Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow የተሻሻለው የባንክ ሥራ አዋጅ፤...
የተሻሻለው የባንክ ሥራ አዋጅ፤... Print E-mail
Sunday, 24 February 2008
የተሻሻለው የባንክ ሥራ አዋጅ፤ የተጻፉና ያልተጻፉ ድንጋጌዎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ተሻሽሎ የቀረበ ረቂቅ የባንክ ሥራ አዋጅ ለባንኮች በትኗል፡፡ ለዚህም ነው የባንኮች ማኅበር በአንድነትና እና እያንዳንዱ ባንክ በተናጠል አስተያየቱን ለብሔራዊ ባንክ ያቀረበው፡፡ ባንኮችን ከሌሎች ባንክ ያልሆኑ ተቋማት የሚለዩዋቸው በርካታ ባህርያት ያሉ ቢሆንም ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ አራቱን እወስዳለሁ፡፡
 
አንደኛው ባህሪ በራሳቸው ሳይሆን "የሌላ ሰው ገንዘብ" ተጠቅመው "ገንዘብ" ለመነገድ የተቋቋሙ ድርጅቶች መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት የሚነግዱት እቃ ወይም ሸቀጥ ሣይሆን "ገንዘብ" ነው፡፡ ገንዘቡ ደግሞ የራሳቸው አይደለም፡፡ የሌላ ነው፣ የሕዝብ ነው፣ የሀገሪቱ ነው፡፡ ከተሜውና ከተማ ቀመስ የሆነው ሰው ከእለት ተእለት ጉርሱ የቆጠባትን ገንዘብ ለክፉ ቀን እንድትሆነው ወይም አጠረቃቅሞ አንድ ጉዳይ ላይ ለማዋል ባንክ ያስቀምጣል፡፡ ሻል ያለ አቅም ያላቸው ሰዎች ደግሞ ለገንዘባቸው ደህንነት እንዲሁም ጠቀም ያለ ወለድ ለማግኘት ሲሉ ገንዘባቸውን ባንክ ያስቀምጣሉ፡፡ መንግሥት በታክስ መልክ ያሰባሰበውን ገንዘብ ጥቅም ላይ እስኪያውለው ባንክ ያስቀምጣል፡፡ የንግድ፣ የማምረቻና የአገልግሎት ድርጅቶች (መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ) ለጊዜው የማይጠቀሙበትን ገንዘብ ባንክ ያስቀምጣሉ፡፡ ከተለያየ የኢኮኖሚ ተዋናይ በአደራ የሰበሰቡትን ገንዘብ ይህንን  ባንኮች ለፈለጉት ጉዳይ ያውሉታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን ገንዘቡን ለሌላ የኢኮኖሚ ተዋናይ በብድር ይሰጣሉ፡፡ በዚህም ትርፍ ያገኛሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ገንዘብ ለማስቀመጥም ሆነ ገንዘብ ለመበደር ስንፈልግ ባንክ እንሄዳለን፡፡ አንዱ ተዋናይ ያስቀምጣል፤ ሌላው ይበደራል፡፡ ባንኮች ከአንዱ ተዋናይ ገንዘብ ተቀብለው ለሌላው አሳልፈው በመስጠት ትርፍ ያገኛሉ፡፡ ሁለተኛው ባህሪያቸው ከመጀመሪያው የሚመነጭ ነው፡፡ ባንኮች የሚነግዱት ሸቀጥ ወይም ዕቃን ሳይሆን ገንዘብን እራሱን በመሆኑ ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በእጃቸው ያለው ገንዘብ (ያውም የራሳቸው ሰይሆን የሌላ ሰው) በጥንቃቄ ካልተያዘ በስተቀር ስርቆትና ምዝበራ ከማናቸውም ባንክ ካልሆኑ ድርጅቶች ይልቅ በባንኮች ሊካሄድ ይችላል፡፡ ገንዘብን ሜዳ ላይ እንደሚፈስ የቦይ ውሃ በቀላሉ ወደፈለጉት አቅጣጫ እንዲያመራ ማድረግ ይቻላል፡፡ የባንኮች ሥራ በጥንቃቄ ሊያዝ የሚችለው ደግሞ የሕዝብን ገንዘብ የሚያስተዳድሩት የባንኩ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ታማኝና ቅን ከሆኑ በባንኮች ላይ መንግሥት ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ከአደረገ ነው፡፡ ሶስተኛው ባህሪ አሁንም ከመጀመሪያው ይመነጫል፡፡ ባንኮች የውስጥ አካላቸው በሥራ ሂደት ኪሣራ ወይም አልፎ አልፎ በዘራፊ የባንክ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተቦርቡሮ አልቆም ቢሆን ጉዳታቸውን በውስጡ ካሉ የባንክ ኃላፊዎች በስተቀር ተቆጣጣሪውን ባለሥልጣን ጨምሮ ማንም ሳያውቅ በሕይወት መቆየት ይችላሉ፡፡ ልክ እንደ ፀጉራም ውሻ ናቸው፡፡ ሕዝቡ ገንዘቡን ለባንኮች የሚሰጠው ሽርፍራፊ እንኳ ሳትቀር፣ ከነወለዱ በሚፈለገው ጊዜ እንደሚመለስለት በማመን ነው፡፡ በተግባር እንደምናየው አንዱ ሲያስቀምጥ ሌላው ያወጣል፡፡ በየቀኑ ሰዎች የሚያስቀምጡት ገንዘብ በሌሎች አስቀማጮች ከሚወጣው እስከበለጠ ባንኮች ልዩነቱን እየበሉ በሕይወት መኖር ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሁኔታው የተገላቢጦሽ ሆኖ በየቀኑ የሚቀመጠው ገንዘብ ከሚወጣው ሲያንስ ሞታቸው ይፋጠናል፡፡ ሲሞቱ ደግሞ የአንዳችንን ወይም የሌላችን ብቻ ሳይሆን የሁላችንንም ገንዘብ ይዘው ነው፡፡ አራተኛው የባንኮች ባሕሪ በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸው ልዩ ቦታ ነው፡፡ ባንኮች በኢኮኖሚ ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ልብ በሰውነት ውስጥ ደም እንዲዘዋወር ከሚጫወተው ጋር ይመሳሰላል፡፡ ገንዘብ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው በባንኮች ነው፡፡

ከላይ በዘረዘርኳቸውና ሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች በማናቸውም ሀገር ያለ መንግሥት ባንኮችን ይቆጣጠራል፤ በባንኮች ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት የማይስማማ ሰው ያለም አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም ሁልጊዜ የማያስማማው ነጥብ ቁጥጥሩ እስከምን ድረስ መጥበቅ አለበት የሚለው ይመስለኛል፡፡ ተቆጣጣሪ የሚሆነው ተቋም የሕዝብና የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ የተጣለበት ኃላፊነት ከፍተኛ በመሆኑ ሰፋ ያለ ሥልጣን ሊሰጠኝ ይገባል ብሎ ቢከራከር፤ በተቃራኒው ቁጥጥር የሚደረግበት ተቋም ደግሞ ሥራዬን በአግባቡ ለመሥራት እንድችል ቁጥጥሩ ላላ ያለ ይሁንልኝ ቢል አያስገርምም፡፡ ሁለቱም የሚያራምዱት የየራሳቸውን ፍላጎት ነውና፡፡ ሁለቱም ተከራካሪዎች ቁጥጥሩ መጥበቁ ወይም መላላቱ የሚያደርሰውን ጉዳት ወይም የሚሰጠውን ጥቅም እንደየፍላጎታቸው አሳማኝ በሆነ መንገድ ማቅረባቸው የሚጠበቅ፣ ተገቢም ነው፡፡ ነገር ግን የአዋጁን ጥቅም ወይም ጉዳት እጅግ አግዝፎና አጋኖ ማቅረቡ ለረቂቅ አዋጁ መዳበር ያለው ጠቀሜታ እጅግም ነው፡፡ ለምሳሌ አቶ የኢየሱስወርቅ ዛፉ ለሪፖርተር እና ለጋርዲያን ጋዜጦች በሰጡዋቸው ቃለ ምልልሶች እንደገለፁት ለባንኮች የተበተነው ተሻሽሎ የቀረበው የባንክ ሥራ አዋጅ ፀድቆ በሥራ ላይ ከዋለ እርሳቸውን ጨምሮ የባንክ ባለሀብቶች አዋጁ በፀደቀ ማግስት በባንክ ያላቸውን አክስዮን በሙሉ ይሸጣሉ፡፡ ያውም ገዢ ከተገኘ፡፡ የባንክ ቦርድ አባላት፣ ፕሬዚዳንቶችና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችም ሥራቸውን ይለቃሉ፤ ሃገሪቱ ወደ አልተፈለገ የባንክ ክፍለ ኢኮኖሚ ቀውስ ትገባለች፡፡ በመሆኑም አዋጁ የተረቀቀው እንደ አቶ የኢየሱስ ወርቅ ከሆነ የባንክንና የፋይናንስ ሥራን አይን ለማጥፋት ነው፡፡ ይህ አባባል እጅግ የተጋነነ ከመሆኑም በተጨማሪ እ.ኤ.አ በ2002 ብሔራዊ ባንክ የመጠባበቂያ መመሪያ ያወጣ ሰሞን ይነገርና ይጻፍ የነበረውን ያስታውሰናል፡፡ ያኔ አቶ የኢየሱስ ወርቅን ጨምሮ ብዙ የባንክ ኃላፊዎች "ባንኮችን ለማጥፋት የወጣ መመሪያ ነው፤ በመሆኑም ሁሉም ባንኮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ኪሣራ በመግባት ከገበያ ውጭ ይሆናሉ፤ ሀገሪቱንም የባንክ ቀውስ ይገጥማታል" በሚል በተደጋጋሚ በጋዜጦች በመጻፍ ተንብየውና ተናግረው ነበር፡፡ አሁን ወደኋላ ተመልሰን ስናይ ይህ ትንቢት እንበለው ንግርት እውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ይልቁንም ባንኮች ይበልጥ አትራፊ መሆናቸው፣ የተበላሸ ብድር በመቀነሱ ምክንያት መጠናከራቸውን እየነገሩን ነው፡፡ ይህም ረቂቅ የባንክ ሥራ አዋጅ የሚባለውን ዓይነት ቀውስ ያስከትላል ብሎ ማመን ያዳግታል፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት የተጋነነም ነው፡፡ ሕግ አውጪውን አካል ለማሳመን ወይም የሕዝብን ቀልብ ለመሳብ ሲባል  እንዲያው ያልሆነ ነገር፣ አንዳንዴም በረቂቅ አዋጁ ያልተጻፈውን ጭምር እንደተፃፈ አድርጎ ማቅረብ ረቂቅ አዋጁን አያዳብረውም፡፡ እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ አቀራረብ አቅራቢዎቹን ትዝብት ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ የዚህም ጽሑፍ ዓላማ በጋዜጦች በተደጋጋሚ ስለረቂቅ አዋጁ ከቀረቡት ውስጥ ተገቢ ያልሆኑ ናቸው ብዬ ያመንኳቸውን ጉዳዮች በማንሳት በአዋጁ ላይ ሃሣብ መለዋወጡን ለማስቀጠል ነው፡፡ በቀና መወያየታችን አዋጁን ለማዳበር ይረዳናል፡፡

በመጀመሪያ ረቂቅ "አዋጁ ብሔራዊ ባንክን ራሱ ከሳሽና ዳኛ ሆኖ በባንክ ኃላፊዎች ላይ እስከ 15 ዓመት የሚደርስ እስራት ሊጥል ያስችለዋል" በተባለው ሃሳብ ላይ ላተኩር፡፡ ብሔራዊ ባንክ በእርግጥም ከሳሽም ፈራጅ ለመሆን አስቦ የአዋጅ ረቂቅ አዘጋጅቶ ከሆነ ተሳስቷል፤ መታረምም አለበት፡፡ አሁን ባለን አሠራር ሕግ ሲጣስ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ነው፡፡ ፍርድ ሰጪም ዳኛ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከእነዚህ ሁለት ሥራዎች አንዱንም ሊይዝ አይገባም፡፡ እኔ እንደተረዳሁት ረቂቅ አዋጁ የተባለውን ሥልጣን ለብሔራዊ ባንክ አይሰጥም፡፡ ለባንኮች የተበተነው ረቂቅ አዋጅ በአንቀጽ 5"7) እንዲህ ይነበባል "የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 ወይም 6 ድንጋጌዎችን የጣሰ ማናቸው ሰው የወንጀል ድርጊት እንደፈጸመ ተቆጥሮ ሲፈረድበት በ15 (አስራ አምስት) ዓመት እሥራት እና ከብር 50ሺህ (ሃምሳ ሺህ ብር) እስከ ብር 100 ሺህ ብር (መቶ ሺህ ብር) በሚደርስ መቀጫ ይቀጣል"፡፡ እንደሚታወቀው ፍርድ የሚሰጠው በብሔራዊ ባንክ ሳይሆን በፍርድ ቤት ነው፡፡ በመሆኑም የዚህ አንቀጽ ድንጋጌ ብሔራዊ ባንክን ከሣሽም ዳኛም አያደርገውም፡፡ ይህ ድንጋጌ የእስር ዘመን ጣሪያን በሚመለከት በሥራ ላይ ካለው አዋጅ 84/1986 አንቀጽ 30"3) ላይ የተገለበጠ ነው፡፡ ስለሆነም አዲስ የተጨመረ አይደለም፡፡ ሆኖም በነባሩ አዋጅ የእስር ቅጣቱ መነሻ 10 ዓመት ሆኖ ጣሪያው 15 ዓመት ነው፡፡ የገንዘብ መቀጫውን በሚመለከት በሥራ ላይ ባለው አዋጅ "ከብር 50 ሺህ ያላነሰ" ሲል በረቂቅ አዋጁ ላይ "ከብር 50 ሺህ እስከ 100 ሺህ" ይላል፡፡ የገንዘብ ቅጣቱን በሚመለከት ልዩነቱ በረቂቅ አዋጁ ጣሪያ መቀመጡ፣ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ግን አለመኖሩ ነው፡፡ እዚህ ላይ መነሣት ያለበት ጥያቄ በሥራ ላይ ያሉት የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ኃላፊነታቸውን የተረከቡት የእስርም ሆነ የገንዘብ ቅጣት መኖሩን እያወቁ ነው ወይስ ሳያውቁ? የሚለው ነው፡፡ እያወቁ ከሆነ እንዴት ረቂቅ አዋጁ በፀደቀ ማግስት ሥራቸውን ይለቃሉ? ወይም የሥራ ማቆም አድማ ያደርጋሉ እንበል?፡፡ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ? ሥራ የሚለቁ ወይም አድማ የሚመቱ ከሆነ የረቂቅ አዋጁን መጽደቅ መጠበቅ ለምን አስፈለጋቸው? እስካሁንስ ይህንን ጉዳይ ለምን አላነሱም? እነዚህን ጥያቄዎች አንስተን ስንወያይ የአቶ የኢየሱስ ወርቅ ትንበያ ትክክል አለመሆኑን የምንረዳ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ በአዋጁ መውጣት ምክንያት የሚደርስ አገር አቀፍ ቀውስ አይኖርም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ ባንክ በሥራ ላይ ያለው የእስር ቅጣት ዘመን መነሻ 10 ዓመት መድረሻው 15 ዓመት መሆኑ ቀርቶ መነሻም መድረሻም ሳይኖረው 15 ዓመት እንዲሆን ለምን ፈለገ? በእኔ እምነት የእስር ቅጣት ዘመኑ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 84/1986 አንቀጽ 30(3) ላይ በተቀመጠው መሠረት ምንም ለውጥ ሳይደረግበት ቢቀረጽ መልካም ነው፡፡

ወደ ሁለተኛው ነጥብ ልለፍ፡፡ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 84/1986 አንቀጽ 33 ላይ የተደነገገው እንዲህ ይነበባል "ይህንን አዋጅ ለመፈጸም ሲባል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎችና ተጠሪዎች በቅን ልቦና ለሚፈጽሙት ማናቸውም ድርጊት በግል ክስ፣ ኪሣራ ወይም ማናቸውም ጥያቄ አይቀርብባቸውም"፡፡ ይህ ድንጋጌ ቃል በቃል ተገልብጦ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 4(2) ላይ ተቀምጧል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ድንጋጌውን እንደ አዲስ በረቂቅ አዋጁ እንዳስገባ ተደርጎ በጋዜጦች ተተችቷል፡፡ ይህም ለባንክ ሥራ ኃላፊዎች ሥራ መልቀቅ አንዱ ምክንያት ይሆን እንዴ? በዓለም የባንክ ቁጥጥር መሠረታዊ መርሆዎችን የሚያወጣ "ባዝል ኮሚቴ" የሚባል ተቋም አለ፡፡ የብዙ ሀገሮች የባንክ ሥራ ሕጎች መሠረት ያደረጉት ይህ ተቋም ያወጣቸውን መርሆዎች ነው፡፡ ይህ ተቋም እ.ኤ.አ በ2006 ካወጣቸው 25 መሠረታዊ መርሆዎች ውስጥ መርህ ቁጥር 1(5) በግርድፉ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ሲተረጎም እንዲህ ይነበባል፡፡ "የባንክ ተቆጣጣሪ ተቋምና የተቋሙ ሠራተኞች የመቆጣጠር ተግባራቸውን ሲያከናውኑ በቅን ልቡና ለፈፀሙት ተግባር የሕግ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል"፡፡ የዚህ መርህ ዓላማ የባንክ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ካለምንም ስጋት የቁጥጥር ሥራ ግዴታውን ለመወጣት እንዲችል ማገዝ ነው፡፡ በዓለም ላይ የባንክ ተቆጣጣሪ አካል ለማቋቋም የወጡ አዋጆች ሁሉ የዚህ ዓይነት ድንጋጌ አላቸው ብሎ በሙሉ ልብ መናገር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ይህ ድንጋጌ መጀመሪያ አዲስ የተጨመረ ባለመሆኑ፣ ሁለተኛ በሌሎች አገሮችም የተለመደ፣ ሦስተኛም ተገቢም በመሆኑ አከራካሪ ሆኖ መቅረብ የለበትም ባይ ነኝ፡፡

ሦስተኛው በጋዜጦች ብዙ የተባለለት ስለዳይሬክተሮች ሹመት በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው ነጥብ ነው፡፡ "ብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮችን ሹመት ለምን ያጸድቃል?፣ "ለምን እዚህ ዳይሬክተር ከሆንክ እዚያኛው መሆን አትችልም የሚል ድንጋጌ ማውጣት አስፈለገ?" "ባንኮችን ማስተዳደር ያለባቸው እኮ ባለቤቶቹ ናቸው"፣ "ብሔራዊ ባንክን ምን እዚህ ጥልቅ አደረገው?" የሚሉ ክርክሮች ተነስተዋል፡፡ በጉዳዩ በሰፊው መወያየት የሚቻል ቢሆንም የጋዜጣውን አምድ ላለማጣበብ በአጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ ባንኮች በሰው/ በሕዝብ ገንዘብ የሚሠሩ በመሆናቸው፤ ለአደጋ እጅግ በጣም የተጋለጡ ስለሆኑ፣ በኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑና፤ ግልጽነት የሚጎድላቸው በመሆኑ በየትም በዓለም ላይ ባለ ሀገር ቁጥጥሩና ክትትሉ የሚጀምረው ከባንኩ ባለቤቶችና ኃላፊዎች ነው፡፡ ባንክ የሚወከለው በእነዚህ ሰዎች ነው፡፡ አለዚያማ ግዑዝ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ታማኝ፣ ቅን እና በጥቅም ግጭት ውስጥ ያልተዘፈቁ የመሆናቸው ጉዳይ የቁጥጥሩ አንድ ክፍል እና ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም ተቆጣጣሪው አካል የእነዚህ ሰዎች ማንነት አጥንቶና ለክቶ ይሁንታ መስጠት መቻል አለበት፣ አለዚያ ግዑዙን ባንክ እቆጣጠራለሁ ብሎ አሰራሩ ላይ ብቻ በማተኮር ተፍ ተፍ ቢል ዓላማውን አያሳካም፡፡ ቦርድን በሚመለከት የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌዎች በጣም የጠበቁ ምናአልባትም ለመጥበቃቸው በዓለም ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ስለመሆኑ አንዳንድ መከራከሪያዎች ቀርበዋል፡፡ ነገር ግን እኔ እስከማውቀው ይህ ትክክል አይደለም፡፡ የብዙ አገሮች አዋጆችን ብሔራዊ ባንክ ባዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ስለቦርድ ከተደነገገው ጋር ማነጻጸር ይቻላል፡፡ በአጭሩ አንደኛ የባንክ ቁጥጥር መርሆዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያወጣው የባዝል ኮሚቴ በማያወላውል ሁኔታ የባንክ ባለቤቶችና የሥራ ኃላፊዎች የተቆጣጣሪውን አካል ይሁንታ ማግኘት እንዳለባቸው ያምናል፡፡ (የኮሚቴውን መርህ ቁጥር 3(6) እና 3"8) ይመልከቱ) ሁለተኛ በቅርብ ያለችው የኡጋንዳ ባንክ ሥራ ሕግ ውስጥ የባንክ ባለቤቶችንና ቦርድን በሚመለከት የሰፈረውን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ለመተርጎም ሳልሞክር አንባቢ ብሔራዊ ባንክ ስለቦርድና የባንክ ባለቤቶች ከአቀረበው ረቂቅ ድንጋጌ ጋር ማነፃፀር እንዲችል ከዚህ በታች አቀርባለሁ፡፡


Financial Institution Act 2004
Art 19: A person or group of persons who do not satisfy the criteria for fit and proper test relating to substantial shareholders as determined by the Central Bank ". shall not acquire more than 5% of shares of a financial institution. (ሠረዝ የተጨመረ)
Art 52(4) .... the central bank shall vet all persons proposed as directors of a financial institution" (ሠረዝ የተጨመረ)  
57 (1) The Central Bank may for sufficient cause:
a) remove a director of a financial institution or
b) remove or suspend the whole board of directors of a financial institution.
57 (3) No director serving the board of a financial institution shall simultaneously serve as a board member, or in any executive capacity, with any other financial institution or a subsidiary or affiliate of the financial institution in Uganda.

   ከላይ እንደጠቀስኩት በኡጋንዳ ሕግ ውስጥ የሚገኙት ብሔራዊ ባንክ ባቀረበው ረቂቅ አዋጅ ስለባለአክስዮኖችና ቦርድ ከተደነገጉት የተለዩ አይደሉም፣ እንዲያውም ከዚሁ የተገለበጡ ይመስላሉ፡፡ እንደሚከተለው ይነበባሉ፡፡

 3(1) ... ተደማጭነት ያላቸው ባለአክስዮኖች .... ብሔራዊ ባንክ የሚያወጣቸውን መመዘኛዎች ማሟላት አለባቸው፡፡ (ከኡጋንዳው አዋጅ አንቀጽ 19 ጋር የሚነፃፀር)

5(1) የማንኛውም ባንክ ዳይሬክተር .... ሹመት ... በማናቸውም ጊዜ በብሔራዊ ባንክ በጽሑፍ ካልፀደቀ በስተቀር ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ (ከኡጋንዳው አዋጅ አንቀጽ 52(4) ጋር ያነጻጽሩት)

5(3) የአንድ የፋይናንስ ድርጅት ዳይሬክተር ... በተመሳሳይ ጊዜ በሌላ የፋይናንስ ድርጅት ዳይሬክተር ሆኖ ሊያገለግል አይችልም፡፡ (ከኡጋንዳው አዋጅ አንቀጽ 57(3) ጋር ያስተያዩት)

5(8) ... ብሔራዊ ባንክ በቂ ነው ብሎ በሚያምንበት ምክንያት የማንኛውንም ባንክ ዳይሬክተር ... ከሥራ ሊያሠናብት ይችላል፡፡ (ከኡጋንዳው አዋጅ አንቀጽ 57(1) ጋር የሚመሳሰል)

ለማጠቃለል በረቂቅ አዋጁ በተቆጣጣሪውና ቁጥጥር ተደራጊው መካከል የሚደረገው ክርክር መቀጠል አለበት፡፡ አዋጁ የሚዳብረውም ይሄ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ሁላችንም እንደምናውቀው የባንክ ሥራ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል ሊደረግበት የሚገባ በመሆኑ የተቆጣጣሪውን ባለሥልጣን ሥጋት እንረዳለን፡፡ ሆኖም ተቆጣጣሪው ገደብ የሌለው፣ ራሱ ከሳሽ ራሱ ፈራጅ የሚሆንበት ሕግ ሊወጣለት አይገባም፡፡ ቁጥጥር ተደራጊውም ልቀቁኝ፣ እንደፈለግሁ ልሁን፣ የሕዝብ ገንዘብ ማስተዳደሬ እውን ቢሆንም ሕዝቡ ገንዘቡን አምኖ የሰጠኝ ለእኔ ነው፤ መንግሥት ምን አገባው? የሚል ጫፍ ይዞ ቢከራከር ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ መንግሥት የሕዝብን ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ እንደምረዳው ከሆነ ሕዝብ ባንክ ወስዶ ገንዘብ የሚያስቀምጠው ከአንድ ባንክ ዳይሬክተር ወይም ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር ስለሚተዋወቅ ሳይሆን መንግሥት ምንጊዜም ጥቅሜን ያስጠብቅልኛል ብሎ ነው፡፡ መንግሥት በባንኮች የሚያደርገው ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትልም በአንድ እውቅ የፋይናንስ ባለሙያ በአንድ ወቅት በአደባባይ እንደተነገረው ወደ ሶሻሊስት ዘመን ተመልሶ ባንኮችን እንደመውረስ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ በዓለም ያሉት የካፒታሊስት ሥርዓት አራማጆች በሙሉ በባንኮች ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ማንም ሰው ሊገነዘብ ይገባል፡፡ እውቁ የፋይናንስ ባለሙያም "መንግሥት ባንኮችን ሊወርስ ነው" ብለው በባለአክስዮኖች ስብሰባ ላይ የተናገሩት ይህንን ሳያውቁ ቀርተው ሳይሆን ሳያስቡት (በምላስ ወለምታ) ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ሕግ አውጪው ሚዛኑን የጠበቀ፣ የግለሰብን መብት የማይጋፋ፣ የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚረዳ ወይም የሚያስችል ሕግ ማውጣት አለበት፡፡ ሕግ አውጪው ይህንን ኃላፊነት እንዲወጣ ለመርዳት ሁላችንም የየበኩላችንን ገንቢ ሃሣብ እናቅርብ፡፡ ከላይ እንደተገለፀው ረቂቅ አዋጁን በትክክል ሳንረዳውና ሳናነበው በስሜትና በዘፈቀደ በረቂቅ አዋጁ ፍጹም ያልተጻፉትን ወይም አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ውስጥ በግልጽ የተጻፉትን እንደ አዲስ በማድረግ የምናቀርበው ሃሣብ ገንቢ አይደለም፡፡

ለረቂቅ አዋጁ መዳበር ሊጠቅሙ ይችላሉ ብዬ ያመንኳቸውን ሦስት ሃሳቦች አቅርቤ ጽሑፌን ላብቃ፡፡ የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ መሠረት አክስዮን ማኅበራት ማስተዳደር የሚችሉት ባለአክስዮኖች ናቸው፡፡ አሁን አሁን በብዙ አገሮች እየተለመደ የመጣው በቦርድ ውስጥ ከባለአክስዮኖች ውጭ የሆኑ ነጻ የቦርድ አባላት (ኢንዲፔንደንት ቦርድ ሜምበርስ) የተወሰነ (ብዙ ጊዜ ከአንድ ሶስተኛ በላይ) መቀመጫ እንዲይዙ አስገዳጅ ሕግ ማስቀመጥ ነው፡፡ እነዚህ ነጻ የቦርድ አባላት በባንኩ ውስጥ ምንም አክስዮን የሌላቸው ሲሆኑ፣ የሚመረጡት በባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ነው፡፡ ወደ ቦርድ የሚገቡት በብቃታቸው፣ በሙያቸው እና በሥነ ምግባራቸው ተገምግመውና በባለአክስዮኖች ተመርጠው እንጂ ከፍተኛ ባለሀብት ወይም ባለአክስዮን በመሆናቸው አይደለም፡፡ በመሆኑም የጥቅም ግጭት ሳይኖርባቸው ለተመረጡበት ባንክ ጤናማ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ በተሻሻለው የባንክ ሥራ አዋጅ ውስጥ በእኔ እምነት ነጻ የቦርድ አባላት የተወሰነ የቦርድ መቀመጫ እንዲይዙ የሚያስገድድ ድንጋጌ ቢገባበት መልካም ይመስለኛል፡፡

ሁለተኛው አሁንም በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ መሠረት ኩባንያዎች የባንኮችን አክስዮኖች መግዛትና የባንክ ባለቤት መሆን ይችላሉ፡፡ ባለአክስዮን በመሆናቸው በቦርድ አባልነት እንደማንኛውም ሰው ይመረጣሉ፤ ነገር ግን ኩባንያዎች ግዑዝ ናቸው፡፡ በመሆኑም የአንድ ባንክ የቦርድ አባል ሆነው ሲመረጡ በተፈጥሮ ሰው ይወከላሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ተጠያቂነት ሲመጣ ማን ኃላፊ እንደሚሆን ግልጽ አይደለም፡፡ ወካዩ ኩባንያ ወይስ ተወካዩ የተፈጥሮ ሰው? ጉዳዩ በሕግ አጠያያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የኡጋንዳ የባንክ ሥራ አዋጅ የባንክ ቦርድ አባል መሆን የሚችለው የተፈጥሮ ሰው ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ በእኛ አዋጅ ውስጥም እንዲህ ዓይነት አስገዳጅ ድንጋጌ ቢኖር ተጠያቂነትን ግልጽ የሚያደርግ ይመስለኛል፡፡

ሦስተኛ የአነስተኛ ባለአክስዮኖችን መብት የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ባለው አሠራር በአክስዮን ማኅበራት ድምጽ የሚሰጠው በማህበሩ ባለው አክስዮን መጠን ነው፡፡ ይህ ማለት ከፍተኛ የአክስዮን መጠን ያለው አንድ ሰው በዚያው ልክ ከፍተኛ ድምጽ ሲኖረው ዝቅተኛ አክስዮን መጠን ያለው ደግሞ ትንሽ ድምጽ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም ማናቸውም ውሳኔ የሚያልፈው ከፍተኛ ባለአክስዮኖች ከደገፉት ብቻ ነው፡፡ አሁን በባንኮች እንደምናየው ከፍተኛ ባለአክስዮኖች የሚባሉት ቁጥራቸው በጣም ትንሽ (ከ10-20 የማይበልጡ) ሲሆን ዝቀተኛ ባለአክስዮኖች በሺህ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ሆኖም እነዚህ በሺህ የሚቆጠሩ ባለአክስዮኖች ስለባንኩ በሚደረግ ማናቸውም ውሳኔ ላይ ይህ ነው የሚባል ሚና አይጫወቱም፡፡ ስለዚህ አሁን በንግድ ሕጉ ስለአነስተኛ ባለአክስዮኖች መብት ከተደነገገው በተጨማሪ በባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ እነዚህ ባለአክዮኖች በቦርድ ውስጥ ተመርጠው ሊሳተፉ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያመቻች ድንጋጌ ቢኖር መልካም ይመስለኛል፡፡

ከጀንበር ኃይሉ
 
< Prev   Next >