Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ሚሌኒየም የሕክምና ትምህርት ቤት...
ሚሌኒየም የሕክምና ትምህርት ቤት... Print E-mail
Sunday, 24 February 2008
Image
ወ/ሮ በላይነሽ ውብሸት፤ዶ/ር አለማየሁ ተገኝ፤ አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ
ሚሌኒየም የሕክምና ትምህርት ቤት ከሳምንት በኋላ ሥራውን ይጀምራል


በቅዱስ ጳውሎስ ሪፈራል አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የተቋቋመው ሚሌኒየም የሕክምና ትምህርት ቤት የካቲት 24 ቀን 2000 ዓ.ም መደበኛውን የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀምር ፕሮፌሰር ጎርደን ዊሊያምስ የትምህርት ቤቱ ዲን ገለፁ፡፡
"ዘ ላይፍ ሰከንድ ቻንስ ፋውንዴሽን" የተባለው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው በሸኖ ከተማ አንድ የካንሰር ሪፈራል ሆስፒታል በ130 ሚሊዮን ዶላር ለመገንባት የሚያስችል እንቅስቃሴ በማከናወን ላይ መሆኑን ዶክተር አለማየሁ ተገኝ የፋውንዴሽኑ ተወካይ አስታውቀዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዊሊያምስ በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት በኢትዮጵያ ውስጥ በዓይነቱ ልዩ የሆነው ይኸው ሚሌኒየም የሕክምና ትምህርት ቤት ሥራውን የሚጀምረው 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ነው፡፡ ለሦስት ዓመት ተኩል የሚሰጠውን ይህንኑ የሕክምና ትምህርት ለመከታተል ከተመዘገቡት ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው፡፡ ከአጠቃላዩም ተማሪዎች ውስጥ አሥራ አምስቱ ከአፋር፣ ከጋምቤላ፣ ከቤንሻንጉል ጉምዝና ከሶማሌ ክልሎች የመጡ ሲሆን የቀሩት 35ቱ ደግሞ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች ነው፡፡

የሕክምና ትምህርቱ የሚሰጠው በሆስፒታሉ ሦስት ዋርዶች በመገልገል ነው፡፡ የመጀመሪያው ዋርድ ለኮምፒዩተር ላይብረሪ አገልግሎት ሲውል፣ ሁለተኛ ዋርድ፣ ለአናቶሚ ላብራቶሪ፣ ሶስተኛው ዋርድ ደግሞ ለትምህርት መስጪያ ክፍሎች እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የተማሪዎችም መኖሪያ ቤት በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተደራጅቷል፡፡   

ቀደም ሲል የተቋቋሙት አምስት ነባር የሕክምና ትምህርት ቤቶች የሚከተሉት የትምህርት ካሪኩለም ከአያሌ ዓመታት ጀምሮ ሲሰራባቸው የቆዩ በመሆናቸው በአሁኑ ጊዜ ከአገሪቱ ፍላጎትና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እንደማይጣጣሙ እና ስፔሻሊስት እካልተሆነ ድረስ ለማወቅ የማያስፈልጉ ትምህርቶች ሁሉ እንደተካተቱባቸው ፕሮፌሰር ዊሊያም ጠቁመዋል፡፡ የሚሌኒየሙ ትምህርት ቤት ግን እንደዚህ አይነቱን የትምህርት ካሪኩለም በመሰረዝ ወይም በማስቀረት ለአገሪቱ የሚበጁና ተስማሚ የሚሆኑ አዳዲስ የትምህርት አይነቶች እንዲካተቱ ማድረጉን፣ ከተካተቱት መካከል ስነ ምግባር፣ የሕክምና ሕጋዊ ችግሮች፣ የኮምፒዩተር ስልጠና ወዘተ. እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡

አገሪቱ ካላት የሐኪሞች እጥረት የተነሳ የሥልጠናው ጊዜ በሦስት ዓመት ተኩል እንዲገደብ ተደርጓል፡፡ ተማሪዎች በሥልጠና ላይ በሚቆዩበት ጊዜ ወደ ኅብረተሰቡ ዘልቀው በመግባት የኅብረተሰቡን የጤና ችግር እንዲረዱት ይደረጋል፡፡ በዚህም ጊዜ የድንገተኛ (ኢመርጀንሲ) ሕክምና፣ የቀዶ ሕክምና፣ የማህጸንና የሕፃናት በሽታዎችን በመከላከልና በመፈወስ ተግባር ላይ በመሰማራት ጠቃሚ ልምድ እንዲቀስሙ ይደ ረጋል፡፡

ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለአገልግሎት ወደ ገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በሚሰማሩበትም ወቅት ሙያቸውን በርቀት ትምህርት ፕሮግራም ያዳብራሉ፡፡ ለዚህም እውን መሆን በርቀት ትምህርት ፕሮግራም ኤክስፐርት የሆኑ ሁለት እንግሊዛውንያን ፕሮፌሰሮች እንደሚመጡ የትምህርት ቤቱ ዲን ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ በአገሪቱ ቀደም ብለው ከተቋቋሙት አምስት ነባር የሕክምና ትምህርት ቤቶች የሚለየው በነባር ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉት ተማሪዎች ለ18 ወራት ያህል የሕክምና ሳይንስ ብቻ ሲማሩ የሚሌኒየሙ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ግን ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በሽተኞችን በመጎብኘት ጭምር በመሆኑ፤ ከማኅበረሰቡ ጋር በቅርበት እንዲንቀሳቀሱ መታለሙ፤ በመጀመሪያው ዓመት ስምንት ሳምንታት ውስጥም መሠረታዊ የሕክምና አናቶሚና ፊዚዮሎጂ ትምህርቶች የሚከታተሉ መሆኑ፤ በሁለተኛው ተርም ደግሞ የልብ፣ የሳምባና የሌሎችንም የሰውነት ውስጥ አካላት ይዞታ ላይ የሕክምና ሥራ የሚያከናውኑበት ሁኔታ መመቻቸቱ ነው፡፡

የሕክምና ትምህርቱ የሚሰጠው ተማሪ ተኮር በሆነ መርህ መሠረት ነው፡፡ ይህም ማለት መምህራን አቅጣጫ ለማስያዝ ካልሆነ በስተቀር አብዛኛው ሥራ የሚከናወነው በተማሪው ጥረትና ብርታት ነው፡፡ ኢንተርኔትና ድረ-ገጽ ውስጥ ተማሪው እየገባ በሕክምና ሙያ ላይ ትኩረት ያደረጉ ጽሁፎችን በማውጣት ራሱን ማሻሻል ይጠበቅበታል፡፡ በሆስፒታሉ የሚገኙ ሐኪሞችም በማስተማሩ ሥራ ላይ እንደሚሳተፉ፣ ሌሎች ስድስት እንግሊዛውያን ፕሮፌሰሮችም በቅርቡ ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቁ፣ ከፕሮፌሰር ዊሊያም ማብራሪያ ለረመዳት ተችሏል፡፡

ፕሮፌሰሩ እንደገለፁት አገሪቱ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ 9ሺህ የሕክምና ተማሪዎችን የማስተማር አቅም የሚኖራቸው 13 የሕክምና ትምህርት ቤቶች የማቋቋም እቅድ አላት፡፡ በእንደዚህ አይነት ትምህርት ቤቶችም ውስጥ የርቀት ትምህርት ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ፕሮግራም እውን መሆን የሐኪሞች እጥረትን በመሸፈን ረገድ የጎላ ሚና ይጫወታል፡፡

ዶክተር አለማየሁ ተገኝ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን በኩል 80 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ በሚገኘው በሸኖ ከተማ 68 ሔክታር መሬት ላይ የሚቋቋመው ይህ የካንሰር ሪፈራል ሆስፒታል በተጓዳኝ የሥልጠናና የምርምር ማዕከላት፣ የሐኪሞች፣ የሠልጣኞችና የሠራተኞች መኖሪያ ቤቶች ይኖሩታል፡፡

ግንቦት 2 ቀን 2000 ዓ.ም የሆስፒታሉ መሠረት ድንጋይ የማኖር ስነስርዓት እንደሚካሄድ፣ እስከ 2003 ድረስ የግንባታው ሥራ ተጠናቅቆ ለመጀመሪያ ጊዜ ለ500 ሕሙማን የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ ለዚህም 400 አልጋዎች እንደሚኖሩትና በ2004 ዓ.ም የአልጋዎችም ቁጥር ወደ 700፣ በ2005 ዓ.ም ደግሞ የታካሚዎች ቁጥር በቀን ወደ 1000 ከፍ እንደሚል ተወካዩ አስረድተዋል፡፡

አንድ የካንሰር ታካሚ በአሁኑ ጊዜ ሕክምና ለማግኘት 80ሺህ ብር ያስፈልገዋል፡፡ ይህም ከኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም ጋር ሲነፃፀር በጣም ከባድ ነው፡፡ በአፍሪካ አራተኛ የሚሆነው ይህ ሆስፒታል ሥራውን ሲጀምር ለሕክምና ወደ ውጭ አገር መሄድን ያስቀራል፡፡ እስከ 30 በመቶ የሚሆኑት ሕሙማንም ከአፍሪካ አገሮች የሚመጡ የካንሰር ሕሙማን ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል፡፡

የካንሰር የሥልጠና ማዕከሉ ሥራ ሲጀምርም እስከ 5ሺህ የሚሆኑ ሰልጣኞችን በሦስት ምዕራፎች ያሰለጥናል፡፡ የሆስፒታሉም ሕንፃ ግንባታ ተጠናቅቆ ሥራ እስከሚጀምር ድረስ ፋውንዴሽኑ አሁን በአገልግሎት ላይ ካሉት ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር አስፈላጊውን እርዳታ በመስጠት ድጋፉን ያበረክታል፡፡

ሕዝቡ በካንሰር በሽታ ያለውን ግንዛቤ ለማዳበርና በጋራ ለመዋጋትም እንዲነሳሳ የካቲት 22 ቀን 2000 በሚሌኒየሙ አዳራሽ የገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ኮንሰርት ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡ በቀጣዩም በጅማ ከተማ ለተጨማሪ ገቢ የሚውል የሩጫ ውድድር ለማከናወንና በአዲስ አበባም የቴሌቶን ፕሮግራም ለማከናወን ታቅዷል፡፡

በኢትዮጵያ የካንሰር ሕሙማን ቁጥር በዓመት 200ሺህ እንደሚሆን፣ በብቸኝነት አገልግሎለቱን እየሰጠ ወደሚገኘው ጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደርሰው ዕርዳታ የጠየቁ ታካሚዎች ብዛት በዓመት እስከ 150 ሺህ እንደሚደርስ፣ ከእነዚህም መካከል ርዳታውን ማግኘት የሚችሉት ታካሚዎች ቁጥር 500 እንደሚሆንና ይህም ከአጠቃላዩ ታካሚዎች አንድ በመቶ ብቻ እንደሆነ ዶክተር አለማየሁ ገልፀዋል፡፡

ዘላይፍ ሰከንድ ቻንስ ፋውንዴሽን በሰብዓዊነት ላይ ተመስርቶ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ በጤናው ዘርፍ ቀዳሚ ችግር የሆነውን የካንሰር በሽታ ለመቀነስ የተቋቋመ ድርጅት ነው ያሉት ዶክተር አለማየሁ ፋውንዴሽኑንም ያቋቋሙት በካንሰር በሽታ ታመው ከአገር ውጭ በከፍተኛ ሕክምና የተፈወሱ ወይም የዳኑ አንዲት ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ወይዘሮ በላይነሽ ውብሸት የፋውንዴሽኑ ሴክሬታሪት በበኩላቸው "የሆስፒታሉ ግንባታ ሸኖ ላይ እንዲሆን የተደረገበት ምክንያት አካባቢው ከብክለት የፀዳ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው" ብለዋል፡፡ ለሕንፃውም ማሰሪያ የዋለን ቦታ በነፃ የሰጠው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሲሆን ለሕንፃው ግንባታ በአገር ውስጥ የሚካሄደው ይህ አይነት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ለማከናወንም መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ የሠራዊት መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ባለቤት እንዳብራራው ፕሮጀክቱ ከፋውንዴሽኑ ጋር በመተባባር እንደሚሰራ ገልጾ "ጤና ይስጥልኝ" በሚል መርህ በሚካሄደው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ታዋቂ አርቲስቶች፣ የኪነጥበብ ሰዎች፣ ድምፃዊያንና ተወዛዋዦች እንደሚሳተፉበት አስረድቷል፡፡    

በታደሰ ገብረማርያም
 
< Prev   Next >