| የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል... |
|
|
| Sunday, 06 January 2008 | |
|
የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል በዳርፉር ተልዕኮውን ሊጀምር ነው በሱዳን ዳርፉር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠላም አስከባሪ ኃይል ተልዕኮውን የሚጀምር መሆኑን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ በዘገባው መሠረት የሰላም አስከባሪ ኃይሉ /ዩናሚድ/ በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረውን የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድንን በመተካት የሠላም ማስከበር ሂደቱን ይጀምራል፡፡ ቡድኑ ሃያ ስድስት ሺ ወታደሮችን ያካተተ ሲሆን በወታደር ብዛት ከተመድ ሰላም አስከባሪ ቡድኖች ከፍተኛውን ቁጥር እንደያዘ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዘጠኝ ሺ ወታደሮችን በመያዝ በአካባቢው የተሰማራ ሲሆን ቀሪው በቅርቡ ወደ አካባቢው እንደሚደርሱ ተገልጿል፡፡ የሠላም አስከባሪ ኃይሉ ስምሪት ከሱዳን መንግሥት ጋር በወታደሮቹ አሰፋፈርን አስመልክቶ በነበረው ያለመግባባት ሳይሳካ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ የሚያስፈልጉትን የሄሊኮኘተር አቅርቦት ሳያገኝ መቆየቱ ተገልጿል፡፡ ዩናሚድ እ.ኤ.አ ከ2ዐዐ3 ጀምሮ በዳርፉር የነገሰውን ጦርነት እንደሚያስቆም ይጠበቃል፡፡ በጦርነቱ ከሁለት መቶ ሺ ሰዎች በላይ መሞታቸው ይታወቃል፡፡ ቻድ በዳርፉር ጥቃት ሰነዘረች የቻድ መንግሥት ከሱዳን ዳርፉር አማፅያን ጋር በመተባበር ያለፈው አርብ ጀምሮ በአካባቢው ጥቃት ማድረሱን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ፡፡ የሱዳን ባለሥልጣናት በምዕራባዊ ዳርፉር አካባቢ የቻድ መንግስት ከፍተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ገልፀዋል፡፡ የሱዳን መንግሥት የቻድን ጥቃት አስመልክቶ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ አቅርቧል፡፡ የቻድ መንግሥት በበኩሉ በድንበር አካባቢ በሚገኙት የቻድ አማፅያን ላይ በአየር ኃይልና በምድር ኃይል ከፍተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ገልጿል፡፡ የቻድ መንግስት ወደሱዳን ድንበር አለመሻገሩን አክሎ ገልጿል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ጥቃቱን ተከትሎ በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን ከአካባቢው እንዲወጡ ማድረጉ ተዘግቧል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ዘራፊዎች በታንዛንያ ዲኘሎማት ላይ ጥቃት አደረሱ በደቡብ አፍሪካ የታንዛንያ ከፍተኛ ኮሚሽነር ኤማኑኤል ሙዋሙ ቡሉኩቱ በዘራፊዎች ከፍተኛ ጥቃት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውን የደቡብ አፍሪካን ፖሊስ በመጥቀስ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገበ፡፡ ዘራፊዎቹ የዲኘሎማቱ መኖሪያ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመግባት ጥቃት ማድረሳቸው ተገልጿል፡፡ በጥቃቱ ከዲኘሎማቱ በተጨማሪ ስድስት የፖሊስ አባላት እንዲሁም የዲኘሎማቱ ሚስት መቁሰላቸው ተዘግቧል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በዓለም ከፍተኛ የዘረፋ ወንጀል የተስፋፋባት ሀገር መሆኗን ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡ የሀገሪቱ ፖሊስ ከዘራፊዎቹ ውስጥ አንድ አባል መያዛቸው ታውቋል፡፡
በፓኪስታን በሚቀጥለው ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን የምርጫ ስነ ስርዓት እንዲራዘም የሃገሪቱ መንግሥት ያቀረቡትን ሀሳብ የምርጫ ኮሚሽኑ ውሳኔ ያልሰጠበት መሆኑን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ የቤናዚር ቦቶን ሞት ተከትሎ በሀገሪቱ በተከሰተው ረብሻ ምክንያት የምርጫ ስነ ስርዓቱ በታቀደለት ጊዜ ስለመከናወኑ አጠያያቂ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫው በእቅዱ መሠረት እንዲከናወን ጥያቄ ሲያቀርቡ የሀገሪቱን የመንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረው የ..ፒ ኤም ኤል ኪው.. ፓርቲ ምርጫው ለሳምንታት ጊዜ እንዲራዘም ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ውሳኔ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡ |
| < Prev |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |