚያመርተውን ምርት በማስፋት በቅርቡ በ6400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ምርት ማምረት ይጀምራል፡፡ ይህ የማስፋፊያ ሥራው በቀን 25 ተሽከርካሪዎችን ለመገጣጠም ያስችለዋል፡፡ "አባይ" የተባለችው ተሽከርካሪ ሊፉን ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር በጋራ ሞጆ በሚገኘው ፋብሪካ የምትገጣጠም መኪና ስትሆን በአሁኑ ጊዜ በአገር ውስጥ ገበያ 140 ሺህ ብር ዋጋ በመሸጥ ላይ ነች፡፡ ሆላንድ ካር በ2006 የተቋቋመ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው የተቋቋመውም በኔዘርላንድ መንግሥት ድጋፍ ነው፡፡ አባይ የተሰኘችውን መኪና ገጣጥሞ ለገበያ ከማቅረቡ በፊት ዶክ በሚል ስያሜ የምትታወቀውን መኪና ለገበያ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በቅርቡም አዋሽ በሚል መጠሪያ ፒካፖች ማምረት ይጀምራል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |