Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Friday
Nov 21st
Home arrow Sections arrow ማየት የተሳናቸው ተረሱ ወይስ ታወሱ?
ማየት የተሳናቸው ተረሱ ወይስ ታወሱ? E-mail
Sunday, 06 January 2008
በዓለም ላይ በየአምስት ሰከንድ አንድ ሰውና በየአንድ ድቂቃ አንድ ሕፃን ማየት የተሳናቸው /ዓይነስውራን/ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም 37 ሚሊዮን ማየት የተሳናቸውና 124 ሚሊዮን እይታቸው የቀነሰ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ከአሥሩ ዘጠኙ የሚኖሩት አነስተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ መሆኑን አቶ ዘገዬ ኃይሌ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሌሎች በሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ቡድን መሪና የአገር አቀፍ የዓይነ ስውርነት መከላከል ኮሚቴ ሊቀመንበር አስታወቁ፡፡

ዋልታ የዓይነ ሥውራን ማህበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል አዳራሽ ታህሳስ 2ዐ ቀን 2ዐዐዐ ባካሄደው አውደጥናት ላይ አቶ ዘገዬ እንዳመለከቱት ለዓይነስውርነት መንስኤ የሆኑት ካታራክት /ዓይነሞራ/፣ ትራኰማ፣ ግላኮማ፣ ሪስራክቲቭ ኤረር /በመነፅር ሊስተካከል የሚችል የእይታ ችግር/፣ የቫይታሚን ኤ እጥረት ወዘተ. ናቸው፡፡

ከእነዚህም መካከል ዓይነ ሞራን ማከም፣ ትራኮማን ደግሞ መከላከል ይቻላል፡፡ ዓይነሞራ ብዙውን ጊዜ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው፡፡ ይህንንም በ3ዐ ደቂቃ ውስጥ በቀዶ ሕክምና መገላገል ሲቻል ቁጭ ብሎ ዓይነስውር የሚኮንበት ጊዜ አለ፡፡

ይህም የሚሆነው ካለማወቅ፣ መድኃኒቱን በጊዜው ካለማግኘት፣  ማነስ ምክንያት ህክምና በቅርብ ለማግኘት አለመቻል ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ዓይነስውርነት የድህነት በሽታ እየተባለ ይጠራል፡፡

ዓይነስውርነት ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች በብዛት ይከሰታል፡፡ እ.ኤ.አ እስከ 2ዐ2ዐ ድረስ በዓለም ውስጥ 1ዐዐ ሚሊዮን ህዝብን ከዓይነስውርነት የማዳን ዓላማ ያነገበና ..ትዌንቲ፣ ትዌንቲ.. የተባለ ግሎባል ኢኒሼቲቭ መኖሩን አቶ ዘገዬ ገልፀው ኢኒሼቲቩ በዓለም ደረጃ የተጀመረው በ1999 ሲሆን በአገራችን የተጀመረው ደግሞ በ2ዐዐ2 መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያ ውስጥ የአገር አቀፍ ዓይነስውርነት መከላከል ኮሚቴ መቋቋሙን፣ ኮሚቴውም ሁሉንም ክልሎች፣ እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ያላቸውን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ሲቪክና ኘሮሞሽናል ድርጅቶች የዓለም ጤና ድርጅቶችን ማቀፉን አቶ ዘገዬ አስረድተዋል፡፡

ኮሚቴው እ.ኤ.አ ከዲሴምበር 2ዐዐ5 እስከ ሴኘቴምበር 2ዐዐ6 ድረስ በዓይነ ስውርነት፣ በእይታ መቀነስና በትራኮማ ላይ ያተኮረ ጥናት አካሂዷል፡፡

በጥናቱም መሠረት በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሚሊዮን 2ዐዐ ሺህ 456 ማየት የተሳናቸው፣ 2 ሚሊዮን ሺህ 776 ሺህ 54 እይታቸው የቀነሰ፣ ከአንድ እስከ ዘጠኝ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙና ለአክቲቭ ትራኮማ የተዳረጉ 9 ሚሊዮን 34 ሺህ 931 ህፃናት እንደሚገኙ ከአቶ ዘገዬ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህም ሌላ የቅንድብ ፀጉር ዓይንን ሲፈቀፍቀው እንደጭስ ዓይነት ነገር የዓይን ኳስ ላይ ይወጣል፡፡ ይህም ከዓይነ ስውርነት በፊት ለሚከሰተው ትራኮማ መጨረሻ ደረጃ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የተጠቁ 1 ሚሊዮን 255 ሺህ 977 ሰዎች አሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ቶሎ ህክምና ካላገኙ ለዓይነ ስውርነት ይዳረጋሉ፡፡

አቶ ትዕዛዙ አሳረ በትምህርት ሚኒስቴር የኘላንና ፖሊሲ ትንተና መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው፣ በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ ያተኮረ የፆታና የትምህርት ፍትሃዊነት መምሪያ መቋቋሙን ገልፀው ያሉትን የመማሪያ ማስተማሪያ መፃህፍትንና ሲብለሶችንም ጭምር ማየት ለተሳናቸው በሚስማማ መልኩ ተዘጋጅቶ ወደ ብሬል በመገልበጥ ለመምህሩ መምሪያ፣ ለተማሪዎች ደግሞ የተማሪ መፅሐፍ ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ በመመቻቸት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ማየት በተሳናቸው ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ ትምህርት ቤቶች በመቀሌ፣ በሰበታ ወዘተ አሉ፡፡ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ማየት የተሳናቸውን ለብቻቸው አግልሎ ከማስተማር ይልቅ ከዓይናማ ወይም ጤነኛ ከሆኑ ተማሪዎች ጋር ሁሉንም በአንድ ላይ ቀላቅሎ ማስተማር ነው፡፡

ይህ ዓይነቱም አካሄድ ማየት የተሳናቸው ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር መቀላቀልና መላመድ ይችላሉ፡፡ የሚያስፈልጋቸውንም ማመቻቸት የትምህርት ሚኒስቴር ሥራ እንደሆነ ነው አቶ ትዕዛዙ የተናገሩት፡፡

በተለይ ለ1ዐኛና ለ12ተኛ ክፍል ፈተና የተለየ ዝግጅት ተደርጎላቸው ነበር ያሉት የመምሪያው ኃላፊ፣ ይህም ማለት ለእያንዳንዱ ተፈታኝ ዓይነስውር አንድ ፈታኝ ተመድቦለት እንደተፈተነ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ከ1ዐኛ ወደ 11ኛ፣ ከ12ኛ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲሸጋገሩ የተለየ ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አሁን ያሉት የትምህርት ተቋማት መጀመሪያ ሲገነቡ ለአካል ጉዳተኞች በሚሆን መልኩ የተመቻቹ አይደሉም፡፡ ከእንግዲህ ግን ለአካል ጉዳተኞች በሚመች መልክ መገንባት አለባቸው የሚል አቋም ተይዞ በዚሁ እየተኬደበት ነው ያለው፡፡

አቶ ትዕዛዙ እንደገለፁት ለሚሌኒየሙ የልማት ግብ እውን መሆን እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች አቅም ማንቀሳቀስ የግድ ይላል፡፡ ትልቁ ችግር ግን ኀብረተሰቡ እነዚህኑ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት አለመላኩ ነው፡፡

አቶ ደለለኝ ሳሙኤል በትምህርት ሚኒስቴር የውጭና የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ..ማየት የተሳናቸው ከሌሎች አካል ጉዳተኞች ሁሉ ቀደም ብለው ትምህርት የጀመሩ ቢሆንም የሚፈለገው ደረጃ ላይ ግን አልደረሰም.. ብለዋል፡፡

ማየት ለተሳናቸው ከዚህ በፊት ይደረጉ የነበሩ ድጋፎች በአንዳንድ ሁኔታ ተስተጓጉሎባቸዋል፡፡ በቤተመፃህፍትና በማጣቀሻ መፃህፍት በኩልም ክፍተቶች አሉ፡፡ በመንግሥት አቅም ብቻ የተስተጓጐሉትን ለማስተካከልና ክፍተቶችንም ለመሙላት ስለማይቻል በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚገኙ ድጋፎችን በማስተባበር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ማህበሩና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

የዋልታ የዓይነ ሥውራን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ስንታየሁ ገብረማርያም በበኩላቸው የዓይነ ሥውራን ጉዳይ በዓለማችን የሁሉም አገሮችና ህዝቦች ከሁሉም በላይ ደግሞ የራሳቸው የዓይነ ሥውራኑ ጉዳይ መሆኑ የሚታወቅ መሆኑን ገልፀው ሁሉም ወገኖች የየበኩላቸውን ኃላፊነት ይወጡ ዘንድ የተቀነባበረና ሁሉንም የሚያሳትፍ ዕቅድ ነድፎ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ የሚነደፈው ዕቅድ ውጤታማ እንዲሆን ወይም እንዲሳካ በውል የተደራጀ ዓላማና ግብ በአግባቡ የተቀመጠና በዓይነ ሥውራን ጉዳዮች ዙሪያ ያገባናል ከሚሉ ወገኖች ጋር በመተጋገዝ የሚሠራ ድርጅት አስፈላጊ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ቅድሚያ የተሰጠውን የማኀበሩን ዓላማ በተግባር ለመተርጎም በቅርቡ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመሥራት አጠቃላይ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በመሆኑም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ዓይነሥውራን ተማሪዎች የሚያገኙት የቤተመፃህፍት አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ እንዲደራጅና ወቅቱን የጠበቁ መፃህፍትና የትምህርት መገልገያዎች በነፃ እንዲቀርቡላቸው ጥረት ይደረጋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምን ያህል ዓይነሥውራን ተማሪዎች እንዳሉ ለማወቅ እያንዳንዱ ተቋም ያሉትን የዓይነሥውራን ተማሪዎች ብዛት በፆታ ለይቶና የሚሰጡትን የትምህርት ዓይነቶች ዘርዝሮ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዲያሳውቅ ትምህርት ሚኒስቴር ለ54 ተቋማት ደብዳቤ ፅፏል፡፡ መልስም እያገኘ ነው፡፡

አቶ ስምኦን ተክለሃይማኖት የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው ለ4ዐ ዓመታት ያህል በዓይነስውራን የትምህርት ተቋም ማገልገላቸውን፣ በቆይታቸውም ወቅት ማየት ለተሳናቸው ጨምሮ ለአካል ጉዳተኞች በጀት ተይዞ መፃህፍት የተገዛበት ወቅት እንዳላጋጠማቸው፣ ለፈተና ጊዜ በማስታወቂያ ሠሌዳ ላይ የሚለጠፉት ማስታወቂያዎች የሚያገለግሉት ለዓይናማዎቹ ብቻ እንደነበር ማየት የተሳናቸው የሚያነብላቸው ዓይናማ ጓደኛ ከሌላቸው ማወቅ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ አብርሃም ፀጋዬ የኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ድርጅቶች ኔትወርክ ሊቀመንበር ማየት በተሳናቸው ላይ ተጋርጠው ከነበሩት በርካታ ችግሮች መካከል አንዳንዶቹ እንድተቀረፉላቸው ጠቁመዋል፡፡ በኬኔዲ ቤተመፃህፍት ውስጥ የነበረው የብሬል ክፍል በአሁኑ ጊዜ ተስፋፍቷል፡፡ የኮምፒውተር ትምህርት ወይም የኮምፒውተር መረጃ መሳሪያዎች ማየት ለተሳናቸው እየቀረበላቸው ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኞች ማዕከልም ተቋቁሟል፡፡ በሌሎች ትምህርት ተቋማት ግን ማየት ለተሳናቸው መገልገያዎች ወይም የድጋፍ አገልግሎቶች የሚታወቁም አይደሉም፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከፍተኛ ትምህርት ቢበዙም ማየት የተሳናቸውን ፍላጎት አላካተቱም፡፡

በታደሰ ገብረማርያም

 
< Prev   Next >