|
Wednesday, 27 February 2008 |
|
ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የዓባይ ቀን በዓባይ ተፋሰስ አገሮች ባለፈው ዓርብ (የካቲት 14 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም”. ተከብሯል፡፡
የኢትዮጵያ ውሃ ሀብት ሚኒስቴር ከአገሪቱ ጋር ትስስርና ባህላዊ ቁርኝት ካለው ዓባይ ይልቅ “የናይል ቀን” ብሎ ቢጠራውም፣ እኛ ግን ለብሔራዊ ክብረት ዓባይን መርጠናል፡፡ ክብረ በዓሉ “የዓባይ ትብብር ለሕይወታችን፣ ለመጪው ትውልድ” (ኮኦኘሬሽን ኦን ዘናይል፡ ሰስቴኒንግ አወር ላይፍ፣ አወር ፍዩቸር) በሚል መሪ ቃል ታስቧል፡፡ ስመ ገናናው ዓባይ ለሥልጣኔ፣ ለባህል፣ ለእምነት ታላቅ ምንጭና ብሔራዊ ኩራት ለመሆኑ ሁሉንም የሚያስማማ ነው፡፡ አዳምና ሔዋን የተፈጠሩባትን ኤዶም ገነት ከከበቡት ዓበይት አፍላጋት (ታላላቅ ወንዞች) አንዱ ዓባይ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህን አፈታሪክ በአርኪዮሎጂና በአንትሮፖሎጂ ጥናትም መደገፉም ይነገራል፡፡ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ በ”ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት” ዓባይን እንዲህ ይፈቱታል፡፡ “አባትያ፣ የወንዞች አባት ከአራቱ ወንዞች አንደኛው መዥመሪያው ወንዝ ታላቅ ዠማ፣ በግእዝ አዋልድ ፈለግ አባዊ ይባላል፡፡ እሱም በዳሞት ሰኮላ ሚካኤል ከሚባል አገር ከደንገዛ ተራራ ሥር ፈልቆ ጐዣምን ይከባል፣ ምንጩም ግሼ ዓባይ ይባላል፤ በጣና ላይ ዐልፎ ወደ ካርቱም ከዚያም ወደ ምስር ረግብፅሪ ይኼዳል፡፡ ፈሳሹም ሰማይ መስሎ ስለሚታይ ጥቁር ዓባይ ይሉታል፡፡” ገነትን የሚከቡት ወንዞች በምሥራቅ ኤፍራጥስና ጤግሮስ፣ በምዕራብ ኤፌሶንና ግዮን መሆናቸው በድርሳናት ተጽፏል፡፡ ግዮን ጥቁር ዓባይ ነው የሚሉ ቢኖሩም እንደ አለቃ ደስታ አገላለጽ ዓባይን ኤፌሶን ሲሉት በደቡባዊ አፍሪቃ አካባቢ ኒያንዛ ከሚባል ሐይቅ የሚወጣው ነጭ ዓባይን ግዮን ብለው ይጠሩታል፡፡ በውጮች ዘንድ የኢትዮጵያ ዓባይ ከጣና ሐይቅ የሚነሣውን “ብሉ ናይል” ከማዕከላዊ አፍሪካ የታላላቅ ሐይቆች አካባቢ የሚወጣውን “ኋይት ናይል” ሲሉት ሁለቱ ወንዞች ሱዳን ካርቱም ተገናኝተው ወደ ግብፅ በሚያደርጉት ጉዞ “ናይል” በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ፡፡ ናይል ጥንተ ቃሉ ከግሪክ “ኒሎስ” የተገኘ ሲሆን፣ ፍችውም የወንዝ ሸለቆ ማለት ነው፡፡ ለግብፃውያን ዓባይ ህይወታቸውም መሠረታቸውም ነው፡፡ በጥንታዊው ታሪክ ጸሐፊ ሔሮዶቱስ እንደተገለጸው “ግብፅ የዓባይ ስጦታ” በመባል ትታወቃለች፡፡ በጥንታውያን ግብፃውያን ውሃ ኡዋት (Uat) ተብሎ ሲጠራ፣ ፍችውም አረንጓዴ ማለት ነው፡፡ ውሃና አረንጓዴ ተመሳሳይነት እንዳላቸውና የነፍስ መገለጫም እንደሆነ በአፈ ታሪክ ይነገራል፡፡ ሊዶር ከሮቭኪን፣ የጥንቱ ዓለም ታሪክ ባሉት መጽሐፋቸው፣ ግብፃውያን የዓባይ ወንዝ ከየት እንደሚመነጭ ባለማወቃቸው የዓባይ አምላክ ከሰማይ በባልዲ እየቀዳ ቁልቁል ወደ መሬት እንደሚያንቆረቆርላቸውና የጐርፍ ማጥለቅለቅ የሚያጋጥመውም የሚንቆረቆርላቸው የውሃ መጠን ሲጨምር እንደሆነ ያምኑ ነበር፡፡ በመሆኑም ማሳቸውን ያለመልምላቸውና ህይወታቸውን ይጠብቅላቸው ዘንድ ዓባይን ዘወትር ይማፀኑት፣ ምስጋናቸውን ይዘምሩለትና ውዳሴያቸውን ያቅራሩለት ነበር፡፡ ለዓባይ ወንዝ ይዘመር ከነበረው መዝሙር ከፊሉ እነሆ” ለግብፅ ተሐድሶ ልትሰጥ ለመጣኸው ዓባይ፣ ክብርና ምስጋና ይገባሃል፣ ስትዘገይብን ሕይወት ሁሉ ቀጥ ይላል፣ ስትቆጣ ነጐድጓድ ያስገመግማል፡፡ ዓባይ ከተፍ ሲል መሬት በደስታ ትፈካለች፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ በፍሥሐ ይፈነድቃሉ፡፡ የተትረፈረፈ ሲሳይ የምትመግበን አንተው ነህ፣ የተዋቡ ነገሮችን ሁሉ ታቀርብልናለህ፣ ወጣቶችና በደስታ እየዘመሩ፣ ንጉሣችን ዓባይ እንኳን ደህና መጣህ ይሉሃል፡፡ ትንሣኤ ያገኘው አምላክ አፈታሪክ ከዓባይ ጋር የተያያዘ ወግ አለው፡፡ በግብፅ በበጋ ወራት ሞቃት ነፋስ ለሃምሳ ቀናት ያለማቋረጥ እየነፈሰ አካባቢውን ሁሉ ድርቅና ቸነፈር ያላብሰዋል፡፡ ተፈጥሮ ቀጥ ፀጥና ለጥ ያለች ትመስላለች፡፡ ከዚያ በኋላ ከባሕሩ የሚነፍሰው ቀዝቃዛ አየርና የዓባይ ጎርፍ ለአካባቢው አዲስ ሕይወትና ብሩህ እፎይታ ይለግሳሉ፡፡ ተፈጥሮ ትንሣኤ እንዳገኘች ሁሉ ዳግም ሕያው ትሆናለች፡፡ ዓባይ ከኢትዮጵያውያን ሕይወት ጋር ጥልቅ ትስስር አለው፡፡ በተለይ የታላቁ ወንዝ መጋቢ በሆኑት አካባቢዎች የሚኖረው ኅብረተሰብ ከእምነቱ ጋር የሚያያይዘው ብዙ ነገር አለው፡፡ ለዓባይ የንግሥ በዓል ሁሉ የሚያደርጉለት አሉ፡፡ ከተረትና ምሳሌ ጋር አቆራኝተው ሕይወታቸውንም ይገልጹበታል፡፡ ይሔሱበታልም፡፡ በአረንጓዴው ዘመቻ ወቅት “ምድሪቱን አረንጓዴ እናለብሳታለን” የሚለውን አብዮታዊ ጥሪ የሰማ አንድ ገበሬ “አንተ የአገሬ ውሃ አረንጓዴ አትልበስ፤ እጠጣህ ይሆናል ምናልባት ስመለስ” ብሎ መግጠሙ ይነገራል፡፡ ከዓባይ ጋር የተያያዙ ምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ ዘይቤዎች አያሌ ናቸው፤ ኑሮን ይገልጣሉ፡፡ “ውሃ ቀለብ ሆኖ ሰውን ካሳደረ፣ ዓባይና ጣና አገሬ ነበረ፡፡” የኢትዮጵያን ዓባይ ከነጭ ዓባይ ለመለየት ዓባይ ጣና ተብሎ ይጠራል፡፡ የዓሳ ማኅደር ስለሆነችው ጣና፣ ድምፀ መረዋው አሰፋ አባተ “ዓሳ አበላሻለሁ ዓባይ ዳር ነው ቤቴ፣ ዶሮ መረቅማ ከወዴት አባቴ” ብሎ ያንጎራጎረው ይጠቀሳል፡፡ ሌላው ድምፃዊውም ፀሐዬ ዮሐንስ ወዳጁ ያለችበት ስፍራ ዓባይ ዳርቻ መሆኑን የሚያጠይቅበት ሥራው በብዙዎች ልቡና አለ፡፡ “ዓባይ ነው አሉኝ ቤቷ ዓባይ ነው አሉኝ ልጫን ፈረሴን እኔን ልቤ ዕረፍት ያግኝ” ስለዓባይ በተረትና ምሳሌ ከተነገሩት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል፡፡ ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል፡፡ የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው፡፡ ዓባይ የተጸውዖ ስም ኾኖ ለሁለቱ ጾታ ያገለግላል፡፡ ዓባይነህ፣ ዓባይነሽ፣ ዓባይጋረደሽ ወዘተ. በዘይቤ ደረጃም “ዋናተኛ ዓባይን በዋና የሚያቋርጥ በዓባይ ላይ የሚንፈላሰስን ለመግለጽ “ዓባይ መስኩ” ይሉታል፡፡ ዓባይና ጣና ለጥበብ ንሸጣ ዓይነተኛ መሳሪያ እንደሆኑ በምድራችን በሰውነት ኅልው ሆነው የኖሩት የአለቃ ገብረ ሐና አንዱ ጥበባዊ ሥራ ማሳያ ይሆናል፡፡ አለቃ ለያሬዳዊው ማሕሌት ማጀቢያ ያደራጁትንና በልጃቸው የሰየሙት “የተክሌ አቋቋም” የሚሰኘው የአቋቋም ሥርዓት የፈጠሩት ዓባይ-ጣና ሐይቅ ዳርቻ ተተክለው ከነበሩት የሸምበቆ ተክሎች ከውሃው ውስጥ ሲወዛወዙ በማየታቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዓባይ ጋር የተያያዘ ጥንታዊነትንና መሠረታዊ ሕይወትን የተነተነ ግጥም ካቀረቡት ልጨኛ ባለቅኔዎች መካከል ዋነኛው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ነው፡፡ “ዓባይ የምድር ዓለም ሲሳይ የቅድመ-ጠቢባን አዋይ አባይ የጥቁር ዘር ብሥራት የኢትዮጵያ ደም የኩሽ እናት የዓለም ሥልጣኔ ምስማክ ከጣና በር እስከ ካርናክ በጡትሽ እቅፍ እንዲላክ ለራህ ለፀሐዩ ግማድ፣ ለጣህ ለከዋክብት አምላክ ከጥንተ-ፍጠራን ጮራ የመነጨሽ ከኩሽ አብራክ፡፡” በሔኖክ ያሬድ |