Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
May 17th
Home arrow Sections arrow “ሕዝቡ የሚፈልገውን እንዲመርጥ ካልተደረገ...
“ሕዝቡ የሚፈልገውን እንዲመርጥ ካልተደረገ... Print E-mail
Sunday, 02 March 2008
“ሕዝቡ የሚፈልገውን እንዲመርጥ ካልተደረገ የተረጋጋ ፖለቲካ ይኖራል ብዬ አላምንም”

(አቶ ቡልቻ ደመቅሳ)

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የቀበሌ፣ የወረዳና የማሟያ ምርጫ ዙሪያ ፓርቲያቸውና ሌሎች ተቃዋሚዎች ስለሚኖራቸው ተሳትፎ እንዲሁም በዚህ ምርጫ ሊጠብቁ የሚችሉትን ውጤትና ሌሎች ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ በሚካሄደው ምርጫ የፓርቲያችሁ ዝግጅት ምን ይመስላል? ሕዝቡን በዚህ ምርጫ ተሳታፊ እንዲሆን ያደረጋችሁት ጥረት አለ?

አቶ ቡልቻ፡-
ዘንድሮ ከአንድ ወር ተኩል በኋላ የወረዳ የቀበሌና የማሟያ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ የቀበሌና የወረዳ ምርጫ ግን የዛሬ አመት አካባቢ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም አልተካሄደም፡፡ አንድ አመት እንዲዘገይ ተደርጓል፡፡ ይህ ምርጫ ባለመካሄዱ የቀበሌ የወረዳና የዞን አስተዳዳሪዎች ሳይመረጡ ከአንድ ዓመት በላይ ገዝተዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ሕገመንግሥታዊና ፍትሐዊ አሰራር አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚለው ያልተመረጠ ሰው ሕዝብን አያስተዳድርም፡፡ ይህ ህገወጥ ተግባር እንዳለ ሆኖ የወረዳ የቀበሌና የማሟያ ምርጫው በቅርቡ ይካሄዳል፡፡ እንደደንቡ ከሁለት ወራት በፊት መዘጋጀት ነበረብን የመጀመሪያው ዝግጅት ሰዎቻችን እንዲመዘገቡ ማደፋፈር ነበረብን፡፡ ለምርጫው ተመዝገቡ፡፡ በመብታችሁ ተጠቀሙ ብለናል፡፡ በበኩላችን በተወሰነ ደረጃ ሕዝቡ እንዲመዘገብ ቅስቀሳ አድርገናል፡፡ ይህንን ተመዝገቡ የሚለውን ቅስቀሳ ስንጀምርና እጩ ለማድረግ ያሰብናቸው ሰዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ብንቀሰቅስም ፈሩ፡፡ ሕዝቡ ፈራ፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢ ሰዎች ፍርሃት ይታይባቸው ነበር፡፡ ለምርጫ ያለው ጉጉታቸው እንደቀነሰም ያሳያል ያልተጠበቀ ፍራቻ ይታያል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የሆነው የት አካባቢ ነው? ለምንስ ሕዝቡ ፈራ?

አቶ ቡልቻ፡-
ይህንን የታዘብነው እጩ እናቀርብባቸዋለን ብለን ባሰብናቸው አንዳንድ በኦሮሚያ አካባቢዎች ነው፡፡ ፍራቻው ሊከሰት የቻለው ከምርጫ 97 በኋላ ነው፡፡ በዚያን ወቅት ሕዝቡ ተቀጠቀጠ ታሰረ፣ ተደበደበ ተሰቃየ፡፡ ስለዚህ ፈራ፡፡ ለምሣሌ እኔና ስድስት የኦፌዴን ሰዎች በተመረጥንበት በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ለምንድነው እነርሱን የመረጣችሁት ተብለው ኢሕአዴግ ቀጠቀጣቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ኦነግ ናችሁ ብለውም ተሰቃይተዋል፡፡ ኦነግ እንዳልሆኑ ግን ኢሕአዴግ ራሱ ያውቃል፡፡ ግን በዚህ ምርጫ ልናሸንፍባቸው የምንችልባቸውን ሰዎች ማግለል በመሆኑ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሕዝቡ ለእኛ እጩ ሆኖ  ሊመዘገብ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ለመመረጥ የሚቀርበው አብዛኛው ሰው የኢሕአዴግ ብቻ በመሆኑ ቀጣዩ ምርጫ የኢህአዴግ ብቻ ነው ለማለት የደፈርኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በዚህ ምርጫ እንደቀድሞው እጩዎችን ማቅረብ አልቻላችሁም ማለት ነው?

አቶ ቡልቻ፡-
የጠየቅነው ሰው ሁሉ ፈራ፡፡ ምንአልባት ከሺህ አንዱ ነው እሺ ያለው፡፡ ይህም ይበዛል ከአምስት ሺው አንዱ ብቻ እሺ ብሎ እጩ ሆኖ ሊመዘገብ ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል እንጂ የጠበቅነውን ያህል እጩ አላገኘንም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በዚህ ምርጫ ያሰባችሁትን ያህል እጩ ተወዳዳሪ አላገኛችሁም ማለት ነው? ግን ምን ያህል እጩ አቅርባችኋል፡፡

አቶ ቡልቻ፡-
በጭራሽ አላገኘንም፡፡ ያቀርብነውም እጩ በጣም ትንሽ ነው፡፡ እሺ ያለም ሰው የለም፡፡ ፍርሃት አንድ ነገር ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ሊመዘገቡ ያልቻሉት ሰባት ስምንት የሚሆኑ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የምርጫ ቦርድ እኛ ያሰብነው የምርጫ ቦርድ አለመሆኑና ምክንያቱም ይሄ ምርጫ ቦርድ ኢሕአዴግ ብቻውን የመረጠው ነው፡፡ በሌላ አገር ምርጫ ቦርድ የተቃዋሚዎችንም አመለካከት ያንፀባረቃል፡፡ የእኛ ግን በፍፁም የተቃዋሚዎችን አመለካከት የማያሳይ ነው፡፡ ይሄ ቦርድ ስለኢሕአዴግ ብቻ ነው የሚጠነቀቀው፡፡ ተቃዋሚዎችን ጉዳዬ ብሎ አይመለከትም፡፡

ሪፖርተር፡- ቦርዱ ገለልተኛ መሆኑን አሳውቋል የምሠራውም ገለልተኛ ሆኜ ነው በማለት እየተናገረ ነው፡፡

አቶ ቡልቻ፡-
እንዴት ገለልተኛ ይሆናል? የሾመውን ሃይል ፍላጐት ነው የሚያንፀባርቀው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ችግር ካለ በአግባቡ ለቦርዱ በማሳወቅ አለብን የምትሉት ችግር እንዲቀረፍ ያደርጋችሁት ጥረት አለ?

አቶ ቡልቻ፡-
ብዙ ጊዜ አድሏዊ መሆናቸውን በደብዳቤ ጭምር ደጋግመን አሳውቀናቸዋል ያገኘነው መልስ ግን የለም፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ቦርዱ አዲስ ነው፡፡ ምንም ቢሆን ከድሮው ቦርድ ይሻላል ብለን ነበር፡፡ አንፃራዊ ለውጥ ቢኖርም ብዙ የተለየ ነገር አላየንም፡፡

ሪፖርተር፡- በመጪው ምርጫ እጩ ሆኖ ለመቅረብ ሕዝቡ የፈራባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ ብለውናል፡፡ የምርጫ ቦርድ አድሏዊነት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ሌላ ሌሎች ምክንያቶች ናቸው የምትሉት ምንድነው?

አቶ ቡልቻ፡-
ሌላው በመላ አገሪቱ ያሉ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ቢሮዎች የሚሠሩ አግባብነት የሌላቸው ሥራዎችን ነው፡፡ እነዚህ ቢሮዎች እጩ አድርገን ያቀረብናቸው ሰዎች እድሜህ አልደረሰም እያሉዋቸው ይመልሱብናል፡፡ በህጉ የተመለከተው ከ21 ዓመት በላይ የሆነው ሰው እጩ ሆኖ መቅረብ ይችላል፡፡ ይህንን ህግ ተከትለን 25 እና 26 ዓመት ወጣቶችን ስናቀርብ እድሜህ አልደረሰም ይሉብናል፡፡

እነዚህ እጩ ሆነውን በቀረቡት ሰዎች በዚያ አካባቢ ተወልደው ያደጉ ናቸው፡፡ ግን የምርጫ ቢሮዎች እዚህ አልተወለድክም ይሏቸውና ከቀበሌ መታወቂያ አምጡ ይባላሉ ቀበሌ ሲሄዱ ደግሞ ቀበሌው አናውቅህም ይለዋል፡፡ ይህ የሚሆነው እንዳይመረጥ ለማድረግ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ችግር የገጠማቸው በርካታ ዕጩዎች አሉን፡፡

አንዳንድ ቦታ ለምሳሌ ያያ ጉለሌ የሚባል ወረዳ ውስጥ ፓርቲያችን እጩ ያደረጋቸው ወጣቶች ለመመዝገብ ሲሄዱ እናንተንማ ስንፈልጋችሁ ነበር ብለው አራት ወጣቶችን አሰሩብን፡፡ ስምንቱ ደግሞ የአራቱን ወጣቶች መታሰር ሰምተው ሸሹ፡፡ ወጣቶቹ የታሰሩበትን ምክንያት ስንጠይቅ ድሮ ወንጀል ሰርታችኋል በሚል ነው፡፡ በምርጫ ሕጉ ላይ ግን ወንጀል ሰርቶ የታሰረ ካልሆነ በስተቀር ወይም ወንጀል እየሰራ ካልታየ በስተቀር ወንጀል ሰርተሃል ተብሎ ከምርጫ አይታገድም፡፡ ሕጉ አይፈቅድም፡፡ ይባስ ብሎም የእኛ የሁኑ ሰዎችን ስለሚያውቁ ሊመዘገቡ ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲሄዱ ቢሮው ተዘግቶባቸዋል፡፡ ይህም የሚሆነው ደጋፊዎቻችን በምርጫው ተሳታፊ እንዳይሆኑ ነው፡፡

እጩ ሆነው ለመመዝገብ የሄዱ የእኛ ሰዎች ሲጠይቁ ምርጫ መወዳደር እንደምትፈልግ ከሆነ ማመልከቻ አምጣ የሚል ነበር፡፡ ማመልከቻውን ጽፎ ሲመለስ ቢሮው ተዘግቶ ይጠብቀዋል፡፡ በዚህ ሂደት ምዝገባው ያመለጠው ሰው አለ፡፡ እንዲህ አይነትና ሌሎችም ችግሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሁን የዘረዘርኳቸው ጥቂቶቹን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለመጪው ምርጫ ምን ያህል እጩ እናቀርባለን ብላችሁ ነበር ያቀዳችሁት?

አቶ ቡልቻ፡-
በዚህ ምርጫ ቢያንስ ቢያንስ ከቀበሌ ምክር ቤት ጀምሮ እስከ ፓርላማ ድረስ ፓርቲያችንን ወክለው እጩ ተወዳዳሪ ይሆናሉ ብለን አስበን የነበረው ወደ 6ሺህ እጩ ነበር፡፡ ይህ ቁጥር ብዙ ሊመስል ይችላል፡፡ ቁጥሩ የበዛው በአንድ ቀበሌ 300 የምክር ቤት አባላት ስለሚያስፈልጉ ነው፡፡ በአንድ ወረዳ ደግሞ ከ180 በላይ ነው፡፡ እነዚህ እጩዎችን እናቀርባለን ብለን ያሰብነው ደግሞ ከሁሉም ኦሮሚያ ሳይሆን በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በእቅዳችሁ መሰረት ከ6ሺው ምን ያህል እጩዎች ለውድድር ማቅረባችውን አረጋግጣችኋል?

አቶ ቡልቻ፡-
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስካሁን አልነገረንም፡፡ ለምሳሌ በአንድ አካባቢ 25 እጩዎች ያቀረብንበት አለ፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ስላቀረብናቸው እጩዎች ዛሬ ያገኘነው መረጃ አንዱ ብቻ ፓርቲያችንን ወክሎ ተወዳዳሪ እጩ ሆኖ የተመዘገበላችሁ ተባልን፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ቡልቻ፡-
ቀደም ብዬ በጠቀስኩት ምክንያቶች ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ወረዳው ሳያስመዘግባቸው ቀርቶ አንድ ብቻ መዝግበንላችኋል ሲሉ የእኛን እጩዎች በሰበብ አስባቡ እንዳይወዳደሩ ያደርጓቸዋል፡፡ ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚፈልጉት የኢሕአዴግ ሰው ብቻ እንዲመዘገብላቸው ነው፡፡ በአንድ ወረዳ ከተቃዋሚዎች ጥቂት ሰዎችን ብቻ በመመዝገብ ምርጫው እንዲካሄድነው የሚፈለገው፡፡ ከተቃዋሚዎች ቢበዛ ሁለት ሦስት ብቻ እንዲሆን የተፈለገው፡፡ እንደውም ለእኛ ፓርቲ በአንድ ወረዳ ሦስት እጩዎች የተመዘገቡልን አይመስለኝም፡፡ በጠቅላላው ተቃዋሚ በዚህ ምርጫ እንዲገባ የተፈለገ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በተደረገ ክርክር እነዚህ የምታቀርቧቸው ምክንያቶችና በተለይ ደግሞ ታስረውብናል ለምትሏቸው አባሎቻችሁ ስለመታሰራቸው መረጃ የላቸውም ዝም ብለው ነው የሚጮሁት በማለት ኢሕአዴግ ይወቅሳችኋል፡፡ ለዚህ መረጃ አላችሁ?

አቶ ቡልቻ፡-
መረጃ አለን፡፡ በየቀኑ ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አሳውቀናል፡፡ የታሰሩበትን ቦታ ቀንና ሌሎች መረጃዎችን ለምርጫ ቦርድ ያሳወቅንበትም ደብዳቤ ግልባጭ በእጃችን አለ፡፡ አስር ጊዜ የፃፍንበት ደብዳቤ ኮፒ አለን፡፡ ያለመረጃ ነው የሚናገሩት የተባለውን አንቀበልም፡፡ መረጃ የላቸውም የሚባለውን ነገር በቴሌቪዥን ስመለከት አዝኛለሁ፡፡ በተለይ የምርጫ ቦርዱ ተወካይ እኛን ምንም መረጃ የላቸውም በማለት የኛ አቤቱታ ጅምላ ውንጀላ በማለት የሰጡት አስተያየት በጣም አሳዝኖኛል፡፡ በነገራችን ላይ አሁንም በእስር ላይ ያሉ አባሎቻችን አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርቲያችሁ በአዲስ አበባ ያቀረባቸው እጩዎች አሉ?

አቶ ቡልቻ፡-
አዲስ አበባ ችግር የለም፡፡ አዲስ አበባ ውድድር ላይ እንዳንገባ በግልጽ የሚከለክል የለም፡፡ የዓለም አቀፍ ሰዎች ስላሉና የበላዮችም እዚሁ ስለሆኑ በገጠር የገጠመንን አይነት ችግር አልገጠመንም፡፡ ፊት ለፊታቸው እንደዚህ ዓይነት ወንጀል አይሠራም፡፡ በአዲስ አበባ ፓርቲያችን ለፓርላማ ብቻ እስከ አስር የሚደርሱ ተወዳዳሪዎችን ያቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ የወረዳ፣ የቀበሌና የማሟያ ምርጫ የምትጠብቁት ውጤት ምንድነው?

አቶ ቡልቻ፡-
እኛ ከዚህ ምርጫ የምንጠብቀው ነገር የለም፡፡ አሁን ባዶ እጃችንን ወጥተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ቡልቻ፡-
እጩዎችን ለማቅረብ ያደረግነው ጥረት እንዲበላሽ ተደርጓል፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት የእኛ ሰዎች ፈርተው እንዲቀሩ ተደርጓል፡፡ ደፍሮ የቀረበውም ሲመጣ እንዳይመዘገብ የተለያዩ ምክንያቶች ስለተሰጡ የእጩዎቻችን ቁጥር በማነሱ ብዙ የሚጠበቅ ውጤት የለም፡፡ ሰው ስላልተመዘገበልን ምን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- በሚዲያ የቅስቀሳ ሰዓት አልተደላደለላችሁም?

አቶ ቡልቻ፡-
አልነገሩንም፡፡ በቀደም እለት በቃል ሰዓት ይመደብላችኋል፡፡ በዚያ በተመደበላችሁ ሰዓት ትናገራላችሁ ቅስቀሳ ታካሂዳላችሁ ብለውናል፡፡

ሪፖርተር፡- የወረዳና የቀበሌ እንዲሁም የማሟያ ምርጫ ከ1997 ምርጫ ጋር አነፃፅረው ሊነግሩኝ ይችላሉ?

አቶ ቡልቻ፡-
ያለፈው ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው የተሻለ ነው፡፡ ሰው ድምፅ እስኪሰጥ ድረስ ያለው ሂደት የተሻለ ነው፡፡ ልመረጥ ብሎ የቀረበ ሁሉ ይመዘገብ ነበር፡፡ ሕዝቡ ይወስን ብለው ይመዘግቡ ነበር፡፡ አሁን ግን እንቢ አሉ፡፡ ይህ ትልቅ ልዩነት ነው፡፡ ሌላው በቅስቀሳ ጊዜ እንደልባችን ተንቀሳቅሰን ተናግረናል፡፡ እርግጥ የሚዲያ ሰዓት እንደልባችን አላገኘንም፡፡ ሆኖም ግን የተወሰነ ሰጥተውን ነበር አሁን ግን የሚሆነው አይታወቅም፡፡

ሪፖርተር፡- በ1997ቱ ምርጫ ተቃዋሚዎች በጋራ የምትንቀሳቀሱበት አሰራር ትከተሉ ነበር? የጋራ ምክክር መድረክም ነበራችሁ፡፡

አቶ ቡልቻ፡-
የጋራ ምክክር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከተቃዋሚዎች ጋርስ በምርጫው ዙሪያ በጋራ የምትሰሩበት አሰራር አለ?

አቶ ቡልቻ፡-
ከዚህ በፊት ከህብረት ጋር ስላለው ጠቅላላ ችግር መግለጫ አውጥተን ነበር፡፡ አሉብን ያልናቸው ችግሮች ዘርዝረን ለምርጫ ቦርድ አቅርበናል፡፡ የምርጫ ቦርድ ይህንን ችግር ካልፈታ ማን ይፈታዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዘንድሮ የወረዳና የቀበሌ እንዲሁም የማሟያ ምርጫ የተቃዋሚዎች ተሳትፎ አነስተኛ ነው ማለት ነው?

አቶ ቡልቻ፡-
በኦፌዴን በኩል እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በስተቀር፡፡

ሪፖርተር፡- ለምርጫ የሚወዳደር ፓርቲ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግለታል፡፡ ይህንን አግኝታችኋል?

አቶ ቡልቻ፡-
በኢትዮጵያም ሆነ በአለም አቀፍ ሕግ የታወቀ ተቃዋሚ ፓርቲ ሁሉ ገንዘብ ይሰጠዋል፡፡ የበጀት ድጎማ ይደረግለታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በግልፅ እንቢ አለ፡፡ እስካሁን አላገኘንም፡፡ በምርጫ 97 የውጭ አገር እርዳታ ሰጪዎች እቃ ገዙልን፣ (እንደ ኮምፒውተር ድምፅ ማጉያ”፡፡ ካሽ አልሰጡንም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ያሉዋቸው ተሳትፎ አነስተኛ ነው፡፡ በተለይ በቅርቡ ከወርቅ መጭበርበር ጋር በተያያዘ ስለተፈጠሩ ችግሮችና የኑሮ ውድነትን በተመለከተ እንደ ሕዝብ ተወካይነታቸው ሃላፊነታቸውን አልተወጡም እየተባለ ነው፤

አቶ ቡልቻ፡-
የኢትዮጵያ ፓርላማ እንደሌላው አገር ፓርላማ አይደለም፡፡ በአፍሪካና በአሜሪካ ብዙ ዘመን ኖሬያለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ፓርላማ ከሌላው አገር የተለየ ነው ያልኩት መንግሥት ሲሠራ ፓርላማን ላስፈቅድ አይልም፡፡ አሁን ለምሣሌ ኢትዮጵያ ወደ ዳርፉር ሂሊኮፕተር ላከች የሚል ዜና ሰምተናል፡፡ ይሄ ጉዳይ በቀጥታ ፓርላማን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ የሚያወጣበት ነው፡፡ ግን ፓርላማ አልተጠየቀም፡፡ ስለኑሮ ውድነት ፓርላማ ውስጥ አንድ ጊዜ ተናግረናል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ስለጉዳዩ ሪፖርት አይቀርብልንም፡፡ በሌላ አገር መንግሥት ለፓርላማ ሪፖርት ያቀርባል፡፡ እኛ አገር ግን አይቀርብም፡፡

የወርቁን ጉዳይ በተመለከተም በጋዜጣ ነው ያነበብኩት፡፡ መንግሥት ለፓርላማው ያቀረበው ሪፖርት የለም፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲከሰት ሪፖርት መቅረብ ነበረበት፡፡ የኢኮኖሚው ሁኔታ ምድነው ተሻሽሏል? ተባብሷል”. የዋጋ ንረት ቀንሷል፡፡ ጨምሯል? ሪፖርት የለም፡፡ በጥቅሉ የእኛ አገር ፓርላማ ከመንግሥት የተገለለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ጉዳይ ለምን መንግሥትን ብቻ ተጠያቂ ታደርጋላችሁ? እንደ ፓርላማ አባልነታችሁ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትችት ለምን አታቀርቡም? የግድ ፓርላማ ውስጥ ብቻ መሆን አለበት?

አቶ ቡልቻ፡-
በምን መድረክ እናቅርብ፡፡ በፓርላማ በቂ ጊዜ የለንም፡፡ ለምሳሌ እኔ በፓርላማ ውስጥ የሚሰጠኝ ሁለት ደቂቃ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ትናገራለህ እንዳንናገር አፋችን ታስሯል፡፡ በፓርላማ አንድ የፓርላማ አጀንዳ ኮሚቴ የሚባል አለ፡፡ ለፓርላማው አጀንዳ የሚያቀርብ ማለት ነው፡፡ እዚያ ኮሚቴ ውስጥ በጣም ብዙ የኢሕአዴግ ሰዎች አሉ፡፡ ተቃዋሚዎች በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ ማናቸውም ጉዳይ እነርሱ ካልፈቀዱ በስተቀር ወደ ፓርላማ አይቀርቡም፡፡ እኛ ያለን ትንሽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወር አንዴ ይመጣሉና ጥያቄ መጠየቅ ትችላላችሁ በሚባልበት ጊዜ የሚቀርብ ጥያቄ ብቻ ነው፡፡ እሳቸው ይመጣሉ ለጥያቄው መልስ ሰጥተው ይሄዳሉ፡፡ ስለአመላለሳቸው ስለሰጡት መልስ መናገር ብንፈልግ ወይም ተጨማሪ ጥያቄ ለመጠየቅ እድል አይሰጠንም፡፡ ሚኒስትሮችም ሲመጡ እንዲሁ ነው፡፡ እንደሌላው አገር ፓርላማ በተለይ ተቃዋሚዎች ለመናገር እድል የላቸውም፤ የተመሰቃቀለ ነው፡፡

በሌላ አገር ፓርላማ ሲያስፈልግ አስፈቅዶ አንድና ሁለት ሰዓት መናገር ይችላል፡፡ እዚህ ሁለት ደቂቃ ትናገራለህ፡፡ የአጀንዳ ኮሚቴው የፈለገውን ነው የሚያቀርበው፡፡ ምንም እድል የለንም፡፡ ሌላ መናገሪያ መድረክም የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤት ስልጣን ከፍተኛ እንደሚሆን ይነገራል ትልቁ ስልጣን ወደ ወረዳና ቀበሌ አካባቢ ይወርዳል ስለሚባለው ጉዳይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

አቶ ቡልቻ፡-
በ2002 ዓ.ም ዋና ሆኖ የሚገኘው ይሄ አሁን የሚቋቋመው የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ ከፍተኛ የሆነ ስልጣንም የሚኖረው እነርሱ ጋር ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  በዚህ ትልቅ የስልጣን አካል ነው በሚባለው የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤቶች ውስጥ ምን ያህል ወንበሮች ወይም ምን ያህል ድርሻ ይኖረናል ብላችሁ ታስባላችሁ?

አቶ ቡልቻ፡-
ስድስት ሺህ ከሚገመቱ አንድ መቶ ሰው አላቀረብንም፡፡ በእነዚህ ምክር ቤቶች ሊኖረን የሚገባው ተሳትፎ ያንሣል፡፡ ይህም የሆነው በጫና እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም፡፡ ስለሌሎች ተቃዋሚዎች ባላውቅም በዚህ ምርጫ ተመሳሳይ የሆነ ችግር እንዳጋጠማቸው እገምታለሁ፡፡ ኢሕአዴግ ግን የፈለገውን ያህል አቅርቧል፡፡

ሪፖርተር፡-  በቀጣዩ ምርጫ ያላችሁ ስጋት ይህ ከሆነና ምርጫው ኢሕአዴግ እንደፈለገ የሚሆንበት ነው ካላችሁ ወደፊት የፓርቲዎችም ሆነ የአገሪቱ ፖለቲካዊ የሁኔታ ምን ሊመስል ይችላል?

አቶ ቡልቻ፡-
አሁን ይሄ ነው ብዬ የምመልሰው ነገር የለኝም፡፡ የወደፊቱ ሁኔታ ያሳስበኛል፡፡ ነገሩ ራሱ ወዴት እንደሚሄድም አላውቅም፡፡ በዚህ ምርጫ የታዘብነው ነገር ኢሕአዴግ እኔ ብቻ ካልተመረጥኩ የሚለውን አቋሙን አጠናክሯል፡፡ እኔ በጣም አዝኛለሁ፡፡

ሪፖርተር፡-  የውድድር መድረኩ ሁሉንም በእኩልነት እንዲያስተናግድ ከኢህአዴግ ጋር በተናጠል ያደረጋችሁት ድርድር የለም? ጥያቄስ አቅርባችሁለታል?

አቶ ቡልቻ፡-
ባለፈው ዓመት የፓርቲዎች የጋራ መድረክ የሚባል ነበር፡፡ አሁን የለም፡፡ ምክንያቱም ባለፈው ዓመት ኦፌዴን፣ ህብረትና ቅንጅት በተለያየ ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር እየተወያየን ቀርቦ የነበረን ሀሳብ ተቃውመን ከውይይቱ ወጣን፡፡ በእንዲህ ዓይነት ውይይት ነገሩ ካልተስማማን መውጣት በየትም አገር የተለመደ ነው፡፡ የትግልም ዘዴ ነው፡፡ አንድን ሃሳብ የሚቀበልህ ሲጠፋ ለቀህ መውጣት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር የተለመደ ነው፡፡ ወጥተህ መመለስ ግን ትችላለህ፡፡ ኢሕአዴግ ግን እኛ ስንወጣ ሁለተኛ ከእናንተ ጋር አንነጋገርም አለ፡፡ ለመነጋገር ከፈለጋችሁ ይቅርታ ጠይቁ አሉን፡፡ እኛ ጥፋት ሳንሠራ እንዴት ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ሳንግባባ በመቅረታችን የጋራ መድረኩ ከተቋረጠ 15 ወራት ሆኖታል፡፡ በዚህም ምክንያት በምርጫ ጉዳይ በጋራ ለመስራት የታሰበ ነገር የለም፡፡ አልተነጋገርንም፡፡ ለውይይት ብለን ሳናጠፋ ይቅርታ ብንጠይቅ የመረጠን ሕዝብስ ምን ይለናል? በሞራል ደረጃስ ሳናጠፋ ይቅርታ መጠየቁ አግባብ አይደለም፡፡ የሚል መልስ ሰጥተናል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ዓይነት ፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ወደፊት መደረግ አለበት ብላችሁ የምታቀርቡት መፍትሔ አለ?

አቶ ቡልቻ፡-
ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አማራጭ የሌለው የወደፊት ጎዳና ነው፡፡ ዴሞክራቲክ ለመሆን መምረጥ መመረጥ አለብን፡፡ ዴሞክራቲክ ከመሆን ውጪ የምንመርጠው ነገር የለም፡፡ ጮማ ነው መንገዱ አንድ ፓርቲ ብቻ እኔ እበቃችኋለሁ አውቅላችኋለሁ፡፡ እኔን ብቻ መልሳችሁ ምረጡኝ ማለት ለኢትዮጵያ በጣም መጥፎ ነው፡፡ ይህንንም ብዙ ጊዜ ተናግረናል፡፡ ከሁሉም የተውጣጣ ውክልና መኖር አለበት፡፡ በዚህ መልክ መሄድ ሳይቻል አንድ ፓርቲ ብቻ የኢትዮጵያን ጉዳይ ለማወቅ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድር ቅይጥ ፓርቲ መሆን አለበት የሚል እምነት አለን፡፡ አንድ ፓርቲ ብቻ በየአራትና አምስት አመቱ እኔ እመረጣለሁ ሌላ ሰው አይገባም የሚለው ለአገራችን እጅግ አስጊ ስለሆነ ኢሕአዴግ ክፍት ማድረግ አለበት፡፡ ተቃዋሚዎች ይመዝገቡ፡፡ ሕዝቡም የሚፈልገውን እንዲመርጥ እስካልተደረገ ድረስ የተረጋጋ ፖለቲካ ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ ይህ እንዳይሆን ነፃ ለሆነ ምዝገባ መንግሥት በሩን ይክፈት ለቅስቀሳ መንገዱን ይክፈት፡፡

ሪፖርተር፡- በምርጫ 97 በምርጫ ተሣታፊ የነበሩ ፓርቲዎች መገናኛ ብዙሃን ሲከራከሩ ነበር በዚህ ምርጫ እንደዚያ ያለ ነገር አለ?

አቶ ቡልቻ፡-
ምርጫው የቀረው ጊዜ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ ነው፡፡ ግን ፕሮግራሞቻችን ለማስተዋወቅና ቅስቀሳ ለማድረግ ምን ያህል ሰዓት እንኳን እንደተመደበልን አያውቅም፡፡ ክርክሩም እንደበፊቱ አይነት ይሁን አይሁን ወይም ይኑር አይኑር ምንም መረጃ የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ብለው በተካሄዱ ምርጫዎች በተለይም በምርጫ 97 ከምርጫው ጋር በተገናኘ የውይይት መድረክ ሲዘጋጅና ትምህርትና ቅስቀሳዎችን ሲያደርጉ የነበሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ነበሩ በዘንድሮ ምርጫስ?

አቶ ቡልቻ፡-
ባለፈው ምርጫ በዚህ ጉዳይ ይሰሩ የነበሩ ብዙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ በኔ በኩል እስካሁን ምንም አልሰማሁም፡፡ እነርሱም ደነገጡ መሰለኝ ጠፍተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ የደረሰኝ መረጃ የለም፡፡ በኛ በኩል አንድ ፓርቲ እባካችሁ መድረክ አዘጋጁልኝ ማለት አንችልም፡፡
 
< Prev   Next >