Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow በዲያስፖራ ምሁራንን የማምጣቱ ...
በዲያስፖራ ምሁራንን የማምጣቱ ... Print E-mail
Sunday, 24 February 2008
በዲያስፖራ ምሁራንን የማምጣቱ ጥረት የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም

በዲያስፖራ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በአቅም ግንባታ ጥረቶችና በሌሎች ልማትን የማገዝ ተግባራት እንዲሳተፉ ለማድረግ የተከናወነው እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣቱ ተጠቁሟል፡፡
በካናዳ በኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ላይ የሚሠራ ፣አሄድ ካናዳ፣ የተሰኘ ተቋም ይፋ ያደረገው ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የተመለከተ ጥናት ሪፖርት እንዳለው ኢትዮጵያውያንን ተመልሰው እንዲሰሩ የማድረጉ ሀሳብ ውጤታማ አይደለም፡፡ በመሆኑም በገቢ ማሰባሰቢያና ድንገተኛ አደጋዎች ላይ ብቻ የተወሰነውን ጥረት ማጠናከርና ኢትዮጵያውያኑ በያሉበት ሆነው አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ ተገቢ ነው፡፡

በጥናቱ እንደ ምሳሌ የተጠቀሰው የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የሰለጠኑ የአፍሪካ ሀገራትን የመመለስና በሀገራቸው እንዲሠሩ የማቀላቀል ኘሮጀክት ነው፡፡ ይኸው በአውሮፓ ህብረትና በስደተኞች ድርጅት የሚደገፍ ኘሮጀክት ለተመላሾቹ የመዘዋወሪያ ወጪ፣ ደመወዝና የመሳሰሉ ጥቅማ ጥቅሞችን አመቻችቶ ለማሠራት አቅዶ ቢንቀሳቀስም ላለፉት ከአስር ለሚበልጡ ዓመታት ወደ ሀገር ውስጥ ማምጣት የቻለው 66 ኢትዮጵያውያንን ብቻ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የጥናት ውጤቱ ሪፖርት እንዳለው ኢትዮጵያውያኑ ሀገራቸው ከሚመለሱ ይልቅ እዚያው ሆነው በሀገር ግንባታ ቢሳተፉ የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህም እንደ መነሻ የተጠቆመው ኢትዮጵያውያኑ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በዲያስፖራው ሆነው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ኮሚቴዎች አቋቁመው የተቻላቸውን ለማድረግ የሚጥሩ መሆናቸው ነው፡፡ ምናልባትም እነኚህን ወቅት ጠብቀው የሚቋቋሙ ኮሚቴዎች ወደ ረጅም ጊዜ እቅዶችና የልማት ኘሮጀክቶች እንዲለወጡ ማድረግ የተሻለ ውጤት ሊኖረው ይችላል እንደ ሪፖርቱ፡፡ ካልሆነ ግን እንደ እስከ ዛሬው ሁሉ ዲያስፖራውያኑ ግለሰብና ቤተሰቦችን ብቻ በመርዳት ላይ ያተኩራሉ፡፡ ለሀገር ልማት አስተዋፅኦ ሊያበረክቱም አይችሉም፡፡

የጥናት ሪፖርቱ በካናዳና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ባካተተበት መጠይቅ የዲያስፖራ አባላቱ በደሀው ኢትዮጵያዊ ገንዘብ በነፃ የትምህርት ዕድል ያገኙ በመሆናቸው ኢትዮጵያን የመርዳት የሙያና የሞራል ግዴታ እንዳለባቸው ማመናቸውን ይጠቅሳል፡፡ በተጨማሪም የዲያስፖራ አባላቱ ኢትዮጵያን የመገንባት ኃላፊነት እንዳለባቸው በፅኑ ቢያምኑም እንዴት? ለሚለው ግን አያውቁትም፡፡

በዲያስፖራ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ልማት ንቁ ተሳታፊ እንዳይሆኑና አስተዋፅኦም እንዳያበረክቱ ያደረጋቸው ደግሞ የመነጋገሪያ መንገድ አለመኖር፣ ዲያስፖራውንም የሚያስተባብር ተቋም መጥፋት መሆኑ በጥናት ሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ ሌላው በሀገር ውስጥ እንዳለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በውጪ የሚገኙት ይልቁንም በከፋ ሁኔታ በብሔረሰብ፣ በፖለቲካና በመሳሰሉ ልዩነቶች የተከፋፈሉ በመሆናቸው ለአንድ ዓላማ መሰባሰቡ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል፡፡ ሆኖም እነኝሁ የዲያስፖራ አባላት በሀገራቸው አመቺ የፖለቲካ ሁኔታ እስኪፈጠር በሚል በሀገራቸው የልማት እንቅስቃሴ ሳይሳተፉ ጠቃሚ ጊዜያትን ማባከናቸውን ያምናሉ፡፡

እንደ ጥናቱ መረጃ ከሆነ ኢትዮጵያ በተለይ ቀደም ባሉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ በተማረ የሰው ኃይል ስደት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛ ቆይታለች፡፡ እ.ኤ.አ ከ1980 እስከ 1991 ባሉት አስርት 74.6 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የተማረ የሰው ኃይል ተሰዶ ነበር፡፡

መረጃው እንደሚተነትነው ወደ ውጪ ለትምህርት የሚላኩ ኢትዮጵያውያንም በአብዛኛው ወደ ሀገራቸው አይመለሱም በዚህ ምክንያት ዩኒቨርሲቲዎች ለከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረትና ከውጪ ምሁራንን ለመቅጠር ተገደዋል፡፡

ለምሳሌ በጥናቱ እንደተጠቀሰው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሂሳብ ትምህርት ክፍል የተላኩ ምሁራን አንዳቸውም ባለመመለሳቸው በድህረ ምረቃ ትምህርት የሰለጠኑ የትምህርት ክፍሉ ምሁራን ቦታዎች በሙሉ የውጪ ሀገር ዜጐች ተይዘዋል፡፡

በጥናቱ የተጠቀሱ የኢትዮጵያ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ባለሙያዎቹ ላለመመለሳቸውና አገር ውስጥ ያሉትም በራሳቸው ወጥተው ለመቅረታቸው ዋናው ምክንያት የፖለቲካ ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ምክንያት ለኢትዮጵያውያኑ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያኑም የሚሠራ ነው፡፡ የልማትና መልካም አስተዳደር እጦት ኢ-ዲሞክራሲያዊ አሠራርና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተለይ ምሁራኑ አገር ጥለው እንዲሰደዱ እያደረጉ ነው፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር
 
< Prev   Next >