| በሶማሊ ተራ አደባባይ ላይ ሊሰራ... |
|
|
| Wednesday, 27 February 2008 | |
|
በሶማሊ ተራ አደባባይ ላይ ሊሰራ የታሰበው ሀውልት ግንባታ ታደገ
“በየትኛውም አገር ኮሚኒቲ ስም የተሰየመ ሀውልት የለም” የአዲስ አበባ አስተዳደር በተለምዶ ሶማሊ ተራ ተብሎ የሚጠራው አደባባይ ላይ የኢትዮ-ሳውዲ ታሪካዊ ግንኙነትን በመዘከር ሊሰራ የታሰበው ሀውልት ታገደ፡፡ የአዲስ አበባ ጊዜያዊ አስተዳደር በየትኛውም አገር ኮሚኒቲ ስም የተሰየመ ሀውልት የለም ብሏል፡፡ የጂዳ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ተወካይ አቶ መሀሪ ተካ በአደባባዩ ላይ የሁለቱ ሀገራትን ግንኙነት ለመዘከር የሀውልት ግንባታ ለማካሄድ ከአዲስ አበባ ሚሌኒየም ፅህፈት ቤት ጋር ውል መዋዋላቸውን ገልፀዋል፡፡ በውሉ መሠረት በአደባባዩ ላይ የሀውልት ግንባታ ለማካሄድ አስፈላጊው የዲዛይን ሥራ ተሰርቶ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡ አቶ መሀሪ የሀውልቱን ሥራ በተመለከተ ጳጉሜ 5/1999 ዓ.ም የአዲስ አበባ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ ብርሃነ ደሬሣ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር መሐመድ ድሪር፣ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ሀሰን አብደላና በኢትዮጵያ የሳውዲ አምባሳደር ኢሳም ኢብራሂም ቤተልማል በጋራ የመሠረተ ድንጋይ ማኖራቸውን አስታውሰዋል፡፡ አቶ መሀሪ ለግንባታው ማከናወኛ ከ300 ሺህ ብር በላይ የኮሚኒቲው አባላት ማዋጣታቸውን ገልፀው፤ “ግንባታው እንዳይካሄድ ፈቃድ ተነፍጎናል” ሲሉ አማርረዋል፡፡ በዚህም በአንድ ወር ይጠናቀቃል የተባለው የሀውልት ሥራ እስከአሁን አልተገነባም፡፡ ተወካዩ የሀውልቱን ዲዛይን በሚሌኒየም ጽ/ቤቱ አማካይነት ተገምግሞ ተቀባይነት ማግኘቱን ነገር ግን ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ግንባታው መታገዱን ገልፀዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ ጊዜያዊ አስተዳደር ጽ/ቤትን ቢያነጋግሩም ምላሽ አልተሰጣቸውም፡፡ የአዲስ አበባ የሚሌኒየም አከባበር ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ሀይለስላሴ ለሀውልቱ ግንባታ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አንፃር ለግንባታው እንቅፋት የሆኑትን የኤሌክትሪክ ሀይል ምሰሶና መሰል ነገሮች እንዲወገዱ ደብዳቤ መጻፉን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ግንባታው መታገዱን መስማታቸውን አቶ ኪሮስ ገልፀዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ኢንጂነር ወብሸት ብርሃኑ በኮሚኒቲው ተወካዮችና በሚሌኒየም ጽ/ቤት መካከል የተደረሰው ስምምነት አደባባዩን የማስዋብ እና የመንከባከብ እንጂ የሀውልት ግንባታን የማያጠቃልል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም “ለየትኛውም ሀገር ኮሚዩኒቲ ያልተሰጠ የሀውልት ግንባታ ለጂዳ ኮሚዩኒቲ የሚፈቀድበት ምክንያት የለም” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ አያይዘውም ኮሚዩኒቲውና የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት “ጉዳዩን ሽፍንፍን አድርገው ባለሥልጣናት የመሠረተ ድንጋይ እንዲያኖሩ አድርገዋል” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ በከተማዋ ሕግ መሠረት ግንባታ የሚካሄደው በሕጋዊ ካርታ መሆኑን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ፤ “የሀውልትም ሆነ የአደባባይ ፈቃድ አልተሰጠም” ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ ዶ/ር ውብሸት እንደሚሉት የሀውልት ግንባታ ውዝግቡን ለመፍታት የአስተዳደር ጽ/ቤቱ ካቢኔ አባላት በ6/6/2000 ዓ.ም ባደረጉት ስብሰባ ምንም ዓይነት የአደባባይ ስያሜ እንዲሁም የሀውልት ግንባታ ተቀባይነት እንደሌለው ወስኗል፡፡ ኮሚዩኒቲው ከሚሌኒየም ጽ/ቤት ጋር በተስማማው ውል መሠረት አደባባዩን ማስዋብና መንከባከብ የሚችል መሆኑን ካቢኔው አሳውቋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ብዙ ሀገሮች ውስጥ መኖራቸውን ጠቅሰው “በየትኛውም ኮሚዩኒቲ ስም የተሰየመ፣ ሀውልት የለም” ያሉት ዶ/ር ውብሸት “በጊዜያዊነት የተቋቋመው የሚሌኒየም ጽ/ቤት ቢሮ አደባባይ የመሰየም ስልጣን የለውም” ሲሉ የተወሰነው ውሳኔ ሕጋዊ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |