| ደብረ ሲና ለዳኛቸው ወርቁ አደባባይ አቆመች |
|
|
| Wednesday, 27 February 2008 | |
|
ለታላቁ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ መታሰቢያ በትውልድ አካባቢው በደብረ ሲና ከተማ የተሰራለት አደባባይ ባለፈው ቅዳሜ (የካቲት 15 ቀን 2000 ዓ.ም) በልደቱ ዋዜማ ተመርቋል፡፡
የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር (ኢደማ) ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ገብሬ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ከ22ሺህ ብር በላይ ወጪ ተደርጎለት በከተማው መሃል አውቶቡስ መናኸሪያ አካባቢ የቆመውን አደባባይ ያሠራው የወረዳው ምክር ቤት ነው፡፡ “የደራሲ ዳኛቸው ወርቁ የሚሌኒየም መታሰቢያ አደባባይ” የሚል ጽሑፍ ያረፈበት ለታላቁ ደራሲ መታሰቢያ የቆመው አደባባይ፣ ለሌሎች የላቀ አብነት ያለው መሆኑን ያወሱት አቶ ደረጀ፣ ኢደማ ብርሃን ፈንጣቂዎቻችን ተገቢ የክብር ቦታ እንዲያገኙ ለመዘከር የሺህ ዓመት አጀንዳ አሳትሞ ማውጣቱን ገልጸዋል፡፡ አስቀድመው ከልባቸው አቅንተው፣ ከመንፈሳቸው አስርፀው የጻፉልን አበውና እመው ደራስያንን ማመስገንና የደብረ ሲና ወረዳ ምክር ቤትን አርአያ መከተል እንደሚገባ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል፡፡ የካቲት 16 ቀን 1928 ዓ.ም ተወልዶ ኅዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም ያረፈው ደራሲና ምሁሩ ነፍስኄር ዳኛቸው ወርቁ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ልዩ ልዩ የፈጠራ ድርሰቶችንና ጽሑፎችን የጻፈ በመሆኑ በተለይ ደግሞ በዩኒቨርሲቲ መምህርነቱ፣ አደፍርስ በተባለው የአማርኛ ልብ ወለዱ፣ ዘ ሰርቲንዝ ሰን በተሰኘው የእንግሊዝኛ ልብ ወለዱ እና እምቧ በሉ ሰዎች በተባለው የግጥም መድበሉ፣ የጽሑፍ ጥበብ መመሪያ በተሰኘው መጽሐፉና ከዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ጋር ባዘጋጀው የአማርኛ ፈሊጦች በተማሪዎችና በሥነ ጽሑፍ ተመራማሪዎች ዘንድ የታወቀ መሆኑ የሥነ ጽሑፍ መምህር ዶክተር ፈቃደ አዘዘ በጥናታዊ ጽሑፋቸው ገልጸውታል፡፡ እንደ ዶ/ር ፈቃደ አገላለጽ “እስከዛሬ የታተሙትን የአማርኛ ልብ ወለዶች በቅርብ ስንመረምር የምናስተውለው ዓቢይ ነጥብ አደፍርስ በተለይ በአጻጻፍ ቴክኒኩ እመርታ የታየበት ልብ ወለድ መሆኑ ነው፡፡” የአደፍርስ አጀማመር ከብዙ “ታዋቂ” የአማርኛ ልብ ወለዶች ማለትም በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ዘንድ ከሌሎቹ የአማርኛ ልብ ወለዶች ይበልጥ ስማቸው ተደጋግሞ ከሚነሳው የተለየ ነው፡፡ ቁም ነገሩ የመለየት ብቻም አይደለም፡፡ የልዩነቱ ምንጭ በአማርኛ ልብ ወለድ ውስጥ ያልተለመደ የገለፃ ቴክኒክ በዚህኛው ውስጥ መታየቱ ነው፡፡ በሔኖክ ያሬድ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |