| የኤርትራና የተመድ ወዝግብ ቀጥሏል |
|
|
| Sunday, 24 February 2008 | |
የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራን በድጋሚ አወገዘየኤርትራ መንግሥት የተመድ የኢትዮ-ኤርትራ ልዑክ አንሚ ነዳጅ እንዳያገኝ በመከልከሉ ድርጅቱ ወታደሮቹን ለማስወጣት የወሰነ ቢሆንም ኤርትራ እንቅፋት ከመፍጠር አልተቆጠበችም፡፡ በመሆንም ባለፈው ሐሙስ የፀጥታው ምክር ቤት የአገሪቱን ድርጊት አውግዟል ሲል አጃንስ ፍራንስ ኘሬስ ዘግቧል፡፡ ኤርትራ በበኩልዋ የተመድ ውሳኔን ተቸች፡፡ አሥራ አምስት አባላት ያሉት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በዝግ የምክክር ስብሰባ ካደረገ በኋላ ያወጣው መግለጫ፣ "ኤርትራ በፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችና በኘሬዚዳንቱ ማስጠንቀቂያዎች ላይ ጥሰት በመፈፀሟ እናወግዛለን" ይላል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት የድርጅቱ ዋና ፀኃፊ ባን ኪሙን ችግሩን ለመፍታት እያደረጉ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉና ለችግሩን አጠቃላይ መፍትሄ የያዘ ልዩ ሪፖርት ከእሳቸው እየተጠባበቁ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የተመድ የኢትዮ-ኤርትራ ሰላም አስከባሪ (አንሚ) ባለሥልጣናት ከአካባቢው ለማስወጣት ድርጅቱ ከያዘው ዕቅድ ቀደም ባለው ጊዜ በአስመራ እየተሰባሰቡ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ሚካኤል ሞንታስ ባለፈው ሐሙስ ተናግረዋል፡፡ "የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ለመተባበር ፈቃደኞች ባለመሆናቸው በአገሪቱ የሚገኙት የሰላም አስከባሪው ወታደሮች ከአገሪቱ የሚወጡበትን መንገድ ለማመቻቸት ወደ አስመራ እየተሰበሰቡ ነው" ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለሰላም አስከባሪው አባላት ምግብ ሲያቀርብ የነበረው የኤርትራ የንግድ ኩባንያ ውሉን በማቋረጡ ወታደሮቹ የምግብ እጦት እንዳጋጠማቸው የኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ ጠቅሷል፡፡ አንሚ ሰራተኞቹን ወደ ኢትዮጵያ ለማዛወር የወሰነው፣ ኤርትራ ለሰላም አስከባሪው ነዳጅና ምግብ እንዳይተላለፍ በመከልከሏ መሆኑን ይታወሳል፡፡ ይህ የኤርትራ እርምጃ ሰላም አስከባሪው በድንበሩ አካባቢ የነበረው እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ እንዲያቋርጥ ያደረገ ሲሆን፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድርጊቱን ተቃውሟል፡፡ ባለፈው ሳምንት የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰላም አስከባሪው ጊዜያዊ መዛወርም ሆነ በሌላ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ እንዳልሆኑ አስታውቀዋል፡፡ በኤርትራ የሚገኘው የአንሚ ወገን በኤርትራ መንግሥት ችግር እየገጠመው ነው የሚለውን የተመድ ሪፖርት የአገሪቱ መንግሥት አስተባብሏል፡፡ "የተመድ ዜና አገልግሎትና ሌሎች ዓለም አቀፍ የግል ሚዲያዎች አንሚ በኤርትራ ስለገጠመው ሁኔታ ያወጡ ያሉት ዘገባ እጅግ ከእውነት የራቀ ነው" ይላል በአንሚ የኤርትራ ልዑክ መግለጫ፡፡ በኤርትራና በተመድ የተፈጠረው ውዝግብ አሁን የተጀመረ አይደለም፡፡ ችግሩ መታየት የጀመረው ባለፈው ታህሳስ ወር ኤርትራ አንሚ ነዳጅ እንዳያገኝ መከልከል በጀመረችበት ወቅት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጎልቶ የወጣው ባለፈው ሳምንት አገሪቱ የሰላም አስከባሪው አባላትን ምግብም ጨምሮ መከልከሏ ተከትሎ ነው፡፡ አንሚ አሁን መጨረሻ ከአካባቢው እንዲወጡ በተመድ ትዕዛዝ ከተላለፈበት በፊት ለወራት ያህል የነዳጅ ክልከላውን በሰላማዊ መንገድና በድርድር በመፍታት ሲሞክር ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2ዐዐዐ ሁለቱም አገሮች በአልጀርስ የፈረሙት የሰላም ስምምነት መሠረት ለችግሩ የመጨረሻ መፍትሄ ያስገኛል ተብሎ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ በካርታ ላይ በማመልከት በመሬት ላይ ወሰኑን ለማመልከት ምንም ዓይነት ተግባር ሳያከናውን ከሦስት ወር በፊት መበተኑ ይታወቃል፡፡ ሁለቱም አገሮች ወደ ጦርነት መግባት እንደማይፈልጉ ቢናገሩም በተግባር ግን በድንበሩ አካባቢ ከ200,000 በላይ ወታደሮች ማስፈራቸው ይታወቃል፡፡ ፣ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩኘ፣ የተባለው ቡድን በአካባቢው ያለው ሁኔታ አስጊ መሆኑንና ጦርነት አይቀሬ መሆኑን ሰፊ ትንታኔ መሰጠቱ አስመልክተን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የደቡብ አፍሪካ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ሪቻርድ ኮርንዌል በበኩላቸው የሰላም አስከባሪ ኃይሉ መውጣት ውጥረቱን የሚያባብስ እንደሆነ መግለፃቸውን የአሜሪካ ድምፅ ዘግቧል፡፡ "አንሚ ከአካባቢው ማስወጣት ማንኛውም ነገር እንዲፈጠር መፍቀድ ነው" ያሉት ኮርንዌል፣ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ሁለቱን ወገኖች አንዱ በአንዱ ላይ ወቀሳውን መሰንዘሩ አይቀርም ብለዋል፡፡ እንደ ተንታኙ አባባል ኘሬዚዳንት ኢሳያስ በውስጥ ችግሮች ተወጥረው ይገኛሉ፡፡ "ኤርትራ የጦር ሀገር ሆናለች፤ የአገሪቱ መንግሥት የውስጥ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውሶችን ለመሸፈን ጦርነት መቀስቀሱ ግድ ይለዋል፤ ባለፈው ጦርነት ተቀናሽ የተደረጉ ወታደሮችም ሳይቀነሱ ቀርተዋል" ብለዋል ሪቻርድ ኮርንዌል፡፡ ገለልተኛው የድንበር ኮሚሽን የጦርነቱ እምብርት የሆነችውን "ባድመ" ለኤርትራ አሳልፎ የሰጠ ሲሆን ኢትዮጵያ ውሳኔውን በመርህ ደረጃ መቀበልዋን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በተለያየ ወቅት አቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ውሳኔው መንደሮች ትምህርት ቤቶችና ቤተክርስቲያኖች ለሁለት የሚከፍል በመሆኑ በአፈፃፀም ላይ ውይይት ካልተደረገ ዘላቂ ሰላም አያመጣም ይላሉ፡፡ የኤርትራ መንግሥት ከዚህ በተቃራኒ ውሳኔው ያለምንም ድርድርና ውይይት ተፈፃሚ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ ለውሳኔው ተፈፃሚነት መዘግየትም ምዕራባውያን በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ አሜሪካን ይነቅፋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በድንበሩ አካባቢ በተመድ የተከለለው ጊዜያዊ የደህንነት ቀጠና ሲጠብቅ የነበረው አንሚ ከኤርትራ መንግሥት በደረሰበት ጫና ለመልቀቅ መገደዱ የሁለቱ አገሮች ውጥረት ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋት አይሏል፡፡ በጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |