| በተመጣጣኝ የሚሸጡ ነጋዴዎች ቢበራከቱ |
|
|
| Sunday, 24 February 2008 | |
|
ሰሞኑን በተለያዩ ጉዳዮች፣ ሰዎች ሰብሰብ ባሉባቸው አካባቢዎች ባደረግሁት ቆይታ አንድ ተመሳሳይ የሆነ የመወያያ ርዕስ ወይም መሪ ጨዋታ ሆኖ የታዘብኩት ጉዳይ የኑሮ ውድነት ነበር፡፡
ኑሮ ስለመወደዱ ብዙም ቁብ አይሰጣቸውም የሚባሉ ሰዎች ሳይቀሩ እንደ አብዛኞቻችን ምሬት ሲያሰሙም ሰምቻለሁ፡፡ እያሻቀበ የመጣው ኑሮ ውድነት "መፍትሄው ምን ይሆን?" በማለት ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎች ተበራክተዋል፡፡ በተደጋጋሚ በዚህ አምድ ላይ ሲገለጽ እንደታየው የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት መጥቷል፡፡ በቀናት ልዩነት የሚታየው የሸቀጦችና የተለያዩ ምርቶች ዋጋ ማሻቀብ ሸማቹን አማሯል፡፡ መንግሥት ይህንን እጅግ አሳሳቢ የሆነ ችግር እንዴት ሊፈታው እንደሚችል ግራ እያጋባን ቢሆንም ከመንግስት ውጭ ያሉ ኃላፊነት ያለባቸው ወይም ሊሰማቸው የሚችሉ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላትም ይህንን ችግር ለማርገብ የሚጫወቱት ሚና ቀላል እንደማይሆን መጠቆሙ ተገቢ መሆኑን ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ ይህንን ሃሳብ ለመሰንዘር የፈለግሁት የአንዳንድ ምርቶች ዋጋ ጭማሪ ፈጽሞ ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመታዘቤ ነው፡፡ ነዳጅ ጨመረ በሚል እሳቤ ብቻ የተጋነኑ ጭማሪዎች የታየባቸውና ሸማቹን ምሬት ውስጥ የከተቱ በርካታ ምርቶች አሉ፡፡ በእኔ እሳቤ አቅም አላቸው የሚባሉ ኢንቨስተሮች ኅብረተሰቡ አነስተኛ በሆነ ዋጋ ሊገለገልባቸው የሚችሉ ትልልቅ የገበያ ማዕከላትንና ሱፐር ማርኬቶችን በመክፈት አገልግሎት መስጠት ቢችሉ በሰበብ በአስባቡ ሸማቹን ከሚያማርሩና ኃላፊነት ከማይሰማቸው ነጋዴዎች እንዲገላገል ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እንዲህ አይነቱ ተግባር ሰበብ እየፈለጉ በየእለቱ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችም ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲገቡ በማድረጉ ረገድም የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ይህንን እንድል ያነሳሳኝ በቅርቡ መስቀል አደባባይ አካባቢ በሚገኝ አንድ ሱፐር ማርኬት ገብቼ ያጋጠመኝ አንድ ድርጊት ነው፡፡ በወቅቱ ወደ ሱፐር ማርኬቱ የገባሁት የፈለግሁትን እቃ ለመግዛት ነበር፡፡ ነገር ግን በሱፐር ማርኬቱ ውስጥ "ሉና ስጋ" የሚል የተፃፈበት ሥጋ አየሁና ዋጋውን ጠየቅሁ፡፡ ሉና የሚባለው ኩባንያ በራሱ ቄራ የሚያርደውን ስጋ ወደ ውጭ መላኩን እንጂ ለአገር ውስጥ ገበያ እንደሚያቀርብ ባለማወቄ ጉዳዩን ለመረዳት የበለጠ ጓጉቼ ነበር፡፡ ለማንኛውም የአንድ ኪሎ ሥጋ ዋጋ 30 ብር መሆኑን ተገነዘብኩና ገዛሁ፡፡ በሌሎች ልኳንዳ ቤቶች አንድ ኪሎ ስጋ እስከ 60 ብር እየተሸጠ መሆኑን ስለማውቅ ነገሩ ገረመኝ፡፡ በዚህ ወቅት በመሃል ከተማ በሚገኝ አንድ ትልቅ ሱፐር ማርኬት አንድ ኪሎ ስጋ በ30 ብር መግዛት ትንሽ ሊያስገርም ይችላል፡፡ የሥጋው ጥራት ጥሩ መሆኑንም አረጋገጥኩ፡፡ ይበልጥ የገረመኝ ደግሞ አንድ ኪሎ ተብሎ የተሸጠልኝ ሥጋ በእርግጥም አንድ ኪሎ ብቻ ነው ወይ? የሚያስብል ነው፡፡ ለምን ቢባል ከልኳንዳ ቤቶች የምገዛው ስጋና ይሄ በመጠን ስላልተገናኙ ነው፡፡ ከሳምንታት ቆይታ በኋላም ተመልሼ ግማሽ ኪሎ ገዛሁ፡፡ አሁንም መጠኑ ብዙ ነው፡፡ አንድ ነገር ለማረጋገጥ ፈለግሁና የምኖርበት አካባቢ ከሚገኝ አንድ ልኳንዳ ቤት ገባሁና ግማሽ ኪሎ ሥጋ ገዛሁ፡፡ የሁለቱን መጠን ሲነፃፀር በጣም ልዩነት አለው፡፡ ከሱፐር ማርኬቱ የገዛሁት ስጋ ምንም አጥንት ያልነበረው ሲሆን ከልኳንዳ ቤቱ የገዛሁት ግን አጥንት ያለው (ሥጋ አጥንት ካልተጨመረበት ብቻውን ስለማይሸጥ ተመዝኖ) የተሰጠኝን ነው ይዤ የገባሁት፡፡ በሚገርም ሁኔታ በልኳንዳ ቤቱና ከሱፐርማርኬቱ በገዛሁት ግማሽ ኪሎ የሥጋ መጠን ላይ ልዩነት እንዳለውም ተገነዘብኩ፡፡ የሱፐር ማርኬቱ ሥጋ በትንሹ የ100 ግራም ብልጫ እንዳለው ታዘብኩ፡፡ ይህ ገጠመኝ ለእኔ ትልቅ ትርጉም ሰጥቶኛል፡፡ እንዲህ አይነት ኩባንያዎች አገልግሎታቸውን በየቦታው በማድረግ ሸማቾች አቅራቢያቸው ካለ ቦታ በተመጣጠነ ዋጋ ግብይት ቢያደርጉ ምን ያህል እንደሚታደጉ ያሳየናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ አይነት እቃ በዚህን ያህል የዋጋ ልዩነት መሸጡ የከተማችን ልኳንዳ ቤቶች ፣እኛ የምናርደው ከብት ከውጭ የምናስመጣው ነው፣ ካላሉ በስተቀር ዋጋ እየቆለሉ ያሉት ያለ አግባብ እንደሆነም ያሳየናል፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ የሚዛን ነው፡፡ የሱፐር ማርኬቱ ሥጋ ጉዳይ የእነርሱ ሚዛን ትክክለኛ አለመሆኑን የሚያሳየን ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ይህ የሚያሳየው ልኳንዳ ቤቶቹ በትክክል በሚሰራ ሚዛን እየሸጡ አለመሆኑንና ሸማቹ ሆን ተብሎ ትክክለኛ ባልሆነ ሚዛን አገልግሎት እየተሰጠው አለመሆኑን ነወ፡፡ ይህ ችግር በልኳንዳ ቤቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ተመዝነው በሚሸጡ ምርቶች ላይ የሚታይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሥጋ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የሚቻል መሆኑንና አማካይ በሆኑ ቦታዎች ትላልቅ ሱፐር ማርኬቶችን በመክፈት አገልግሎት መስጠት የሚቻል እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡ በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉ ምርቶችን በተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ሊሸጡ የሚችሉ ትላልቅ ሱፐር ማርኬቶች ቢከፈቱ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት በመታደጉ ረገድ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖዋል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችም ቢሆኑ ነጋዴዎች በሚቆልሉት ሰፊ የሆነ የትርፍ ስፋት በመቀነስ በእነዚህ ሱፐር ማርኬቶች ለመገንባት ጊዜ ቢፈጅ እንኳን ለጊዜውም ቢሆን አሁን ባሉት በመጠቀም ልምድ መዳበር የሚችል እንደሆነም መጠቆሙ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በናታን ዳዊት |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |