Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ብሔራዊ ባንክን አንድ ግለሰብ 29 ጊዜ...
ብሔራዊ ባንክን አንድ ግለሰብ 29 ጊዜ... Print E-mail
Sunday, 02 March 2008
ብሔራዊ ባንክን አንድ ግለሰብ 29 ጊዜ ወርቅ መሰል ብረት በማቅረብ አጭበርብሮታል

ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የተጠረጠረ ከፍያለው ዑመታ የተባለው ግለሰብ 29 ጊዜ ለብሔራዊ ባንክ ወርቅ መሰል ብረት በማቅረብ ማጭበርበሩን የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት የካቲት 20 ቀን 2000 ዓ.ም ቀርበው አስረዱ፡፡
መርማሪው ይህን ያስረዱት የፌደራል ሥነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ በወርቅ ማጭበርበር ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉት የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና በተለያዩ ሥራዎች ላይ በተሰማሩ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራውን አጠናቆ ክስ እንዲመሰርት ፍርድ ቤቱ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የፈቀደለት ቢሆንም፣ ምርመራው ውስብስብ በመሆኑ ክስ መመስረት ያልቻበትን ምክንያት ቀርበው ባስረዱበት ዕለት ነው፡፡

“የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ድርጊት በመሆኑ ምርመራው በጣም ውስብስብ ነው፡፡ በመሆኑም በአሥር ቋሚ መርማሪዎችና ከስድስት በላይ ደጋፊ የሠው ኃይል ሌሊትና ቀን እየሰራን ነው፡፡ ሁሉም ምርመራ ተመሳሳይ በመሆኑ፣ ለየብቻው ሳይሆን የሁሉንም አንድ ላይ እየሰራን ነው” በማለት መርማሪው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በተለያዩ የክስ መዝገብ ቁጥሮች የነበሩትን በአንድ የክስ መዝገብ ቁጥር እንዲጠቃለልለት በጠየቀው መሠረት መጠቃለሉ ተገልፆ፣ ተሰጥቶት በነበረው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ፣ ከተጠርጣሪዎች ዝርዝር ቃል መቀበሉን፣ ወርቅና ጥሬ ገንዘብ መያዙ፣ ሲሸሹ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን ይዞ ቃል መቀበሉንና ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተጠርጣሪ ሰራተኞችን መያዙን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ተጨማሪ ሥራዎች የሚላቸው፣ ዝርዝር ቃል መቀበል፣ ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ የወርቅ ምርመራ ሰርተፍኬት መቀበል፣ ከኦዲተር ቃል መቀበል፣ በተመዘበረው ብር የተገዙ ወርቆችን መያዝና 113 ሚሊዮን ጥሬ ብርና ወርቅ ይዘው የተሰወሩትን መያዝ እንደሚቀረው ገልፆ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች አበበ ወርቄና ብርሃኑ አበራ ባቀረቡት ተቃውሞ፣ የተከሳሾች የክስ መዝገብ ቁጥር መዝገቡ ሳይጠቃለል ሊነገራቸው ይገባ እንነበር ተናግረው፣ “ግራና ቀኝ ብንጠይቅ ኖሮ አንዳይጠቃለል እንቃወም ነበር” በማለት ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ አያይዘውም በዋናነት ሥራውን ማጠናቀቁን መርማሪው መናገሩን፣ ቀረኝ የሚለው ምርመራ በተደጋጋሚ የሚለውን በመሆኑ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንደማያስፈልገው ተናግረው፣ ኮሚሽኑ ክስ መመስረት እንደሚገባው፣ አለበለዚያም ደንበኞቻችን በዋስ ሊለቀቁ ይገባል በማለት አመልክተዋል፡፡

አንድ እስረኛ በቁጥጥር ሥር ሲሆን ከቤተሰቡና ከጠበቃው ጋር መነጋገር እንደሚገባው የተናገሩት ጠበቃ አበበ ወርቄ፣ “እስረኛ በሚጠየቅበት ረቡዕና ዓርብ ለአራት ቀናት ያህል ሄጄ ሁለቱን ደንበኞቼን አንድ ጊዜ ብቻ ሳገኝ፣ አንደኛውን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ሕገ መንግስታዊ መብት አልተከበረም፡፡ በዚህ ላይ ጠንከር ያለ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ” በማለት ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል፡፡

ጠበቃ ወንድአወቅ አየለ ተመሳሳይ ችግር እንዳጋጠማቸው ገልፀው፣ እስረኛን መጠየቅ በሚቻልበት ሰዓት፣ ጠዋት ከአምስት እስከ ስድስት፣ ከሰዓት ከሰባት እስከ 11 ሰዓት ብሄድም አንድ ጊዜ ሰዓት ገና ነው፣ ሌላ ጊዜ ሰዓት አልፏል በማለት ፖሊሶች ከደንበኞቼ ጋር ሊያገናኙኝ አልቻሉም በማለት አመልክተዋል፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አብዱልሺኩር መሀመድ በበኩሉ፣ “የእኔ ችግር ከጠበቃዬ ጋር አንድ ጊዜ ነው የተገናኘሁት (ሌላ ጊዜ ጠበቃው ስላልሄዱ”፣ ከውጭ የመጣሁት አገሬ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ነው፡፡ ሥራዬ እየተጓተተ ነውና ዋስ ይፈቀድልኝ” በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ሁሉንም ተጠርጣሪዎች እኩል እንደሚያዩ፣ በነበረው ጊዜና በጠየቁት መሠረት እስረኞችን ከጠበቆቻቸው ጋር እንደሚያገናኙ፣ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ተጠርጣሪዎቹን ለምርመራ ይዘዋቸው ሲወጡ፣ ጠበቆች መጥተው ሊያጧቸው እንደሚችሉና አንዳንድ ጊዜ የሥራ ሰዓት አክብረው ሳይመጡ በመቅረታቸው መሆኑን መርማሪው ፖሊሰ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ጠበቆቹ በሄዱበት ሰዓት ሁሉ ክፍት ይሆናል የሚል እምነት እንደሌለው፣ የራሱ ሰዓትና ጊዜ ስላለው በፕሮግራሙ መሠረት ከሄዱ እንደሚያገኙ፣ ፍርድ ቤቱ ጠበቆቹ ላነሱት ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል፡፡  

 “ደንበኛዬ ከመንግሥት ሠራተኞቸ ጋር ግንኙነት የላቸውም፡፡ የታሰሩት ወደ ውጭ የሄደ ሰው ረድተሃል በሚል ስለሆነ ምርመራቸው ተጠናቋል፡፡ በመሆኑም የዋሰትና መብታቸው ይጠበቅልኝ” በማለት የአብዱልሺኩር መሀመድ ጠበቃ ሚሊዮን አሰፋ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

የኮሚሽኑ መርማሪ በበኩላቸው ተጠርጣሪው ሰውን በመርዳት ብቻ የተጠረጠሩ እንዳልሆነና ከሙደሲር መሀመድ ጋር በመተባበር የወንጀሉ ተሳታፊ ናቸው በሚል የተጠረጠሩ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ምርመራው መስፋቱን፣ ለዚህም ዋና ምክንያት የሆኑት፣ የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦች የምርመራውን ሂደት ለማደናቀፍ፣ መርማሪዎችን በገንዘብ ማስቆም፣ ከአገር ማስወጣት፣ በማጭበርበር የተገኘውን ገንዘብ ማሸሽና በሌላ ሰው ስም ማዛወር በመሆኑ ጉዳዩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውስብስብ እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜው አስፈላጊ መሆኑን የፌደራል ፖሊሰ መርማሪ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁሉንም ግራና ቀኝ ካዳመጠ በኋላ በይደር ለየካቲት 21 ቀን 2000 ዓ.ም ቀጥሮ፤ የካቲት 21 ቀን 2000 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በዋለው ችሎት፣ የክስ መዝገቡ ቁጥር በአንድ እንዲጠቃለል የተደረገው፣ በመርማሪዎች ሃሳብ ተሰጥቶበት የነበረ መሆኑንና በዛ ምክንያት እንደተጠቃለለ አስታውሶ፣ የተጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ፣ ለ12 ቀን ብቻ በመፍቀድ ለመጋቢት 2 ቀን 2000 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱ ተመላሽ ሆኗል፡፡  

በታምሩ ጽጌ
 
< Prev   Next >