| ወርቅ ናቸው የተባሉ ታዋቂዎችና... |
|
|
| Sunday, 02 March 2008 | |
ወርቅ ናቸው የተባሉ ታዋቂዎችና ሹመኞች ባሌስትራ ሲሆኑ!ከብሔራዊ ባንክ ጋር በተያያዘ የገባው ወርቅ፣ የተያዘው ወርቅ እውነተኛ ወርቅ ሳይሆን ባሌስትራ ሆኖ ተገኘ የሚል ዜና ከምግብ፣ ከመጠጥ፣ ከሥራና ከጨዋታ ጋር አብሮ የሚሄድ የሕዝቡ የየዕለቱ መነጋሪያ ሆኗል፡፡ ቁም ነገሩም ባሌስትራን ወርቅ ነው ብለው አጭበረበሩ፣ የሕዝብ ገንዘብ ዘረፉ ነው፡፡ የሚያሳዝንም የሚያናድድም ነው፡፡ የወርቁ መጭበርበር ብቻ ሳይሆን ከሰው ጋር የተያያዘ ተመሳሳይ ወይም ከዚያም በላይ የሆነ የሚያሳዝንና የሚያናድድ ነገርም አለ፡፡ ወርቅ ናቸው ተብለው የተለያየ ሹመትና ኃላፊነት የተሰጣቸው ሹመኞችና ባለሥልጣናት፣ ወርቅ ናቸው ተብለው የሚከበሩ ባለሃብቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ባለሙያዎችም ሲከፈቱ ባሌስትራ ሆነው እየተገኙ ነው፡፡ “ቢከፍቱት ተልባ” ይባል የነበረው ምሣሌያዊ አነጋገር ነው በዘመናዊና በቴክኖሎጂ ዘመን “ቢከፍቱት ባሌስትራ” የሆነው፡፡ መንግሥት አምኖና አክብሮ፣ በፓርላማም ተከራክሮ፣ ወርቅ ሰዎች ናቸው ብሎ የሕይወት ታሪካቸውን አስነብቦ ሰዎችን ለሹመት ያበቃል፡፡ ተሿሚዎችም እውነተኛ ወርቅ ነን በመሾማችንና በወርቅነታችን ማንም ሊያስብ አይገባም ብለው በየዓመቱ ፓርላማ ገብተው ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ በመገናኛ ብዙሃንም “በእውነቱ፣ በመሰረቱ” እያሉ መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ ያሳዩትን እድገት በግራፍ ሰርተው ያሰራጫሉ፡፡ ዌብ ሳይት ይከፍታሉ፡፡ በመፅሄታቸውም “የሚኒስትሩ መልእክት” ወይም “የሥራ አስኪያጁ መልእክት” እየተባለ ይህ በወርቅ ሰዎች ተመርቶ ወርቅ ውጤት የተገኘበት ሥራ ወደኋላ እንዳይመለስ “አደራ” ይባላሉ፡፡ የድፍረታቸው ድፍረት ባልተሰራ ሥራ ላይ ክቡር ፕሬዚዳንቱን፣ ሚኒስትሮችንና ዲፕሎማቶችን ጋብዘው በዓል ያከብራሉ፣ ያስመርቃሉ፡፡ ሲከፈት የሌለና የውሸት ነው፡፡ ወርቅ የተባሉት ሲከፈቱ ባሌስትራ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በባንክና በቴሌ ዙሪያ በተደጋጋሚ የታየውም ይኸው ነው፡፡ ወርቅ የተባሉት ሹመኞች ባሌስትራ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ይህ ችግር የመንግሥት ሹመኞች ችግር ብቻ አይደለም፡፡ በግል ዘርፉም እየታየ ነው፡፡ አንዱ ባንክ ተነስቶ ይህን ያህል አተረፍኩ ይላል፡፡ በትልቅ ሆቴል የእንኳን ደስ አለን ግብዣ ይዘጋጃል፡፡ ባንኩን እዚህ ላደረሱት ተብሎ ምስጋና ይቀርባል፣ አበባ ይሰጣል፣ የደስታ መልዕክት ይተላለፋል፡፡ ቦርዱም አመራሩም ይጨበጨብላቸዋል፣ መስራቾችም ይደነቃሉ፡፡ ውስጡ ተመርምሮ ሲታይ ባንኩ አያተርፍም፡፡ ባንኩ በተለያዩ ሰዎች ይዘረፋል፡፡ መስራቾችም፣ ቦርዶችም ማኔጅመንትም በቡድን ይከፋፈሉታል፡፡ ሲታይ እነሱን አምኖ አክስዮን የገዛውና ገንዘብ ያስቀመጠው ይሰረቃል፡፡ ሲመረመር ሰማንያ ከመቶ ብድር ወሳጆች መስራቾቹ ይሆናሉ፡፡ ባንኩ ለምን ከሰረ ሲባል አጥጋቢው መልስ ወርቅ የተባሉት ባሌስትራ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ ትልቅ ኩባንያ ነው ይባላል፣ ካፒታሉ ይዘረዘራል፡፡ የሰው ሃይሉ እልፍ ነው ይባላል፡፡ እህት ወንድም አጎት፣ አክስትና አያት በዙሪያው ኩባንያዎች በርካታ ናቸው፡፡ እየቆዩ ሲሄድ አንዱ አትራፊ አይደለም፣ አንደኛው ማኔጅመንት የለውም፣ አንደኛው ሥራ ካቆመ ቆይቷል፣ የአንደኛው ግንባታው ተቋርጧል፣ አንደኛው ብዙ የባንክ ብድር አለበት፣ አንደኛው የሕግ ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡ አንደኛው የሊዝ አልከፈለም፡፡ የፕራይቬታይዜሽን ዕዳ አለበት፡፡ ሳር በቅሎበታል፡፡ እንዳለ ተረስቷል፣ ተነጥቋል፡፡ ወርቅ የተባሉት ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ሲከፈቱ ባሌስትራ ይሆናሉ፡፡ በፖለቲካው ዙሪያም ተመሣሣይ ነገር እያጋጠመ ነው፡፡ ኢሕአዴግ “የእረኞች” ድርጅት ነው፣ የምሁራንና የሊቃውንት ድርጅት መጣ ይባላል፡፡ አስር ዲግሪ፣ አምስት ዲግሪ፣ ዶክተር፣ ፕሮፌሰር፣ ከክሊተን ጋር ተምሯል፡፡ ድሮ ኬኔዲ መርቆታል እየተባለ ይነገራል፣ ይፃፋል፣ ይዘመራል፡፡ ሕዝብ ያምናል፣ ይከተላል፣ ይመርጣል፡፡ ጥቂት ቆይቶ ሕዝብ ይመራል የተባለው እንኳን ሕዝብን ሊመራ ለራሱ የሚሄድበት አቅጣጫ ጠፍቶት መሃል መስቀለኛ መንገድ ላይ እንደ ሕፃን ስቅስቅ ብሎ ሲያለቅስ ይስተዋላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምራኝ እያለው ሕዝቡን ትቶ አሜሪካ ሄዶ “ኤሎሄ ኤሎሄ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ ዶናልድ ፔይን ትዘረጋለች” ብሎ ይማፀናል፡፡ ሰው እግር ላይ ወድቆ ስለት ይገባል፡፡ ብራስልስ ሄዶም “ቅድስት አና ጎሜዝ ሆይ ኢትዮጵያ ያንቺ ናትና ከመከራ አድኝያት” ብሎ የወርቅ ጃንጥላ ይሳላል፡፡ ወርቅ የተባለው ምሁርና ፖለቲከኛ ሲከፍቱት ባሌስትራ” ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ እንዴት ይጥፋ ይባላልና እኛም ሚዛናችንን መጠበቅ እንፈልጋለን፡፡ በኢትዮጵያ ወርቅ ተብሎ እውነተኛ ወርቅ ሆኖ የተገኘ የለም ማለት ነው? ሁሉም ባሌስትራ ነውን? መልሱ አይደለም ነው፡፡ ወርቅ ናቸው ተብለው እውነተኛ ወርቅ ሆነው የቆዩና አሁንም የቀጠሉ አሉ፡፡ ባሌስትራ ያልሆኑ እውነተኛ ወርቅ የሆኑ፣ ለአገርና ለሕዝብ የሚያስቡ፣ ለልማት የሚቆረቆሩ ሹመኞችም አሉ፣ ግለሰቦችም አሉ፣ ፖለቲከኞችም አሉ፡፡ ወርቅ ተሹመው ባሌስትራ ሆነው የተገኙ ግን በዝተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወርቅ ናቸው ተብለው ሲከፈት ባሌስትራ ሆነው የተገኙትን ያህል ባሌስትራ ናቸው ተብለው ሲናቁ የነበሩ ሲከፈቱ ወርቅ ሆነው የተገኙም አሉ፡፡ አቅም እንገነባለን፣ ሲቪል ሰርቪስን እናጠናክራለን ብለው እልፍ መግለጫ፣ እልፍ ሴሚናርና ዎርክ ሾፕ አዘጋጅተው እረፍት ሲያሳጡን የነበሩ ወርቅ ናቸው ብለን እንድናምን ያደርጉን የነበሩ ባሌስትራ ሆነው ሲገኙ እንደነግጣለን፡፡ በሌላ በኩል ባሌስትራ ናቸው ተብለው ሲዘለፉ የነበሩት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መሪዎችና መስራቾች ድምጻቸውን አጥፍተው በተግባር እየሰሩ ያሉትና በተግባር ያስመዘገቡት የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራምና ለውጥ ባሌስትራ ሲባል የነበረው ወርቅ ሆኖ መገኘቱን ያረጋግጣል፡፡ ሁሉም ባሌስትራ አይደለም፡፡ ወርቅ ተብሎ ወርቅ ሆኖ የቀጠለና ባሌስትራ ነው ሲባል ወርቅ ሆኖ የተገኘም አለ፡፡ በእነዚህ ወርቅ ሥራ ተሰርቷል፤ እየተሠራም ነው፡፡ ነገር ግን በውሸትና በቅጥፈት ወርቅ ነው እየተባለ ባሌስትራ ሆኖ የሚገኝ በዝቷል፡፡ አገርንና ሕዝብን እየጎዳም ነው፣ ጉዳቱም ከባድ ነው፡፡ ቁጭ ብለን ልናስብበት፣ ታግለን ልንቋቋመውና ልናሸንፈው ይገባል፡፡ በጊዜ ካልተገታ የተወሰነ ፕሮጀክትና መሥሪያ ቤት ሳይሆን መላው አገሪቷ፣ ታሪኳንና ባህሏን፣ ኢኮኖሚዋንና እድገቷን ወደ ባሌስትራ ሊቀይረው ይችላል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |