| ጣልያን የተወልንን የቤት ሥራ ጨርሰናልን? |
|
|
| Sunday, 02 March 2008 | |
|
የዛሬ 112 ዓመት ነበር ሁሉም የአገራችን ሕዝቦች ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ክተት ተባብለው ዓድዋ ላይ የዋሉት፡፡ የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን ለእኛ ነፃነትና ክብር ሲሉ መስዋዕት የሆኑባት፣ የጥቁሮችና የነጮች የሃይል ሚዛን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዛባባት ስፍራ፣ ዓድዋ”“
በአምሳያ ሰው የተፈጠሩ፣ የኢትዮጵያን ነፃነት እንዲጠብቁ ሆን ተብለው የተሰሩ ይመስላሉ፡፡ ከነሙሉ ግርማ ሞገሳቸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት ሰንሰለታቸውን ጠብቀው፣ ለዘለዓለም ቆመው የነፃነት መቃብር ሳይሆኑ የነፃነት አበቦች መቃብር ሆነው ኖረዋል፣ ይኖራሉም፡፡ ደጋግመን ብናያቸው የማንጠግባቸው የነፃነት ተምሳሌቶች፣ የማይሰለች የነፃነት ምንጮች፡፡ የዓድዋ ተራሮች”. የዛሬ ቀን፤ ኢትዮጵያ በወረሪው ጣልያን ላይ ድል የነሳችበት ቀን 112ኛ የዓድዋ ድል የሚከበርባት የተቀደሰች ቀን ናት፡፡ የድሉ አድማስ ከኢትዮጵያ ወጥቶ የሁሉንም ጥቁሮች ስሜት የቀሰቀሰ፣ ትምክህተኞችን ዘረኞች የጣልያን ሞሰሊኒዎች የተዋረዱበት ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን አውሮፓውያን የበርሊን ኮንፍረንስ (1884 - 85) መሠረት አፍሪካን የመቀራመት ህልማቸውን ለማሳካት የዘመቱበት ወቅት በመሆኑ የጣሊያን መልካም ዜና ለማሰማት ሲጠባበቁ የዋሉበት ቢሆንም፣ ነገሮች ሁልጊዜ እንደተፈለጉ አይሆኑምና፣ ለማመን ያቃታቸው የጣልያንን መርዶ ሰሙ፡፡ በተቃራኒው ጥቁሮችና የጥቁሮች ደጋፊ የሆኑት ሁሉ በያሉበት ተደሰቱ፣ ተነሳሱ፣ ተነቃቁ፡፡ ዓለም ለአንዱ አልጋ ለሌላው ቀጋ ሆነች፡፡ ነገሮች ተለዋወጡ፡፡ የዓድዋ ጦርነት የኢትዮጵያ ነፃነት፣ የኢትዮጵያ ክብር፣ የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል የታደገ ድል ቢያቀናጅም እንደ ነፃነታችን ሁሉ ነዋሪ የሆኑ እንከኖች አስቀምጠው አልፈዋል፡፡ በእርግጥ በቅኝ ገዢዎች አልተገዛንም፣ ቋንቋችን፣ ባህላችንና ታሪካችን ተጠብቆ ኖሯል፡፡ ይሁን እንጂ አውሮፓወያን ልክ በሌሎች አገሮች ቀብረውት የሄዱት እሳት እኛንም አልተወም፡፡ አውሮፓውያን የአፍሪካ ቅርሶች፣ ስልጣኔዎች፣ ባህሎችና (መንፈሳዊና መንፈሳዊ ያልሆኑት እሴቶች) ሁሉ አውድመው የራሳቸውን ባዕድ የሆነው ዕሴት ተክለውልን ሄደዋል፡፡ ይህ ለእኛ አፍሪካውያን አልተዋጠልንም፣ አልተስማማንም የራስ ምታት ሆኖብናል፡፡ አልተስማማንም ብቻ ሳይሆን እርስ በርሳችን እያግባባን ሳይሆን፣ እያባላን፣ እያናቆረን ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር አውሮፓውያን በአፍሪካ መስርተውት የሄዱት ትልቅ በሽታ አለ፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት በእያንዳንዱ የአፍሪካ አገር ያሉ ግጭቶች 90 በመቶ መንስኤያቸው ከቅኝ ግዛት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እንዴት? አውሮፓውያን በበርሊን ኮንፍረንስ (1984-85) መሠረት አፍሪካውያን የተቀራመቱዋቸው ለራሳቸው ግዛት እንዲመቻቸው በሚያስችል የአስተዳደር ክፍፍል ነው፡፡ ይህ ሂደት በአንድ በኩል የአንድ ብሔር አባላት ለሁለት ወይም ለሶስት ቦታዎች የከፋፈሉ ሲሆን የተለያዩ ብሄሮች/ጎሳዎችም በአንድ ላይ ጨፍልቀው መግዛት አስችሎዋቸዋል፡፡ ይህንን አገዛዝ ያስከተለው መጥፎ ውጤት እስከአሁን በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች እየታየ ያለው ግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት የሚገለፅ ነው፡፡ አውሮፓውያን ለአስተዳደር እንዲመቻቸው ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ቡድኖች ይነሳ የነበረውን ዓመፅ ለመቀልበስ አንዱ የተሻለ ሌላኛው ዝቅተኛ አድርገው በመሳል እርስ በርሳቸው እንዲናቆሩ በማድረግና በራሳቸው ላይ የሚነሳ ዓመፅ ለመቀነስ የተጠቀሙት ትልቅ መሳሪያ ነበር፡፡ እንዲሁም የራሳቸው “አርቲፊሻል” ድንበር ከመፍጠር ባሻገር የፈጠራ የሆነው ታሪክ በመፍጠር አንድን ብሔር ለሁለት ወይም ለሶስት በመክፈል የተለያዩ እንደሆኑ በማድረግ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ ያደርጋሉ፡፡ የተለያዩ ማንነቶች በማላበስም የተሳካላቸው ሆነዋል፡፡ ለዚህ ትልቁ ምሳሌ የሩዋንዳ የኢንተርሃምወይ (የሁቱና ቱትሲ) እልቂት ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው አፓርትይድ፣ የታላላቅ ሃይቆች የእርስ በርስ ግጭት (ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ”፣ የሱዳን (የደቡብ ሱዳን ቀውስ፣ የዳርፉር ቀውስና የምሥራቅ ሱዳን ዓመፅ) ወዘተ. ሁሉም የቅኝ ገዥዎች በረከቶች ናቸው፡፡ ቅኝ ገዢዎች ቀብረውት የሄዱት ይህ መርዝ እያደረ የሚፈነዳ፣ በየቦታው እየተበራከተ ያለው በሽታ በዚህ ብቻ የሚገለፅ አይደለም፡፡ የአፍሪካ አገራት በውስጣቸው የጎሳ ግጭት ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት አገርም የድንበር ግጭት ሰለባ ሆነዋል፡፡ የካሜሮንና የናይጀሪያ የሶማሊያና የኬንያ፣ የሶማሊያና የጅቡቲ እንዲሁም ኤርትራ ከሱዳን ከየመንና ከኢትዮጵያ ያካሄደችው ጦርነቶች/ግጭቶች ሁሉ የድንበርና የግዛት ጥያቄዎች መንስኤ ያደረጉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች አገር ናት የሚል ጥያቄ አንዳንድ ምሁራን ያነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን አልተገዛንም እያልን የምንስለው ካርታ እስከ ቀይ ባህር ሲሆን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እርስ በርሱ የሚጣረስ ነውና፡፡ በአንድ በኩል ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ናት እያልን በሌላ በኩል ከዓድዋ ድል በኋላ አፄ ምኒሊክ ከጣልያን ተዋውለው “ከመረብ ምላሽ”“. በሚል የሰጡት የኤርትራ ግዛት በጣልያን ከ60 ዓመት በላይ ቀጥሎም በእንግሊዝ ለ10 ዓመት በቅኝ ገዢዎች የወደቀው የቀድሞ የኢትዮጵያ አካል አለ፡፡ ሁለት ነገር ማጣቀስ አይቻልም፡፡ አንድም፣ ኤርትራ (ራሳቸውን ኤርትራውያን እንደሚሉት) እ.ኤ.አ በ1952 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የተቀላቀለችው በቅኝ ገዢነት እንጂ በታሪክ የኢትዮጵያ አካል አልነበረችም፣ አልያም ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ስለነበረችና ከዓድዋ ጦርነት በኋላ ለጣልያን ስለተሰጠችው ኢትዮጵያ በከፊል ቅኝ ግዛት ስር ወድቃለች የሚል ወደድንም ጠላንም ሐቁን እየመረረንም ቢሆን መቀበል ነው፡፡ በእርግጥ የኤርትራ ግዛት ከዓድዋ ድል በኋላ ለጣልያን መስጠት ነበረበት ወይስ የሚል አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሎዋል፡፡ አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ዓፄ ምኒሊክ ዓድዋ ላይ ከተቀናጁ በኋላ እስከ መጨረሻ ያልቀጠሉበት ምክንያት ወታደሩ ስንቅና ትጥቅ ስለጨረሰ ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ይገኙባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል አፄ ምኒሊክ የኤርትራ ግዛት ለጣልያን የሰጡት በወቅቱ ከትግራይ (ትግራይ ትግርኚ) ይነሳባቸው የነበረ የስልጣን ተቀናቃኝነት ለመቀልበስ ትግራዮቹን ለሁለት ለመክፈል ስለፈለጉ ነው የሚል ማከራከሪያ ነጥብ ያነሳሉ፡፡ በተለይ የውጭ ፀሐፊዎች እንደ ፕሮፌሰር ጆን ማርካኪስና ፕሮፌሰር ሃጋይ ኤርሊክ ይገኙባቸዋል፡፡ እንዲሁም ከአገር ውስጥ ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ተጠቃሽ ናቸው፡፡እነዚህ ወገኖች ሌላ ማከራከሪያ ነጥባቸው አፄ ምኒሊክ በዓድዋ የቆሰለውና የበከተው የጣልያን ወታደር እስከ መጨረሻ ማሳደድ ከፍተኛ ስንቅና ትጥቅ አስፈላጊ እንዳልነበረ በመጥቀስ፣ ቢሆንም እንኳ ራስ አሉላ ራሳቸው (ብቻቸውን) ጣልያኖች እስከ መጨረሻ ላባራቸው ብለው አፄ ምኒሊክን ፈቃድ መጠየቃቸውና እንዳልፈቀዱላቸው እንደማስረጃ ያስቀምጣሉ፡፡ ፍርዱን ለታሪክ ምሁራኑ እንተወውና ሀቁን ተገንዝበን ለወደፊቱ ልንማርበት ይገባል፡፡ ይህንን ጉዳይ አወዛጋቢ ሆኖ ይቀጥል እንጂ አንድ የማይካድ ሃቅ ግን አለ፡፡ ጥቅምት 1989 ዓ.ም በአፄ ምኒሊክና በጣልያኖች መካከል በአዲስ አበባ በተደረገው የሰላም ስምምነት ጣልያን ለኢትዮጵያ ዕውቅና እንድትሰጥና ኢትዮጵያ በበኩልዋ ከመረብ ምላሽ ትግራይ (የአሁኗ ኤርትራ) ለጣልያን እንዲሆን ተስማምተዋል፡፡ በመሆኑም ኤርትራውያን ከወንድሞቻቸው ኢትዮጵያ ተለይተው በጣልያን ቅኝ ግዛት ስር እንዲወድቁ ተደርገዋል፡፡ ለ60 ዓመትም ተገዝተዋል፡፡ ኤርትራ እ.ኤ.አ በ1952 ዓ.ም በተመድ ውሳኔና በአፄ ኃይለስላሴ ጥረት ኤርትራ ዳግሞ ወደ ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል ተደረገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኤርትራውያን ከኢትየጵያውያን ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንደ በፊቱ ሊሆን እንዳልቻለ የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በተለይ ጣልያን ከኢትዮጵያ ለመዋጋት ሲፈልግ (ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ1935 ዓ.ም) ኤርትራውያንና ከሁሉም አፍሪካውያን የተሻለ ዘር ሃረግ እንዳላቸው እየቀሰቀሰ በመካብ እንዲከፈሉ አድርገዋል፡፡ ይህ የጣልያን የውሸት ፕሮፖጋንዳ በኤርትራውያን ላይ የተለየ ስሜት እየፈጠረባቸው በሥነ ልቦናቸው ላይ ቀላል ልዕልና የተናወጠው መንፈስ (Superiority complex) አላሳደረባቸውም፡፡ በተዘዋዋሪ በጨዋ የኢትዮጵያዊነትና ሀበሻ ባህላቸው ላይ ጥቃት ፈፅመዋል፡፡ ሌላ የባዕድ ባህል፣ አመለካከትና ስነልቦና አላብሶባቸዋል፡፡ ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ “በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት”“. በሚል መጽሐፋቸው “ሠቈቄቃሸ self ሽቂሮሸስ” ብለውታል፡፡ ይህንን ሁኔታ አፄ ኃይለስላሴ በኤርትራ ላይ የተከተሉት መንገድና ደርግም የቀጠለበት የግፍ ስርዓት ተጨምሮበት ለ30 ዓመት ከኢትዮጵያ ጋር ተዋግተዋል፡፡ በአፍሪካ ረዥሙ ዓመፅ፡፡ ነፃነታቸው ከተቀናጁም በቅርቡ በ1990 ዓ.ም በድንበር ስም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተካሄደው ከ100 ሺህ በላይ የሰዎች ህይወት የበላው ጦርነት መንስኤው በከፊል ከዚህ ስነልቦና የመነጨ መሆኑን የሚያሳይ ንግግር አሰምተው ነበር፡፡ ኢሳያስ አፈወርቅ በአንድ ወቅት የአፍሪካ መሪዎች ሁሉ ከኤርትራ መመልመል አለባቸው የሚል ንግግራቸው የዚሁ የውሸት የራስ ምስል ነፀብራቅ ነው፡፡ ይህ ባህሪ ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከሱዳን፣ ከየመንና ከጅቡቲ ጋርም አናክሰዋቸዋል፡፡ ተላላፊ በሽታ፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ይህ ተላላፊ በሽታ ከአጎራባች አገሮች ጋር ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካ፣ ከተመድ ከሌሎች ታላላቅ አገሮች ጋርም አጋጭቶዋቸዋል፡፡ በኤርትራ መንግሥትና በአሜሪካ መካከል የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተቋርጠዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበሩት ሰላም አስከባሪዎች (አንሚ) ከአካባቢው እንዲወጡ ተገደዋል፡፡ ይህም የሆነው በኤርትራ መንግሥት መጥፎ ድርጊት ነው፡፡ ሰላም አስከባሪዎቹ ጠቅልለው እየወጡ ሲሆን ጦርነት ዳግሞ ይጀመራል የሚል ስጋት እያየለ መጥቷል፡፡ ላልታወቀ ጊዜ የተላለፈው ጦርነት ሊጀምር ነው፡፡ አሁንም ክተት”. ይህ ሁሉ ጣልያን ከዓድዋ ጦርነት በኋላ የተወችልን የቤት ሥራ ነው፡፡ ጣልያን ከመቶ ዓመት በፊት በዓድዋ ተዋግተን፣ በአዲስ አበባ የተዋዋልነውን “የመረብ ምላሽ” መዘዝ እስከአሁን እያቃጠለን ነው፡፡ መረብ ላይ የተቀበረው ረመጥ-በየጊዜው የሚፈነዳው ቦንብ የጣልያን የቤት ሥራ ጨርሰነዋልን? በየማነ ናግሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |