Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow "በኢትዮጵያ ደረጃ በአሁኑ ወቅት...
"በኢትዮጵያ ደረጃ በአሁኑ ወቅት... Print E-mail
Sunday, 24 February 2008
Image"በኢትዮጵያ ደረጃ በአሁኑ ወቅት በማዕድኑ ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ያለው አቅም ውሱን ነው"
አቶ ገብረእግዚአብሔር መኮንን፣
በማዕድንና ኤነርጂ ሚኒስቴር የማዕድን ሥራዎች መምሪያ ኃላፊ

አቶ ገብረእግዚአብሔር መኮንን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጂዎሎጂ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኔዘርላንድ በኢኮኖሚክ ጂዎሎጂ አጠናቅቀዋል፡፡ በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር የማዕድን ሥራዎች መምሪያ ኃላፊ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በማዕድናት ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ብርሃነ ዓለሙ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አገሪቱ በማዕድን ዘርፍ ምን ያህል ተጉዛለች?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡
- በማዕድኑ ዘርፍ ቀደም ሲል ከነበሩት የማዕድን ልማት እንቅስቃሴዎች በተሻለ ሁኔታ እየተሠራ ነው፡፡ በግሉ ሴክተርም ያለው የማዕድን ልማት ከቀድሞው ሲነፃፀር በጣም በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ባለሃብቶች በማዕድኑ ዘርፍ ገብተው እንዲያለሙ አዲስ የማዕድን እቅድ ከወጣ ከ1985 ዓ.ም ወዲህ የግል ባለሃብቶች በማዕድን ልማት ዘርፍ መሳተፍ ጀምረዋል፡፡ እኛም በግሉ ዘርፍ ላሉ ባለሃብቶች ፈቃድ በመስጠትና በማስተዳደር ረገድ ያለን ልምድ የመጀመሪያ ስለነበረ በአንዳንድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የፍቃድ ጥያቄዎችን የማስተናገድ ችግሮች ለተወሰኑ ዓመታት የታየበት ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚያ የታዩትን ችግሮች በማስወገድና በተቻለ መጠን የባለሙያዎችና የአገልግሎት አሰጣጡ በመሟላቱና በመሻሻሉ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግል ሴክተሩ በማዕድን ልማት ላይ የተሳተፉ ባለሃብቶች ቁጥራቸው በርካታ እየሆነ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ፈቃዶችን ሰጥታችኋል?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
በፌዴራል ማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአምሳ አምስት ኩባንያዎች በላይ ፈቃድ ወስደው ከአንድ መቶ በላይ የፈቃድ ዓይነቶች ተሰጥተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት (በተለይ ከሦስት ዓመታት ወዲህ) የማዕድን ሥራ ፈቃድ በመውሰድ ላይ ያሉት በርካታ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በማዕድን ላይ የተሰማሩት መበራከት ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
አንደኛ በዓለም ገበያ በአሁኑ ጊዜ የማዕድናት የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ከፍ እያለ ሄዷል፡፡ ሁለተኛ በዚህ ዘርፍ ያለው የግል ባለሐብት ተሳትፎ እንዲጨምር መንግሥትም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራ ነው፡ ብዘ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች እየሠሩ ነው፡፡ የልማት ሥራ ከሚካሄድባቸው ማዕድናት መካከል በዋናነት ወርቅና ቤዝ ሜታል የሚባሉት እንደ ኮፐር ሊድ ዚንክ የሚባሉ ማዕድናት የምርመራ ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው፡፡ ከምርመራ ሥራዎቹም በጣም በጥልቀት ብዙ እየተሠራ የክምችት መጠኑ ሊታወቀ ወደሚችልበት ሁኔታ እየደረሱ ያሉ የፈቃድ ቦታዎች አሉ፡፡ አንዱ በቅርብ የለገደንቢ ወርቅ የሚያመርተው ሜድሮክ ኩባንያ ፈቃድ ተሰጥቶት የምርመራ ቦታና የክምችት መጠኑን አውቆ ወደ ልማት ሥራ የሚሄደው የጽንሰ ወርቅ ማዕድን ክምችት ቦታ ነው ያለው፡፡ ሌሎችም የወርቅ ክምችቶች በሌላ ቦታ እንደሚገኙ የጥናት ውጤቶች እያመላከቱ ነው፡፡ በምዕራብና በሰሜን ኢትዮጵያ በርካታ ኩባንያዎች የምርመራ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡

ከብረት ነክ ማዕድናት በተጨማሪ በኢንዱስትሪ ማዕድናት ላይ የምርመራ እንዲሁም የማምረት ፈቃድ በቅርብ ጊዜ የተለያዩ ኩባንያዎች እየወሰዱ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ለሲሚንቶ ጥሬ ዕቃነት የሚያስፈልጉ የማዕድናት ፍለጋና የማምረት ሥራ እያካሄዱ ነው ያሉት፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ ሌሎች፣ የማዕድን ውኃ፣ የጌጣጌጥ ማዕድናት ፈቃድ ወስደው እየሠሩ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢንዱስትሪውን የሚያውቁ ወደ አገራችን ገብተው እየሠሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በማዕድኑ ዘርፍ ለመሠማራት?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
በማዕድኑ ዘርፍ የልማት ሥራ ለማካሄድ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ካፒታል ያስፈልጋል፡፡ ያ የኢንቨስትመንት ካፒታል ደግሞ ነገ የተወሰነ የመነሻ ሥራ ተሠርቶ ትርፍ የሚገኝበት ላይሆን ይችላል፡፡ ገንዘብን የማጣት ሥጋትን ሊያመጣ የሚችል ልማት ነው፡፡ እንደ ሌላው ሴክተር ኢንቨስትመንት በወጣ ቁጥር፣ ካፒታል በወጣ ቁጥር ትርፍ ይገኝበታል ተብሎ የሚታሰብበት አይደለም፡፡ በአብዛኛው የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ለምርመራ ብለው የሚያፈሱት ገንዘብ አለ፡፡ ያንን ገንዘብ ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉት የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ በአሁኑ ወቅት በዚህ ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ያለው አቅም ውሱን ነው፡፡ የተወሰኑ ጥያቄዎች ይኖራሉ፤ በርካታ ግን አይደሉም፡፡ የውጭ ባለሐብቶች ወደዚህ ሥራ ገብተው እንዲሠማሩና ልማቱን እንዲያለሙ ነው የሚፈለገው፡፡ አንድ ባለሃብት የልማት ሥራውን ሠርቶ ወደ ምርት ለመሸጋገር ክምችት ካገኘ ግን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ የሆነ፣ ለባለሃብቱም ካወጣው ወጪ በበርካታ እጥፍ ሊያስመልስበት የሚችል ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ያንን ቢዝነሱን ወይም የኢንዱስትሪውን ባህርይ የሚያውቁ ኩባንያዎች ናቸው እየሠሩ ያሉት፡፡ በአገራችን በሰፊ ቦታ ላይ ተጨማሪ የማዕድን ልማት ለሚሠሩ የምርመራ፣ የፍለጋም ይሁን የማምረት ሥራ ፈቃድ ወስደው መቀጠል ለሚፈለጉ ሁሉ አሁንም በቂ ቦታዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በዘርፉ የአገር ውስጥ ባለሐብቶች ቁጥር ምን ያህል ደርሷል?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
የአገር ውስጥ ባለሐብቶች ውስን ናቸው፡፡ ትልቁ ነገር የኢንቨስትመንት ካፒታሉ ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአገር ውስጥ ባለሐብቶች የተሠማሩበት ዘርፍ ከፋፍለው ሊነግሩኝ ይችላሉ?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
ማዕድን ለማምረት ከሃያና ከሰላሳ ማሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያውያን በማዕድን ውኃ ማምረት ሥራ ውስጥ እየተሳተፉ ነው፡፡ ደብረብርሃን የተፈጥሮ ማዕድን ውኃ የሚባለውን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል፡፡ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች በማዕድን ውኃ ማምረት ሥራ ላይ ተሠማርተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

በሌሎችም በወርቅና በቤዝ ሜታል ምርመራ ሥራ ላይም ቢሆን በመነሻነት ይሠሩና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የአቅም እጥረት ሲፈጠርባቸው የውጭ ባለሃብቶች (እንደ ፓርትነር ሆነው) ከእነርሱ ጋር እንዲሠሩ የማፈላለግ ሥራም ስለሚሠሩ በመነሻው ሕጋዊ ጉዳዮችን አስፋፍተው በሌላውም ማዕድን ላይ የተወሰነ ኢንቨስት እያደረጉ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያንም አሉ፡፡ እነሱን የበለጠ እያበረታታናቸው ነው፡፡ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ዜጎችን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግበትን ዕድል እንዲፈጠር ተገቢውን ማበረታቻ፣ ድጋፍና የቅድሚያ መብት እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- በባሕላዊ መንገድ የሚመረቱትን ማዕድናት በዘመናዊ መልኩ ለማድረግ መምሪያችሁ ምን አደረገ? ለምሳሌ በባሕላዊ መንገድ የሚመረት ወርቅ ብክነት እንዳለበት መገመት ይቻላል፤ ሜድሮክና የመሳሰሉት የተወሰኑ ኩባንያዎች በዘመናዊ መልኩ የሚያመርቱ ይመስለኛል፤

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
ሜድሮክ በዘመናዊ የማምረቻ መሣሪያ በከፍተኛ ደረጃ የሚመረተውን (ላርጅ ስኬል ማይኒንግ ኦፐሬሽን) የሚሠራው፡፡ በጽንሰ ወርቅ ደረጃ የሚገኝ ወርቅ ነው የሚያመርተው፡፡ በባሕላዊ መንገድ የሚመረተው በደለል ወርቅ ደረጃ የሚገኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባህላዊ አመራረቱ ሜድሮክ ከመጣ በኋላ አልተቀየረም?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
ሜድሮክ ከመምጣቱና ካለመምጣቱ ጋር ሳይሆን ሜድሮክ በራሱ እንደማንኛውም አንድ ባለፈቃድ እየሠራ ነው፡፡ ሥራውን በአግባቡ ይሠራል፡፡ ባሕላዊ አምራቾችን ሕጋዊ ማድረግ፣ ማደራጀት፣ ለምርታቸው የተመቻቸ የግብይት ሥርዓት እንዲኖረው ማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለረዥም ዓመታት ጥናት አድርጎ የአካባቢው ነዋሪዎች በተሻለ ሁኔታ መጠቀም እንዲችሉ፣ የሚያመርቱትን ደግሞ ለአገር ጥቅም እንዲውል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከሌሎች የማዕድን ኩባንያ ሥራ እንቅስቃሴ ጋር አይያያዝም፡፡

የሚመረተው ግን በባህላዊ መንገድ ነው፡፡ በአነስተኛ የማምረቻ መሣሪያዎች በዶማ፣ በዲጂኖ፣ በአካፋና በመሳሰሉት የሚመረት ነው፡፡ ቀደም ሲል የተመቻቸ ገበያ አልነበረም፡፡ አሁን ግን የተመቻቸ የገበያ ሥርዓት ኖሮ ያመረቱትን ወርቅ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንደ መብታቸው አጓጉዘው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዓለም ገበያ ዋጋ እንዲሸጡ ወይም ደግሞ በዓለም ገበያ ዋጋ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ውጭም ኤክስፖርት እንዲያደርጉ የሚፈቅድ የወርቅ ግብይትን በተመለተ በኢትዮጵያ ብሐራዊ ባንክ መመሪያ ወጥቷል፡፡ በዚያ መሠረት ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ እየታየ ያለው ውጤት ቀደም ካሉት ከአራትና ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር አሁን ያለው በጣም የሚያበረታታ ነው፡፡ ከአንድ ቶን፣ ከሁለት ቶን በላይ ወርቅ በየዓመቱ ለማዕከላዊ ገበያ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እየቀረበ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የማዕድን ክምችት በአገሪቱ የትኛው ክፍል ነው በብዛት የሚገኘው? በምሥራቅ፣ በምዕራብ በሰሜን ወይስ በደቡብ ኢትዮጵያ?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
በማዕድን ደንብ መሠረት ኢትዮጵያውያን ዜጎች ወይም ኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች ከክልል የማዕድን ቢሮዎች ፈቃድ ይወስዳሉ፡፡ እኔ አሁን እየገለጽኩት ያለው በፌዴራል ማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለውጪ ኩባንያዎች ወይም ኢትዮጵያውያን ከውጭ ኩባንያዎች በጋራ የሚሠሩትን ነው፡፡ በሕጉ መሠረት ለፌዴራል መሥሪያ ቤቱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይሠራል፡፡ ብዙ ኢኮኖማያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ብዙ ማዕድናት በአገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች አሉ፡፡ የእነዚህ ማዕድናት ሥራ በኢትዮጵያም በውጭ ኩባንያዎችም ይካሄዳል፡፡ በዋናነት ብረት ነክ የሆኑ ማዕድናት እንደወርቅና የከበሩ ማዕድናት ወይም ቤዝ ሜታልስ የሚባሉ ማዕድናት የሚገኙባቸው በአብዛኛው በአገሪቱ በስተደቡባዊ በኩል፣ በስተምዕራብና በሰሜን ኢትዮጵያ አለቶች አካባቢ ነው፡፡ በመሃል ኢትዮጵያ አካባቢ የሚገኙት በአብዛኛው የኢንዱስትሪ ማዕድናትና የጌጣጌጥ ማዕድናትና የኮንስትራክሽን ማዕድናት ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያም በርካታ የኮንስትራክሽን ማዕድናት አሉ፡፡ በአብዛኛው የሚስተናገዱት በክልል ማዕድናት ቢሮ አማካይነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታንታለም የተባለው ማዕድን ማምረት ተጀምሯል?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
ታንታለም በአንድ የመንግሥት የማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር በተባለ ኩባንያ ነው እያመረተ ያለው፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡ የማዕድን ክምችቱ በጥናት ተረጋግጦ እያመረተ ነው፡፡ ሌሎች በባሕላዊ መንገድ በዚያው አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች የሚያመርቱት ነው፡፡ ፐርሰንቱና ጥራቱ ልዩነት ቢኖረውም የተወሰነ ታንታለም በደለል ደረጃ ይመረታል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቱም የማምረት አቅሙን እያስፋፋ ይሄዳል፡፡ እንዲሄድም የመንግሥት አቅጣጫም የኩባንያው እቅድም ሆኖ በዚያ መልኩ የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ የተሻለ የማምረት ሥራ ለማካሄድ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው ያለው መረጃ፡፡

ሪፖርተር፡- በአጭርና በረዥም ጊዜ ዕቅድ የተያዙ ሌሎች የከበሩና ውድ ማዕድናትን የመፈለግ መርሃ ግብር አላችሁ? ለምሳሌ ዩራንየምንና ሌሎች፤

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
ማዕድናትን በአንድና በሁለት ዓመት ማልማት አይቻልም፡፡ በጥቂቱ ከአራት እስከ ስምንትና ዘጠኝ ዓመታት የሚፈጅ፣ በርካታ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅና ሙያዊ ጥናትን የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ በመካከለኛ ወይም በረዥም ጊዜ ሊለሙ የሚችሉ የማዕድናት አለኝታዎችና ምክንያቶች ናቸው ያሉት፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚለሙት የኢንዱስትሪ ወይም የኮንስትራክሽን ማዕድናት ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱም እየተሠራባቸው ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ዩራኒየም በባሌ አካባቢ ተገኝቷል የሚል ፍንጭ ነበር፤

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
አዎ፡፡ መንግሥት የዩራኒየም ፍንጭ መኖሩን በጥናት አረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚያዊ ነው አይደለም ለሚለው ተጨማሪ ሥራ ሠርቶ የግሉ ሴክተር እንዲያለማው ነው የሚፈለገው፡፡ ለግል ሴክተር ክፍት ነው፡፡ ፈቃድ አልተሰጠበትም፡፡ ያንን ወደፊት ጥያቄዎች ሲቀርቡ በዚያ መሠረት የምናስተናግደው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው ማዕድናት እነማን ናቸው?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
የደለልም የጽንሰ ወርቅም ተመርቶ ለውጭ ገበያ ይቀርባል፡፡ ፕላቲኒየም፣ ታንታለም ይላካሉ፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ቀላል ያልሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የተለያዩ ማዕድናት እየተመረቱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የማዕድናቱ ምርመራ በማካሄድ በኩል የእናንተ እገዛ አለ? ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ ተብሎ የቀረበ ማዕድን ውዝግብ እያስነሳ ነው፤

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
ወርቁ ትክክለኛ ነው አይደለም ብሎ የመለየት ችግር አይደለም፡፡ እርሱ ራሱን የቻለ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ናሙና ወይም የተሟላው ማዕድን ወደ ላቦራቶሪ ቢሄድ በላቦራቶሪ ባለሙያዎች ለመለየት ችግር አይሆንም፡፡ በገበያ ሂደት ግን የሚፈጠሩ የማጭበርበር ሂደቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ዝርዝሩን በሌላ ጊዜ ማየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በጌጣጌጥ ድንጋዮች ልማትስ ምን ያህል ተኪዷል?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
በርካታ የጌጣጌጥ ማዕድናት አሉ፡፡ በአብዛኛው በባሕላዊ አምራቾች ይመረታሉ፡፡ በተወሰነ ደረጃ በማኅበራት እንደ ሩፒስ፣ ሳፋየር፣ ጋርሜት፣ ኦሜቲስት፣ አሜዞአይትና የመሳሰሉት እየተመረቱ ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቴክኒካዊ ድጋፍ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በማዕድን ሃብቷ ከጎረቤትና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ስትነፃፀር ደረጃዋ የት ነው?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
ኢትዮጵያ ሊለሙ የሚችሉ ማዕድናት ይኖሩባቸዋል ከሚባሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ጥሩ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ከአብዛኞቹ ጎረቤት አገሮች የተሻለ ክምችት እንዳላት በየጊዜው በሌሎች ወገኖች በጥናቶች ተረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ዝርዝር ጥናት ተጠንቶ የሚለማ የታወቀና የተረጋገጠ የለም፡፡ ብዙ እየተሠራ ስለሆነ ነው፡፡ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከጋና፣ ከታንዛኒያ ቀጥሎ ጥሩ ክምችት አላት የምትባለው ኢትዮጵያ ናት፡፡

ሪፖርተር፡- ባለሃብቶች በማዕድ ዘርፍ እንዲሰማሩ የምታደርጉት ቅስቀሳና የምትሰጡት ድጋፍ ምንድነው?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡
- በማዕድን ሕጉ መሠረት መብታቸውንና ግዴታቸውን አውቀው መሥራት እንዲችሉ ተገቢውን ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ በሕጉ መሠረት ማበረታቻና ቀልጣፋ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ተሳትፈን ስለ ሁኔታው እናስረዳለን፡፡ መረጃዎችን እናቀርባለን፡፡

ሪፖርተር፡- የተካሄዱ እንቅስቃሴዎች ምን ያህል ውጤት አምጥተዋል?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
የተፈለገውን ያህል ባይሆኑም የተወሰዱ ጥረቶች አሉ፡፡ በጥረት የሚገኙ የተሻሉ ነገሮች አሉ፡፡ የበለጠ መሥራትና ማስተዋወቅ እንዳለብን እንገነዘባለን፡፡

ሪፖርተር፡- በማዕድኑ ዘርፍ የፌደራል ማዕድንና ኤነርጂ ሚኒስቴር እና የክልል የማዕድንና ኤነርጂ ቢሮዎች ድርሻ ምንድነው? በምን ይገናኛሉ? በምን ይለያያሉ?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
ሁለቱም በማዕድን ሥራ ላይ ነው ትኩረታቸው፡፡ ክልሎች ለኢትዮጵያውያን ዜጎችና ለኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች እንዲሁም ባህላዊ ማዕድን ለማምረት እና ለሌሎች የምርመራ ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ከሆነ ወደ ፌዴራል ማዕድንና ኤነርጂ ሚኒስቴር ይመጣል፡፡

ሪፖርተር፡- የእናንተ ትብብር ምን ድረስ ነው?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የተወሰነ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ቴክኒካዊ ጥያቄዎች ሲመጡ መልስ ያገኛሉ፡፡ ዋናው የመረጃ ልውውጥ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ማዕድናትን በዋነኛነት የሚቀበሉ አገሮች እነማን ናቸው?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
ወርቅ በአብዛኛው የሚላከው ወደ አውሮፓ ነው ስዊዘርላንድ፡፡ ሌላው ኤክስፖርት የሚደረገው ማዕድን ታንታለም ነው፡፡ በግልፅ ጨረታ ነው የሚሸጠው፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚገዙት ቻይናዎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢንዱስትሪ ማዕድናትስ አሉ?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
በአብዛኛው ለአገር ውስጥ ጥቅም ነው የሚውሉት፡፡

ሪፖርተር፡- ከማዕድን ኤክስፖርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ምን ያህል ነው?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
ባለፈው ዓመት በጀት ዓመት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ወደ ዘጠና ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በማዕድኑ ዘርፍ ለመሰማራት የጠየቁ ባለሃብቶች አሉ?

አቶ ገብረእግዚአብሔር፡-
በተለያዩ ማዕድናት ዘርፍ ለመሰማራት የጠየቁ ወደ አሥር የሚሆኑ ባለሃብቶች አሉ፡፡
 
< Prev   Next >