Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የኢትዮጵያ ወጣቶች አደገኛ የወሲብ…
የኢትዮጵያ ወጣቶች አደገኛ የወሲብ… Print E-mail
Sunday, 06 January 2008

የኢትዮጵያ ወጣቶች አደገኛ የወሲብ አዝማሚያ ያሳያሉ

ውሀቤ ማሪያ የተባሉ የአፍሪካ ጆርናል የሥነ ተዋልዶ አጥኚ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ወጣቶች ጋር ሲነፃፀሩ ከተቃራኒ ፆታ ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት የመፈፀሙ አጋጣሚያቸው ዝቅተኛ ቢሆንም በዚህ ረገድ የሚያሳዩት ባህሪይ (ሴክሽዋል ቢሄቪየር) ግን አደገኛ መሆኑን ባደረጉት ጥናት ይፋ አድርገዋል፡፡

ጥናቱ ከአስራ አምስት እስከ ሀያ አራት ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ያካተተ ሲሆን ማኅበራዊና የሥነ ሕዝብ ሁኔታዎች በስነተዋልዶ ባህሪያት ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ለመዳሰስና ወጣቶች ስለ ኤች.አይ.ቪና በግብረ ስጋ ግንኙነት ስለሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎች ያላቸውን ግንዛቤ ለመጠቆም የተካሄደ ነው፡፡

በ2007 ይፋ የሆነው የውሀቤ ማሪያ ጥናት በኢትዮጵያ ግንኙነት ከጀመሩ ሴቶችም ሆነ ወንዶች ብዙዎቹ የቤተሰብ ምጣኔ ምክር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳልሆኑ፣ ስለ ኤች.አይ.ቪ ጥሩ ሊባል የሚችል ግንዛቤ ቢኖራቸውም በግብረ ስጋ ግንኙነት ስለሚተላለፉ በሽታዎች ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ እንደሆነ ያሳያል፡፡

በኤች.አይ.ቪና በሌሎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች መስፋፋትና ባልተፈለገ እርግዝና መጨመር ምክንያት የወጣቶች የስነ ተዋልዶና የተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ዓለም አቀፍና አገራዊ ትኩረትን እያገኘ ሲሆን እነዚህ ችግሮች ከስነ ሕዝብና ከማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር ያላቸው ቁርኝት ከፍተኛ እንደሆነ ግልፅ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከዓለም ሕዝብ ሰላሳ በመቶ የሚሆነው ከአስር እስከ ሀያ አራት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል ሲሆን ይህ ቁጥር በተለይም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ነው፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የተቀመጠው ደግሞ የወጣቶች በለጋ ዕድሜያቸው የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመር ሲሆን ይህ በወጣቶቹ የወደፊት የሕይወት እጣ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡

ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ትምህርት ቤቶችን መሠረት በማድረግ የተካሄዱ ተደጋጋሚ ጥናቶችን በመጥቀስ በእነዚህ አገራት ከግብረ ስጋ ግንኙነት ጋር በተያያዘ የወጣቶች እንቅስቃሴ ከፍተኛ እንደሆነ፣ የተለያዩ የእርግዝና መከላከያዎችን ኮንዶምን ጭምር በተከታታይ የመጠቀም ሁኔታ አነስተኛ መሆኑንና ከሁለት በላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር ግንኙነት የማድረግ ሁኔታ መኖሩን ወሀቤ አመልክተዋል፡፡ በኢትዮጵያም የተደረገው ጥናት ከሰሀራ በታች እንዳሉ አገራት በትምህርት ቤቶች የተወሰነ ሲሆን ግኝቱም ከሌሎቹ የተለየ አለመሆኑን ጥናቱ አሳይቷል፡፡

ጥናቱ ከአስራ አምስት እስከ ሀያ አራት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ያማከለ ሲሆን እድሜ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የመኖሪያ አካባቢ፣ ሀይማኖት፣ የቅጥር ሁኔታና መገናኛ ብዙሃን የመከታተል ዕድል ጥናቱ ትኩረት ያደረገባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጐን ለጐን የተቃራኒ ፆታ ግንኙነቶች፣ የወሲብ ጓደኞች ብዛትና ኮንዶም የመጠቀም ሁኔታ ላይ ጥናቱ ትኩረት ሰጥቷል፡፡

ስምንት መቶ ዘጠና ወንዶችና ሦስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ስምንት ወጣቶች በጥናቱ ተካተዋል፡፡ የአብዛኞቹ እድሜ ከሀያ በታች ሲሆን ከከተማ ውጭ የሚኖሩ ናቸው፡፡ በጥናቱ ከተካተቱት ወጣቶች አብዛኞቹ ሴቶች ከወንዶቹ ጋር ሲነፃፀር አልተማሩም፡፡ ስልሳ አንድ በመቶ የሚሆኑት ወንዶች መገናኛ ብዙሃን የመከታተልና የመጠቀም ዕድል ያላቸው ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ ደግሞ የተለያዩ መፅሔቶችንና ቴሌቪዥን የመመልከት እድል አላቸው፡፡ በተቃራኒው ሴቶቹ መገናኛ ብዙሀን፣ ለመፅሔትም ሆነ ለቴሌቪዥን ያላቸው ዕድል አነስተኛ እንደሆነ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

ሴት ወጣቶች ገና በአፍላ እድሜያቸው (15 ዓመት) ለወሲብ እንደሚነሳሱ የሚያብራራው ይህ ጥናት ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ለመጀመሪያ ጊዜ ለወሲብ ከተነሳሱ በኋላ ሁለትና ከዚያ በላይ የወሲብ ጓደኛ ሊኖራቸው እንደሚችል ይጠቁማል፡፡ ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ ከሴቶች የተሻለ ስለቤተሰብ ምጣኔ አማራጮች ወንዶቹ የተሻለ ግንዛቤ አላቸው፡፡ አብዛኞቹ ወጣቶች ስለ ኤች.አይ.ቪ በቂ ግንዛቤ እንዳላቸው በመግለፅ በመታመን፣ በመቆጠብና ኮንዶም በመጠቀም ኤች.አይ.ቪን መከላከል እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ ከእነዚህ ውጭ ስላሉ የመከላከያ መንገዶች ወጣቶቹ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ ሲሆን ስለት ነገሮችን ማስወገድ፣ ብዛት ያላቸው የወሲብ ጓደኞች ካላቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት አለመፈፀምና ሴተኛ አዳሪዎች ጋር አለመሄድ እንደቀዳሚ የመከላከያ ስትራቴጂ በተለያዩ ወጣቶች ተጠቅሰዋል፡፡

ወጣቶቹ ስለ ኤች.አይ.ቪ ካላቸው ግንዛቤ ጋር ሲነፃፀር በግብረ ስጋ ግንኙነት ስለሚተላለፉ በሽታዎች ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ ከመሆኑ ባሻገር ሴቶቹ በእነዚህ በሽታዎች ምክንያት ሴቶችም ወንዶችም ላይ ሊታዩ ስለሚችሉ ምልክቶች የተሻለ ግንዛቤ ሲኖራቸው በወንዶች ላይ ብቻ ስለሚታዩት ምልክቶች መጠነኛ ግንዛቤ አላቸው፡፡

በከተማ የሚኖሩና ሥራ ያላቸው ወጣቶች ግንኙነት የመፈፀም እድላቸው ከፍተኛ ሲሆን የእድሜ መጨመር፣ የሥራ ሁኔታ፣ ሀይማኖት፣ የትምህርት ደረጃና ግንኙነት መፈፀም በሴቶች ከፍተኛ ትስስር እንዳላቸው ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ሥራ ያላቸው ወጣት ሴቶች ሥራ ከሌላቸው ይልቅ ግንኙነት የመፈፀም አዝማሚያ ይታይባቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የትምርት ደረጃ ግማሽ በመቶ ያህል ብቻ ወጣት ሴቶች ወደ ግንኙነት እንዳያመሩ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡

ኢትዮጵያ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ያሏት አገር በመሆኗ የተለያዩ አካባቢዎች ባህል የስነ ተዋልዶ ባህሪያት ላይ የራሳቸው የሆነ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ወሀቤ በጥናታቸው ገልፀዋል፡፡ በግብረ ስጋ ግንኙነት ስለሚተላለፉ በሽታዎች ለሕዝብ ማስተማር ብዙም ተቀባይነት እንደሌለው የሚያስረዳው የወሀቤ ጥናት ለሕብረተሰብ በአደባባይ የሚሰጡት የስነ ተዋልዶ ትምህርቶች ኤች.አይ.ቪን ብቻ ትኩረት ያደረጉ እንደሆኑ ያስረዳል፡፡ በተቃራኒው በሌሎች የአፍሪካ አገራት ላይ ተካሄዱ ጥናቶች በእነዚህ አገራት ያሉ ወጣቶች በዚህ ረገድ ያላቸው ግንዛቤ የተሻለ እንደሆነ ጥናቱ አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሁለትና ከዚያም በላይ የወሲብ ጓደኞች በመያዝ፣ በተወሰነ ደረጃ ኮንዶም ባለመጠቀም፣ ዘላቂና ወጥ የወሲብ መከላከያ ባለመጠቀም ከፍተኛ አደጋ ያለው የስነ ተዋልዶ ባህሪያት እንደሚያሳዩ የጥናቱ መደምደሚያ ያሳያል፡፡ ስለ ኤች.አይ.ቪም ያለው ግንዛቤ ጥልቅ እንዳልሆነና ማኅበራዊና የስነ ሕዝብ ሁኔታ በወጣቶች የስነ ተዋልዶ ባህሪያት ላይ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ የጥናቱ ግኝት አመልክቷል፡፡ አጠቃላይ የጥናቱ ግኝት በአገሪቱ ያለውን የወጣቶች የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ደረጃ ያሳያል፡፡   

በጋዜጣው ሪፖርተር

 

 
< Prev