| አፍሪካ ለቅኝ ገዢዎች ዳግም እድል ትሰጥ ይሆን? |
|
|
| Wednesday, 27 February 2008 | |
|
አንዳንድ የአፍሪካ ወዳጆችና ጠላቶች የአፍሪካ አህጉር፣ የሀገሪቱ መሪዎች እና ህዝቦቿን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውድቀት በማየት አፍሪካውያን እራሳቸውን ለመምራት አይችሉም ይላሉ፡፡ ቅኝ ገዥዎች ከአፍሪካ የወጡት ያለጊዜአቸው ነው በማለትም ቁጭታቸውን ይገልፃሉ፡፡
በተናጠል ለውጥ ማምጣት የሚችሉ አፍሪካውያን በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ ባይታጡም ተባብረውና ተግባብተው ለመስራት ግን ክንዳቸው ሁሌም እንደዛለ ነው፡፡ አፍሪካ ነፃ ከወጣች ዓመታት ቢቆጠሩም ዛሬም ከውድቀቷ ይበልጥ ድል መለያዋ አልሆነም፡፡ ተራው የአፍሪካ ህዝብ ከገዛ ልጆቹ ያተረፈው ጉስቁልና፣ ብጥብጥ እና በራስ ያለ መተማመንን ነው፡፡ ትናንት በዘመነ ቅኝ ግዛት ጥቁሮች ለራሳቸው ይሰጡት የነበረው ዝቅተኛ ግምት መነሻው የአውሮፓውያን የተጠና የማንነት ማዛባት ውጤት ነው ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ዛሬ አውሮፓውያን ከአህጉሪቱ ቢወጡም የአፍሪካ ልጆች በራሳቸው ለመቆም ህዝቦቹንም ከአህጉሪቱ ትሩፋት ለማቋደስ ሳይታደሉ አፍሪካውያን ቅኝ ገዢዎች ህዝባቸውን መገልገያ እያደረጉት ነው፡፡ በዘመነ ቅኝ ግዛት አፍሪካውያን ራሳቸውን ለማሳየት የነበራቸው ህልም ዛሬ በተስፋ መቁረጥና አንገት በመድፋት ተተክቷል፡፡ አንዳንዶች ቅኝ ገዥዎች ከአፍሪካ አልወጡም እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ምዕራባውያን በእርዳታቸውና በሁሉን አቀፍ የገንዘብ ተቋሞቻቸው አማካኝነት ዛሬም በእጅ አዙር እንደሚመሩ ያምናሉ፡፡ ሌሎች ግን ቅድመ ቅኝ ግዛት ከድህረ ነፃነት ጋር ተመሳሳይ የነበረ መሆኑን በማስረዳት በአፍሪካውያን ችግር አውሮፓውያን ተጠያቂ ሊሆኑ አይገባም በማለት ይከራከራሉ፡፡ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተቋም መፅሄት ላይ ሮበርት ዊለን በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ፅፎ ነበር፡፡ “ድንበር ዘለል ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አፍሪካን በጨረታ ተወዳድረው እስከ 21 ዓመት በሚደርስ ሊዝ እንዲያስተዳድሯት መብት ቢሰጣቸው ጥሩ ነው፡፡ ግብር ከሰበሰቡ አገልግሎት ይሰጣሉ፣ በአግባቡ ያስተዳድራሉ ስነ ስርዓትም ያስከብራሉ” ሞቡቱ ሴሴሴኮ እና ጃን በደል ቦካሳን የመሳሰሉ መሪዎች ያፈራችው አፍሪካ የአምባገነኖች መፈልፈያ ከሆነች ሰንብታለች፡፡ የመሪዎች ለውጥ ትልቅ ተስፋን ይዞ ቢመጣም ተተኪዎቹም የራሳቸውን መንገድ በመጠቀም ተመሳሳይ ሰቆቃ፣ ድህነት፣ ባርነትን የመጨረሻ ግባቸው አድርገውታል፡፡ የመንግሥታቱ ለውጥ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን፣ ሙስናን፣ የሀብት ብክነትን፣ ወደ ኋላ የሚጓዘውን የኢኮኖሚ ልማት አላስቀረም፡፡ ሌሎች ደግሞ የአፍሪካ ህዝቦች ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ባህላቸውና የአኗኗር ብሒላቸው የተነሳ ለመሪዎቹ አምባገነንና ለራስ ክብር፣ ኃይልና ሀብት ብቻ የሚጨነቁ መሆን አስተዋፅኦ የጎላ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ መልካም አስተዳደር የመሪውን ብቃት ብቻ ሳይሆን ተመሪውም ሊኖረው በሚችለው ምላሽ ይወሰናል ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ህዝቦቹ ብቃት ያንሳቸዋል በማለት ይከራከራሉ፡፡ እንደምክንያትም ከመሪዎቹ እጅ ውጭ ለጋሽ ሀገሮችና ዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎች ለመፍጠር የሞከሩት የአቅም ግንባታ ኘሮግራም ላይ የህዝቦቹ ንቁ ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑንን ያቀርባሉ፡፡ አቅም ግንባታው የህግ የበላይነት፣ የዲሞክራሲ ድጋፍ፣ የተጠያቂነትና የግልፅነት መስፋፋትን በተቋም ደረጃ ለማሻሻል ያለመ ቢሆንም ከመሠረተ ልማት እጥረትና ከእውቀት ማነስም ባሻገር ህዝቡ ለፖሊሲዎችና ለስትራቴጂዎቹ የሰጠው ምላሽ ደካማ ነበር፡፡ ይህን ያዩ ናቸው ቅኝ ገዢዎች ከአፍሪካ ከመውጣታቸው በፊት አፍሪካውያን እንዴት ራሳቸውን መግዛት እንዳለባቸው ማስተማር ነበረባቸው የሚሉት፡፡ አፍሪካ ለማደግ ሳንካ የሆነባት አስተዳደራዊ፣ የፍትህ ሰርዓትና የባለሙያ እጥረት ስላለበት ነው የሚለው ምክንያት አሳማኝ አይደለም፡፡ እነዚህን ያለአግባብ የሚጠቀመው የመንግሥት ኃይል የፈጠረው ሰበብ ነው፡፡ አፍሪካውያን ማስተዳደር ያውቃሉ፣ ፍትህ ምን እንደሆነ እንዴትና የት ለማን እንደሚሰጥም አይጠፋቸውም፡፡ አፍሪካውያን ባለሙያዎች በመላው ዓለም ብቃታቸውን እያሳዩ ነው፡፡ ነገሩ ግን መሪዎቹ የሚፈልጉት ሰቆቃን፣ ደምን፣ ረሀብንና ባርነትን እንጂ በጎውን አለመሆኑ ነው፡፡ መሪዎቹ የራሳቸውን ፍላጐትና ስሜት ለመከተል ሚሊዮኖች ቢጠፉ ደንታ የላቸውም፡፡ የአፍሪካ መሪዎች አንዳንዶች እንደሚያስቧቸው ደደቦች አይደሉም፡፡ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፖሊሲና ስትራቴጂያቸው ከምዕራባውያኑ የሚሻል ሁሉ አሉ፡፡ የኢኮኖሚ መርህና የአስተዳደር ስልትን በአግባቡ ያውቃሉ፡፡ ለጋሽ ሀገሮችን በእግራቸው ሥር የሚያስገቡትም በዚሁ ስልት ነው፡፡ የሚጠቅመው ብዙሀኑን ህዝብ እንጂ ባለሥልጣናቱን እንዳልሆነ ለማስረዳት የሚሰንፍ ምላስም የላቸውም፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችንና መሪዎቹንም በህዝቦቹ አልያም በለጋሾቹ ፊት ቂል እና ሞኝ ለማድረግ በተደጋጋሚ አልተሳናቸውም፡፡ አፍሪካውያን ልሂቃን መሪዎች በግርግርና በኢኮኖሚ ድቀት የሚጠቃውን ሀገራቸውን ከውጭ መልካምና ያማረ እንዲመስልም ማድረግ ይችላሉ፡፡ ብዙዎችን ግራ የሚያጋባው ግን ህዝቦቹን ሳይጐዱ እነሱ መጠቀም አይችሉም ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ አሁን ያሉት የአፍሪካ መሪዎች ሀገራቱን የሚያዩዋቸው እንደ ግል ንብረታቸው ነው፡፡ ከዚህ ንብረት ለመካፈል የሚፈልግ ግለሰብም ሆነ ቡድን በጎሳ በመለያየትና በማጋጨት ካልቻሉ በቁንጥጫና ኩርኩም ድምፆችን ያፍናሉ፡፡ ወታደሩ፣ ሲቪሉ ወይም የፖለቲካ ፓርቲው ለዚህ ሀይል ሲሻኮቱ ሀገሪቷ አትረጋጋም፡፡ ይህ ደግሞ አጥብቀው የሚፈልጉት ነገር ነው፡፡ የህዝቦችን ጥያቄ በሀይል ያፈኑት መንግሥታት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዳይበረታ አልፎ አልፎ ህገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብና የመሠረተ ልማት ግንባታን በማድረግ ጥቂት ልሂቃንን ወደ ጉያቸው በመክተት የጥቅሙ ተጋሪ በማድረግ ዲሞክራት መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፡፡ መልካም አስተዳደር ጉልበትና ሥልጣንን ለህዝብ ጥቅም የመጠቀም ጉዳይ በመሆኑና ይህም ማህበረሰቡ ለእድገት አስተዋፅኦ እንድያደርግ ግለሰቡም የራሱን ህይወት ራሱ እንዲወስን እድል ስለሚሰጥ ለአፍሪካ መሪዎች የሚወደድ አይደለም፡፡ የራስ ኩራቱን ለውይይት የሚያቀርብ አፍሪካዊ መሪ ለማግኘት መጓዝ ያለብን ርቀት ረጅም ነው፡፡ እነዚህ ድህነትን ለማጥፋት ቁርጠኝነት የሚያንሳቸው አፍሪካዊያን መሪዎች የታሪክ ውጤቶች ናቸው፡፡ ዋነኛው የፖለቲካ ጉዳይ ከማህበረሰቡ አኗኗርም ሆነ ከኢኮኖሚው ግንባታ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ አፍሪካ የቅኝ ግዛት ድባብ ሳያጠላባት በፊት ወደ 10”000 የሚጠጉ ጎሳዎች የሚኖሩበት አህጉር ነበረች፡፡ ብዙዎቹ በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋም ሆነ በሀይማኖት የሚገናኙ አልነበሩም፡፡ በኮንጐ 6”000፣ በናይጄሪያ 250 የሚጠጉ ጎሳዎች ነበሩ፡፡ አንድ የነበረው ትልቁ የባኮንጎ ጎሳ ወደ ፈረንሳይ ኮንጎ፣ ቤልጅየም ኮንጎና ፖርቹጋል አንጎላ ተቆራረጠ፡፡ ሶማሊላንድ ወደ ብሪታኒያ፣ ጣልያንና ፈረንሳይ ተከፈለች፡፡ ከዛምቢያ ሎዚላንድ ብሔርና ከጋና አሻንቴ ብሔር ብዙም የሚስማሙ ባይሆኑም በጉልበት እንዲቀላቀሉ ሆኑ፡፡ በዛሬዋ ኡጋንዳ የሚገኙት የቡጋንዳ እና ቡንዬሮ ብሔሮችም ተመሳሳይ ነገር ነው የገጠማቸው፡፡ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሲደመደም የተሸናፊዋ ጀርመን ቅኝ ግዛቶች ወደ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጅየምና ደቡብ አፍሪካ ተዘዋወሩ፡፡ ታንጋኒካ ወደ ብሪታኒያ፣ ሩዋንዳና ብሩንዲ ወደ ቤልጅየም ሲተላለፉ ቶጎና ካሜሩን በብሪታኒያና በፈረንሳይ መካከል ተቃረጡ፡፡ አውሮፓውያን ግዛቶችን አንዴ ወደ ቀኝ አንዴ ወደ ግራ ማዘዋወርን እንዴ ትልቅ ጉዳይ ባይቆጥሩትም ዛሬ አህጉሪቷን የሚያምሳት የጎሳዎች የእርስ በርስ ጥላቻና ሽኩቻ ቅሪት መሆኑ ግን አልቀረም፡፡ አንዳንዴ በውል ሌላ ጊዜ በጦርነት ያገ”ቸው የነበሩትን ግዛቶች ለማስተዳደር የጎሳ አለቆችን አጋር ማድረጉ የአገዛዝ ስልት የነበረ ቢሆንም አንዱ ብሔር በሌላው የመከዳት ስሜት እየተሰማው ልዩነቱ ይሰፋ ነበር፡፡ በጣም ጥቂት ቁጥር የነበራቸው የቅኝ ገዢዎች ተወካዮች በሚሊዮን የሚቆጠረውን የአፍሪካን ህዝብ ለመግዛት የጎሳ አለቆችን መጠቀማቸው የውዴታ ምርጫ ሳይሆን ግዴታቸው ነበር፡፡ በገፍ የአህጉሪቱ የተፈጥሮ ሀብት ወደ አውሮፓ ከመጋዙ በፊት ሀገራቱ እራሳቸውን እንዲችሉ፣ አስተዳደራቸው እንዲዋቀር፣ ትምህርት እንዲስፋፋ፣ እድገት እንዲቀላጠፍ፣ ንግድ እንዲስፋፋ የተደረገው ጥረት አነስተኛ ነበር፡፡ መንገድና የባቡር ሀዲድ ያስፋፉ የነበሩት ቅኝ ግዥዎች ህግና ስርዓትን በማጠናከር ግብር መሰብሰብን ግን አልዘነጉም ነበር፡፡ በዝግታ ነገሮችን እንዲፈፅሙ ያነሳሳቸው ምክንያት ቅኝ አገዛዙ ለመጪዎቹ በርካታ መቶ ዓመታት እንደሚቀጥል ያስቡ ስለነበር ነው፡፡ በቁጥር አነስተኛ የነበሩት የቅኝ ገዥዎቹ ተወካዮች እንደፖሊስ አለቃ፣ ዳኛ፣ ግብር ሰብሳቢ፣ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ፣ ልዩ ተወካይና የበላይ ተመልካች ያገለግሉ ነበር፡፡ ይህን ማድረግ ሲያቅታቸውም ተመሳሳይ ሥልጣን ለጎሳ አለቃው ይሰጡ ነበር፡፡ ይህ ለእንግሊዝ የተዘዋዋሪ ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ ነበር፡፡ የጎሳ አለቆቹ ተግባር በአብዛኛው ነዋሪ በበጎ ጎኑ የሚታይ አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹ ከቅኝ አገዛዝ በፊት ባህላዊ መሪ የነበሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ግን በአገልግሎትና በታች የታዛዥነታቸው የተፈጠሩ አዲስ የአመራር ልሂቃን ናቸው፡፡ እነዚህን ህዝቡ በጣም ይንቃቸው ነበር፡፡ በተለይም በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ የተማሩት ልሂቃን ያደርጉት የነበረው ትግል የጎሳ አለቆቹን ሥልጣን መወሰድ እንጂ የጭቁኑን የአፍሪካ ህዝብ ኑሮ መለወጥን አልነበረም፡፡ ምናልባትም በጣት የሚቆጠሩ ብሔራዊ ስሜት የነበራቸው መሪዎች ነበሩ፡፡ የሰሜን ናይጄሪያ ታዋቂ መሪ የነበረው አቡበከር ታፈዋ በለዋ በ1948 እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ “ከ1914 ጀምሮ ብሪታኒያ ናይጄሪያን አንድ ለማድረግ ትሞክር ነበር፡፡ የናይጄሪያ ህዝቦች ግን ከታሪክም አንፃር ራሳቸው የተለያየ መነሻ ያላቸው፣ በሀይማኖትና በእምነት እንዲሁም በባህል የማይገናኙ ከመሆናቸው አንፃር አንድ ለመሆን ፈፅሞ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ አንድነት የእንግሊዝ የፈጠራ ሥራ ነው” ከበለዋ የተለየ አቋም ያለው የዩሩባ ጎሳ መሪና የምዕራቡ ናይጄሪያን ፖለቲካ ከ1940ዎቹ ጀምሮ ለ3ዐ ዓመታት በበላይነት ይመራ የነበረው ኦባፌሚ አዎሎዎ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለየ አቋም አልነበረውም፡፡ “ናይጄሪያ የሚባል ሀገር የለም፡፡ አንድ ምድራዊ ገፅታ ብቻ ነው፡፡ “እንግሊዞች”፣ “ዌልሶች” እና “ፈረንሳዮች” በሚለው ፅንሰ ሀሳብ ደረጃ “ናይጄሪያውያን” የሚባሉ ህዝቦች የሉም፡፡ ናይጄሪያውያን በናይጄሪያ ክልል የሚኖሩትን ከማይኖሩት የምንለይበት ስም ነው” በማለትም ሀሳቡን ያብራራል፡፡ ይህ የማንነት ጥያቄ፣ የብሔርና ብሔረሰቦች መብት፣ የሀገር ግንባታ ጉዳይ የሚያጨቃጭቀው፣ የሚያጋጨውና ደም የሚያቃባው ናይጄሪያን ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የሌሎች በርካታ የአፍሪካ ሀገራትና የመሪዎቿ ጉዳይም ነው፡፡ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አፍሪካን የለወጣት በሀይለኛው ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በጦርነቱ በወታደርነት አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ከብሪታኒያ ጦር ጋር ብቻ 374”000 ወታደሮች አብረው ዘምተዋል፡፡ በተለይ ወደ ህንድና በርማ የዘመቱት ወታደሮች እነዚያ ድሀና ያልተማሩ ህዝቦች ለነፃነት ትግል የነበራቸውን ፅኑ አላማ በማየት ትምህርት ቀስመው ነው ወደ አህጉራቸው የተመለሱት፡፡ በ1941 የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቼርችል እና የአሜሪካው ኘሬዚዳንት ቲዎዶር ሩዝቬልት የአትላንቲክ ቻርተርን ሲያረቁ የሁሉንም ህዝቦች የራስ አገዛዝ መብትን የደገፉ ቢሆንም በቸርችል አእምሮ የሚመላለሰው ሀሳብ ግን ጉዳዩ ለአፍሪካ ቅኝ ግዛቶች ሳይሆን ለአውሮፓ ቅኝ ግዛቶች ብቻ ተፈፃሚ እንደሚሆን ነው፡፡ ሩዝቬልት ከዚያም በኋላ ቢሆን አፍሪካ ነፃ እንድትሆን የወተወተ ሲሆን ይህ የአሜሪካ ጫና አፍሪካ በፍጥነት ነፃ እንድትወጣ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ ዓለም ለሰብአዊ መብት መከበር በተነሳበት ወቅት የአፍሪካ የተማሩ ልሂቃን የአገልግሎት ልምዳቸውን፣ ሀሳባቸውን፣ ብቃታቸውን፣ የሙያ ልምዳቸውን እንዲሁም የነገ ብሩህ ተስፋቸውን በመያዝ ሀገራቸውን በአዲስ መልክ ለማቋቋምና ለመምራት ያገኙትን ቀዳዳ ሁሉ መጠቀም ጀመሩ፡፡ የሥራ አጥነትን፣ የዋጋ መናርን፣ የመጠለያ እጦትን፣ አነስተኛ ደመወዝን እና የሸማቹን እጥረት ጉዳይ በድፍረት በማንሳት አዲስ ዓይነት የነፃነት እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ ጭቆና ያንገፈገፈው ህዝብም ድጋፉን አበረከተላቸው፡፡ በ1945 ግብፅ፣ ላይቤሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና ኢትዮጵያ ብቻ ነፃ የነበሩ ሲሆን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በ1963 አቋቁመው መላው አፍሪካውያን ነፃ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን የነፃነት ትሩፋት ሳይታይ 5ዐ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ከላይ ያየነው የተጠላለፈ ችግር ጥቅም ለማግኘት ሲሉ አፍሪካዊያን መሪዎች ቀጥለውበታል፡፡ ልዩነቱም ሆነ አንድነቱ ያለ እነሱ ቡራኬ የሚሆንም አልሆነም፡፡ በፍቅርና በሰላም የሚኖረው ህዝብ ከመሬት ተነስተው “እኛ ታሪካዊ ጠላት በመሆናችን . . . “ በማለት ያለፈ ታሪክን የተረሳ በደልን ከአያት ቅድመ አያት ወደ ልጅ በማውረድ ፣የተቀየሰ፣ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ ከግለሰቦች የሀሳብ ልዩነት ወደ ብሔርና ብሔረሰብ ጥል ተቀይሮ የተከበረ የሰው ልጅ በየጎዳናው ታርዶ ሲያዩ አንጀታቸው ቅቤ ይጠጣል፡፡ አውቆ አጥፊዎች የሚፈፅሙትን ይህን አሰቃቂ ጨዋታ ላለማየት የአህጉሪቷ ንፁሀን ምሁራን ስደትን ተቀዳሚ የህይወታቸው ግብ አድርገውታል፡፡ የቀደሙት ቅኝ ገዢዎች ከአሁኖቹ ቅኝ ገዢዎች ጋር እስከተስማሙ ድረስ የህዝቦቿን ጩኸት ሰምቶ ዘላለማዊ መፍትሔ የሚያመጣ እስካልተፈጠረ መሪዎቹ ጆሯቸው ላይ የተኙ በመሆናቸው ፣አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም፣ እንዲሉ ለውጥ ለማምጣት አስቸጋሪ ነው፡፡ በሲቪል ማህበረሰቡ፣ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በህዝቡ ንቃተ ህሊና መዳበርና ጫና ማሳደር የተነሳ በአፍሪካ ብልጭ ያለው የዲሞክራሲ ባህል ይንቦገቦግ ይሆን? በሠለሞን ጐሹ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |