| ኋላ የቀረው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ ማኅበር |
|
|
| Sunday, 24 February 2008 | |
![]() አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ በጎርፍም ሆነ በድርቅ የተመታን አገር ይረዳሉ፡፡ ምላሻቸውም ፈጣን ነው፡፡ ለመተባበርም ጊዜ አይፈጅባቸውም፡፡ በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተከስቶ ለነበረው የረሃብ ቸነፈርም “ዊ አር ዘ ወርልድ” በሚል የተዘጋጀው ኮንሰርት ለአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይረዳሉ ይረዳዳሉ፡፡ ሙያቸውን በመሸጥ ለሚፈለገው አላማ ያውሉታል፡፡ ሙያው በራሱ ሃብት ነውና፡፡ ወደ አገራችን መለሰ ስንል ደግሞ የኪነጥበብ ባለሙያው ተጠናክሮና ተደራጅቶ የሚሰራበት የሰለጠነ ዘዴ የለውም፡፡ አጋጣሚን ተጠቅሞ ካልሆነ በስተቀር ይሄንን ላድርግ ብሎ በተነሳሽነት የራሱን አቅም የሚገነባበት መላ የለውም፡፡ አንድ ነገር መጣ ሲባል እንደ ብረት ምጣድ ይግልና ወዲያው ይበርዳል፡፡ ቀጣይነት ያለው ስራ አይሰራም፡፡ እርስ በርስ የመረዳዳት አቅሙ ደካማ ነው፡፡ የስም እንጂ የሃብት ባለቤት ያልሆኑት አብዛኞቹ አንጋፍ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በችግር መውደቅ፣ ታሞ መታከሚያ ማጣትና አንገታቸውን የሚያስገቡበት ጎጆ አለመኖር በዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ምን ያህል ያልተጠናከረ ግንኙነትና ኋላ የቀረ የመረዳዳት ባህል እንዳላቸው የሚያሳይ ነው፡፡ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉት የኪነጥበብ ባለሙያዎችም የመረዳዳት ባህልን ከሰጠነው አለም የተማሩት አይመስልም፡፡ ሁሉም ለየግሉ ሩጫውን ይሮጣል፡፡ የኢትዮጵያ የኪነጥበብ ሞያተኞች የመረዳጃ ማህበር ከሁለት ዓመት በፊት ሲቋቋም በህመምና በችግር ላይ ያሉ የኪነጥበብ ሙያተኞችን ለማቋቋም ነበር፡፡ በወቅቱ ታመው የነበሩ ባለሙያዎችንም ለመድረስ ሞቅ ባለ ሃይልና ስሜት የኪነጥበብ ባለሞያዎች ተነሳስተው የሙዚቃ ዝግጅት በብሄራዊ ቴአትር አደረጉ፡፡ በዝግጅቱ ተካፋይ የነበረው አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ብዙ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች በችግርና በህመም ላይ በመሆናቸው ተጠናክረው መስራትና መርዳት እንዳለባቸው ሃሳብ አቀረበ፡፡ ተቀባይነት በማግኘቱም ራሱን ጨምሮ አርቲስት መሐሙድ አህመድ፣ አርቲስት ታምራት ሞላ፣ አርቲስት ምኒልክ ወስናቸው፣ አርቲስት አለማየሁ እሸቴ፣ አርቲስት ተሾመ ሲሳይ፣ አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ፣ አርቲስት ፀጋዬ እሸቱና አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ በመሆን ኮሚቴውን መሰረቱ፡፡ የሙዚቃና የቴያትር ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን የስዕል፣ ቅርፃ ቅርፅና... በአጠቃላይ የኪነጥበብ ባለሙያውን ያካተተ ማህበር እንዲሆንም ተወሰነ፡፡ ማህበሩን በፍትህ ሚኒስቴር ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ ተጀመረ፣ ከገቢዎች ሚኒስቴርም ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ የቀረጥ ነፃ ትኬት ፈቃድ ተገኘ፡፡ ሞቅ ባለ ስሜትም ወደ ሃያ የሚጠጉ በችግርና በህመም የነበሩ የኪነጥበብ ባለሞያዎች የእርዳታው ተቋዳሽ ሆኑ፡፡ ሽልማት የተበረከተላቸውም ነበሩ፡፡ በወቅቱ በስሜት የተቋቋመውና ለጥቂቶች ደርሶ የነበረው ማህበር ዛሬ ፋይዳ ቢስ ሆኗል ይላል ተዋናይ የሙዚቃ ክሊፕና የፊልም ዳይሬክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ፡፡ የማህበሩ ኮሚቴ አባላት በግል ስራ መወጠር፣ መታመምና ለስራ ከአገር መውጣት በሞቅታ የተጀመረውን የመረዳዳት ስራ ባንዴ ውሃ አደረገው፡፡ ስራውም እንደታሰበውና እንደታቀደው ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ማህበሩ በሁለት ሰው ስም ባንክ ያስቀመጠውን ገንዘብ እንኳን አውጥቶ ለአርቲስት ደስታ ገብሬ መድረስ አልቻለም፡፡ አንዱ ፈራሚ መሐሙድ አህመድ ከአገር ውጭ በመሆኑ ምክንያት፡፡ ኮሚቴው በፋክስና በስልክ መሐሙድን ለማግኘት ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ እንደሚለው የአርቲስት ደስታ ገብሬ መታመም ኮሚቴው ራሱን ዞር ብሎ እንዲፈትሽና ወደኋላ የቀረበትን ስህተት አርሞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክንያት ይሆናል፡፡ ይህ እድል ካመለጠና ማህበሩም አሁን ተፍረክርኮ እንዳለው ከቀጠለ ጥቅም አይኖረውም፡፡ “ድጋሚ መንቀሳቀሱ ለተፈጠሩትና ወደፊት ለሚፈጠሩት ችግሮች መፍትሄ ይሰጣል፡፡ እዚህ ካለው ኮሚቴ ጋርም ለመወያየት አስበናል” ብሏል፡፡ አርቲስቱ ላይ ችግር በደረሰ ቁጥር እርዳታ መጠየቅ የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ህብረተሰቡ ለአርቲስቱ ያለውን አመለካከት ይቀይራል፡፡ አርቲስት እከሌ/ እከሊት ይህን ሰራች እየተባለ በየሚዲያው ሲሰማ ቆይቶ ታሟልና/ ታማለችና እርዷት ሲባልም የሰሩበትን ገንዘብ የት አደረጉት የሚል ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም፡፡ አብዛኞቹ አንጋፋ አርቲስቶች ኑሯቸው ከጅ ወደ አፍ ነው፡፡ አቅም የላቸውም የሁልጊዜ ምክንያት ነው፡፡ ችግር ደረሰባቸው ሲባል አርቲስቱ ከሚረባረብ ችግር ውስጥ ሳይገቡ ህይወታቸውን ሊያስተካክሉ የሚችሉበትን መንገድ ማበጀት ይችላል፡፡ ሙያው ለዚህ የተመቸ ነው፡፡ ሆኖም ይህ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ የኪስን ገንዘብ አውጥቶ ለሌላ የመስጠትንና የመረዳዳትን ባህልም ይጠይቃል፡፡ “አንዴ ሆይ ካሉን ቶሎ የሚበስል ነገር እንሆንና ወዲያው እንቀዘቅዛለን፡፡ ኮሚቴው ሲመሰረት የሚወድቅ አልመሰለንም፡፡ በተለይ አንጋፋ አርቲስቶችን ይዘን እንወድቃለን ብለን አላሰብንም ነበር፡፡ ለመስራትም ተነሳሽነቱ ነበር፡፡ ወጣቱ አርቲስትም ፍላጎቱን ገልጾ ነበር፡፡ እንነሳና እንበርዳለን” ነው ያለው አርቲስት ቴዎድሮስ የማህበሩን መንገድ ላይ መቅረት ሲገልጽ፡፡ ማህበሩ ከተቋቋመና እየቀዘቀዘ ባለበት ወቅትም የታመመ አርቲስት አለመኖሩ ወይም ፈታኝ ነገር አለመግጠሙ ጭራሽ ማህበሩ እንዲዘነጋ አድርጓል፡፡ “የሚፈትን ነገር አሁን መጥቷል፡፡ የአርቲስት ደስታ ገብሬ መታመም፡፡ አሁን ዝም ካልን መጥፎ ነው፡፡ መስራት አለብን አለዚያ የኮሚቴውን ሥራ ለሌሎች ማስረከብ አለብን” ብሏል አርቲስት ቴዎድሮስ፡፡ የማህበሩ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተሾመ ሲሳይ እንዳሉት ማህበሩ ወደኋላ ሊቀር የቻለው የኮሚቴው አባላት አርቲስቶች ለረዥም ጊዜ በውጭ በመቆየታቸውና ሊሰባሰቡ ባለመቻላቸው ነው፡፡ የተጠናከረ ቡድን በችግር ሰዓት ብቻ ሳይሆን ችግር ሳይደርስ ሊከላከል የሚችል ሃይል ይኖረዋል፡፡ አርቲስቱ ግን ይህንን ሃይል መመስረት አቅቶታል፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ “እንደ አሁኑ አይነት የድረሱልኝ ጥሪ ይብቃ ተጠናክረን እንስራ” ብሏል፡፡ የኪነጥበብ ሰዎች በኢትዮጵያ የስም ብቻ ሳይሆን የገንዘብም መሆን አለባቸው፡፡ ቢታመሙ በሙያቸው እንዲታከሙ፣ ቢቸገሩ ሙያቸው እንዲደርስላቸው የሚለው አመለካከት በህብረተሰቡ ዘንድ መፈጠር አለበት፡፡ ሁልጊዜ ተረጂ መሆን የአመለካከት ለውጥ አያመጣም፡፡ “የሃብት ድሆች ነን የሙያ ድሆች አይደለንም” የሚለው አርቲስት ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ሕብረት ነውና በህብረት ማደግ የግድ በመሆኑ እንሰባሰብ ብሏል፡፡ በአንጋፋዎቹና በወጣት አርቲስቶች ከሁለት አመት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ የኪነጥበብ ሞያተኞች የመረጃ ማህበር ሊሰፋና ሊጠናከር የሚችልበት አጋጣሚ አሁንም አለ፡፡ አርቲስቱ ፍላጎቱና የመረዳዳት ባህሉ ካለው፡፡ ማህበሩ ሁሉንም የኪነጥበብ ሞያተኞች ያቀፈ ሊሆን ይችላል፡፡ ማድረግም ይቻላል፡፡ ሲቋቋምም አላማው ይህ ነበር፡፡ እስካሁን ባይሳካም፡፡ ማህበሩን በተወሰነ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ብቻ እንዲያንቀሳቅሱት ማድረግም የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ስሙ “የኪነጥበብ ባለሙያዎች” እስከሆነ ድረስ በሁሉም የኪነጥበብ ዘርፍ ያሉ ሙያተኞችን ሊያቅፍ ይችላል፡፡ ይህ መሆኑ በእያንዳንዱ ሙያ ዘርፍ ያሉ እንደ የሙዚቃ ሰዎች ማህበር፣ የተውኔት ሞያተኞች፣ ማህበርና ሌሎችም በአንድ ጥላ ሥር ተሰባስበው ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ የአርቲስቱ በህብረት ተቀናጅቶ መስራት ለራሱ ለአርቲስቱ ብቻ ሳይሆን በድህነትና በችግር ለወደቁ ኢትዮጵያውያን ወገኖችም ለመድረስ ያስችላል፡፡ የሙያው ባህሪም ለሰው ማሰብን፣ መርዳትን ማስተማርን ይጠይቃልና፡፡ የስም ብቻ ሳይሆን የገንዘብም ባለቤት ለመሆን እንዲሁም ከራስ ተርፎ ህብረተብን ለመርዳት በሁሉም ዘርፍ የተሰማሩ የኪነጥበብ ሞያተኞች የኢትዮጵያ የኪነጥበብ ሞያተኞች የመረዳጃ ማህበርን እንዲቀላቀሉና በተጠናከረ መልኩ ከወደቀበት እንዲያነሱ አርቲስት ቴዎድሮስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ በምሕረት ሞገስ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |