Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
May 17th
Home arrow Sections arrow ዘግይቶ የደረሰ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ
ዘግይቶ የደረሰ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ Print E-mail
Wednesday, 27 February 2008
Imageመንግሥት የሚወስዳቸው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች የእሳት ማጥፋት እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ እሳቱ ከመነሳቱ በፊት መቆጣጠር እየተቻለ እርምጃው ሳይወሰድ ይቀርና እሳቱ ይነሳል፡፡ እሳቱ አደጋ ካደረሰ በኋላ ይሮጣል፡፡ የእሳት ማጥፋት እርምጃ ይወስዳል፡፡ የሚመረጠው እሳቱ ከመነሳቱ በፊት የሚወሰደው እርምጃ ነው፡፡ እሳቱ ተነስቶ አደጋ ካደረሰ በኋላ መሆን የለበትም፡፡ ሆኖም ግን ዘግይቷል ይባላል እንጂ የእሳት ማጥፋቱ እንቅስቃሴ አያስፈልግም አይባልም፡፡ የማጥፋቱ እርምጃ ባይወሰድ የቃጠሎው አደጋ ቀጣይና መጠነ ሰፊ ይሆናልና፡፡
መልዕክታችን ከእሳት አደጋ መከላከል ወደ ክትባት እንዲለወጥ ነው፡፡ ሆኖም ግን አበረታችና ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩ ናቸው፡፡

በደርግ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን የታየው እንቅስቃሴ ለሕዝብም ለመንግሥትም ግልጽ ነው፡፡ ብዙ ገንዘብና ንብረት ባክኗል፡፡ መንግሥት በወቅቱ ፈጣን እርምጃ ባለመውሰዱ ሙሰኞች በሚገባ ተጠቅመውበታል፡፡ ገንዘብ ሰርቀው ውጭ አገር ቪላ ገዝተው መኖር የጀመሩ የቴሌ ሹማምንት አሉ፡፡

ሆኖም ግን ቢዘገይም መንግሥት ሁሉት ጊዜ አመራር ቀይሯል፡፡ አመራር ሲቀየር ግን ቁንጮውን ሳይነካ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቀድሞ መሪ የነበሩትንም በቁጥጥር ሥር አውሏል መንግሥት፡፡

ይህ ቢዘገይም የሚያስመሰግን እርምጃ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ እንቅስቃሴ እንዳለም ታይቷል፡፡ አልነካም ባይ ሁሉ ሊነካ እንደሚችልም ምልክት ሰጥቷል፡፡ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ማንም ከሕግ በላይ የለም የሚል አመኔታን ሊፈጠር ስለሚችል እንቅስቃሴውና እርምጃው ተስፋ ሰጪነት አበረታች ነው፡፡

በወርቅ ዙሪያ ነጋዴዎች ሲታሰሩ ብሄራዊ ባንክ ስለሚመለከተው እንዴት እዚያ ተጠያቂ የለም የሚል ጥርጣሬ ፈጥሮ ነበር፡፡ ሰሞኑን የዘገየ ግን ተስፋ ሰጪ እርምጃ ተወስዷል፡፡ የባንክ ሃላፊዎች ተይዘዋል፡፡ እየተመረመሩ ነው፡፡ አደጋው እንዳይደርስ የአስቸኳይ እርምጃ ቢወሰድ ይመረጣል፡፡ አደጋው ከደረሰ በኋላም ቢሆን ዝም ሳይባል በመንግሥት መሥሪያ ቤት ያሉ ተጠርጣሪዎች መያዛቸው የሚያስመሰግን ነው፡፡

ብሄራዊ ባንክ ልማት ባንክ ሰባት መቶ ሚሊዮን ከሰረ ብሎ ለሚመለከታቸው ሪፖርት አድርጓል፡፡ በሽታው ሳይዛመት ክትባት ቢደረግ ይመረጣል፡፡ ሆኖም ግን አደጋው ከደረሰም በኋላ ቢሆን የልማት ባንክን ሃሳብ መርምሮ ኪሳራውን ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡ አደጋውን ከመደበቅ ይልቅ በግልፅ ይቀመጥ መባሉ ፋይዳ አለውና፡፡

የመንግሥት የፋይናንስ ተቋሞች ኤጀንሲ ለሶስት ዓመታት ተዘግቶ መቀመጡና ሥራውን አለመወጣቱ አደጋ አድርሷል፡፡ ቢዘገይም በአሁኑ ጊዜ ኤጄንሲው እንደገና እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ማድረጉና የድርሻውን እንዲወጣ ማበረታት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ምክንያቱም የዚህ ዓይነት መመሪያዎችን አፋጣኝ ትግበራ ለሌሎችም ይጠቅማል፡፡

የአንድ መሬት ካርታ በተለያዩ ሰዎች እጅ ውስጥ እንዳይኖር ጥንቃቄ ማድረግ ትክክለኛና የክትባት መድኃኒት በሆነ ነበር፡፡ አልተደረገም፡፡ እጅግ ዘገየ፡፡ ብዙ አደጋም ደረሰ፡፡ ሆኖም ግን ቢዘገይም የተምታታና የውሸት ካርታ እንዳለ በመገንዘብ ሕዝቡ በተጭበረበረ ካርታ እንዳይታለል፣ አጭበርባሪዎችም እንዳይጠቀሙ ለመግታት የተደረገው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡

መፍትሄዎች ዘግይተው በመድረሳቸው አደጋ አስከትለዋል፡፡ በዚህም መንግሥት ይወቀስበታል፤ አሁን በወሰደው እርምጃ ደግሞ ይመሰገንበታል፡፡ የዘገየበት ምክንያት ግን ስለችግሩ መረጃ ጠፍቶ አይደለም፡፡ ሰሚ ስለጠፋ ነው፡፡ የምላስ ችግር ሳይሆን የጆሮ ችግር ስላለ ነው፡፡ በአጭሩ ሲቀመጥ  የማዳመጥ ችግር አለ ነው፡፡

ከአሁን በኋላ ያለው እርምጃስ ምን መሆን አለበት? በሽታው እንዳይዛመት ክትባት ወይስ በሽታው ከተዛመተ በኋላ አምቡላንስ ማስጮህ?

በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ቆም ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ እርምጃ የዘገየበት ምክንያት ለምንድን ነው? አደጋ ለምን ደረሰ? በባሌስትራ እንዴት ተታለልን? እያልን መጠየቅ ይገባናል፡፡ በተለይም መንግሥት ሊመከርበት ይገባል፡፡

ደሃ ነን፡፡ ወለድ ከፍለን የምናገኘው ብድር አለን፡፡ ስንቱን ጫና አልፈን ባገኘነው ገንዘብ ለመስራት የምናቅደው ልማት በሌቦች የሚገታ ከሆነ የሚያሳዝን ነው፡፡

ከአሁን በኋላ መንግሥት ለሁሉም ነገር ፈጣን እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ራስን ብቻ ከማዳመጥ ይልቅ ሌሎች የሚሉትን፣ ሕዝብ የሚለውን ማዳመጥ አለበት፡፡

አሁን እርምጃ የመውሰድ እንቅስቃሴ ታይቷል እንጂ ዳር አልደረሰም፡፡ ፍርድ ቤት የሄደው ፍርድ ቤት ዳር ሊያደርሰው ይገባል፡፡ መንግሥት በራሱ እንቅስቃሴ የሚጨርሰውም በሕዝብ ድጋፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊቋጨው ይገባል፡፡

አንድ ነገር በግልፅ ሊቀመጥ ይገባል፡፡ ቢዘገይም አዎንታዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ አዎንታዊ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን አዎንታዊ ተሳትፎም እናድርግ፡፡
 
< Prev   Next >