| “የአድዋ ድል አፍሪካውያን በአውሮፓ ቅኝ... |
|
|
| Sunday, 02 March 2008 | |
“የአድዋ ድል አፍሪካውያን በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ላይ የተቀዳጁት ድል ነው”ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በትውልድ እንግሊዛዊ ሲሆኑ ለግማሽ ምዕተ ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ኖረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በታሪክ ተማራማሪነት ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፤ እያገለገሉም ነው፡፡ በአድዋ ድል እና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግረናቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የልጅዎ ስም አሉላ ነው፡፡ ፕ/ር ፓንክረስት፡- አዎ፡፡ ሪፖርተር፡- አሉላ ለምን መረጡት? ፕ/ር ፓንክረስት፡- ራስ አሉላ ተወዳጅ የጦር መሪና ጀግና አፍሪካዊ ጄነራል ነበር፡፡ ወራሪዎች የአሉላን ስም ሲሰሙ ይደነግጡ ነበር ይባላል፡፡ በእሱ የታሪክ እሳቤ ነበር ልጄን አሉላ ያልኩት፡፡ ሪፖርተር፡- የአድዋ ድል ያስተላለፈው ዋናው መልዕክት ምንድነው? ፕ/ር ፓንክረስት፡- የአድዋ ድል አፍሪካውያን በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ላይ ያገኙት ድል ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ለነፃነት ያደረጉት ታላቅ ተጋድሎ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1885 በርሊን ላይ የተካሄደው በርሊን አክት እየተባለ የሚታወቀው ኮንፈረስ አፍሪካን በቅርጫ ለመከፋፈል የተወሰነበት ነበር፡፡ ይህ እቅድ በኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ እንዳይሆን በማድረግ ለአፍሪካውያን ተምሳሌት የተሆነበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለአፍሪካዊያን አንድ ጠንካራ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች በጥቁር ሕዝቦች ሊሸነፉ እንደሚችሉና ነፃነትን በትግል መጎናፀፍ እንደሚቻል አሳይቷል፡፡ በእርግጥ ሌሎች አፍሪካዊያን ከቅኝ ገዢዎች ነፃ ለመውጣት ከአድዋ ድል በኋላ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ፈጅቶባቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የአድዋ ጦርነት ከመደረጉ በፊት በተከታታይ የተደረጉ ጦርነቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ጦርነቶች ለአድዋው ድል ያበረከቱት አስተዋፅኦ ነበር? ፕ/ር ፓንክረስት፡- ከአድዋ ጦርነት በፊት የተለያዩ ጦርነቶች ተካሄደዋል፡፡ ዶጋሊ ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ዋናው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1888 ጣሊያኖች ምፅዋን ከተቆጣጠሩ ከሁለት ዓመት በኋላ ራስ አሉላ እ.ኤ.አ በ1887 ጣሊያኖቹ ከምፅዋ ወደ ደጋው የኤርትራ ክፍል እንዲያፈገፍጉ አድርገዋል፡፡ ዶግዓሊ ከምፅዋ ወደብ በሃያ ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው፡፡ በተጨማሪም እ.ኤ.አ በ1875 እና በ1876 አፄ ዮሐንስ በጉንደት እና በጉራዕ በግብፅ ላይ የተጎናፀፏቸው ድሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሪፖርተር፡- እነዚህ የጠቀሷቸው ጦርነቶች በምን መልኩ ነው ለአድዋ ድል አስተዋፅኦ ያደረጉት? ፕ/ር ፓንክረስት፡- በተለይ የዶግዓሊው በጣሊያኖቹ ላይ የተገኘ ድል በመሆኑ በስነ ልቦና በኩል በኢትዮጵያ ጦር ላይ በራስ የመተማመንን መንፈስ ፈጥሯል፡፡ ሪፖርተር፡- አንዳንድ ወገኖች ኢጣሊያ በአድዋ ጦርነት ተሸንፋ ሳይሆን ከጦርነቱ የምታገኘው ትርፍ ብዙም ስላላጓጓት በጦርነቱ መግፋት ስላልፈለገች ነው የሚሉ አሉ፤ ፕ/ር ፓንክረስት፡- አድዋ ላይ የጣሊያን መሸነፍ እኮ ግልፅ ነው፡፡ ምንም የሚያሻማ ነገር የለውም፡፡ ይህን ለማሳየት በጦርነቱ ጣሊያኖች ያጡትን የሰው ህይወት፣ የቆሰሉባቸውን የተማረኩ ወታደሮቻቸውን እንዲሁም የተማረኩ የጦር መሣሪያዎችን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ ለምሳሌ ሃምሳ ከመቶ የሚሆኑት የጣሊያን ወታደሮች የተገደሉበት፣ ከአምስቱ የጣሊያን ጦር መሪዎች ሶስቱ የሞቱበት፣ አንዱ የቆሰለበት አንዱ የተማረከበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ ይህን ሁሉ መስዋዕትነት ለምን ከፈሉ? የተማረከውን የጦር መሳሪያ ሳናስብ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ለሚያስቡ ጣሊያኖች በትክክል ሽንፈትን እየመረራቸውም ቢሆን አምነውበታል፡፡ ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስር ከነበሩ አገሮች ጋር ስትነፃፀር በጣም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ በቅኝ ብትገዛ ይሻል ነበር የሚል አመለካከት ያላቸውም አሉ፡ ፕ/ር ፓንክረስት፡- ከቅኝ ግዛት ነፃ መሆን ማለት የራስን ክብር፣ ታሪክ፣ ባህልና ወዘተ. ጠብቆ መኖር ነው፡፡ ቅኝ ግዛት ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት አምጥቷል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሲጀመር ቅኝ ግዛት የተቀረፀው ሕዝቦችን ለመበዝበዝ ነው፡፡ አፍሪካውያን በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ተበዝብዘዋል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ በቅኝ የተገዙ አገሮች ኢኮኖሚያቸው አድጎ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ግን አውሮፓውያን ከዚያ በላይ ወስደዋል፡፡ መጀመሪያ የሕዝቦቹ ልብ ለማግኘት የተሻለ የሚመስል ስርዓትና ለውጥ ያመጣሉ፡፡ ይህ ግን ሃብት ለመበዝበዝ እንዲመቻቸው የፈጠሩት ሴራ ነው፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ያንን ያቆሙታል፡፡ ለምሳሌ የመሬት ፖሊሲ መለወጥ፡፡ በኤርትራ ጣሊያን ከዓድዋ ጦርነት በፊት ትከተለው የነበረውን የመሬት ፖሊሲ ከዓድዋ በኋላ ቆመ፡፡ የኢትዮጵያ ድህነት ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በንፅፅር ስትታይ ደካማ የኢኮኖሚ መሰረት ነው ያላት፡፡ ይሁን እንጂ ትልቅ ባህል አላት፡፡ ኢትዮጵያ የበለፀገ ባህል ያላት ግን በኢኮኖሚ የደኸየች አገር ናት፡፡ ለትንታኔ የሚያስቸግር ነው፡፡ ምክንያቱም ጥሩ ባህል ያለው አገር ኢኮኖሚያዊውም ያድጋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ ሪፖርተር፡- ጦርነቱ ያስከተለው አሉታዊ ተፅዕኖስ ምንድነው? ፕ/ር ፓንክረስት፡- በኢትዮጵያ በኩል የሞተው የሰው ኃይል በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ በአገሪቱ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ሪፖርተር፡- የአድዋ ድል ለጥቁር ብሄርተኝነት መፈጠር ያበረከተው አስተዋፅኦ አለ? ፕ/ር ፓንክረስት፡- በወቅቱ አብዛኛዎቹ ጥቁሮች ሃይላቸውን አሟጥጠው መጠቀም ያልቻሉና የነበራቸው ትምህርትም ንቃትም ዝቅተኛ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ ጣሊያንን ስታሸንፍ ጥቁሮች ነጮችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ጥቁሮች መገንዘብ ችለዋል፡፡ ለጥቁሮች ንቃተ ህሊና መነሳሳት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ይህንን ዜና የሰሙ ጥቁሮች ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አይተዋል፡፡ በተለይ ጥቁር አሜሪካውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ይህንን ድል በማየታቸው አጋጣሚውን ተጠቅመው ጥቁሮች የፓን አፍረካ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ ሆኗቸዋል፡፡ ይሁን እንጅ የአድዋ ድል በአፍሪካውያን ላይ ትልቅ መነቃቃትና መነሳሳት የፈጠረው ከብዙ ቆይታ በኋላ ነው፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ለሚያደርጉት የፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ድሉ ረድቷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ምሳሌ እየጠቀሱ፣ ኢትዮጵያ ጣሊያንን አሸነፈች፤ እኛም ማሸነፍ እንችላለን እያሉ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ አድዋን እንደግመዋለን በማለት እንዲያምፁ ኃይል ፈጥሮላቸዋል፡፡ የአድዋ ድል በሌሎች ጥቁሮች ላይ የፈጠረው ስሜት በጣም ቀጥተኛ አይደለም፡፡ በዋናነት ቀስ በቀስ፣ ትምህርትና ንቃት እየጨመረ በመጣ ቁጥር የኢትዮጵያን ድል ለጥቁሮች ያለው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያየለ መጥቷል፡፡ ሪፖርተር፡- በእርሶ ዕይታ የኢትዮጵያ መፃኢ እድል ምን ሊሆን ይችላል? ፕ/ር ፓንክረስት፡- (ሳቅ) እኔ ነብይ አይደለሁም”. ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች ተደቅነውባታል፣ እንዴት ልታልፋቸው ትችላለች? ፕ/ር ፓንክረስት፡- በእርግጥ ብዙ ፈተናዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ማሸነፍ ይቻላል፡፡ ይህን ለማድረግ ዋንኛ መሣሪያዎች አንደኛ ጥሩ ጥሩ ፖሊሲዎችን ማውጣት ነው፡፡ ሁለተኛ የውይይትን ባህል ማድረግ ነው፡፡ በእነዚህ መሳሪያዎች የተጋረጡብንን ፈተናዎች ድል ማድረግ እንችላለን፡፡ ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ምን እንዲደረግ ይመክራሉ? ፕ/ር ፓንክረስት፡- ለነፃነት የሚደረገው ተጋድሎ እንዲቀጥል፡፡ የዓድዋ ድል ነፃነትን፣ አንድነትን እና ባህልን ጠብቆ ከማቆየት አንፃር ያበረከተችው አስተዋፅኦ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ አሁን እኛ በጣም ልናስብበት የሚገባን ባህላችንን ጠብቀን ማቆየት ነው፡፡ አሁን ከፍተኛ የከተሞች መስፋፋት አለ፡፡ አዳዲስና ግዙፍ ህንፃዎች እየተገነቡ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ አዲስ መገንባት ብቻ ሳይሆን የነበሩትንም ጠብቆ ማቆየቱ ነው፡፡ ባህሎች፣ በተለይ ደግሞ ልዩ የሆነው የኢትዮጵያ ታሪክ ተጠብቀው ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንደ አርአያ ሆነው ሊያገለግሉ ይገባል፡፡ እንዲሁም የአክሱም ሀውልት መቆም አለበት፡፡ ያልተጠኑ ታሪኮች፣ ቋንቋዎችና ባህሎች እንዲጠኑ ውበታቸው ተጠብቆ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያን የጽሁፍ ቋንቋ በደንብ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የጽሁፍ ቋንቋ አልነበረም፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ጥንታዊ ታሪክና እና ወግ እንዲሁም ባህሎችን ማጥናትና መመዝገብ ይኖርብናል፡፡ የአድዋ ጦርነት ለነፃነት የተደረገ ጦርነት መሆኑን ማስታወስ አለብን፡፡ የነፃነት መገለጫ የሆኑ ባህሎችና ታሪኮች በትክክል መጠናት መጻፍና መጠበቅ አለባቸው፡፡ አድዋን ስናስታውስ የተለያዩ የታሪክ መረጃዎችን በመሰብሰብና በጥንቃቄ በመጠበቅ መሆን አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ላይ የሚፃፉ አንዳንድ የታሪክ መፃህፍት የሀገሪቱን ህዝቦች ታሪክ በሚዛናዊነት ባለመጻፍ ይወቀሳሉ፡፡ እርስዎ ምን ታዘቡ? ፕ/ር ፓንክረስት፡- እንዲህ ዓይነት ነገሮች የሚከሰቱት ታሪክን በተለያየ መንገድ በመተርጎም ነው፡፡ የተለያዩ ሰዎች ታሪክን በተለያየ መንገድ ይተረጉሙታል፡፡ ነገር ግን ታሪክን ስንተነትን ወይም ስንተረጉም በመረጃ ላይ በመንተራስ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ታሪክ ተረት ተረት አይደለም፡፡ ቤተሰብ ወይም የምትቀርበው ሰው የሚነግርህ ሁሉ ታሪክ ሊሆን አይችልም፣ በማስረጃ ካልተደገፈ፡፡ ስለዚህ የታሪክ ጸሀፊዎች ታሪክን ሲጽፉ በመረጃ ላይ መመርኮዝ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የታሪክ ፀሃፊ ፖለቲከኛ አይደለምና፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |