Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow የግልና የመንግሥት አጋርነት ፎረም...
የግልና የመንግሥት አጋርነት ፎረም... Print E-mail
Wednesday, 27 February 2008
ImageImage የግልና የመንግሥት አጋርነት ፎረም የተፋጠነ ውጤት አላመጣም

በግሉ ማኅበረሰብና በመንግሥት መካከል ያለውን አጋርነት ለማጠናከር ፎረም ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቢቆይም የተፈለገውን ያህል የተፋጠነ ውጤት አለማምጣቱ ተጠቆመ፡፡ ፎረሙን ማጠናከር እንደሚገባ፣ የሁለቱ አካላትም በጋራ መሥራት ታምኖበት መንግሥት የግሉን ዘርፍ ድርሻ የተቀበለበት ሁኔታ መኖሩም ተገልጿል፡፡
የ12ኛው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት አንድ አካል ሆኖ ባለፈው እሁድ በተከበረው ፣ኢትዮጵያን ሪፍሌክሽን ዴይ፣ ላይ ፣የግልና የመንግሥት አጋርነት በኢትዮጵያ፣ በሚል ርዕስ ጽሁፍ ያቀረቡት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አየነው ፈረደ እንዳሉት የግሉና የመንግሥት አጋርነት (Public Private partnership) በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን መተማመን ከማጠናከር ባሻገር የግሉን ሴክተር ንቁ ተሳትፎ በማበረታታት ዘላቂ ልማት ለማምጣት ያግዛል፡፡

በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ የአገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ ለመሥራት ከማስቻሉም በላይ በሁለቱ አካላት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ያስቀራል፡፡

በተጨማሪም የገበያና የተቋማትን ትስስር በማጠናከር የመዋቅርና ሌሎች ለውጦች እንዲደረጉ ያበረታታል፡፡ የመወያያ መድረክ (ፎረም) ለማዘጋጀትም ያግዛል፡፡

በኢትዮጵያ የግሉና የመንግሥትን ትብብር በተመለከተ ገለፃ ያደረጉት አቶ አየነው ፎረሙ በኢትዮጵያ መንግሥት ካመቻቸው የፖሊሲ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ እንደሆነ ሲጠቁሙ በምሳሌነት ያስቀመጡት አገሪቱ በቅርቡ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ከሚገኙ አገሮች ተርታ ለመመደብ ያላትን ብሔራዊ እቅድ /ራዕይ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ የአገሪቱ ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ የግሉን ሴክተር እንደ ኢንዱስትሪው ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር ማስቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ሌላ አጋርነቱን ማጠናከር የአገሪቱን የዘላቂ ልማት ለድህነት ቅነሳ ፕሮግራም ለመተግበር እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች አንዱ መንግስትንና የግሉን ሴክተር ለማቀራረብ መሆኑን አቶ አየነው ሲገልፁ የግሉና የመንግሥት አጋርነት ፎረምም በዚሁ ዓላማ መሠረት የተቋቋመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፎረሙ የታሰበለትን ያህል አለመሄዱን፣ በታቀደው መሠረት የፎረሙ ሴክሪታሪያት ሊመሰረት አለመቻሉን ሲጠቅሱ ያስቀመጧቸው ምክንያቶች ደግሞ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ወደ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ተለውጦ የሚዋቀርበት ሁኔታ መዘግየቱ እንዲሁም ጉዳዩ /ፎረሙን የማቋቋሙ ሃሳብ/ ለመንግሥትም ሆነ ለግሉ ሴክተር አዲስ መሆኑ የሚሉ ናቸው፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ1997 ዓ.ም የተቋረጠውን የምክክር ፎረም ለመቀጠል ከምክር ቤቱ ጋር እየተነጋገረ መሆኑንም አቶ አየነው ጠቅሰዋል፡፡

ፎረሙ ተጠናክሮ የታሰበውን ያህል እንዳይጓዝ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ በሁለት ወገን ያለ የአቅም ማነስ የዕውቀት እና የክህሎት እጥረት አንዱ እንደ መሆኑ ተገቢውን ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ ሥልጠና ለሁለቱም ወገኖች ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ዓለም ባንክ ፎረሙን ለማጠናከርና ሴክሪታሪያቱ እንዲቋቋም ለመርዳት የገባውን ቃል እንዲተገብር ማድረግ፣ የፎረሙ መዋቅር በብሔራዊ ደረጃ እንዲሆን በዞኖች ደረጃ እንዲቋቋም ማድረግ አቶ አየነው ያቀረቧቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ሲሆኑ በመጨረሻም ፎረሙን ለማጠናከር ከሁለቱም ወገኖች ፈቃደኝነት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

በመቀጠል ገለፃ ያደረጉት ከ12ኛው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ዋነኛ ስፖንሰሮች ከሆኑት አንዱ የሆነው ብሪቲሽ ካውንስል የቢዝነስ ዳይሬክተር አቶ ነፃነት ደመወዝ ናቸው፡፡ አቶ ነፃነት በዓለም 110 አገሮች የሚንቀሳቀሰውን፣ በኢትዮጵያም ላለፉት 50 የሚበልጡ ዓመታት የሰራው ድርጅታቸው የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትን ሊጠቅሙ የሚችሉ ፕሮግራሞችን በማካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የድርጅቱ ዓላማ ግለሰቦችና ድርጅቶች ለዕድገትና ራሳቸውን ለማብቃት የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ መሆኑን ሲያብራሩ በተለይ ፣ማኔጅመንት ኤክስፕረስ፣ እና ፣ኢንተር አክሽን ሊደርሺፕ፣ የተሰኙት ፕሮግራሞች ለንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ስለሚኖራቸው ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡

፣ሜኔጅመንት ኤክስፕረስ፣ የተሰኘው ፕሮግራም የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ከመሰል ባለሙያዎች ጋር ተገናኝተው ስለ ችግሮቻቸው/ስኬቶቻቸው የሚነጋገሩበትን መድረክ የሚያመቻችና በዚሁ አካባቢ የሚሰሩ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን በዘርፉ በተሻለ ሁኔታ ሊያሰለጥኑ የሚችሉባቸውን ሁኔታም ያለበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ፣ኢንተር አክሽን ሊደርሺፕ ፕሮግራም፣ ከሰሃራ በታች ባሉ 20 የአፍሪካ አገሮች የሚካሄድና እጅግ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠ ፕሮግራም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ብሪቲሽ ካውንስል በአጋርነት እንደሚያምን አቶ ነፃነት ሲጠቅሱ በዚህም ፣የግሉና የመንግሥት አጋርነት  በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን የንግድ ትርዒት ስፖንሰር ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አቶ የኢየሱስወርቅ ዛፉ “መንግሥት ልማት ለማምጣት ራሱን ብቸኛ አድርጎ ያስቀመጠበት ዘመን አብቅቷል” በማለት ንግግራቸውን ሲጀምሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመንግሥት ሥራ ብቻ ተደርጎ በሚቆጠረው የአገር መከላከል ሥራ ሳይቀር የግል ሴክተር ገብቶ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

፣ከ17 ዓመታት በፊት የተሰማራሁበት የግል ኢንሹራንስና ባንክ ሥራ ለግል መስጠቱ የማይታሰብ ነበር፣ ያሉት አቶ የኢየሱስወርቅ በአጋርነት መሥራቱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው በቅርቡ ከአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር የገቡበትን የትብብር ሥራ በምሳሌነት አቅርበዋል፡፡ ትብብሩ አስተዳደሩ ለምክር ቤቱ 110”000 ስኩዌር ሜትር ቦታ በሊዝ የሰጠበትና በጋራ ፣ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ንግድ ትርዒት ማዕከል፣ ለመገንባት የሚያስችል ነው፡፡

የግልና የመንግስትን አጋርነት በተመለከተም የኢትዮጵያ ሁኔታ በዕዝ ኢኮኖሚ ሥር የቆየ እንደመሆኑና የሽግግር ወቅት ላይ በመሆኑ አሁንም የኢኮኖሚው ብዙ አካል በመንግሥት የሚንቀሳቀስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አይነት አሰራር ወጥቶ የግሉ ሴክተር የበለጠ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ እንዲሆን መስራት አለብን ካሉ በኋላ ፣ውጤቱን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፣ ብለዋል፡፡

የግልና የመንግሥት አጋርነት ምክክር መድረክ (ዳያሎግ) በሁለቱ አካላት መካከል እንደ ድልድይ የሚያገለግል መሆኑን በተለይ የግሉ ሴክተር አባላት ሥጋቶቻቸውን ለመንግሥት የሚገልፁበት፣ ለጥያቄዎቻቸው መልስ ሊያገኙ የሚችሉበት መሆን እንደሚችል ሲጠቅሱ በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ንዑሳን ፎረሞች የነበሩት የምክክር ፎረሙ ከ1997 ዓ.ም በተለያዩ ምክንያቶች መቆሙን ተናግረዋል፡፡

በአትላስ ሪዞርት ሆቴል በተከበረው ፣ኢትዮጵያን ሪፍሌክሽን ዴይ፣ በንግድ ትርዒቱ ላይ ምርቶችና ድርጅቶቻቸውን ለማሳየት ከተለያዩ አገራት የመጡ ተሳታፊዎችን ጨምሮ የንግዱ ማኅበረሰብ አካላትና የብሪቲሽ ካውንስል ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡  

በቤተልሔም ነጋሽ
 
< Prev   Next >