Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 11th
Home arrow Sections arrow የተማሪዎችን ብቃት ለማሻሻል
የተማሪዎችን ብቃት ለማሻሻል Print E-mail
Wednesday, 27 February 2008
Image
ወጣት ቴዎፍሎስ መኮንንን
"ሳክርድ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪ" የተባለ ማኅበር አቋቁመው ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትምህርት ዘርፍ የበኩላቸውን ለማበርከት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሳክርድ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪ የወጣቶች ማኅበር ሀምሳ ሁለት አባላት ያሉት ሲሆን ሃያ ስድስቱ ወንዶች፣ ሀያ ስድስቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ የማኀበሩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በማስመልከት የቦርድ ዋና ሰብሳቢ የሆነውን ወጣት ቴዎፍሎስ መኮንንን አነጋግረነዋል፡፡
"ሳክርድ" የሚለው የማኅበሩ ስያሜ በእንግሊዝኛ ፣ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ፣ የሚል ትርጓሜ እንዳው የሚናገረው ወጣት ቴዎፍሎስ ማኅበራቸው ከፍትህ ሚኒስቴር ፈቃድ አግኝቶ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ከጀመረ አመት ከስድስት ወር እንደሆነው ገልፆልናል፡፡ ፈቃድ ካገኙ በኋላ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት፣ አባላትን በማቀናጀት በአጋርነት ሊሰሩ ከሚችሉ መሠል ተቋማት ጋር ግንኙነት ሲያጠናክሩ ቆይተዋል፡፡

ሳክርድ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪ የተቋቋመው በሰባት የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ያሉት አባላት ከተለያዩ የግልና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተውጣጡ ናቸው፡፡ ማኅበሩ የተቋቋመው ከታች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ባሉ ተቋማት የተማሪዎች ብቃትና ባህሪይ ላይ ትኩረት በማድረግ በትምህርት ዘርፍ ጥሩ እድገት የማምጣት ራዕይ ሰንቆ ነው፡፡

በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ተማሪዎች የሚያስመዘግቡት ውጤትና ትምህርታዊ ብቃት ከቤተሰብ፣ ከሚኖሩበት አካባቢና ከሚማሩበት ተቋም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ እነኚህን ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚንቀሳቀሱ ተቋማት መኖር በትምህርት ዘርፍ ለማምጣት የታሰበውን ውጤት በማሳካት ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ በመጀመሪያ ደረጃ፣ በሁለተኛ ደረጃና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በርካታ እድሎችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች በመኖራቸው ተማሪዎች በትምህርት ተቋማት የሚገጥሟቸውን ችግሮች በመፍታት ብቃታቸውን አጎልብተው ውጤታማ እንዲሆኑ እገዛ የሚያደርግ አካል እንደሚያስፈልግ ወጣት ቴዎፍሎስ ጠቁሟል፡፡ የተማሪዎች የትምህርት ብቃት ከባህሪይ ጋር ያለው ተዛማጅነት ከፍተኛ በመሆኑ ባህሪን ያማከለ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚጠቅምም አመልክቷል፡፡

ተማሪዎች በያሉበት የትምህርት ደረጃ የሚገጥሟቸውን ችግሮችና እድሎች ላይ ያተኮረ አንድ የውይይት መድረክና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን አነስተኛ ፕሮግራሞች ከማዘጋጀታቸው በስተቀር በፍትህ ሚኒስቴር ፈቃድ ካገኙ በኋላ ያለውን ረዥም ጊዜ ማኅበራቸውን በማጠናከር፣ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመመስረት እንዲሁም ማኅበራቸውን ሲያስተዋውቁ መቆየታቸውን አልደበቀም፡፡

ሳክርድ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪ ስድስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ስድስቱም ክፍሎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሴቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች መሆናቸውን በመጠቆም በማኅበሩ የሴቶችና የወንድ አባላት ቁጥር እኩል ከመሆኑ ባሻገር ተሳትፎአቸውም እኩል መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ማኅበሩ እየተንቀሳቀሰ ያለው አባላት በሚያደርጉት ወርሃዊ መዋጮ ሲሆን አባላት በሚችሉት ሰዓትና እንደ ፍላጎታቸው በማኅበሩ ውስጥ ያገለግላሉ፡፡ ሁለት ቋሚ ሠራተኞች ደግሞ በቋሚነት ይሰራሉ፡፡

እስከ አሁን የሳክርድ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪ አባል ለመሆን እንደ መስፈርት የሚታየው ማኅበሩ በተመሰረተበት አላማ ላይ መስማማት ቢሆንም ይህ ማኅበር ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው የወጣቶች የትምህርት ብቃት ላይ በመሆኑ የትምህርት ደረጃን እንደ አንድ የአባልነት መስፈርት ለማስቀመጥ እቅድ አላቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ወጣቶች በተለያዩ ቦታዎች በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ በመገኘታቸውና በተለያየ ዘርፍ እያደረጉ ባሉት እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡ ለወጣቶች ያለው አመለካከት የተሻለ እንደሆነ የሚናገረው ቴዎፍሎስ ወደተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት በሄዱበት አጋጣሚ ያገኙት ምላሽ አበረታች መሆኑን አመልክቷል፡፡ በተቃራኒው የሳክርድ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምን መምሰል ይኖርበታል? በሚለው እቅድ ለማዘጋጀት መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነባቸው አስረድቷል፡፡ የተለያየ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ማኅበራት (ወጣት ማኅበራትን) ጨምሮ ቢኖሩም የትምህርት ዘርፍ ላይ በትኩረት የሚሰሩ ማኅበራትን ማግኘት ለእነ ቴዎፍሎስ አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሰው ደግሞ የትምህርት ዘርፍ ላይ ትኩረት በማድረግ የተማሪዎችን የትምህርት ብቃት ለማሻሻል የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት በብዛት አለመኖር ነው፡፡

እነዚህ ወጣቶች ማርች ስምንት የሚከበረውን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ፣ከታላላቅ ሥራዎች ጀርባ ታላላቅ ሴቶች አሉ፣ በሚል ርዕስ የሴቶች ፌስቲቫል ለማዘጋጀት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ትምህርትን ጨምሮ በተለያየ መስክ ውጤታማ የሆኑ ሴቶች በፌስቲቫሉ ተገኝተው ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ለሚመጡ ሴቶች በአርአያነት የሚታይ ሥራቸውንና የስኬታቸውን ምስክርነት ያቀርባሉ፡፡ በተለያየ ደረጃ የሴቶችን ጉዳዮች ያነሱ፣ ወደፊትም ባሉበት ደረጃ የሴቶችን ድምጽ ለማሰማት ይችላሉ ተብሎ የታሰቡ ሴቶችን በአምባሳደርነት የመሾም ፕሮግራም እንደሚደረግም ይጠበቃል፡፡   

በምሕረት አስቻለው
 
< Prev   Next >