| የ”እብድ ኀሙስ” ኹለት ገጽታዎች |
|
|
| Sunday, 24 February 2008 | |
|
በኢትዮጵያ ትውፊት ውስጥ ከሚታወቁት መካከል “እብድ ኀሙስ” አንዱ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ትስስርም አለው፡፡ ስለ እብድ ኀሙስ የትመጣ ኹለት ገጽታዎች አሉ፡፡
አንደኛው እብድ ኀሙስ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሥርዓት የሦስት ቀን ጾም (ጾመ ነነዌ) ካበቃ በኋላ በክብሩ ቀን ኀሙስ የሚውልበት ነው፡፡ /ኀሙስ የካቲት 13 ቀን 2000 ዓ.ም እንደዋለው፡፡/ እንደ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ አገላለጽ “የእብድ ዐሙስ ሰዎች እንደ እብድ እየኾኑ የተጫወቱበትና የተደሰቱበት ከነነዌ ቀጥሎ ያለው ዐሙስ፡፡ ፈረንጆች ካርናባል ከሚሉት ይስማማል፡፡” በጥንት ጊዜ ጾመ ነነዌ ሲጾም ልጅ፣ አዋቂ ብቻ ሳይሆን እንስሳትም እንዲጾሙ በመደረጉ በመፍቻው ዕለት ጥጃ ከላም የተገናኙበት፣ ረሃባቸውን ያስታገሱበት፣ የፈነጠዙበት ዕለት ስለሆነ እብድ ኀሙስ ተሰኘ ይባላል፡፡ ሁለተኛው ገጽታ እብድ ኀሙስን ከዋናው ዐቢይ ጾም (ሁዳዴ) ዋዜማ ጋራ ያያይዘዋል፡፡ /ኀሙስ የካቲት 20 ቀን 2000 ዓ.ም እንደሚውለው፡፡/ እንደ መምህር ካሕሣይ ገብረ እግዚአብሔር አገላለጽ፣ በሀገር ቤት የመጨረሻዋ የፍስክ ዕለተ ኀሙስ “እብድ ኀሙስ” ይሏታል፡፡ ምክንያቱም የመጨረሻ የሠርግ ዕለት ስለሆነችና ሰው ሁሉ ስለሚዋከብ ነው፡፡ ከእብድ ኀሙስ ቀጥላ ያለችው የመጨረሻዋ የጾም መግቢያ /ቅበላ/ እሑድ ደግሞ “ጥምብ አንሣ” ትባላለች፡፡ ምክንያቱም ከሠርጉ ወይም ከድግሱ የሚተርፈው ሥጋና ሌላም የተነካካ ምግብ ቢኖር የሚበላው ስለማይኖር ነው፡፡ በተለያዩ ሀገሮች እንደሚደረገው ሁሉ ከሃይማኖታዊ ወይም ከአሕዛባዊ ክብረ በዓላት በመነሳት ዘመናዊ በዓላት እንደ ቫለንታይንስ ዴይ፣ ካርኒቫልስ ወዘተ. እንደሚከበሩት የእኛን “እብድ ኀሙስ” የምናነግሥበትን ስልት መቀየስ ከሚመለከታቸው ሁሉ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ “የእብድ ቀን፣ እብድ ዐሙስን የመሰለ፡፡ እብድ ቀን አይመሽ፣ እብድ ለእብድ ቀን ይበጃል እንዲሉ” አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ፡፡ በሔኖክ ያሬድ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |