Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow ኪነ ጥበብን ለማኅበራዊ ዕድገት
ኪነ ጥበብን ለማኅበራዊ ዕድገት Print E-mail
Sunday, 24 February 2008
Image
ዶክተር ንጉሤ ተፈራ
“ኪነ ጥበብን ለማኅበራዊ ዕድገት” በሚል መርሕ የሚንቀሳቀሰው ፖኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር (ፒ.ኤም.ሲ) ደራስያንን የበለጠ በማበረታታት የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ ገጽታና ሁኔታ በጥሩ መልኩ ሊያሳዩ የሚችሉ አጫጭር ልብ ወለዶችና ኢ-ልብወለድ ሥራዎችን ከተለያዩ ደራስያን ጋር በመነጋገር አዘጋጅቶ ለማሳተም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ፒ.ኤም.ሲ ባለፈው የካቲት 11 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን ባስመረቀው በሴት ደራስያን የተዘጋጁ አጫጭር ልብወለዶች መድበል ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የፖኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ንጉሤ ተፈራ እንደተናገሩት፣ በቅርቡ በዘጠኝ ደራስያን የተጻፉ ኢ-ልብወለድ ታሪኮችን ያካተተ መጽሐፍ ለማሳተም ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮ ውስጥ በጎ አስተዋጽዖ ሊያሳድሩ በሚችሉ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች፣ በተለይም በጎና ጎጂ በሆኑ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ የሚያተኩሩ፣ የሥነ ምግባር መዳበር፣ የፈጠራ ሥራ ማሻሻልና በዕድገትና ልማት ዙሪያ ገንቢና አስተማሪ የሆኑ ሥራዎች ማቅረብ የሚችሉ ደራስያን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ተጠሪው ገልጸዋል፡፡

ፖኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር አዲስ ያወጣው አራተኛው መድበል “ያልተናበቡ ልቦች” ሲሰኝ በውስጡ አሥራ አንድ አጫጭር ልብ ወለድ ታሪኮች ይዟል፡፡

የድርሰቶቹ ዐቢይ ትኩረት ሴቶችና በሴቶች ሕይወት ዙሪያ የሚታዩ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በአብዛኛው የወጣት ሴት ገፀ ባሕርያትን ታሪክ በመተረክ ደራሲዎቹ በማኅበረሰቡ ውስጥ የታዘቡትን በገዛ ራስ ምናባቸው ቀርፀው አቅርበዋል፡፡

በመድበሉ የተካተቱት ድርሰቶች እንደበፊቶቹ ሦስት መድበሎች በውድድር የተገኙ ሲሆን፣ በቀረበው ጥሪ መሠረት 42 ሥራዎች ቀርበው ተወዳድረው አስራ አንዱ ለመመረጥ ችለዋል፡፡

እንደ ተጠሪው አገላለጽ አጫጭር ልብ ወለድ ታሪኮቹ ተወዳድረው የተመረጡት ለፀሐፊዎቹ አስቀድሞ ለጽሑፎቻቸው መነሻ እንዲሆናቸው በተሰጡ ኪነ ጥበባዊ መመዘኛዎች መሠረት ሲሆን፣ በመጨረሻ ታሪኮቹን ገምግመው የመረጡዋቸውም በሥነ ጽሑፍ መስክ ዕውቀቱና ልምዱ ያላቸው ባለሙያዎች ናቸው፡፡

የተሰየመው የዳኞች ቡድን የሥራ ሂደት አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ኘሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በሰጡት መግለጫ ለደራስያቱ ድርሰቶቻቸውን የሚያመጡባቸው ቀጠሮ ተሰጥቷቸው፣ መመዘኛዎቹ የአጭር ልብ ወለድ ኪነ ጥበባዊ ገጽታዎችና ፒ.ኤም.ሲ የሴቶችን ጉዳይ በሚመለከት እንዲያነሱ የፈለገው ማኅበራዊ ጉዳዮች አጠቃላይ በሆነ መንገድ በማቅረብ ዝግጅቱን መጀመራቸውንና ከደራሲዎች ጋር በሥራቸው ዙሪያ ውይይት አድርገው ማሻሻያዎች ማድረጋቸውንና የተሻሉት አሥራ አንድ መመረጣቸውን ገልጸዋል፡፡

በማኅበረሰቡ ውስጥ የወጣት ሴቶችን ሕይወት የተለያዩ አቅጣጫዎች በራሳቸው ፈጠራ መንገድ አቅርበውታል፡፡ ታሪኮቹ የተለያዩ ሆነው ገፀ ባሕርያቱ እንደየፍላጎታቸው በመረጧቸው ጎዳናዎች ሲጓዙ መሰናክላቸውን ለመጣልና ለማለፍ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡

ተባባሪ ኘሮፌሰሩ በምሳሌነት የሚከተለውን ይጠቅሳሉ፡፡ ዕቃ ዕቃ ጨዋታ የአፈር መፍጨት ደስታዋን ሳትጠግብ ስድቡን ብቻ “ከእንግዲህ ቀረ የእናት እንጎቻ” የሚባልላትን ትንሽዬ ሙሽራ እናገኛለን፡፡ ይህች ሙሽራ የእናቷን እንጎቻ ሳትጠግብ እንጀራ ለመጋገር ለብረት መዝጊያ ትሰጣለች፤ የብረት መዝጊያ ብረት ነውና ደቁሶ አጨረማምቶ ይጥላታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ታሪክ በአጭር ልብ ወለዱ ውስጥ እናገኛለን “ሄደች አሉ ጋራ ጋራውን ነፋሻውን” እየተባለ የተዘፈነላትን ልጅ በዚህ ሁኔታ ተሸኝታ ባህሉ በሰጣት ጎዳና ወድቃ ትቀራለች፡፡

ሌላዋ መሰሏ የመማር ፍላጎቷ አይሎ የተጋረጠባትን ኃይል በራሷ ጥረት ጥሳ ስታመልጥ እናገኛታለን፡፡ በሌላ መልክና ታሪክ የወደፊቱን ብሩህ መልክ እያሰበች የገዛ ራሷን እደርስበት አገኛለሁ ይዛ በንፁህ አእምሮ ስትጓዝ ትታያለች፡፡

በሌላ አንፃር ሕይወትን ለማቆየትና ልጆቻቸውን አስተምረው ከዳር ለማድረስ ጥረት የሚያደርጉ ወጣት እናቶች የተሳሉበት እናገኛለን፡፡ በአርታዒው ማስታወሻ እንደተገለጸው ሰዓዳ መሐመድ በ”የሥዕሉ ነፍሶች” መነሻ ያደረገችው ሊናበቡ ያልቻሉ አባትና ልጅ ታሪክን ነው፡፡ ሰመሀርና አባቷ አልተናበቡም፡፡ በለጋ እድሜዋ ሊሆን እማይገባው ድርጊት ፈጽመሻል ብሎ ዓይንሽን አልየው አላት፡፡ እሷም ፊት ከነሳኝ ድራሽባቴ አይገኝም ብላ ጠፋች፡፡ የአባትንም የልጅንም ችግር የተገነዘበው አጐቷ በመሀከላቸው ገብቶ ነገሩን ለማርገብ ጥሯል፡፡ በታሪክ ሰመሀርን ፍለጋ በየጥጋጥጉ ሲናውዝ እናየዋለን፡፡ እግሩ እስቲነቃ በሴተኛ አዳሪዎች መንደር ቢኳትንም የወንድሙን ልጅ አየኋት የምትል ግን አላገኘም፡፡ በፍለጋው ሂደት ይበልጥ ያየውና የተገነዘበው የወጣት ሴቶች የሰብእና መንጠፍ የሚታይበትን ሕይወት ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ጉርብትና ያገኘው ሠዓሊ የሚነግረው ታሪክም ሆነ በዓይኑ ያየው የሕይወት መልክ ያው ነው፡፡ ለሰመሀርና ለመሰሎቿ እንዲያ መሆን ተጠያቂው ማነው? ማነው ጥፋተኛው? የሰመሀር አጐትም፣ የሠዓሊውም የእኛም ጥያቄ ነው፡፡

የወጣትነት ሞቅታ የችኩልነት ባሕሪ ከአቻ ግፊት ጋር በአንድ ላይ ሁኖ አደገኛ አዘቅት ውስጥ የሚያስገባቸውን ገፀ ባሕሪያት የሣሉ ደራሲዎች አሉ፡፡ በፈጠሯቸው ሁነቶች ውስጥ የከሰቷቸው ኪነጥበባዊ ታሪኮች ደራሲዎቹ ያሰቧቸውን ለማሳየት አግዟቸዋል የሚል እምነት አለ፡፡ እንደ አቶ ዘሪሁን አገላለጽ አጭር ልብ ወለዶቹ ውስጥ ለተሳሉት ሴት ገፀ ባሕርያት እንዲያ መሆን ተጠያቂዎቹ እነማን ናቸው? ማኅበረሰቡ፣ አለማወቅ፣ ድህነት ወይስ ደግሞ የግለሰቦች ባሕሪ? ካነበብን በኋላ የምናነሳቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ታሪኮቹ በሐያስያን ዓይን የተለያየ አስተያየት ሊሰጥባቸው ክፍት ቢሆንም በእኛ በኩል ስንመርጣቸው በየደረጃቸው ሞላ ጎደላዊ በሆነ መንገድ የአጭር ልብ ወለድ ባሕርያት ያሟሉ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡

የሴቶች ጉዳይ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈጠራ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ የተነሳው በ1923 ዓ.ም. በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “የልብ ሐሳብ፣ የብርሃኔና የጽዮን ሞገሳ ጋብቻ” ድርሰት ውስጥ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ዘሪሁን፣ አዲሱ መድበል ላይ የምናገኛቸው አንዳንድ ጉዳዮች ከ1923 ጀምሮ ሲነገርላቸው የኖሩ ናቸው፡፡ ችግሮቹ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉና እስከዛሬ ድረስ ያልተወገዱ በመሆናቸው ይተረካሉ፡፡

በታሪክ ወደ ኋላ ስንመለከት የኢትዮጵያ ሴት ደራሲዎች ተሳትፎ ረዥም ጊዜ እንዳስቆጠረና አንዳንዴም ከወንዶች እኩል እየተነሳ ነው፡፡ ይበልጥ ገንኖ የወጣው ግን ባለፉት ዐሥር ዓመታት (በ1990 - 1999) መሆኑን የሥነ ጽሑፍ መምህሩ ያወሳሉ፡፡

በዚህ ዐሥር ዓመት ውስጥ አጭር ልብ ወለድን በማሳተም ረገድ ፖኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር የተጫወተው ሚናና የሰጠው አስተዋጽዖ ሊጠቀስ ይገባል፡፡ በ1990ዎቹ ውስጥ 21 የአጭር ልብ ወለድ መድበሎች መታተማቸውና ሦስቱ የሴንተሩ ውጤት መሆናቸውና ባለፈው ዓመት 21፣ በ198ዐ ዓ.ም. 26 አጭር ልብ ወለድ መድበሎች ብቻ መሆናቸው ስጋት እንደሚያሳይ አጽንዖት ሰጥተውበታል፡፡

በሔኖክ ያሬድ
 
< Prev   Next >