Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 08th
Home arrow Sections arrow የወርቅ ማጭበርበር ድራማ
የወርቅ ማጭበርበር ድራማ Print E-mail
Sunday, 24 February 2008
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ወርቅ የተጭበረበረ ሆነ
ከወርቅ ጋር በተያያዘ ሁለት የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ኃላፊዎች ታሰሩ
ብሔራዊ ባንክ እንዴት ወርቅ ተጭበረበረ
 
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ወርቅ የተጭበረበረ ሆነ

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በአደራ ያስቀመጠው ወርቅ ብረት ሆኖ ተገኘ፡፡ የጉምሩክ ባለስልጣን 25 ኪሎ ግራም ወርቅ ትክክለኛ ወርቅ ሆነ፡፡

ከሦስት ሳምንት በፊት በተካሄደ ምርመራ እንደተረጋገጠው የተጭበረበረ ወርቅ መሆኑ የታወቀው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ወርቅ ከሦስት ዓመት በፊት ከአውሮፕላን ማረፊያ በኮንትሮባንድ የተያዘ እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወርቁን በአደራ ሲያስቀምጥ እንደ ማንኛውም ድርጅት ከባንኩ የተረከበው "ወርቅ መሰል" በሚል ማስረጃ ነበር፡፡ ምንጮች እንደገለፁት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአደራ ያስቀመጠው ወርቅ የተጭበረበረ መሆኑ የታወቀው በኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት የወርቅ ማቅለጫ ቀልጦ በላብራቶሪ ከመመርመሩ በፊት በተደረገ ምርመራ ነው፡፡

የአይን ምስክሮች እንዳስታወቁት ወርቅ የተባለው የአደራ ንብረት መጀመሪያ በግራም፣ ቀጥሎ በውኃ ተንሳፎ ከተመዘነ (ዌይት ኤች2ኦ) በኋላ ክብደቱ ከተቀመጠው መጠን አንሶ በመገኘቱ ነው፡፡ በተፈጠረው ሁኔታ ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር፡፡

በተመሳሳይ ዜና የጉምሩክ ባለስልጣን በአደራ ያስመጠው ወርቅ በተመሳሳይ ቀን ተመርምሮ ወርቅ መሆኑ ታውቋል፡፡ የባለስልጣኑ መሥሪያ ቤት በተለያዩ ጊዜያት በኮንትሮባንድነት በመያዝ በአደራ ያስቀመጠው ወርቅ መጠኑ 25 ኪሎ ግራም እንደሆነ ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል፡፡

የጉምሩክ ባለስልጣን ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠው ወርቅ ታህሳስ 10 ቀን 2000 ዓ.ም ወርቅ መሆኑ የተረጋገጠው ባለስልጣኑ ለባንኩ ጥያቄ ካቀረበ በኋላ እንደሆነ የባለስልጣኑ ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

ትክክለኛነቱ የተረጋገጠው 25 ኪሎ ወርቅ እንግሊዝ አገር ሄዶ ከተጣራ በኋላ ውጤቱ ለብሔራዊ ባንክ ሲላክ ለባለስልጣኑ ክፍያ እንደሚፈፀም ታውቋል፡፡

የጉምሩክ ባለስልጣን የካቲት 6 ቀን 2000 ዓ.ም ለብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ የወርቅ ማጭበርበር ዜና ይፋ ከሆነ በኋላ ተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀረበው ባለስልጣኑ "".ማርትሬዛ በሚል ከሁለት ዓመት በላይ በሴፍ ከስተዲ ሪሲት በድምሩ 34009-897 ግራም ተረክባችሁ መቆየታችሁ ይታወሳል" ይላል፡፡

ጌጣጌጦቹ ቀልጠው ወደ ግግር /ባር/ መልክ ከተለወጡና በጂኦሎጂካል ሰርቬይ ላቦራቶሪ ምርመራ ተካሂዶ ከተረጋገጠ በኋላ የሽያጩን ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና እንደሚያስገባ ባንኩ ገልፆ እንደነበር ያስታወሰው የባለስልጣኑ ደብዳቤ "". በተቻለ ፍጥነት ለመፈፀም ቀነ ቀጠሮ እንዲያዝልን እንጠይቃለን"

በሌላ በኩል የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ለባንኩ በተለያዩ ጊዜያት ደብዳበ ፅፏል፡፡ ጥቅምት 5 ቀን 2000 ዓ.ም የኤርፖርት ጉምሩክ ጽህፈት ቤት ለባለሥልጣኑ አስተዳደርና ፋይናንሰ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በፃፈው ደብዳቤ

"በአዲስ አበባ ኤርፖርት በኩል ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሲገቡና ሲወጡ ተገኝተው የተያዙ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የከበሩ ጌጣጌጦች በመሸጥ ሂሣቡ ለመንግሥት ፈሰስ ለማድረግ እንዲቻል በተለያዩ ወቅቶች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ የተደረገ ቢሆንም ሽያጩ ተከናውኖ ሒሣቡ ገቢ ያልተደረገልን በመሆኑ በተደጋጋሚ ከባለሥልጣኑ እና ከጽ/ቤታችን ደብዳቤ ሲፃፍ የቆየ ከመሆኑም በተጨማሪ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ስለሁኔታው በግንባር በመቅረብ ጥያቄ አቅርበናል፡፡

በዚሁ መሠረት ሕዳር 22 ቀን 1999 ዓ.ም በቁጥር ባውምዳ /ከማመ/1179/06 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለዋናው መ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ ንብረቶቹን የተረከበና ደረሰኝም የሰጠ ቢሆንም ጌጣጌጦቹን ገዝቶ ክፍያውን ለመፈፀም የጌጣጌጦቹን የጥራት ደረጃ እና ክብደታቸውን ጨምሮ የሚያስረዳ የጥራት ሠርተፍኬት ባለመኖሩ ክፍያውን ለመፈፀም እንደተቸገሩ እና የተጠየቀውን ክፍያ ለማከናወንና ሽያጩንም ለማጠናቀቅ እንዲቻል ጌጦጌጦቹን ቀልጠው ወደ ባር የሚለወጡበትንና የሚፈለጉት መረጃዎች የሚገኙበትን ሁኔታ በጋራ እንድናመቻች ጠይቋል፡፡

በቀረበው ጥያቄ መነሻነት የማቅለጡ ሥራ ያከናወኑ እንደሆነ ለኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት እና ለኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በደብዳቤ ላቀረብንላቸው ጥያቄ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ሥራውን እንደሚያከናውኑ በመግለጽ ዝርዝር ሁኔታውን በቁጥር 4/26/109/99/ በ14/5/99 በተፃፈው ደብዳቤ አሳውቀናል፡፡

ስለዚህ ሌላ አማራጭ መፍትሔ ካለም ታክሎበት የማቅለጥ ሥራው በአስቸኳይ ተከናውኖ ክፍያው ገቢ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲመቻች እንጠይቃለን፡፡" ሲል ይጠይቃል፡፡

በተመሳሳይ ታህሳስ 17 ቀን 2000 ዓ.ም ባለሥልጣኑ የኤርፖርት ጉምሩክን ደብዳቤ መነሻ በማድረግ ለብሔራዊ ባንክ በፃፈው ደብዳቤ

"ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በተለያዩ ጌጣጌጥ መልክ ተሠርተው ወደአገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን ባለ ቀጠና ኤርፖርት ጉምሩክ በኩል ተይዘው ለረጅም ጊዜያት ሳይረጋገጥ "ወርቅ መሰል" በሚል በ "ሴፍ ከስተዲ ሪሲት" በአደራ መልክ በብሔራዊ ባንክ ተቀምጠው የነበሩ ወርቅ መሰል ጌጦጌጦችን በኢትዮትያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ጉዳዩ የሚመለከታቸው በሙሉ በተገኙበት በጋራ ሆነን ታህሳስ 1ዐ ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም ጌጣጌጦቹን አስቀምጠን ወደ /ባር/ ግግር እንዲቀየሩ ማድረጋችን ይታወቃል፡፡ ጌጣጌጦቹ ወደ ግግር ወርቅ ከተቀየሩ በኋላ የተጣራ ዘጠኝ (9) ግግር ወርቅ በግራም 21,775 (ሃያ አንድ ሺ ሰባት መቶ ሰባ አምስት) ሆኗል፡፡ በሚመለከታቸው ባለሙያዎችም የወርቁ የጥራት ደረጃ ተረጋግጧል፡፡

ስለዚህ በ10/4/2000 ዓ.ም በነበረው የዓለም የወርቅ ገበያ ተመን መሠረት ተፈላጊ የአገልግሎት ክፍያዎችንና ተዛማጅ ወጪዎችን በመቀነስ ቀሪው ሒሳብ ብሔራዊ ባንክ በሚገኘው የሒሳብ ቁጥራችን ጂኦቪ. 0160101017000 ገቢ በአስቸኳይ ገቢ እንዲሆን እንጠይቃለን፡፡" ይላል፡፡

በሌላ ዜና ባለፈው ሳምንት በወጣው ተመሳሳይ የወርቅ ዜና ተጭበረበረ በማለት የፃፍነው 36 ኪሎ ወርቅ በመተሃራና ወለንጪቲ መካከል በኮንትርባንድ ከአገር ሊወጣ ሲል የተያዘ ነው ማለታችን ይታወቃል፡፡

ፖሊስ  በአደራ አስቀምጦት የነበረው ወርቅ ከሶስት ሳምንት በፊት የተጭበረበረ ሆኖ የተገኘው ወርቅ በተጠቀሰው ቦታ የተያዘ እንዳልሆነ አረጋግጠናል፡፡

በወቅቱ ክስ ተመስርቶበት የነበረው ይሄው ወርቅ ከወቅቱ ሲውዘርላንድ አርጐር ሀውስ የሚባል ወርቅ አንጣሪ ዘንድ ተልኮ 91.78% ንፁህ ወርቅ፣ 6.8% ብር፣ 1.42 የከበረ ማዕድናት ቀሪው ደግሞ የተለያዩ ማዕድኖች መሆናቸው ተጠቅሶ ለብሔራዊ ባንክ ከተገለፀ በኋላ በወቅቱ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 60/1989፣ በብሔራዊ ባንክ ሲቲጂ/1997 መመሪያ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ለገቢዎች ሚኒስቴር በፃፈው ደብዳቤ መሠረት ፒ64855.46 ግራም (65 ኪሎ) ክፍያ ተከናውኗል፡፡ በወቅቱ በነበረው አሰራር የወርቁ 50% ብር 3,749,639.60 ብር ለጉምሩክ ባለስልጣን ገቢ ተደርጓል፡፡ ዜናውም በዚህ እንዲስተካከል መረጃ ያቀረቡ ጠይቋል፡፡

ከወርቅ ጋር በተያያዘ ሁለት የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ኃላፊዎች ታሰሩ

ሁለት የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከትናንት በስቲያ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰማ፡፡ ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የምርመራ ሥራውን በቅንጅት የሚሠሩት ክፍሎች ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ግለሰቦች በአብዛኛው በቁጥጥር ስር አውለዋል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት የፋይናንስ ቋማ ኮሚቴ በአጥፊዎቹ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የብሔራዊ ባንክ የኮረንሲ ማኔጅመንት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋሱ አዳምና የትሬዠሪ መምሪያ ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ ተክለሐና ዘለቀ ናቸው፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንዳስታወቁት ሁለቱ የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

አቶ ዋሱ አደም የካቲት 11 ቀን 2000 ዓ.ም ለተወካዮች ምክር ቤት የፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ከሰጡት የባንኩ አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ የምርመራ ሥራ ከሚያከናውኑት ክፍሎች ጋር መረጃ የማሰባሰብ ሥራም ሲሰሩ ነበር፡፡

የፌዴራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የፌዴራል ፖሊስና የዋናው ኦዲተር በአንድነት የምርመራ ሥራ እያከናወኑበት ያለው የወርቅ ማጭበርበር ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በአብዛኛው በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆነ ለአሰራሩ ቅርበት ያላቸው ተናግረዋል፡፡ በርካታ ገንዘብም በፍተሻ ተገኝቷል፡፡ የመለሱም አሉ፡፡ እንደ እነዚሁ ክፍሎች ገለፃ የዋናው ኦዲተር በጉዳዩ ዙሪያ ያካሄደውን ምርመራ በማጠናቀቁ ተጠርጣሪዎች ላይ በያዝነው ሳምንት ክስ እንደሚመሰረት ግምታቸውን ገልፀዋል፡፡

የባንኩ ኃላፊዎችም ሆነ የዋናው ኦዲተር ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ያገኙትን የምርመራ ውጤት ለፓርላማ እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት የፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ በወርቅ ማጭበርበር ዙሪያ ወንጀል ፈፅመዋል በተባሉት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ማሳሰቡን የባንከ ባለስልጣናት ማብራሪያ በሰጡበት ባለፈው ሳምንት አሳስቧል፡፡

ብሔራዊ ባንክ እንዴት ወርቅ ተጭበረበረ

ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ብሔራዊ ባንክ ወርቅ ሲረከብ አንዳችም ዓይነት ማጭበርበር አይከናወንም ነበር፡፡ ችግሩ የተፈጠረው አሰራሩ በትዕዛዝ እንዲቀየር ከተደረገ በኋላ ነው በማለት ስለ አሰራሩ የሚያውቁ ይገልፃሉ፡፡ አሰራሩን

"የቀድሞው አሰራር ክፍተት አይፈጥርም" የሚሉት እነዚሁ ክፍሎች ብሔራዊ ባንክ የተጭበረበረውና ለአጭበርባሪዎች በሩን የከፈተው አሰራሩን አሻሽላለሁ በሚል ራሱ ጓዳውን ወለል አድርጐ በማሳየት ነው፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ አባባል ባንኩ የፈፀመው የአሰራር ክፍተት "እጅግ በጣም አስገራሚና አንድ ከፍተኛ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋም ሊፈፅመው የማይገባ አሳዛኝ ድርጊት ነው"

ባንኩ አሻሻልኩት በማለት የቀየረውና ለዝርፊያ ያጋለጠው አሰራር ወርቅ የሚሸጠው (ላኪ) ብቻውን አድራጊና ፈጣሪ የሚሆንበት ነው፡፡ መንግሥትን ሲያጭበረብሩ የነበሩትን አስተያየት የሚሰጡት "ሌቦቹ" ይሏቸዋል፡፡ ሌቦቹ ወርቅ ይዘው በጂኦሎጂካል ሰርቬይ ላቦራቶሪ ከማስመርመራቸው በፊት ተመሳሳይ ቅርፅ፣ ተመሳሳይ ክብደት፣ ተመሳሳይ ይዘት ያለው የተጭበረበረ "ፌክ ወርቅ" ያዘጋጃሉ፡፡ ለዚህም ሥራ የተመረጡ የብረት ዓይነት ሊድ ነው፡፡ ባለሙያዎች የሊድ ብረት ከወርቅ ጋር ተመሳሳይ ክብደት እንዳለው ይናገራሉ፡፡

ትክክለኛ ወርቅ በጂኦሎጂካል ላቦራቶሪ ተመርምሮ ወርቅ መሆኑ ሲረጋገጥ የትክክለኛነት ሰርተፊኬት ይሰጠዋል፡፡ በሳሙና ቅርፅ የተዘጋጀው ወርቅ ይታሸጋል፡፡ ሰርተፊኬቱንና እሽጉን ወርቅ ብሔራዊ ባንክ ይረከባል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ሲሸወድ የነበረው ታዲያ እዚህ ላይ ነበር፡፡ ወርቅ ውጪ አገር የሚልኩ ራሳቸው ወርቁን ያስቀልጣሉ፣ ራሳቸው ላቦራቶሪ ይወስዳሉ፣ ራሳቸው የወርቅነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ይወስዳሉ፣ ራሳቸው ወርቁን ያሳሽጋሉ፣ ራሳቸው ወርቁን ተሸክመው ብሔራዊ ባንክ ያመጣሉ፡፡ ይህ አሰራር ባንኩን "አቅልጦታል"፡፡ ይላሉ ስለአሰራሩ የሚያውቁ፡፡

"ባንክ የሚሸወደው" ይላሉ ለአሰራሩ ቅርበት ያላቸው፡፡ ሁሉንም የሥራ ሂደት አከናውኖ ባንክ መጥቶ ገንዘብ የሚወስደው ወርቅ ነጋዴ ከላቦራቶሪ አስመርምሮ የሚያመጣውን ወርቅ መንገድ ላይ ይቀይረዋል፡፡ በተመሳሳይ ግራም የተዘጋጀ ወርቅ ብሔራዊ ባንክ ሳንቲም በሚያስገባበት ሳጥን ራሱ ያሽግና (ግብረ አበሮች አሉ) ለብሔራዊ ባንክ የግምጃ ቤት ሠራተኞች ከተሰጠው የወርቅ ማስረጃ ሰርተፊኬት ጋር ያቀረባል፡፡ የባንኩ ሠራተኞች ሚዛኑን አረጋግጠው ይረከባሉ፡፡

ወርቅ ሳይሆን የትክክለኛ ወርቅ ሰርተፊኬት ሲገዛ የኖረው ባንክ መጭበርበሩን ያወቀው እንዴትና እንዴት እንደሆነ የሰሞኑን ዘገባዎች በማስታወስ የጠቆሙት ውስጥ አዋቂዎች "ባንኩ ከቀለጠ በኋላ አሰራሩን ቀየረ" ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለተቀበለው ወርቅ የሚሰጠው መረጃ ሴፍ ከስተዲ ሪሲት "ወርቅ መሰል ብር መሰል" የሚል ሀረግ በመጥቀስ በመሆኑ ድርጅቶች በአደራ ያስቀመጡት ወርቅ ከዓመታት በኋላ "ባዕድ ብረት" ሆኖ ሲገኝ "ወርቅ አስረክበን ተቀየረብን" ብለው አቤቱታ ለማቅረብ አይችሉም፡፡ ስለአሰራሩ የሚያውቁ እንደሚጠቁሙት ወርቅ በአደራ ያስቀመጡ ድርጅቶች ግን የተሰጣቸው ደረሰኝ ወርቅ ለማስቀመጣቸው እንደ ትክክለኛ ማስረጃና መተማመኛ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል የጉምሩክ ባለስልጣንና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ይጠቀሳሉ፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ "ብሔራዊ ባንክ እጅ ወርቅ ነበረኝ" ሲል የቆየው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ሰሞኑን በተካሄደ ምርመራ 36 ኪሎ ግራም የሚሆን ወርቅ ባዕድ ነገር መሆኑ ታውቋል፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ "ወርቅ ቅብ የተቀባ የነሀስ ብረት" ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ግርማ ብሩ የአሰራሩ ክፍተት ዝርፊያ እንዲካሄድ በር መክፈቱን ከሁለት ሣምንት በፊት ከጋዜጣው ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

በዚሁ የአሰራር ክፍተትም ይሁን በቁርኝት ባንኩ እስከ 200 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ዝርፊያ እንደተከናወነበት መግለፃችን አይዘነጋም፡፡   

አሁን በተቀየረው አዲስ አሰራር ወርቅ ሲመረመር የወርቁ ባለቤት፣ ከፌዴራል ፖሊስ 5፣ ከደንነትና ከብሔራዊ ባንክ 2 አባላት ያካተተ ቡድን በእማኝነት ይቆማሉ፡፡ ከዚህም በላይ ባንኩ ራሱ ላቦራቶሪ መክፈቱ ዋንኛ መፍትሄ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ገልፀዋል፡፡

በአሰግድ ተፈራ
 
< Prev   Next >