| አዲስ አበባን የገደላት ሥራ ወይስ ወሬ |
|
|
| Sunday, 24 February 2008 | |
|
በአንድ ሀገር ውስጥ ነፃ አስተያየት መስጠት መጀመሩ አንደኛውና ዋነኛው የዴሞክራሲ መጎልበት መገለጫ ሊሆን እንደሚችል እንረዳለን፡፡ ነገር ግን ከማንኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ገንቢና ለችግሮች መፍትሔ ሊሰጡ ካልቻሉ በማቆጥቆጥ ላይ ያለን ዴሞክራሲን ከማቀጨጭ ባለፈ የሚፈይዱት ነገር እንደሌለም እናምናለን፡፡
ይህንን ለማለት ያስቻለን የካቲት 2 ቀን 2000 ዓ.ም በሪፖርተር ጋዜጣ እኔ የምለው ገጽ "አዲስ አበባ ከገዳዮቿ ለመሸሽ ወዴት ትሂድ?" የሚለውን ጽሑፍ አንብበን አብዛኛው የፅሁፉ ይዘት ሚዛናዊነት የጎደለውና ጥቃቅን ጉድለቶችን ግንድ አሳክሎ የማሳየት ባህርይ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ችግሮች ሲፈጠሩ የችግሩ ምንጭ ምንና ማን እንደሆነ እንኳ ጠንቅቀን ሳናውቅ በመሰለን ብቻ ስለምንጓዝ ስህተት ላይ እንወድቃለን፡፡ አዲስ አበባን እየገደላት ያለው ሥራ ፈትነት፣ አሉባልታና ጫፍ ይዞ ማውራት ነው፡፡ ጸሐፊው የአዲስ አበባ ከተማ የባለአደራ አስተዳደር ዘመኑን የብስጭት፣ የማይረሳና የብሶት ጊዜ እንዳደረገው አስመስለው ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ በሚጮሁ ቃላት አንባቢያቸውን ለመሳብ ጥረት አድርገዋል፡፡ የአዲስ አበባን ችግሮች ከምርጫ ጋር ለማያያዝም ሞክረዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ አዲስ አበባን ማስተዳደር እንደነበረበት ለመግለጽ ጥረዋል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓትን የሚከተል መንግሥት በምርጫ ባላሸነፈበት ክልል ውስጥ ይህን ማድረግ እንደማይችል እንዴት አልተረዱም? ስለመልካም አስተዳደር ከሚሰብኩ ጸሐፊ ይህን መስማት ግን እርስ በእርሱ የሚጣረስና ያልጠራ አቋም እንዳለ በግልጽ የሚታይበት ነው፡፡ አዲስ አበባ የሀገሪቷ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና አስተዳደራዊ እንቅስቃሴ ማዕከል ናት፡፡ እንደ አብዛኞቹ የታዳጊ አገር ከተሞች በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተተበተበች ከተማ ነች፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ በአንድ ጀንበር የተፈጠሩ ሳይሆኑ ለረጅም ዓመታት በከተማይቱና በሀገሪቷ በሰፈነው ኋላቀርነት ሳቢያ ስር የሰደዱ ስለመሆናቸው ምስክር ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ ጸሐፊው በአዲስ አበባ የሚታዩት ችግሮች የከተማዋ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር የወለዳቸውና ወደ ሥልጣን ሲመጣ ይዟቸው የመጣ ችግሮች እንደሆኑ ለመሣል ጥረት አድርገዋል፡፡ ባለአደራው አስተዳደር ከመምጣቱ በፊት ችግሮች ነበሩ፤ አሁንም ችግሮቹ እስከሚቀረፉ መቀጠላቸው አይቀሬ ነው፡፡ አስተያየት ሰጪው ባለአደራው አዲስ አበባን ከመረከቡ በፊት አንድም ችግር በከተማዋ ውስጥ አልነበረም የሚል ዓይነት እንድምታ ያለውና ሚዛናዊ ያልሆነ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ስለከተማዋ ባለአደራ አስተዳደር አወቃቀር የሚያውቁት ብዙም ነገር እንደሌለ የሚያሳይ በመሆኑ ትንሽ ግንዛቤ መፍጠሩ ተገቢ ይመስለናል፡፡ የከተማዋ ባለአደራ አስተዳደር ሲዋቀር የተለወጠ ነገር ምንም አልነበረም፡፡ ከዘጠኙ የማዕከል የካቢኔ አባላት፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ ሥራ አስፈፃሚዎች መምጣትና ቋሚ የከተማ መዋቅሩን ከመቀላቀል በስተቀር፣ ቀደም ሲል በከተማዋ ጊዜያዊ አስተዳደር የነበሩ የመንግሥት መዋቅሮች፣ የሲቪል ሰርቪስ አሰራሮችና ሌሎችም በርካታ ተግባራት እንደነበሩ የቀጠሉበት እንደነበርም እናስታውሳለን፡፡ ባለአደራ አስተዳደሩ ወደ ሥራ ሲገባ በምርጫ 97 የተነሳ ለአንድ ዓመት በመላው የአስተዳደሩ ቢሮዎች ሥራ ተቀዛቅዞና ተዳክሞ የአብዛኛው ሰራተኛ የሥራ ሞራል ምን ደረጃ ላይ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ተቀዛቅዞ የነበረውን የሠራተኛ የሥራ ሞራል ከመገንባት አልፎ ሠራተኛው ወደ ሥራ የሚገባበትን ሁኔታ በመፍጠር ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ሠራተኛው በፖለቲካ የመሳተፍ መብት ቢኖረውም አገልግሎት መስጠትና ኅብረተሰቡን ማገልገል እንዳለበት እንኳ በውል የተረዳ ባለመሆኑ ወደ መጀመሪያው አካባቢ ሥራዎች ሲበደሉ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ የአዲስ አበባ ችግሮች በርካታና ውስብስቦች ናቸው፡፡ አንዱ ሲቋጠር ሌላው የሚፈታ መሆኑን በሥራው ሂደት ያሉት የሚያውቁት ነው፡፡ የባለአደራው አስተዳደር የእነዚህን ችግሮች መፍቻ ስልቶችን አጥንቶ አይደለም ወደ ሥራ የገባው፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ክፍተት እንዳይፈጠር በሚል የተዋቀረ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን አስተዳደሩ አደራ ጠባቂ ነኝ ብሎ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም፡፡ በርካታ በጎ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በከተማዋ ውስጥ በርካታ ችግሮች ነበሩ፣ አሁንም አሉ፣ ወደፊትም በተወሰነ መልኩ ይቀጥላሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮች ደግሞ ባለአደራ አስተዳደሩ በአንድ ጀንበር ይፍታቸው ብሎ ማሰብና መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ ፀሐፊው በፅሁፋቸው ሕገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ የባለአደራ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ፈቃድ አግኝቶ እንደሚከናወንና የአስተዳደሩ አላማና አጀንዳ ብቻ አድርገው አስቀምጠዋል፡፡ የማንኛውም ከተማ አስተዳደር ሕገ ወጥ ግንባታን ለመከላከል ጥረት ማድረጉ አይቀሬ ቢሆንም በከተማችን ግን ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በማስፋፊያ አካባቢ ባሉት ክፍለ ከተሞች ከሕገ ወጦችና ከአንድ አንድ የአስተዳደሩ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በመተባበር ሕገወጥነትን የሚያስፋፉ፣ አስተዳደሩ ቀን የሠራውን ማታ የሚያበላሹ በርካቶች ናቸው፡፡ ሆኖም የባለአደራውን አስተዳደር ሥራ እሰይ አልንም አላልንም ይህ ሕገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ቁልፍ መፍትሔና ምላሽ እንዲያገኝ በማድረጉ በኩል ይኸው ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ጥሩ ሚና ተጫውቷል፡፡ ይህም ሲባል ከተማዋንና ነዋሪውን እንዲያስተዳድሩ ኃላፊነት የተጣለባቸው ባለሥልጣናት ሁሉም በተፈለገው መጠን አደራቸውን ተወጥተዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ጥቂትና የተወሰኑ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ኃላፊዎች እንደሚኖሩ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ከኑግ ጋር የተገኘ ሰሊጥ እንደሚባለው ሁሉንም አንድ ላይ ጨፍልቆ ያለ ስም ስም ማውጣቱ ተገቢ ነው የሚል እምነት የለንም፡፡ ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው የሕዝብን መሬት ሲዘርፉና ሲያዘርፉ የነበሩ ባለሥልጣናትም በአሁኑ ወቅት ጉዳያቸው በሕግ እየታየ ነው፡፡ ነገር ግን አስተያየት ሰሚው እንደዚህ ዓይነት እርምጃዎችን ለመጠቃቀስና ሕገወጥነትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አድንቀው ከመጻፍ ይልቅ የተሳሳተውን መንገድ ብቻ መርጠዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አስተዳደሩ ሕገ ወጥ ግንባታን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከስሩ ለማድረቅ ከፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ሰፊ ዘመቻ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም በርካታ ሕገወጥ ግንባታዎች ፈርሰዋል፤ ከ100 በላይ የሚሆኑ በሕገወጥ መንገድ ቦታ የወሰዱ ማኅበራት እንዲታገዱ ተደርገዋል፡፡ የባለአደራው አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለአንድም ማኅበር ቦታ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ነገር ግን አስተያየት አቅራቢው ባለአደራው አስተዳደር ለማኅበራት ቦታ በሕገወጥ መንገድ እንደሸነሸነ አድርገው ማቅረባቸው ኃላፊነት የጎደለውና ማንንም የማያስተምር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በአስራ አንደኛው ሰዓት ላይ አስተዳደሩ እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም እንደ ድክመት ተነስቷል፡፡ አስተዳደሩ ቋሚ አስተዳደር እስኪመጣ እጁን አጣጥፎ ቁጭ ብሎ መጠበቅ ያለበት አይመስለንም፡፡ ማንኛውም ለሀገር የሚያስብ ሰው ልብ ሊለው የሚባው አስተዳደሩ በከተማው ላሉት ችግሮች እቅዶችን አውጥቶና መፍትሄ አዘጋጅቶ ለቀጣዩ አስተዳደር ቢያስረክብ ነውሩ ምኑ ላይ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም በአዎንታዊ ጎኑ መታየት ሲገባው ሁሉን ነገር ገልብጦ ማሰብ ለየትኛውም አካል አይጠቅምም፡፡ የባለአደራ አስተዳደሩ ከመምጣቱ በፊት የተጀመሩ የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እንደነበሩ እናስታውሣለን፡፡ መልካም አስተዳደር በቢሮክራሲው መልካም ፈቃድ ብቻ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ መልካም አስተዳደርን በማስፈኑ ተግባር ግንባር ቀደም ሚና የሚጫወተው ተገልጋዩ ኅብረተሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰባችን መብቱን በአብዛኛው ለቢሮክራሲው አሳልፎ የሚሰጥ በመሆኑ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉት አሰራሩን ወደቀድሞው አሰራር ለመመለስ ለሚፈልጉ ክፍሎች ሲመቻች ቆይቷል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት የከተማዋ ዋነኛ ችግር ሆኖ የቆየና ነዋሪውም የሚማረርበት ጉዳይ እንደሆነ ባለአደራ አስተዳደሩ ይገነዘባል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩን ለመቅረፍ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደሩ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም፡፡ ቀደም ሲል የነበረው አስተዳደር ጀምሮት የነበረውን የመልካም አስተዳደር ዝርጋታ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለማስቀጠል ተችሏል፡፡ በመሆኑም በአስተዳደሩ የሽግግር ዘመን ዴሞክራሲያዊ ባህል በማስፈን፣ ያልተማከለ አስተዳደርና አሰራር በማጠናከር፣ የሲቪል ሰርቪሱን የአገልግሎት አሰጣጥና የማስፈፀም አቅም በማሻሻልና በማሳደግ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ አገልግሎት አሰጣጡ ተገልጋዩ ኅብረተሰብ ወዳለበት ወደ ታችኛው እርከን ወርዶ ነዋሪው ግልጋሎቱን በአቅራቢያው እንዲያገኝ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ለምሳሌ የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱን እስከ ቀበሌ ድረስ በማውረድና በመረጃ መረብ የታገዘ አሰራር በመዘርጋት ለተገልጋዮች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባሻገር የከተማዋን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ የሚያስችል ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በአቅም ግንባታውም ረገድ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም ተቀርጾ ተግባራዊ መሆን በመጀመሩ በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ እጅግ አመርቂ ባይባሉም በርካታ ውጤቶች እየታዩ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ ችግሮች የሚታዩ ቢሆንም ሠራተኛው በሥራ ሰዓት ሙሉ አቅሙን አሟጦ ለተመደበበት ሥራ ማዋልና ተገልጋዩን በቅንነት ማስተናገድ እንደሚገባው፣ ያለውን ውሱን ሀብት በአግባቡና በቁጠባ ተጠቅሞ ለበለጠ ውጤት መዘጋጀት እንዳለበት ግንዛቤ እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ከአደረጃጀት ጋር ተይይዞ አሁንም የተለያዩ የአሰራር ችግሮች መስተዋላቸው አልቀረም፡፡ አስተዳደሩ በዚህ ውስን ጊዜ ውስጥ ሰፊ የቤቶች ግንባታ ሥራና ትልልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ በርካታ የመሠረተ ልማት ተግባራትና የግንባታ ሥራዎች፣ መልካም አስተዳደርን የማስፈን፣ ሥራ አጥነትንና ድህነትን የማቃለል፣ የአቅም ግንባታና የሲቪል ሰርቪሱን የማጠናከር፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ልማት የማስፋፋት፣ የጤናና የትምህርት ሽፋንን የማሳደግ፣ ኤች.አይ.ቪ ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር፣ የገቢ አቅምን የማሳደግ፣ ኢንቨስትመንትን የማስፋፋት፣ የፍትህ ስርዓትን የማሻሻል ሥራዎችንና ሌሎች በርካታ ተግባራትን በስፋት አከናውኗል፡፡ አዳዲስ የልማት አውታሮችን በተለይም መንገድን ከመስራትና ነባሮችን ከማሻሻል አኳያ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ በተለይም በመንገድና የፍሳሽ ማስወገጃ ሥራዎች ላይ የሚታየው ለውጥ ለማንኛውም የከተማው ነዋሪ በግልጽ የሚታይና ሥራው ራሱ አፍ አውጥቶ የሚናገር ስለሆነ ዋቢ መጥቀሱ ተገቢ አይደለም፡፡ በርካታ የሚባሉ አዳዲስ መንገዶች ተከፍተው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ከመስጠታቸውም በላይ ለከተማው ያላበሱት ውበት ቋሚ ምስክር ነው፡፡ ሥራቸው ተጓትቶና አቅም አጥተው ሲያንከባልሉ ከነበሩ ተቋራጮች ጋር ውሉን በማቋረጥ ለሌሎች በመስጠት በነዋሪዎች ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ ተችሏል፡፡ ከእነዚህ ከተጀመሩ በርካታ የመንገድ ግንባታዎች ውስጥ የጎተራ የትራፊክ ማሳለጫ መንገድ ይገኝበታል፡፡ የከተማው ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰባቸው ካሉት የልማት ሥራዎች አንዱ የንጹህ ውሃ ችግርን መቅረፍ ነው፡፡ ይህን ችግር ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎችን በጥናት ከለየ በኋላ በእቅዱ በማካተት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ቀላል የማይባሉ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በዘርፉ እየተከናወኑ ካሉት ሥራዎች አንዳዶቹን ለመጥቀስ ያህል ባለፈው የበጀት ዓመት ቁጥራቸው 32 የሚሆኑ ጥልቅ የውሃ ጎድጓዶች ቁፋሮ ተጠናቆ በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል የዲዛይንና የማስፋፊያ ቧንቧ ዝርጋታ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩልም ለከተማዋ 23..000 ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ በማቅረብ የሚታወቀውን የገፈርሳ ግድብ ተጨማሪ ጥገና በማድረግና የማስፋፊያ ሥራ በማከናወን የስርጭት አቅሙን ለማሳደግ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የግድቡ ሥራ በሚያዚያ ወር ሲጠናቀቅ የቀን ስርጭት መጠኑ ወደ 30,000 ሜትሪክ ኪዩብ ከፍ ያደርገዋል፡፡ አስተዳደሩ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የ53 ጉድጓዶች ቁፋሮ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የእነዚህ ጉድጓዶች ቁፋሮ ሲጠናቀቅ በቀን ወደ 46 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ለከተማዋ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩልም በመዲናችን ሥር ሰድደው ከሚገኙ ችግሮች አንዱ የመኖሪያ ቤት እጥረት ነው፡፡ ችግሩን ለማቃለል ቀደም ሲል የነበረው የከተማው አስተዳደር ሰፊ የቤት ልማት ፕሮግራም በመንደፍ ከ1996 በጀት ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ በጀት መድቦ ተግባራዊ በማድረግ ላይ የነበረ ቢሆንም ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘና የግንባታ ዕቃዎች አቅርቦት በወቅቱ ሊሟሉ ባለመቻላቸው የቤት ልማት ፕሮግራሙ በተፈለገው ደረጃ አልተጓዘም፡፡ የባለአደራ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለፕሮግራሙ ትኩረት በመስጠት የተጀመሩ ውዝፍ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ነዋሪዎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ የተሰሩ ቤቶችም ፍትሀዊና ግልጽ በሆነ መልኩ ለነዋሪዎች የማስተላለፍ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አስተዳደሩ የቤት ልማት ፕሮግራሙን አጠናክሮ በመቀጠል በያዝነው በጀት ዓመትም የበጀቱን 34 በመቶ ለቤት ልማት በመመደብ የ33ሺህ ቤቶች ግንባታ የጀመረ ሲሆን ተጨማሪ 38ሺህ ቤቶችን ለማስገንባት የዲዛይንና የቦታ መረጣ ተካሂዷል፡፡ የቤት ልማት ፕሮግራሙ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ከማድረግ ባለፈ 750 ለሚሆኑ በኮንስትራክሽን ሥራ ለተሠማሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት ዘርፍም ለ113ሺህ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ለ22..725 ሰዎች ብር 123 ሚሊዮን የብድር አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይም የከተማው አስተዳደር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚንቀሳቀስባቸው ዘርፎች አንዱ ትምህርት ነው፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የወጣውን እቅድ መሠረት በማድረግ፣ ፈረቃን ለማስቀረት ወጣት ተኮር የአካባቢ ልማት ፕሮግራሞችን በመንደፍ በርካታ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን በነባርና አዲስ በሚከፈቱ ት/ቤቶች በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ጭምር እንዲገነቡ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከ1998-99 ዓ/ም 3900 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች፣ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ደግሞ 600 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል፡፡ የከተማዋ ከፍተኛውን ገቢ ከዚህ ቀደም ይሰበስብ የነበረው ከሊዝ ሽያጭ ሲሆን ይህ አካሄድ ዘላቂነት ሊኖረው እንደማይችል በመታመኑ ገቢዎችን አሟጥጦ በመሰብሰብ ከመቼውም ጊዜ በላቀና በተሻለ ሁኔታ የአስተዳደሩ በጀት ወደ 6.56 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ምንም እንኳ የገቢ መሰረቷን ለማስፋት እየተሰሩ ያሉ በርካታ ሥራዎች ያሉ ቢሆንም ያለውን ገቢ አሟጥጦ በመጠቀም በኩል በከተማ ደረጃ ከአፍሪካ አንደኛ በመውጣት ለመሸለም በቅታለች፡፡ የከተማዋን ጽዳት በተመለከተም ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ ሥራ በስፋት የተከናወነ ሲሆን የደረቅ ቆሻሻን በተገቢው ሁኔታ ለማስወገድ እንዲቻል የቆሼን ደረጃ የማሻሻልና ተጨማሪ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ የማዘጋጀት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መኪናዎችን በመግዛት የከተማዋን ቆሻሻ ለማስወገድ አቅም በፈቀደ መልኩ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የጤና አገልግሎትን ይበልጥ በከተማዋ ለማሻሻል 6 ክሊኒኮች ካሉበት ደረጃ ወደ ጤና ጣቢያ የማሳደግ፣ 19 አዳዲስ ጤና ጣቢያዎችና አንድ ዲስትሪክት ሆስፒታል የመገንባት፣ 174 ጤና ኬላዎች ሥራ እንዲጀምሩ የማድረግና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል እቅድ ይዞ በከፍተኛ ደረጃ በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎት ገደብ የለውም፡፡ አንድ ነገር ሲሰራ ሌላው እንደሚቀር እሙን ነው፡፡ አስተዳደሩም የከተማውን ነዋሪ ፍላጎት ለማሟላት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ይችላል ለማለት አንደፍርም፡፡ ሆኖም አስተዳደሩ ዋና ዋና ያላቸውን የነዋሪውን ችግሮች በመለየት ትኩረት እየሰጠ ለመፍታትና ከነዋሪዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት በቂ ናቸው ብሎ ባያምንም በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡ ከችግሮቹ ስፋት አንጻር አሁንም እጅግ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ እናምናለን፡፡ በአገልግሎት አሰጣጡና በመልካም አስተዳደሩም ረገድ ጅምር ሥራዎችን አጠናክረን መቀጠል እንዳለብን እንገነዘባለን፡፡ ነገር ግን የተሰራውን እንዳልተሰራ፣ ያልተደረገውን እንደተደረገ አድርጎ ነዋሪውን ለማሳሳት መሞከር ለየትኛውም ወገን ጠቃሚ አይደለም፡፡ ነፃ የሆኑ አስተያየቶች ሚዛናዊና ፍትሃዊ ከሆኑ ለሕዝቡም ሆነ ለአስተዳደሩ አስተማሪ ስለሚሆኑ ጥንቃቄ ቢደረግባቸው መልካም ነው እንላለን፡፡ (የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር የማስታወቂያና ባህል ቢሮ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |