Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow የዳርፉር ቀውስ
የዳርፉር ቀውስ Print E-mail
Wednesday, 27 February 2008
በዳርፉር ቀውስ ላይ ለሁለት ቀናት ኮንፍረንስ ያካሄዱ አፍሪካውያን ምሁራን ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ለቀውሱ የሰጠው ትኩረት አናሳ ነው በማለት ወቅሰዋል፡፡ በጥቁር አፍሪካውያኑ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈፀመ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል ከሌሎች አገሮች ጋር በመሆን ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው የዳርፉር ኮንፍረንስ ላይ በርካታ ምሁራን የጥናት ጽሑፋቸውን አቅርበዋል፡፡ በኮንፍረንሱ የአዲስ አበባ ፕሬዚዳንት ፕ/ር አንድሪያስ እሸቴን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የጥናት ጽሁፋቸውን ካቀረቡት መካከል ባለፈው ሳምንት በሸራተን አዲስ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጎቴ ኢንስቲትዩት (በጀርመን ማዕከል”ና በሌሎች ቦታዎች ስለአፍሪካ ታሪክ፣ ግጭቶች፣ ማንነት፣ ዲሞክራሲ ወዘተ. በመሳሰሉት ላይ ከተለያዩ ምሁራን ጋር ውይይት ሲያደርጉ የቆዩት ኡጋንዳዊው ፕ/ር ማህመድ ሙንዳኒ ይገኙበታል፡፡

ፕ/ር ማህመድ በዳርፉር ቀውስ ላይ "Regionalization and Internationalization of Darfur Crises" በሚል ርዕስ ንግግር አድርገዋል፡፡ ፕ/ር ማህሙድ የዳርፉርን ሁኔታ “አጠቃላይ የሱዳን የፖለቲካ ቀውስ” ብለውታል፡፡ የዳርፉር ቀውስ የእርስ በርስ ግጭት ብቻ ሳይሆን የሱዳን መንግሥት የአስተዳደር ችግር ነው፡፡ የሱዳን መንግሥት በአካባቢው እየተፈፀመ ባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፍታት ከመንቀሳቀስ ይልቅ ራሱ የጃንጂዊድ ሚሊሻዎችን እየደገፈ በቀውሱ ተሳታፊ መሆኑ አስገርሟቸዋል፡፡

የጃንጂዊድ ሚሊሻዎች የዓረብ ዝርያ ያላቸው ሲሆኑ ምንጫቸው በውል ባይታወቅም ከቻድናከሊቢያ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ጃንጃዊዳች በዳርፉር ጥቁር ሕዝቦች ላይ የሚፈፅሙት ኢሰብዓዊ ጥቃት የቀውሱ ዋና መንስኤ እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በፈረስ ታግዘው ጥቃት የሚፈፅሙ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቁ  በጥቁር የዳርፉር ሕዝቦች ላይ ወረራ ያካሂዳሉ፣ ይዘርፋሉ፣ በሴቶች ላይ የወሲብ ጥቃት ይፈፅማሉ፣ ያሳድዳሉ አስፈላጊ ሲመስላቸውም ይገድላሉ፡፡ የሱዳን መንግሥት ለቀውሱ የሚሰጠው ምላሽ ምን ይመስላል?

የሱዳን መንግሥት ከምሥራቅ፣ ከደቡብና ከማዕከላዊ ሱዳን (ዳርፉር) በሚነሱ የተለያዩ ችግሮች የተወጠረ ነው፡፡ ለዚህ የዳርፉር ቀውስ የሚሰጠው የሃይል ምላሽ ነው፡፡ በዳርፉር ያለው ችግር የተወሳሰበ ከመሆኑ የተነሳ በአካባቢው እስካሁን ከ13 በላይ ዓማፂ ቡድኖች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እነዚህን ለመመከት የካርቱም መንግሥት ሁለት መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ አንደኛው ዓማጺዎች በሚላቸውና እነሱን ይደግፋሉ በሚላቸው ላይ እርምጃ መውሰዱ ነው፡፡ በተለያየ ወቅት ከቻድና ከሊብያ እየተነሱ በአካባቢው ሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ለሚያካሂዱ የጀንጂዊድ ሚልሻዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው (በሕይወት እያሉ) የአካባቢውን ችግር በቅርብ ይከታተሉ የነበሩት ፕ/ር ክንፈ አብርሃም ተናግረው ነበር፡፡

የካርቱም ማዕከላዊ መንግሥት የውጭ ሃይሎች (ሰላም አስከባሪዎች) ወደ አካባቢው እንዳይሰማሩ ሲቃወም ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ከአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ ተጥሎበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ከብዙ ጥረት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ሕብረት ጥምር ወታደሮች እንዲሰማሩ ሱዳን ፈቅዳለች፡፡ ይህንን የሱዳን መንግሥት እርምጃ ብዙዎች በጥርጣሬ ዓይን ይመለከቱታል፡፡

የዳርፉር የእርስ በርስ ግጭት እ.ኤ.አ በ1950/60ዎች እንደተጀመረ የተናገሩት ፕ/ር ማህሙድ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ አነስተኛ በመሆኑ ምላሽ ተችተዋል፡፡ የምዕራብ አገሮች በሱዳን ዳርፉር ላይ የሚከተሉት ፖሊሲ ከራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም አንፃር እንጂ ለችግሩ መፍትሄ ለማስገኘት አልመው እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በምዕራቡ ዓለምና በተለይ ደግሞ በአሜሪካ ላይ ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ቻይናና ሩስያም እንዲሁ፡፡

ቻይና በከፍተኛ ደረጃ ነዳጅ የምታገኘው ከሱዳን ነው፡፡ በአካባቢው የምትከተለው ፖሊሲ ይህንን ጥቅሟን በሚያስጠብቅ መልኩ ነው፡፡ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት (Veto power) ካላቸው አገሮች መካከል የሚጠቀሱት ቻይናና ሩስያ ድርጅቱ በሱዳን ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዳይወስድ ይህንን መብታቸውን ለዚህ ይጠቀሙበታል፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ ከመጮህ የዘለለ እርምጃ መውሰድ አልቻለም፡፡  

ፕሮፌሰሩ በዓለማችን ላይ አሉ ከሚሉዋቸው ችግሮች ሁሉ የዳርፉር ቀውስ የላቀ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ የአውሮፓ ሕብረትም ለዚህ ችግር ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በቻድ ወታደሮችን ማስፈር መርጧል፡፡ የአሜሪካ መንግሥትም ለኢራቅ ቅድሚያ መስጠቱ ለምን ይመስላችኋል? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ኢራቅ ለአሜሪካ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም ታስገኛለች፡፡

ፕ/ር መሐመድ ከማንኛውም ችግር በላይ አፍሪካውያን ስለ ዳርፉር ማውራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ምክንያቱም የዳርፉር ችግር ከኤድስም የላቀ ችግር ነው ይላሉ፡፡ በዳርፉር ሰው እየተሰቃየ ሳይሆን እየጠፋ ነው ብለዋል፡፡

ፕ/ር ማህሙድ የደቡብ ሱዳን ችግርና ዳርፉርን በንፅፅር አይተዋል፡፡ የደቡብ ሱዳን ችግር የፖለቲካ ችግር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በዳርፉር በየቀኑ የሚፈናቀለው፣ የሚገደለውና የሚሰደደው የሕዝብ ቁጥር እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ በሰው ላይ እየተፈፀመ ያለ ከባድ ሰብዓዊ ጥሰት ብለውታል፡፡

የችግሩ መንስኤ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት እንደሆነ የሚናገሩት ፕ/ር መሐመድ፣ አገሪቱን ለከፋፍሉ መግዛት እንድትመቻቸት በዓረቦችና በጥቁሮቹ መካከል እንግሊዝ ቀብራው የሄደችው ቦንብ እየፈነዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፕ/ር ማህሙድ ለችግሩ መፍትሄ ይሆናሉ ያሏዋቸውን በሶስት ደረጃ አስቀምጠዋል፡፡ አገራዊ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ መፍትሄዎች ናቸው፡፡ አገራዊ መፍትሄ ያሉት በአንድ ወገን የስልጣን ማሻሻያ ማድረግ ሲሆን በሌላ በኩል የአካባቢው መሬትና አስተዳደር ማሻሻያ ማድረግ ነው፡፡

ሌላኛው የቀጠና ወይም አህጉራዊ መፍትሄ ያሉት አፍሪካውያን ለችግሩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ነው፡፡ ዓለም ዓቀፋዊ መፍትሄ ያሉት ሀያላን አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ቅድሚያ ሰጥተው በሱዳን መንግሥት ላይ አስፈላጊ ጫና እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል፡፡

ምሁራንም ለችግሩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ሰፊ ጥናት እንዲያደርጉና ሁልጊዜ ስለዳርፉር እንዲያወሩ አሳስበዋል፡፡

ከአፍሪካ ጥናትና ምርምር ማዕከል የመጡ ፕ/ር ሳላሕ ሐሰን በበኩላቸው “ሐሮቂሽቃሸ the Conflict Darfur and the crises of Governance in Sudan" በሚል ርዕስ የጥናት ፅሁፋቸውን አቅርበዋል፡፡

ፕ/ር ሳሊሕ ችግሩ ትልቁ የአፍሪካ የእርስ በርስ ግጭት እንደሆነ በመጥቀስ ቀውሱ ከምዕራብያውያንና ከተቀረው የዓለም ክፍል ዕይታ አንፃር ተመልክተውታል፡፡ ምዕራባውያን ሲጀመርም እነሱ የፈጠሩት ችግር እንደሆነ፣ አሁንም እያባባሱት የሚገኙት እነሱ በመሆናቸው ወቅሰዋል፡፡ ይህ ለችግር ፈጣሪዎቹ በግልፅ ሊነገራቸው እንደሚገባና በዓለም መስተጋባት ያለበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የምዕራብ መገናኛ ብዙኃን ለዳርፉር ቀውስ የሚሰጡት ሽፋን ውሱን እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ፕ/ር ሳሊሕ አባባል ለዳርፉር ቀውስ መፍትሄ ፍትሃዊ የሆነ የሐብትና የስልጣን ክፍፍል ከማድረግ በተጨማሪ የዳርፉር ጥቁር ሕዝቦች ሰብዓዊ ደህንነታቸው በሱዳን መንግሥት ሊጠበቅባቸው ይገባል፡፡

ፕ/ር ሳላሕ በሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት፣ በምሁራንና በሁሉም ዜጎች ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ዘመቻ ሊደረግ ይገባል ይላሉ፡፡ የዳርፉር ቀውስ የሱዳን አጠቃላይ የስርዓት ቀውስ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

በዳርፉር የእርስ በርስ ቀውስ ምክንያት ከ3 ሚሊዮን የማያንሱ  ሲፈናቀሉ እስከ 300ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል፡፡

ከረዥም ጊዜ ጥረት በኋላ የሱዳን መንግሥት፣ የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ህብረት ጥምር ወታደሮች በአካባቢው እንዲሰማሩ ስምምነት ላይ በመደረሱ በቅርቡ ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወደ አካባቢው ወታደሮች ከሚልኩ የአፍሪካ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን 5ሺ ወታደሮች እንደምትልክ ታውቋል፡፡

በየማነ ናግሽ
 
< Prev   Next >