| ብሔራዊ ባንክ ምስጥ የበላው እንጨት |
|
|
| Sunday, 02 March 2008 | |
|
(በአባዋሪ ጅብሪል)
በሪፖርተር ጋዜጣ ጥር 11 ቀን 2000 ዓ.ም.ተሟገት ገጽ ላይ ባንኩ ከገንዘብ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ያለበት ችግር ከተገለጸ በኋላ በመንግስት ችግሩ እንዴት ሊፈጠር እንደቻለና ስለ አሰራሩ የባንኩ መሪዎች መልስና ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጡ ይጠየቃሉ፡፡ መጀመሪያውኑ ሥራውን በአግባቡ መከታተልና መቆጣጠር ስላልተቻለ የተቀመጠ ትክክለኛና በቂ መልስ አልነበረም፡፡ መጀመሪያውኑ ሥራውን በአግባቡ መከታተልና መቆጣጠር ስላልተቻለ የተቀመጠ ትክክለኛና በቂ መልስ አልነበረም፡፡ ገዢዎቹ በጉዳዩ ላይ የባንኪንግና የውጪ ምንዛሬ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርን በተጠየቁት ጥያቄዎች ላይ አስቸኳይ መልስ እንዲያዘጋጁላቸው ይጠይቃሉ፡፡ እሳቸውም የተጣለባቸውን ግዳጅ ለመወጣት የከረንሲ መምሪያ ሥራ አስኪያጅንና የሕግ አገልግሎት መምሪያ ሥራ አስኪያጅን ይዘው በእረፍት ቀናት ጭምር ገብተው አለን የሚሉትን መልስ አዘጋጅተው ለመሪዎቹ አቅርበዋል፡፡ መሪዎቹም ያዘዙት ሪፖርት ከተዘጋጀላቸው በኋላ (ከፊል ሪፖርት ነው በተቀሩት ላይ እየተሰራ ነው) ለሚመለከተው አካል አቅርበውሩ ደግሞ ቀጥሎ ምን ይመጣ ይሆን? ብለው በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ መንግሥት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ እንዲቻል የባንኩ መሪዎች በአፋጣኝ መልስ እንዲሰጡ በመጠየቁ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ማንም አይጠይቀንም ብለው በሀገር ሀብትና ንብረት ላይ እንደፈለጋቸው ሲያዙ ለነበሩና የተጣለባቸውን ሀላፊነት ወደጎን ጥለው ለተቀመጡ ሁሉ ትልቅ መልእክት አለውና ክትትሉ በተጀመረው መንገድ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ስለ ችግሩ መልስና ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት ጥቂት የባንኩ ሀላፊዎች ብቻ ናቸውና እነርሱ የሚሰጡት መልስ ስለ ሁኔታው ቦርዱም ሆነ መንግስት ሙሉ እይታ እንዳይኖራቸው ያደርጋል የሚል ስጋት አለን፡፡ ቦርዱም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በባንኩ መሪዎች መመሪያ እንዴት እየተጣሰ ይሰራ እንደነበር ለማወቅ ከሚያስረዱት ዶክሜንቶች ውስጥ ለምሳሌ ያህል ሁለቱን ብቻ እንኳን ቢመለከት እያልን ያለነው ነገር ትክክል መሆኑን በደንብ መረዳት ያስቸለዋል፡፡ አንደኛው የባለ 50 እና 100 ብር ኖቶች ለቃጠሎ የሚሆን ቆጠራ የሚካሄደው 100 በመቶ ሲሆን ይሄ መመሪያ ተጥሶ 50 በመቶ ቆጠራ እንዲካሄድ ከተወሰነ በኋላ 1 ቢሊዮን 252 ሚሊዮን ብር በፕሮጀክት ስራ ከተቆጠረ በኋላ በውስጡ 9 ሚሊዮን ብር አዲሱ ኖት ሲገኝ ወደ መመሪያው ወይም ትክክለኛው አሰራር ለመመስ እንዳሰቡና ውሳኔ እንዲሰጣቸው እንደሚፈልጉ ስሚናገረው የባንኪንግና የውጪ ምንዛሬ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለባንኩ ምክትል ገዥ ጥቅምት 17 ቀን 1999 ዓ.ም. የጻፉትን ደብዳቤ ወስዶ ቢያይ፣ ሁለተኛው የውስጥ ኦዲት መምሪያ ከገንዘብ መረጣና ቆጠራ ጋር በተያያዘ በተከሰተው ስርቆት ላይ የሰራውንና በአመራር ላይ የነበረው ችግርና ስለ አሰራሩ/ System/ መጣስ የሚገልጸውን ሪፖርት ዋናውን በመመልከት የባንኩ መሪዎች በመምሪያው ውስጥ ከተከሰቱት ችግሮች ጋር በተያያዘ ለተጠየቁት ጥያቄዎች ካዘጋጁት መልስ ጋር ቢያነጻጽረው የበለጠ ይረዳዋል ብለን እናምናለን፡፡ በጣም የሚያሳዝነው የባንኩ መሪዎች የኦዲት ሪፖርቱን ተከትለው ከዋና ክፍሉ ውስጥ የተጠረጠሩ ሦስት ሰራተኞችን ነጥለው ሲያባርሩ የአሰራር ሲስተሙን ሲቀይሩ የቁጥጥር ስርአቱን ባለመቀየራቸው በተፈጠረው ክፍተት ለተሰራው ወንጀል ገዢዎቹ ራሳቸው ጭምር ተጠያቂነት ቢኖርባቸውም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አንድም የአመራር አባል ተጠያቂ አልተደረገም፡፡ ከዝውውር ውጪና ወደ ዝውውር የሚመለሱትን የብር ኖቶች በእጅና በማሽን እንደሚቆጠሩ ሆኖም ግን ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ በተጀመረው አዲስ አሰራር ምክንያት ከዝውውር ውጪ ነው ተብሎ ለመቃጠል ከተቀመጠው ብር ውስጥ የናሙና ቆጠራ ሲካሄድ 85 ከመቶ የሚሆነው ወደ ዝውውር መግባት የሚችል ሆኖ እንደተገኘ መግለጻችን ይታወቃል፡፡ ጉዳዩን የባንኩ መሪዎች አስቀድመው የሚያውቁት ቢሆንም ተገቢውን እርምጃ በጊዜ ባለመውሰዳቸው መቃጠል የሌለበት ብር ሲቃጠል ነበር፡፡ በቅርቡ የባንኩ መሪዎች ጉዳዩን እንደገና ከተመለከቱት በኋላ መቃጠል አለበት ተብሎ የተቀመጠው ብር በሙሉ እንደገና ይቆጠር የሚል ትእዛዝ በማስተላለፋቸው ከየካቲት 4 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ እንደገና በመቆጠር ላይ ነው፡፡ ይሄ የማስተካከያ ስራ ጥሩ ቢሆንም ከዚያ በፊት ግን የተሰራ ስህተት አለ፡፡ ባንኩ በ1998 ዓ.ም. እና በ1999 ዓ.ም. በድምሩ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ከዝውውር ውጪ የሆነ ነው ብሎ እንዲቃጠል አድርጓል፡፡ ይሄ ትክክለኛውን አሰራር ተከትሎ የተሰራ ከሆነ ችግር የለበትም፡፡ ሆኖም ከላይ እንደገለጽነው የባንኩ መሪዎች ግዴለሽነትና ብዛትን እንጂ ጥራትን ሳይመለከቱ በወሰኑት ውሳኔ የተነሳ በርካታ ገንዘብ ያለ አግባብ ተቃጥሏል፡፡ ከየካቲት 4 ቀን 2000 ጀምሮ እየተሰራ ባለው ድጋሚ ቆጠራ በናሙና ቆጠራ ከተገመተው 85 ከመቶ በላይ በዝውውር ላይ መዋል የሚችል ብር ሆኖ ሊገኝ ችሏል፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት ከ1998 እስከ 1999 ዓ.ም. ባሉት ሁለት አመታት ውስጥ ከተቃጠለው ብር ውስጥ የተቀረው በትክክል የተቃጠለ ነው ብለን እናስብና በጣም በትንሹ 1 ቢሊዮን ብሩን ብቻ ወስደን ብናይና ከዚህ ውስጥ በተገኘው የናሙና ቆጠራ መሰረት ከ85 ከመቶው በላይ በዝውውር ላይ መዋል የሚችል ከሆነ የባንኩ መሪዎች ያለ አግባብ ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲቃጠል አድርገዋል ማለት ነው፡፡ መሪዎቹ የወርቁ ጉዳይ ከመጣ በኋላ ተደናግጠውም ቢሆን የተሰራውን ስህተት ለማረም ቢሞክሩም (ሙሉ ለሙሉ መፍትሄ ገና አላገኘም) አለአግባብ እንዲቃጠል ለተደረገው ብር ግን ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ ከመሆን አያድናቸውም፡፡ ምክንያቱም የተቃጠለው ብር የአዲስ አበባ አስተዳደር የሚያስወግደው ቆሻሻ ሳይሆን አገሪቱ በርካታ ሚሊዮን ዶላር አውጥታ ያሳተመችው የሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡ የባንኩ መሪዎች ከገንዘብ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ያለባቸውን የብቃት ችግር ለጊዜው በዚህ ትተን ከአዲሱ ህንጻ ኮንትራትና ግንባታ ጋር በተያያዘ የነበረባቸውንና አሁንም ያለባቸውን በሚሊዮን የሚቆጠር ብር የማባከን ልምድ አንድ በአንድ ለማየት እንሞክር፡፡ ባንኩ ያለበትን የቢሮ ችግር ለመቅረፍ አንድ ዘመናዊ ህንጻ ለመገንባት የታቀደው በ1970ዎቹ መጀመሪያ ነበር፡፡ በኋላም ይሄ ሀሳብ በሰፋ ሁኔታ ታይቶ ማሰልጠኛ ተቋሙንና የባንኩን የስራ ክፍሎች የሚያካትት (Central Service Complex) ለመገንባት ተወሰነ፡፡ ለዚሁም ባንኩ እ.ኤ.አ. በሚያዚያ 1985 የዲዛይን ጨረታ ወጥቶ እ.ኤ.አ. በታህሳስ 1985 አሸናፊ ከሆነው ከስለሺ ኮንሰልትስ የአማካሪ መሀንዲሶችና አርክቴክቶች ድርጅት ጋር ስምምነት አደረገ፡፡ ከዚያም ለ6 አመታት ስራው ከተቋረጠ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1991 ዲዛይኑ ጸድቆ እ.ኤ.አ. በነሐሴ 1992 ለዋና ስራ ተቋራጭነት ጨረታ ወጥቶ ሎዊጂ ቫርኔሮ ኩባንያ አሸናፊ ቢሆንም ባንኩ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር የጨረታው አፈጻጸም እንደገና መታየት አለበት ብሎ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የግንባታው ጨረታ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ በሁለተኛው ጨረታ በርታ ኮንስትራክሽን አሸንፏል ተብሎ ስራው እ.ኤ.አ. በየካቲት 1994 ተጀመረ፡፡ በኮንትራቱ ስምምነት መሰረት በርታ ስራውን እ.ኤ.አ. በየካቲት 1997 ለማጠናቀቅ ተስማማ፡፡ ችግሩ የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው፡፡ መጀመሪያኑ በባንኩ ማኔጅመንት በኩል የረጅም ጊዜ እቅድ ችግር ነበርና ህንጻው ከታለመለት አላማ ይልቅ ለባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ብቻ ይሁን የሚል ሀሳብ በማምጣቱ የህንጻው ዲዛይን እንደገና እንዲለወጥ አድርጎ ህንጻው ይጠናቀቃል ተብሎ በታለመለት እ.ኤ.አ. በ1997 ተጨማሪ ስምምነት ከበርታ ጋር በመፈራረሙ ከፍተኛ ወጪ በባንኩ ላይ አስከትሏል፡፡ የህንጻውም ስራ በ1977 ዓ.ም. ጀምሮ ከ18 አመታት በኋላ በ1995 ዓ.ም. በልዩ ክብረ ወሰን ተጠናቀቀ፡፡ በዚህ ምክንያት ካዘገየ ህንጻካ የሚል ቅጽል ስም ሊወጣለት ችሏል፡፡ ህንጻው 11 ፎቆች” ግምጃ ቤቶች” ከ400 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል መሰብሰቢያ አዳራሽ” ካፍቴሪያ” የምግብ ማብሰያ”የማይሰራ ቢሆንም) የብር ማቃጠያ ክፍል” ባለ 5 ፎቅ የመኪና ማቆሚያ ያለው ነው፡፡ ህንጻው ከ80 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ወጥቶበት እጅግ ዘመናዊ በሆነ መልኩ ለመገንባት ቢታቀድም ከግንባታው በኋላ እየሰጠ ያለው አገልግሎትና መያዝ የሚችለው የሰራተኛ ብዛት ከባንኩ ሰራተኞች ጋር ባለመጣጣሙ ባንኩ በፊት የነበረበትንና የንግድ ባንክ የነበረውን ህንጻ በመንግስት ውሳኔ ከንግድ ባንክ ላይ ተረክቦ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ፈጽሞ ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ የስም ማዞር ሂደት ላይ ነበር፡፡ ህንጻው ወዳሉበት የተለያዩ ችግሮች ስናልፍ 1ኛ እና 2ኛ ፎቅ ከደንበኞችና ከሰራተኛው ቁጥር ጋር ሊጣጣሙ ባለመቻላቸውና የክፍሎቹን ሙቀት ሊቆጣጠር የሚችል ማሽን ስላልተገጠመላቸው ከፍተኛ ሙቀት (በተለይም በበጋ ወቅት) ስላላቸው ለደንበኞችና ለሰራተኞች ምቹ ሳይሆኑ እስካሁን ድረስ አሉ፡፡ ህንጻው የተለያዩ ዘመናዊ የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች ይኖሩታል ተብሎ ታቅዶ ነበር፡፡ የባንኩም ማኔጅመንት የደህንነት መጠበቂያ ማሽኖች ህንጻው ሲጠናቀቅ እንዳልተገጠሙለት እያወቀ በህንጻው ላይ እንደተገጠሙ አድርጎ ከጥቂት አመታት በፊት ባለ 5 ገፅ የአማርኛና ባለ 5 ገፅ የእንግሊዘኛ ሪፖርት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ከእነርሱም ውስጥ አንዳንዶቹሩ የእንቅስቃሴ መቆጣጠሪ መሳሪያ ”“ የመግቢያና መውጫ በሮች መቆጣጠሪያ (Access Control መቨቋ”ስቂ”“ ተሽከርካሪ አስተላላፊ (Vehicles’ Access Control System) እና የመፈተሻ መሳሪያ (Walk Through Metal Detection Equipment) ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ማሽኖች የባንኩ ማኔጅመንት በህንጻው ላይ እንዳልተገጠሙ እያወቀ ተገዝተው እንደተገጠሙ በማስመሰል ሪፖርት ያዘጋጀው ለምንድነው? ባንኩ የሌለውን ነገር እንዳለው አድርጎ በማቅረብ ዘመናዊ ለማስመሰል ወይስ ያወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለመሸፈንና ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን? ግልጽ መልስ የሚያሻው ይመስለናል፡፡ ባንኩ የእንቅስቃሴ መቆጣጠሪ መሳሪያ (Closed Circuit Television) በህንጻው ላይ ለማስገጠም ከጥቂት አመታት በፊት ማጥናት የጀመረ ሲሆን እንኳን ስራው ጥናቱ ገና ባልተጠናቀቀበት እንዲያውም በጣም እየተጓተተ ባለበት ሁኔታ መሳሪያው ተገጥሟል ብሎ ሪፖርት መጻፍን ምን አመጣው? በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በላይ መሄድ የሚቻል ቢሆንም በጥልቀትና በዝርዝር መግባቱ ለጊዜው አስፈላጊ ስላልሆነ ለአሁኑ በዚህ አቁመን ወደ ሌላው ጉዳይ እንለፍ፡፡ የባንኩ መሪዎችና ዳይሬክቶሬቱ ያለባቸው የማስተዳደር ብቃት ችግር ማለቂያ የለውምና በህንጻው ውስጥ የተሰራው የምግብ ማብሰያና ማዘጋጃ ክፍል”ለሽ”ሰሻስቃ) በርካታ ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ በተገዙ እጅግ በጣም ዘመናዊ በሚባሉ ሆቴሎችና በኢትዮጵያ ውስጥ በጥቂት ቦታዎች ብቻ በተተከሉ የምግብ ማብሰያ ማሽኖች የተገጠሙለት ሲሆን ምግብን ከማእድ ቤት ወደ ካፍቴሪያ ለማመላለስ የሚረዳ አነስተኛ አሳንሰር አለው፡፡ ነገር ግን የህንጻው ዲዛይን ሲሰራ የምግብ ማብሰያ ክፍል ሰርተው የጭስ ማውጫ ስላላዘጋጁለት ስራ ሊጀምር አልቻለም፡፡ በካፍቴሪያው ጣሪያ በኩል የጭስ ማውጫ ለመስራት ደግሞ ህንጻውን ለአደጋ የሚያጋልጥ ሊሆን ስለሚችል ጉዳዩ በባለሙያ ይታይ ተብሎ ጥናት ሲደረግ ከ500 ሺህ ብር ያላነሰ ወጪ እንደሚያስፈልገው ተጠቁሟል፡፡ ወጪው የተጠናው ከአንድ አመት በፊት ስለነበር አሁን ገበያ ላይ ባለው የግንባታና ቁሳቁሶች ዋጋ መሰረት እንደገና ቢሰላ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ በዚህ ምክንያት የምግብ ማብሰያ ክፍሉና ማሽኖቹ ያለ አገልግሎት ከተቀመጡ ከ4 አመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ማሽኖቹ የሪፖርተር ጋዜጣ ከዚህ በፊት እንደዘገበው በርካታ ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎባቸው ለብልሽት በመዳረግ ላይ ናቸው፡፡ የባንኩ መሪዎች ለአማካሪውና ለተቋራጭ ድርጅቶች ምን እያዩ ነበር ክፍያ ሲፈጽሙ የነበረው? ጭስ ማውጫ የሌለው ማዕድ ቤት ሲገነባና በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ በክፍሉ ውስጥ የሚገጠሙ ዘመናዊ የምግብ ማብሰያ ማሽኖች ሲገዙ የነበረው በደመ ነፍስ ነበር ማለት ነው? ክስተቱ አስደናቂ የማዕድ ቤት ግንባታና አስደናቂ የማሽን ግዢ ሆኖ መፍትሄ ሳያገኝ እስካሁን አለ፡፡ ሌላው ህንጻው አውቶማቲክ የኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያ” ማለትም በህንጻው ውስጥ የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ሀይል አስፈላጊ ፍጆታ ለመቆጣጠር የሚያስችል ኮምፒተራይዝድ የሆነ ቆጣቢ ሲስተም በህንጻው ውስጥ መገጠሙን ማኔጅመንቱ ስለህንጻው ያዘጋጀው ሪፖርት ያሳያል፡፡ መቼም የባንኩ ሠራተኞች ስለዚህ ጉድ ሲሰሙ ምን ሊሉ እንደሚችሉ መገመት ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም በአዲሱ ህንጻ ውስጥ ያሉት ሰራተኞች ስራ ለመስራት ኮምፒውተራቸውን ከፍተውና ስልክ እያነጋገሩ ሳለ በየቀኑ የሀይል መቋረጥ እያጋጠማቸው ስራቸውን በአግባቡ ለመስራት በችግር ላይ ናቸው፡፡ እንደዚህ አይነት መቆጣጠሪያ በባንኩ ህንጻ ውስጥ ተገጥሟል ብለው የሚመለከታቸው የማኔጅመንት አካላት ሪፖርት እያዘጋጁ ችግሩ ግን ህንጻው ውስጥ ከተገባ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ መፍትሄ ሳያገኝ እስካሁን ድረስ መቀጠሉ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ብቻ ሳይሆን የአስተዳደር ችግርን የሚያሳይ ነው፡፡ ካለው ችግር የተነሳ የሀይል መቋረጥ ሲያጋጥም ኮምፒውተሮቹ ሳይቆሙ ስራ እንዲቀጥሉ ለማድረግ UPS በተናጠል ለእያንዳንዱ ኮምፒውተር ይግባ ተብሎ ከዛሬ 3 አመት በፊት ጥያቄ ቢቀርብም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሰው ሀይልና የአስተዳደር አገልግሎት ዳይሬክቶሬትና የኢንፎርሜሽን ሲስተምስ መምሪያ ሀላፊዎች ምላሽ በተናጠል ሳይሆን ማእከላዊ የሆነ (Central UPS) በየፎቁ ስላለ ያ ስራ ሲጀምር ችግሩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይፈታል ካሉ ይኸው 4ኛ አመታቸው ሊጀምር ነው፡፡ በዚህ የሀይል መቋረጥ ምክንያት በተፈጠረ ችግር በአገር ውስጥ ባንኪንግ መምሪያ ውስጥ የተከሰተው የዳታ መዘበራረቅ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሲሆን አሁንም ተመሳሳይ ችግር ለላለመደገሙ ዋስትና የለም፡፡ ከሁሉም በላይ ለችግሩ መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል አካል መጥፋቱና ጉዳዩን የያዙትም በጊዜ ባለማጠናቀቃቸው የሚጠይቃቸው ሰው ስለሌለ ሰራተኞች እየተማረሩ ስራም እየተበደለ ችግሩ ከአመት ወደ አመት እየተንከባለለ ይገኛል፡፡ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለውን የሀይል መቋረጥ ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ ያልቻለው በባንኩና በሲመንስ ኩባንያ መሀል በተፈጠረ አለመግባባት ነው ይባላል፡፡ በእርግጥ ችግሩ የተባለው ይሁን ወይም ሌላ ለጊዜው በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የሆነ ሆኖ የባንኩ መሪዎች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ መፍትሄ ለመስጠት አለመቻላቸው ምን እያደረጉ ነው? ያሰኛል፡፡ ምክንያቱም ህንጻው ውስጥ የአገር ውስጥ ባንኪንግ” የሪዘርቭ ማኔጅመንት” የውጪ ምንዛሬና የፋይናንስ መምሪያዎች ይገኛሉ፡ በእነዚህ መምሪያዎች ውስጥ ደግሞ በርካታ ቁልፍ የሆኑ ዳታዎች የሚገኙ ሲሆን ከፍተኛ የሆነና በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ክፍያና ዝውውር (ለአገር ውስጥና ለውጪ) የሚከናወንባቸው ናቸው፡፡ በሚከሰተው የሀይል መቋረጥ የተነሳ በኮምፒውተሮች ላይ እየተከሰተ ያለው መበላሸትና ከጥቅም ውጪ መሆን የየቀኑን ስራ በማስተጓጎል ላይ ሲሆን ቶሎ ቶሎ ሴቭ ካልተደረገ ባንዴ በርካታ መረጃዎችን እስከማጣት ያደርሳል፡፡ አስገራሚው ነገር ችግሩ መቼ መፍትሄ እንደሚያገኝ እንኳን እኛ የባንኩም መሪዎች የሚያውቁት አይመስልም፡፡ ሌላው ህንጻው እያንዳንዳቸው በሰአት 250 ኪ.ግ. የብር ኖት ማቃጠል የሚችሉ ሁለት ኮምፒውተራይዝድ ማቃጠያ ማሽኖች”ህቃሰሽቃስቈሮ”ቄቈቋ) ተገጥመውለታል፡፡ ይሄ ስራ የተሰራው ኢንቺንኮ በተባለ ኃ.የተ. የግል ኩባንያ ሲሆን ካምፓኒውም የብር ማቃጠያ መሳሪያዎችን በማቅረብና በመግጠም ስራ ላይ ተሳትፏል፡፡ እነዚህ የብር ማቃጠያ ማሽኖች በርካታ ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎባቸው የተገዙና የተገጠሙ ሲሆን ከሚሰሩበት የማይሰሩበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ ማሽኖቹ ከበድ ያለ ችግር ሲያጋጥማቸውና ጥገና ሲያስፈልጋቸው ስራው የሚሰራው ከውጪ አገር በሚመጡ ባለሙያዎች ነው፡፡ ባንኩ እስከ መቼ ድረስ እንደዚህ ይቀጥላል? ለሚለው ጥያቄ የባንኩ መሪዎች እንኳንስ መልስ ሊሰጡ ችግሩንም በደንብ ያጤኑት አይመስልም፡፡ ሁለቱ ማሽኖች በድምሩ በሰአት 500 ኪ.ግ. የሚሆን የብር ኖቶችን ማቃጠል ቢችሉም ባለባቸው ችግር ምክንያት ባንኩ የብር ኖቶችን የሚያቃጥለው በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ ብሩን አጅቦ በማጓጓዝ ሌላ ቦታ ሄዶ በሌላ ተቋም ማሽን ነው፡፡”ቦታውን መጥቀሱ አስፈላጊ ስላልሆነ ነው”፡፡ ይሄን ሁሉ መያዣ መጨበጫ የሌውን አሰራር ምን ይሉታል? በርካታ ሚሊዮን ብር እያወጡና እያባከኑ በማንም ሳይጠየቁ መቀመጥ አግባብ ነው? መንግስትስ መቼ ነው በቃ የሚላቸው? ባንኩ ከህንጻው ጀርባ በ1115 ስኩዌር ሜትር ላይ በአንድ ጊዜ 150 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ምድር ቤቱን ጨምሮ ባለ 5 ፎቅ የመኪና ማቆሚያ አስገንብቷል፡፡ ሆኖም ግን ከምድር ወደ ላይ ሲወጣ ዳገታማ በመሆኑና ለመውረድና ለመውጣት የግንባታው አሰራር አስቸጋሪ ስለሆነ ከሁለተኛ ፎቅ ጀምሮ የሚገለገልበት ሰራተኛ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ቦታው 150 መኪናዎችን ማስተናገድ ይችላል ስለተባለና ቦታውም ባዶ ሆኖ ስለሚያዩት ያለውን ችግር ተቋቁመው የባንኩ ደንበኞች በቦታው ለመስተናገድ ቢጠይቁም ከተወሰኑት በቀር አብዛኞቹ አልተፈቀደላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት ደንበኞች መኪናቸውን የሚያቆሙት ከመንገድ ማዶ ሲሆን በተለይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የደመወዝ ቀናት ሲደርስ ከባንኩ ትይዩ ያለው መንገድና ቦታ ስለሚጨናነቅ ደንበኞች መኪና ማቆሚያ አጥተው ሲንከራተቱ ባንኩ ያሰራው የመኪና ማቆሚያ ደግሞ ከ2ኛ ፎቅ ጀምሮ ያለ አገልግሎት ከተቀመጠ ይኸው 4ኛ አመቱን ሊጀምር ነው፡፡ እንደ ማሽኖቹ ሁሉ በርካታ ሚሊዮን ብር አውጥቶ ባለ 5 ፎቅ የመኪና ማቆሚያ አስገንብቶ መኪና እንዳይቆምበት መከልከልና ያለ አገልግሎት አስቀምጦ የባንኩን ደንበኞች ለእንግልት መዳረግ ምን ሊባል ነው? ክፋት? የዋህነት? ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፡፡ የፀጥታ ጉዳይ ነው እንዳይባል ለዚህ ተብሎ ተሽከርካሪ አስተላላፊ/ Vehicles’ Access Control System/ በህንጻው ላይ እንዲገጠም መገዛቱንና መገጠሙን ስለ ህንጻው ያዘጋጁት ሪፖርት ይገልጻል፡፡ የተባለው መቆጣጠሪያ የት ቦታ ላይ እንደተገጠመ እኛን ጨምሮ ማንም የሚያውቅ የለም፡፡ ተገዝቶ ያልተገጠመ ከሆነ ደግሞ በምን ምክንያት ሳይገጠም ቀረ? ተገዛ የተባለውስ ማሽን የት ነው ያለው? ወይስ ገና ሊገጥሙ ያሰቡትን (ምኞታቸውን) ነው ወይ በህንጻው ላይ ተገጥሟል እያሉ ሲገልጹ የነበረው? የሚመለከታችሁ አካላት እዚህም ጋ ችግር አለና በደንብ ብትቃኙት፡፡ ህንጻውን ለማጠናቀቅ ከ18 አመታት ያላነሰ ጊዜ የፈጀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የአሁኖቹ ገዢዎች ዋናው ገዥ ከ9 አመታት በላይና ምክትል ገዢው ደግሞ ከገንዘብ ሚኒስቴር ተሾመው ከመጡበት እ.ኤ.አ. ከ1998 ጀምሮ ስራው ተጠናቀቀ አስከተባለበት እ.ኤ.አ. 2003 ድረስ እንደዚሁም የሰው ሀይልና የአስተዳደር አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ባለው ስራ ላይ በተለይም ከአገር ውስጥና ከውጪ አገር ይገዙ ከነበሩት የህንጻውና የቢሮ እቃዎች ግዢ እጃቸው በቀጥታ አለበት፡፡ ተገጥመዋል ተብለው በቦታው ላይ ስለሌሉት” ተገጥመውም ያለስራ ስለተቀመጡትና ጥቂት አገልግሎት ብቻ እየሰጡ ስላሉት ማሽኖች በርካታ ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ወጥቶባቸው ተገዝተው እየባከኑ ነውና መንግስት ጉዳዩን በደንብ ፈትሾ የሚመለከታቸውን ሀላፊዎች ተጠያቂ ማድረግ አለበት፡፡ ሀላፊዎቹ በሪፖርቱ ላይ የተለያዩ ማሽኖች ተገጥመዋል ያልነው ወደፊት ተገዝተው ይገጠማሉ በሚል ነው ካሉ የበለጠ አስቂኝና አሳዛኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ያልተሰራን ስራ ተሰርቷል ብሎ ሪፖርት ማቅረብ የብቃት ችግር ብቻ ሳይሆን ተአማኒነትንም ጭምር ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ በባንክ ውስጥ ደግሞ ታማኝነት ዋንኛ እሴት ነው፡፡ ይሄ እሴት የሌለው የሥራ መሪ ደግሞ አይደለም ባንክን ከባንክም የአገሪቱን ማዕከላዊ ባንክ ቀርቶ ሌላ አነስተኛ የሆነ ተቋምን እንኳን ሊመራ እንደማይገባ ሁሉንም የሚያስማማ ጉዳይ ነው፡፡ ለእኛ ግን ተራ የሪፖርት አቀራረብ ስህተት አይመስለንምና ከላይ ስለጠቀስናቸው ነገሮች በሙሉ ፀረ-ሙስና በደንብ ቢያየው ጥሩ ይመስለናል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ከህንጻው ኮንትራት”ግንባታና እቃ ግዢ ጋር በተያያዘ በቂ ዶክሜንቶች ሳይያያዙ በነጠላ ቲኬት ብዙ ሚሊዮን ብር ይከፈል ነበር ስለሚባል” ጨረታው ከቫርኔሮ ወደ በርታ ኮንስትራክሽን የተሸጋገረበትና ሁለተኛ ጨረታ የወጣበት ሁኔታ ከተራ ጊዜ ማራዘምና ብክነት ባሻገር በውስጡ የጥቅም ግንኙነት ሊኖረው ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት በአግባቡ ያጣሩት እንላለን፡፡ እንደዚሁም የህንጻው ግንባታ ከተጀመረበት ከ1977 ዓ.ም. ተጠናቀቀ እስከተባለበት እስከ 1995 ዓ.ም. ድረስ የተደረጉት ግዢዎችና የተፈጸሙት ክፍያዎች ከዛሬ 5 ወይም 6 አመት በፊት ከቀድሞው የኦዲት መምሪያና ከተለያዩ መምሪያዎች በተወጣጡ ሰራተኞች በተቋቋመ ኮሚቴ ኦዲት ለማድረግ ቢፈለግም በጊዜው የአስተዳደር መምሪያ ስራ አስኪያጅ”በአሁኑ የሰው ሀይልና የአስተዳደር አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር) እና በአንዳንድ የኮሚቴው አባል እንዲሆኑ በተመረጡ ሰራተኞች መካከል በጉዳዩ ስፋትና ጥልቀት” በፕሮጀክቱ ውስብስብነትና ከዚያ በፊት ኦዲት አለመደረጉን ጨምሮ ረጅም ጊዜ የፈጀ ግንባታ በመሆኑ የሚጠይቀው የኦዲት ችሎታ ከፍተኛ በመሆኑ ኦዲት ማድረግ አንችልም የሚል መልስ በመስጠታቸው በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በጊዜው ኦዲት አልተደረገም፡፡ ከዚያም በኋላ አጠቃላይ ኦዲት በባንኩ በራሱ ወይም በውጪ ኦዲተር ኦዲት ስለመደረጉ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ግን አንድ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም ባንኩ ግንባታውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለረጅም አመታት ለምን ኦዲት ሳያስደርገው ቆየ? በጊዜው የአስተዳደር መምሪያ ስራ አስኪያጅ የነበሩት”የአሁኑ የሰው ሀይልና የአስተዳደር አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር) እና የባንኩ መሪዎች በውጪ ኦዲተር ኦዲት ከማስደረግ ይልቅ ለምን በባንኩ ሰራተኞች ኦዲት ለማስደረግ ከፍተኛ ፍላጎት ሊኖራቸው ቻለ? ምርመራ ያሻዋል፡፡ ከሕንጻው ጋር በተያያዘ ባንኩ እስከ 1999 ዓ.ም. ድረስ ከበርታ ኮንስትራሽን (ዋና ስራ ተቋራጭ) እና ከስለሺ ኮንሰልት አርክቴክቶችና መሀንዲሶች (የህንጻውን ዲዛይን የሰራና ኮንትራቱን የሚያስተዳድር) ጋር በስራው መጠናቀቅና አለመጠናቀቅ መግባባት ላይ ያልተደረሰበት ጉዳይ ነበር፡፡ ባንኩም ህንጻውን ከበርታ ሙሉ ለሙሉ አልተረከበም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በ2000 ዓ.ም. የተለወጠ ነገር ኖሮ ችግሩ ይፈታ ወይም ይቀጥል ለጊዜው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ቴዲ አፍሮ ካአልሆንልህ አለኝ እኔ . . ." የሚለውን ዘፈን የዘፈነው ከፊት ሆኖ እየመራ ላለውና እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ሆኖ ከኋላው ያለውን የአገሩን ልጅ ትቶ መሄድ ለከበደው አትሌት ሲሆን የብሔራዊ ባንክ መሪዎች ግን ዘፈኑን እየዘፈኑ ያሉት በተቃራኒው እነርሱ ከኋላ ሆነው ከፊት ባሉት ሌሎች የአፍሪካ ማዕከላዊ ባንኮች ላይ ለመድረስ እንዲቻል ባንኩን በአግባቡ መምራት ስላቃታቸው ነው፡፡ ገዢዎቹና በዙሪያቸው ያሉት ጥቂት ታማኞችና ታዛዦች የወርቁ ችግር ከመጣና ሁኔታው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ተራው ህዝብ ድረስ ትኩረትን ስቦና ከፍተኛ የወንጀል ስራ መሆኑ ተረጋግጦ ምርመራ ከተጀመረ በኋላ ካወይኔ ጉዴ ፈላ”“““" የሚለውን የአስቴር አወቀን ዘፈን በየቀኑ ለመስማትና ለማንጎራጎር ከመገዳደቸው በፊት ብዙ ተመክረው ነበር፡፡ ግን ካሁሉን አውቃለሁካ ባይነት ላለመስማት ጆሮአቸውን ደፈነው እንጂ፡፡ አስቀድሞ የራሳቸውን የቤት ስራ ቢሰሩ ኖሮ ዛሬ ብሔራዊ ባንክ መሳቂያና መሳለቂያ ባልሆነ ነበር፡፡ ዛሬም ወርቁን የተጭበረበርነው ካበአሰራር ክፍተት ነውካ የሚል መከራከሪያ ይዘው ብቅ ለማለት እየሞከሩ ነው፡፡ የአሰራር ክፍተት መሆኑንማ ሁሉም አውቆታል፡፡ ጥያቄው የበፊቱ አሰራር ሲቀየር እንደዚህ አይነት ቁጥጥርን ክፍት ያደረገና ለሌባ አመቺ የሆነ መመሪያና አሰራርን ማነው ተግባር ላይ እንዲውል ውሳኔ ያስተላለፈው? የሚለው ነው፡፡ መመሪያውንስ የባንኩ ገዢዎች አያውቁትም ነበር ወይ? ካወቁትስ እንዴት በደንብ ሳያጤኑት እንዳለ ወደ አፈጻጸም እንዲገባ ተቀብለው ወይም አጽድቀው የበታች አለቆችና ሰራተኞች ተግባራዊ እንዲያደርጉት አስተላለፉ? ይሄ ጉዳይ ተራ የአሰራር ክፍተት ነው በሚል የባንኩ ገዢዎች ተጠያቂ ከመሆን እንዲያመልጡ ያደርጋቸዋል? አይመስለንም፡፡ የምርመራውን ውጤትና የመንግስትን ፈጣን ውሳኔ እንጠብቃለን፡፡ ይሄ ባንክ የግል ድርጅት ወይም ኩባንያ ቢሆን ኖሮ ባለንብረቱ ወይም ባለቤቱ ተቋሙን በአግባቡ እንዲመሩለት በሀላፊነት ላይ ባስቀመጣቸው የስራ ሀላፊዎች ቸልተኝነት፣ ምንቸገረኝነትና በብቃት ማነስ የተነሳ ይሄ ሁሉ የገንዘብ ውድመትና የአሰራር ብልሹነት ሲከሰት ዝም ብሎ ያያቸው ነበር? በጭራሽ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነበር ጠራርጎ የሚያባርራቸው፡፡ ስለሆነም መንግስትም ሌላ ተጨማሪ ውድመት ከመከሰቱ በፊት በተመሳሳይ መንገድ ለተሰራው ከፍተኛ ጥፋት የባንኩን መሪዎች ተጠያቂ በማድረግ በባንኩ ውስጥ የአመራር ለውጥ ማድረግ አለበት፡፡ በእኛ በኩል ከባንኩ ችግር ጋር በተያያዘ እያቀረብናቸው ያሉት ችገሮች በአብዛኛው ሠራተኛና ሀላፊዎች ዘንድ በደንብ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ተቋሙ ከወደቀበት ቦታ የባሰ ተገፍቶ ገደል እንዳይገባና ተቋሙ ካለበት በሽታ ሙሉ ለሙሉ እንዲድን፣ ሰንኮፉም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከስሩ ተነቅሎ አጠቃላይና ዘላቂ ፈውስ እንዲመጣ በዚህ ገጽ በኩል የበሽታውን ምንጮች፣ እያሳዩ የነበሩትን/ያሉትን ምልክቶችና ያመጡትን/እያመጡ ያሉትን አደገኛ ውጤቶች ለመግለጽ ነው፡፡ በተጨማሪም የጽሁፉ አላማ አንዳንዶች እንደሚያስቡት የባንኩን “ክብር” ለመንካት ሳይሆን የተዋረደውን የባንኩን ክብርና በባንኩ ውስጥ ያለውን የዘቀጠ አሰራርና “ተቆጣጣሪ የሌላቸው” የሚመስሉትን የባንኩን መሪዎች ለማረም እንዲቻል ለመንግስትና ለህዝቡ ያለውን ተጨባጭ ገጽታ ለማሳየት ነው፡፡ እንደዚሁም ለፌደራል ሥነ ምግባርና ለፀረ ሙስና ኮሚሽንና ለጄኔራል ኦዲተር በባንኩ ውስጥ ስላለው የተበላሸ አሰራር አጠቃላይ ሁኔታ በማሳየት የወርቁን ምርመራ ከጨረሱ በኋላ በአጠቃላይ በባንኩ ውስጥ ሊደረግ ስለታቀደው ምርመራ ተገቢውን ጥቆማ ለመስጠት ሲሆን ሌላው የዚህ ጽሁፍ አላማ በሌሎችም ተቋማት ውስጥ በተለይም በፋይናንስ ሴክተር ውስጥ ያሉ ሰራተኞች በየድርጅቶቻቸው ውስጥ ያለውን የሙስና ወንጀልና የተበላሸ አሰራር በማጋለጥ መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንዲወሰድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያርጉ ለማሳየትና ለማበረታታት ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |