Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow ውኃና ፍሳሽ በሕገ ወጥ ግንባታዎች...
ውኃና ፍሳሽ በሕገ ወጥ ግንባታዎች... Print E-mail
Wednesday, 27 February 2008
ውኃና ፍሳሽ በሕገ ወጥ ግንባታዎች ምክንያት ለወጪ ተዳረገ

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በ2000 ግማሽ የበጀት ዓመት ከሰጣቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች 94 ሚሊዮን 251ሺ 500 ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡ በውሃ መስመሮች ላይ ሕገወጥ ግንባታ እየተካሄደና የውሃ ግፊት ቫልቮች በሕገ ወጦች እየተዘጉና እየተከፈቱ መሆናቸው ተደረሰበት፡፡
የባለሥልጣኑ የማስታወቂያ እና ሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጌትነት ገሠሠ እንደገለጹት ባለሥልጣኑ በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከሰበሰበው 94 ሚሊዮን 251ሺ 500 ብር ውስጥ 12 ሚሊዮን 932ሺህ 483 ብር መሥሪያ ቤቱ ውዝፍ ሂሳቡን ለመሰብሰብ ባካሄደው  እንቅስቃሴ ነው፡፡

በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወር በውሃ ምርት እና ስርጭት ረገድ የታየው አፈጻጸም ከእቅዱ አንጻር ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፡ ይህም እለታዊውን የውሃ ምርት በ10ሺ ሜትር ኩብ አሳድጎታል ብለዋል፡፡ 43 ሚሊዮን 139ሺህ 301 ሜትር ኩብ ውሃ ለማምረት አቅዶ 44 ሚሊዮን 500ሺ 166 ሜትር ኩብ አምርቶ ማሰራጨቱንም አስታውቀዋል፡፡ ይህም ባለፈው አመት 230ሺህ ሜትር ኩብ የነበረውን እለታዊ የውሃ ምርት ወደ 240ሺህ ሜትር ኩብ እንዳሳደገው አስረድተዋል፡፡

አቶ ጌትነት እንዳስረዱት ባለሥልጣኑ ባለፉት ስድስት ወራት ለ5546 አዲስ ደንበኞች የውሃ መስመር የተቃጠለ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም 67 ኪሎ ሜትር መለስተኛ መስመር፣ 3.7ኪሎ ሜትር ከባድ የውሃ መስመር ዘርግቷል፡፡ 96 ከባድ እና ቀላል ጥገናዎችንም አካሂዷል፡፡ ነባር መስመሮችንም በመቀየር በአዲስ ተክቷል፡፡

በፍሳሽ ማስወገድ ዘርፍም 1 ሚሊዮን 506 ሺህ 169 ሜትር ኩብ ፍሳሽ በባለሥልጣኑ ፍሳሽ መስመር ተሰብስቧል፡፡ በባለሥልጣኑ እና በግል ተሽከርካሪዎች በጥቅሉ 227 ሺህ ሜትር ኩብ ፍሳሽ ተሰብስቦ ተወግዷል፡፡ በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት 1931 ሜትር አዲስ የፍሳሽ መስመር መዘርጋቱን እና ለ144 ደንበኞች አዲስ የፍሳሽ መስመር መቀጠሉንም ጠቁመዋል፡፡  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠሙ ያሉ ሕገወጥ ድርጊቶችን በተመለከተም ሲያብራሩ፣ አንዳንድ ሕገወጥ ግለሰቦች ጨለማን ተገን በማድረግ የውሃ ግፊት መስጫ እና መቆጣጠሪያ ጌት ቫልቮችን በመዝጋት እና በመክፈት የውሃ ስርጭትን የማዛባት ወንጀል እያካሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህም በፈረቃ የሚሰጥ የውሃ እደላ ከማዛባቱም በላይ ለውሃ ብክነትና ለመሣሪያዎች መጎዳት ምክንያት ሆኗል፡፡ ድርጊቱ ባለሥልጣኑ ፍትሀዊ የውሃ ስርጭት ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት ከማደናቀፉም በላይ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን ፓምፖች ሊያበላሽ ስለሚችል አሳሳቢ ድርጊት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በዚህ አይነት ህገወጥ ድርጊት ተሣታፊ የሆኑና ይህንን ድርጊት እየፈፀሙ ያሉት ግለሰቦች በአካባቢያቸው የሚገኘውን የውሃ ግፊት መስጫ መቆጣጠሪያ ጌት ቫልቭ በተደጋጋሚ በመዝጋት እና በመክፈት ከፈረቃቸው ውጭ ውሃ ለማግኘት የሚያደርጉት ሙከራ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሌሎች ነዋሪዎች ለውሃ እጥረት የሚዳረጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በተለይ በቀድሞው ወረዳ 24 ቀበሌ 16 ቀጣና 7 ክልል የሚኖሩ ማንነታቸው ያልታወቀ ሰዎች አዲስ ከተሰራው የረጲ ትምህርት ቤት ከፍ ብሎ የሚገኘውን የግፊት መስጫ መስመር በተደጋጋሚ እየዘጉ ከፈረቃቸው ውጭ ውሃ ለማግኘት እንደሚሞክሩ እንደተደረሰበት አመልክተዋል፡፡ ይህን መሰሉ ሕገወጥ ድርጊትም መስመሮችን በማጨናነቅ ማፈንዳቱን፣ የሮል ጉድጓድ ፓምፕም መስመሮቹ በመፈንዳታቸው ከመቃጠል መትረፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በድብቅ የሚፈፀመው ይህን መሰሉ ድርጊት የባለሥልጣኑን የውሃ ስርጭት የሚያዛባ፣ የብዙሀኑን ደንበኛ መብት የሚጋፋ እና በሀገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ስለሆነ መስሪያ ቤቱ በቸልታ እንደማይመለከተውና ጥብቅ ክትትል በማድረግ እርምጃ እንደሚወስድ የገለፁት ሃላፊው፡፡ እስካሁንም በሕገወጥ ድርጊት በተሳተፉ 15 የአዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ደንበኞች ላይ ቆጣሪ የማንሳት እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በመውሃ መስመሮች ላይ እየተካሄዱ ያሉ ሕገወጥ ግንባታዎች ባለሥልጣኑን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጉት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲስ በተመሰረቱ የመስፋፊያ አካባቢዎች ለምሳሌ 180 ሄክታር፣ ለቡ፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ መካኒሳና የመሳሰሉት አካባቢዎች ይህ ችግር ጎልቶ ይታያል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች ውሃ ያልነበረ በመሆኑ መስመር ለመዘርጋት እየተደረገ ባለ ሥራ ነዋሪዎች በሕጋዊ መንገድ ከያዙት ውጭ ድንበራቸውን ለመግፋት መስመሩን ወደአጥራቸው ውስጥ እያስገቡ የሥራ ማስተጓጎል ተፈጥሯል፡፡

“ለባለሥልጣኑ ከተከለለው የውሃ መስመርና ዲዛይን ውጭ ምንም ነገር ማድረግ ባይችሉም አንዳንድ ነዋሪዎች ድንበራቸውን በማለፍ አጥርና ግንባታ በመስራታቸው ባለሥልጣኑ መስመር ለመዘርጋት ሲነሣ ስራውን ያስተጓጉላል፡፡ ሰው ግቢ ገብቶ መቆፈር ስለማይቻልም ስራውን በአግባቡ ለማከናወን እንቅፋት ሆኖበታል” በማለት አቶ ጌትነት ገልፀዋል፡፡

የረር 180 ሄክታር በመባል በሚጠራው አካባቢ መስመር የተዘረጋላቸውና ቆጣሪ የገባላቸው ጭምር መስመሩን ወደግል ግቢያቸው አስገብተው በማጠር ኩሽና፣ መፀዳጃ ቤት እና የመሣሠሉትን ገብተውበታል፡፡ ይህም ለጤናም ሆነ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡

ይህ ድርጊት የሌሎችን መብት የሚገድብ በመሆኑም ሊታለፍ የሚችልበት ምክንያት ስለሌለ 180 በሚባለው አካባቢ በእንዲህ አይነት ድርጊት የተሰማሩ 15 ግለሰቦች ቆጣሪያቸውን እንዲነሳ መደረጉንና ሕገወጥ ግንባታው ካነሱ በኋላ ግን ቆጣሪው እንደተመለሰላቸው አቶ ጌትነት አስረድተዋል፡፡

አዲስና በዲዛይን የተሰሩ አካባቢዎች እንዲህ አይነት ድርጊት መፈፀሙ ያሳዝናል ያሉት አቶ ጌትነት ገርጂ የሚገኙ የመኖሪያ ቤቶች (ነጫጭ ቤቶች) የተከሰተው ድርጊት በምሣሌነት አንስተዋል፡፡ እነዚህ ቤቶች የኪራይ ቤቶች ድርጅቶች ከ20 ዓመት በፊት ሲሰሩ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የውሃ መስመሮች ሲሰሩ ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ ብዙዎቹ መፀዳጃ ቤት ሰርተውበታል፡፡ ከውሃና ፍሳሽ ጋር አገናኝተውታል ከፍተኛ ውሃ ይባክናል፡፡ መጠገን አልታቸለም ነበር፡፡

ሕገወጥ ግንባታው ከመፀዳጃና ከፍሳሽ ጋር የተናኘ በመሆኑ ይህ ከፍተኛ የጤና ችግር የሚያመጣ መሆኑን ተገንዝቦ ባለሥልጣኑ የውሃ ስርጭቱን አቋርጦ አዲስ መስመር ተክቷል፡፡ ያንን ራሱ ቤት ማስፈረስ ስላልተቻለ ከ1ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አዲስ መስመር ተዘርግቷል፡፡
በለቡ አካባቢም ተመሣሣይ ችግር መፈጠሩን የጠቆሙት አቶ ጌትነት በዚህ አካባቢ 350ሺሚ.ሜ ስፋት ባለው ትልቅ የውሃ መስመር ላይ ሳይቀር ሕገወጥ ግንባታ ተካሄዷል፡፡ እንዲህ አይነቱን ድርጊት በፈፀሙት ላይም ግንባታዎችን እንዲያነሱ በሕግ ጭምር እንዲጠየቁ አመልክተዋል፡፡

የከተማዋን የውሃ ችግር ለማቃለል እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዘርፉም ከ168 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን የውሃ ምርቱን በቀን በ46”000.00 ሜትር ኩብ በማሳደግ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥብ ያስችላሉ ተብሎ ይታመናል፡፡

ቁፋሮአቸው በመካሄድ ላይ ካሉት ጉድጓዶች መካከልም የሃያ ስምንቱ ቁፋሮ በመንግሥት በጀት የሚካሄድ ነው፡፡ የጉድጓድ ቁፋሮው በሁለት የሥራ ተቋራጮች እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው እስካሁን የአምስቱ ቁፋሮ መጠናቀቁንም አቶ ጌትነት አመልክተዋል፡፡ የቀሪዎቹ ጉድጓዶች ቁፋሮም በቅርብ ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅና የእነዚህን ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ የመስመር ዝርጋታ፣ ፓምፕ ተከላ እና ተዛማጅ ሥራዎችን ለማካሄድም ከመንግሥት በጀት 143 ሚሊዮን 110ሺ ብር በጀት መመደቡንም ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ የሃያ አምስቱ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ የሚካሄደው ከአለም ባንክ በተመደበ 23 ሚሊዮን ብር በጀት ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ቁፋሮአቸው ከተጠናቀቀው 32 ጉድጓዶች መካከልም የሃያ አራቱ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች የቅየሰ ሥራ ተጠናቋል፡፡ የማከፋፈያ እና የፓምፕ ተከላ ሥራቸውም በያዝነው በጀት ዓመት መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ገልጸዋል፡ ይህም የከተማውን የውሃ አቅርቦት በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በዚህ ዓመት ቁፋሮአቸው እንደሚጠናቀቅ ከሚጠበቁት 28 ጉድጓዶች እና ባለፈው ዓመት ከተጠናቀቁት 30 ጉድጓዶች በቀን በድምሩ 46”380 ሜትር ኩብ (46 ሚሊዮን 380ሺን ሊትር) ተጨማሪ ውሃ የሚገኝ በመሆኑም ከ920ሺ በላይ ሕዝብን የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል አቶ ጌትነት ጠቁመዋል፡፡

ከከተማው የውሃ ፍላጎት አንፃር ምርቱን ለማሳደግ የገፈርሣ ግድብ ማጣሪያ ጣቢያ እድሳት ሥራ ከ174 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተከናወነ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ማለቂያ ላይ ሥራው ሲጠናቀቅ 7ሺህ ሜትር ኪዩብ ተጨማሪ ውሃ ስለሚያስገኝ በየቀኑ 30ሺህ ሜ.ኪ ማምረት ያስችለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩልም የአዲስ አበባን የውሃ ችግር ለመቅረፍ በባለሥልጣኑ እንዲሠሩ በእቅድ ከተያዙት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነውና ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ የተገመተው የፍሳሽ ኔትዎርክ ማስፋት ሥራ እስካሁን ድረስ ገንዘቡ ባለመገኘቱ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡

ጥናቱ ካለቀ አመታትን ያስቆጠረው ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊሆን ያልቻለው ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ የሚሆን ገንዘብ ባለመገኘቱ ነው፡፡

በዚህ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው አቶ ጌትነት ለፕሮጀክቱ የሚሆን ገንዘብ በማፈላለግ አሁንም በማፈላለግ ላይ ነን፡፡ ለዋናነት የተያዙትም የአለም ባንክና አውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ተጠቃሽ እንደሆኑ አስታውሰው ገንዘቡ እንደተገኘ ስራው የሚጀመር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህ ፕሮጄክት ሲጠናቀቅ አዲስ አበባ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት እንዲኖሯት ያስችላል ተብሎ ይታመናል፡፡  

በዳዊት ታዬ
 
< Prev   Next >