Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
Jul 05th
Home arrow Sections arrow ለኑሮ ውድነት መንግሥት የበጀት ሽግሽግ...
ለኑሮ ውድነት መንግሥት የበጀት ሽግሽግ... Print E-mail
Sunday, 24 February 2008
ለኑሮ ውድነት መንግሥት የበጀት ሽግሽግ በማድረግ ህብረተሰቡን እንዲደጉም ተቃዋሚዎች ጠየቁ

መንግሥት ለሌላ ተግባር የሚያውለውን ወጪ ቀንሶ ለህብረተሰቡ ድጐማ ማድረግ እንዳለበት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ገለጹ፡፡ የኦፊዴን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳና የአዴአፓ መድህን ዋና ጸሐፊ አቶ ሞሼ ሰሙ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጹት የተባባሰውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ለመቀነስ መንግሥት ለመከላከያ፣ ለደህንነት፣ ለጸጥታና ለመሳሰሉት ጉደዮች የሚያወጣውን ወጪ በመቀነስ ለህብረተሰቡ ድጐማ ሊያውለው ይገባል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ንረት የታየው በምግብ ምርቶች ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ቡልቻ የምግብ ሸቀጦች መወደድ በሚከሰትበት ጊዜ መንግሥት ገንዘቡን ለሌላ ነገር ወጭ ማድረግ ትቶ (ለምሳሌ ለመከላከያ) ሕዝብ የሚበላውን ነገር ገዝቶ ማቅረብ ያለበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ለአንድ ቤተሰብ እያቀረበ ያለው 25 ኪሎ ስንዴ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ የዋጋ ንረቱን ሊያረጋጋው አለመቻሉን የገለጹት የኦፊዴኑ ሊቀመንበር ችግሩን ለመቀረፍ የምግብ ምርት በብዛት ለህብረተሰቡ መቅረብ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ መንግሥትም ለዚህ የሚውል ገንዘብ የለኝም ማለት እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡

ከነዳጅ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የማንኛውም ሸቀጦች ዋጋ እንደሚጨምር የገለጹት አቶ ቡልቻ ሁኔታዎችን ባላገናዘበ መልኩ በተለያዩ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉትን ነጋዴዎች በማስረዳትና በማግባባት ከመጠን በላይ ዋጋ እንዳይጨምሩ ማድረግ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ ነጋዴዎችም ለህብረተሰቡ ማዘን እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

አቶ ቡልቻ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ የዋጋ ቁጥጥር አይፈልግም፡፡ የዋጋ ቁጥጥር በተለያዩ አገሮች ተሞክሮ ውጤት አላመጣም፡፡ ቁጥጥር ከማድረግ ይልቅ ነጋዴውን አባብሎ መንግሥትን እንዲተባበር ማድረግ የተሻለ ውጤት ያስገኛል፡፡

የኢዴአፓ መድህን ዋና ፀሐፊ አቶ ሞሼ ሰሙ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በጦርነት የተጐዳ ድሀ አገር መሆኗን ገልፀው አገሪቱ አሁን ያለችበት ደረጃ የረጅም ታሪኳ ውጤት መሆኑንና የኑሮ ውድነቱም በሁለትና በሶስት ዓመት ብቻ የመጣ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መታየት የጀመሩት የተለያዩ አኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ከአገሪቱ ታሪክ ጋር ተጨማሪ በመሆን የኑሮ ውድነቱን እንዳባባሰው የገለጹት አቶ ሞሼ ለተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የሚወጣው የገንዘብ አቅም የዋጋ ንረት እንዲከሰት ማድረጉን አስረድተዋል የአቅርቦት አቅም ትንሽ በሆነበት አገር የገንዘብ የመግዛት አቅም ከሚገባው በላይ ማደጉም በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡

አቶ ሙሼ እንደሚሉት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚፈጥሩ በመሆናቸው በአገሪቱ ያለውን የገንዘብ አቅም በመሻማት የዋጋ ንረት እንዲከሰት በር ይከፍታሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከሚታየው የገንዘብ ግሽበት አኳያ ህብረተሰቡ ፋታ ሊያገኝ እንደሚገባው የጠቆሙት የኢዴአፓ ዋና ፀሐፊ እየተካሄዱ ያሉት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ሳይቆሙ የግንባታ ጊዜያቸውን በማራዘም የኢኮኖሚውን ጫና ማቅለል አንድ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡  

ከመሰረተ ልማት ግንባታው መስፋፋት በተጨማሪ ብድርን መሠረት በማድረግ በአርሶ አደሩ አካባቢ የሚታየው የገንዘብ ብክነት ከፍተኛ መሆኑም ለኑሮ ውድነቱ መባባስ አንዱ ምክንያት መሆኑን አቶ ሞሼ አመልክተዋል፡፡

መንግሥት በተለያየ መንገድ ለአርሶ አደሮች በሚያበድረው ገንዘብ ላይ በቂ ቁጥጥር ማካሄድና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ገንዘቡ የሚመለስበትን ስርዓት ማስተካከል እንዳለበትም አቶ ሞሼ መክረዋል፡፡

እንደ አቶ ሞሼ ገለፃ ለገበሬዎች በብድር መልክ የተሰጠው ገንዘብ ለእለታዊ ፍጆታ የሚውል ከሆነ ተመጣጣኝ ያልሆነ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ይገባል በዚህም የእቃ ዋጋ ንረት ይከሰታል፡፡

መንግሥት ለአርሶ አደሮች የሚሰጠው ብድር የሚያገኘው ህብረተሱ ከሚከፍለው ግብር፣ ከብድር ወይም አዲስ ገንዘብ በማተም ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት ዋና ጸሐፊው በዚህ መልኩ የሚገኘው ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ ካልዋለ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡  

ለዋጋ መናር መንስኤ ነው ተብሎ በአቶ ሞሼ የተጠቀሰው ሌላው ነጥብ የነጋዴው ማህበረሰብ ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ ያለመንቀሳቀስ ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች በዋጋ ንረት ራሳቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡

በአንዳንድ እቃዎች ላይ በማይታመን መልኩ 80 በመቶ የዋጋ ጭማሪ የታየበት ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙት አቶ ሙሼ ይህ የነጋዴዎች እንቅስቃሴ የስግብግብነት ምልክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት አንድ ሊትር ዘይትን በ18 ብር እያቀረበ በየገበያ ማዕከሉ እስከ አርባ ብር የሚሸጥበት ሁኔታ መኖሩ ሊጠና የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ አያይዘውም "ማህበረሰቡ እርስ በርሱ ተሳስቦ የሚቀጥልበት ሁኔታ ከሌለና ነጋዴው በራሱ መንገድ ተንቀሳቅሶ ገደብ የሌለው ትርፍ በማግኘት ህብረተሰቡን የሚበድልበት ሁኔታ ካለ መንግሥት ጣልቃ መግባት አለበት" ብለዋል፡፡

አቶ ሞሼ እንደሚሉት እያንዳንዱ ነጋዴ እያንዳንዱን እቃ በስንት ብር እንደሚያስመጣ መንግሥት የሚያውቅ በመሆኑ አግባብ ያልሆነ ትርፍ በህብርተሰቡ ላይ እንዳይጫን ማድረግ ይቻላል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ በታየው የዋጋ ግሽበት ምክንያት ሰዎች በልተው ማደር የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የገለጹት አቶ ሞሼ አንዳንድ የቤተሰብ ኃላፊዎች የገንዘብ የትምህርት ክፍያና የትራንስፖርት ጥያቄን ለማምለጥ አምሽተው ወደ ቤት እንደሚገቡና በሌሊት ከቤታቸው የሚወጡበት ሁኔታ እየተከሰተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአገሪቱ የተከሰተውን የዋጋ ንረት አስመልክተን ያነጋገርናቸው የቀድሞ የቅንጅት የፓርላማ ተመራጭ አቶ ተመስገን ዘውዴ አሁን እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ከሕዝብ አቅም ውጭ እየሆነ በመምጣቱ በሥራ የሚተዳደረው ሕዝብ ሊወጣው ወደማይችልበት ደረጃ መድረሱን ገልፀዋል፡፡ ለተከሰተው የኑሮ ውድነት መንግሥት መፍትሄ ማምጣት አለመቻሉን የጠቆሙት አቶ ተመስገን አንድ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት በአገሪቱ ያለውን የአቅርቦትና የፍላጐት ሁኔታ መረዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

"የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር መጀመሪያ ችግሮቹን በትክክል የመለየት ሥራ ማከናወን ያስፈለጋል" ያሉት አቶ ተመስገንን የችግሩ መንስኤ ከታወቀ በኋላ መንግሥት ወደ ገበያው ስርዓት ለአጭር ጊዜ ጣልቃ ገብቶ ገበያውን ማረጋጋት አለበት ብለዋል፡፡ ችግሩ የተከሰተው በአቅርቦት ማነስ ምክንያት ከሆነ መንግሥት እጥረት የሚታይበትን ምርት በማቅረብ፣ ወይም እሱን ሊተኩ የሚችሉ ሸቀጦችን በማስገባት የዋጋ ንረቱን ማረጋጋት እንደሚቻልም አክለው ገልጸዋል፡፡

አቶ ተመስገን እንደሚሉት በአገሪቱ የሚታየው የኑሮ ውድነት የመጣው ብሔራዊ ባንኩ ከገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ ውጭ ባለመሆኑ እና የኢኮኖሚና የልማት ተቋማት ጠቅላላ ፍላጐትንና አቅርቦትን መተንበይ ባመቻላቸው ነው፡፡ ብሔራዊ ባንኩ ከገዥው ፖርቲ ተፅዕኖ ውጭ ሆኖ ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ አለመቻሉን የገለጹት አቶ ተመስገን "የገዥውን ፓርቲ የገንዘብ ፍላጐት ለማሟላት ተብሎ ኢኮኖሚው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ገንዘብ እንዲታተም መደረጉ የዋጋ ንረቱን እንዲቀጥል አድርጐታል"፡፡

የአኮኖሚና የልማት ተቋማት ከፓርላማም ሆነ ከሌላ አካል የሚሰጣቸውን ምክር እንደማይቀበሉ የገለጹት አቶ ተመስገን "እኛ እናውቅላችኋለን" የሚለው አካሄድ ችግሩን እያባባሰው እንደመጣ አመልክተዋል፡፡ 10 በመቶ የነበረው የዋጋ ግሽበትም 20 በመቶ መድረሱን አንዳንድ ሪፖርቶችን ጠቅሰው ተናግረዋል፡፡

የዋጋ ንረቱ የታችኛውን የሕብረተሰብ ክፍል እንዳይጐዳ ለማድረግ በመንግሥት የተወሰዱት እርምጃዎች ደካማ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ተመስገን በመንግሥት በኩል ለዋጋ ንረቱ ምክንያት ተደርገው በተጨባጭ የተገለጹ ሁኔታዎች እንደሌሉ አመልክተዋል፡፡

የነዳጅ ዋጋ መጨመር ተከትሎ በምግብ ምርቶችና በሸቀጦች ላይ የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉን? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ "ችግሩን ነጋዴዎች የፈጠሩት አድርጐ ማየት ተገቢ አይደለም" ብለዋል፡፡

"በዓለም የነዳጅ ዋጋ መናር በአብዛኛው ተጐጂ የሚሆነው ዝቅተኛው የህብርተሰብ ክፍል ነው" ያሉት አቶ ተመስገን መንግሥት 300 ሚሊዮን ብር ደጉሜያለሁ ቢልም ድጐማው ለትክክለኛው የሕብረተሰብ ክፍል አለመድረሱን ገልጸዋል፡፡

የኤዴሀህ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስም የኑሮ ውድነት በሚከሰትበት ጊዜ መንግሥት የማረጋጊያ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያምናሉ፡፡

መንግሥት 25 ኪሎ ስንዴ በርካሽ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማከፋፈል እያደረገ ያለው ሙከራ አባይን በጭልፋ የመቀነስ ያህል አስቸጋሪ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር በየነ ከስንዴው ማከፋፈል በተጨማሪ አስፈላጊ በሆኑ ሸቀጣሸቀጦች ላይ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ገበያውን ማረጋጋት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

በግብይት ሂደት ውስጥ ቁጥጥር አለመኖሩ የዋጋ ንረቱ እንዲባባስ ማድረጉን የገለጹት ፕሮፌሰሩ መሠረታዊ በሆኑ ሸቀጣሸቀጦችና የምግብ ምርቶች ላይ የዋጋ ጣራ ሊደረግ ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

ከእድገት ጋር ተያይዞ መጥቷል የተባው የዋጋ ንረት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይገኛል፡፡ የዋጋ ንረቱን ለመግታት በመንግሥት የተወሰዱት አንዳንድ እርምጃዎች ለጊዜው ለውጥ ያስገኙ ቢመስሉም ዘላቂ መፍትሄ አላመጡም፡፡ በእያንዳንዱ የምግብ እህልና ሸቀጣሸቀጥ ላይ በየእለቱ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ለሕብረተሰቡ ፈተና ሆነዋል፡፡ በአንዳንድ ምርቶች ላይ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሰማንያና የዘጠና በመቶ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ባለፈው ዓመት 36 ብር ይሸጥ የነበረው 3 ሌትር ሀያት ዘይት አሁን 60 ብር ገብቷል፡፡

ዝቅተኛ ገቢ ያለው ነዋሪ ኑሮን በብልሀት የሚገፋበት ጊዜ ከፊቱ ርቆታል፡፡ ከአምስት ብር ባነሰ ዋጋ ዳቦና ጭማቂ በመብላት ምሳን መሸወድ የማይታሰብ ሆኗል፡፡ ጭማቂ ስድስት ብር፣ አምባሻ ሶስት ብር ከሀምሳ ገብቷል፡፡ "ለዚህ ለዚህማ በያይነቱ ምን አለኝ" ብለው ወደ ምግብ ቤት ጐራ የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ዋጋ በአጥፍ ጨምሮ ያገኙታል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት 75 ሳንቲም ይሸጥ የነበረ አንድ እንጀራ አሁን በእጥፍ ጨምሮ ከ1.75 ሳንቲም እስከ 2 ብር ይሸጣል፡፡ የኑሮ ውድነቱ እጅግ በመባባሱ የቤተሰብ አባላት እንደ ባህላቸው እርስ በርስ መረዳዳት አልቻሉም፡፡

ከአንድ ዓመት በፊተ ከራሱ አልፎ ቤተሰቦቹን መረዳት ይችል የነበረ ግለሰብ አሁን ለራሱም መሆን ያልቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ቤተሰብን ማገዝ የተሳናቸው ተበራክተዋል፡፡

መንግሥት ለሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ቢያደርግም አሁንም ድረስ የሠራተኛው ገቢና ወጪው አልተመጣጠነም፡፡ ለዚህም ይመስላል አንድ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የጉልበት ሠራተኛ "የአምስት ብር ሥራ ሳልሰራ አስራ አምስት ብር የማወጣበት የምሳ ሰዓት ይደርሳል" ሲል ምሬቱን ለሪፖርተር ጋዜጣ የገለጸው፡፡ የኑሮ ውድነቱ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ ሆቴል ቤት ተገብቶ ምሳ መብላት የማይታሰብበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ መብላት የሚችለውም ቢሆን ከበላ በኋላ ማማረሩ የማይቀር ነው፡፡ በልቶና ጠጥቶ መዝናናት ቀርቷል፡፡ አብዛኛው ሕዝባችን በቀን አንድ ጊዜ መብላት ህልም እንዳይሆንበት ያሰጋል በማለት "በቀን ሶስቴ ትበላላችሁ" መባሉን በምፀት የገለፀው አስተያየት ሰጪ አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ይናገራል፡፡ የችግሩን መንስኤም መንግሥት አጥንቶ በመለየት መፍትሄ ሊፈልግ እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡

በኃይሌ ሙሉ
 
< Prev   Next >