| ምነው ለሸማቹ የሚያስብ ጠፋ? |
|
|
| Sunday, 02 March 2008 | |
|
ሁሌ አይሞላምና የእጅ ስልኬ ቋትዋ አልሞላም ነበር፡፡ የሃያ አምስት ብር ካርድ ለመሙላት እንደሌላው ጊዜ ወኔ አልነበረኝም፡፡
ሞባይሌ ገንዘብ ስላልነበራት አማራጭ መፈለግ ነበረብኝ፡፡ የሕዝብ ስልክ ፍለጋ ጀመርኩ፡፡ ያለሁበት ሰው የሚተረማመስበት አፍሪካ ጎዳና ጫፍ ወይም ፍላሚንጎ አካባቢ ነው፡፡ ግራና ቀኝ ማተርኩ የሕዝብ ስልክ አላገኘሁም፡፡ ጊዜው አመሻሽ ላይ ስለነበር በእግሬ ወደ ደንበል ሕንፃ አካባቢ ተጓዝኩ፡፡ በጉዞዬ ግራና ቀኝ የሕዝብ ስልክ እየፈለግኩ ቢሆንም አንድም ሊያጋጥመኝ አልቻለም፡፡ በቃ ከአንድ ሱቅ ጎራ ብዬ እደውላለሁ በማለት እስከ ወሎ ሰፈር አቀናሁ፡፡ በዚህ ጉዞዬም የሕዝብ ስልክ አላጋጠመኝም፡፡ ነገሩ ገረመኝ፡፡ ትላልቅ ዘመናዊ መገበያያዎች ባሉበትና በርካታ ሰው በሚመላለስበት በዚህ ጎዳና ለምልክት የሚሆን አንድ ሕዝብ የሚገለገልበት ቴሌፎን አለመኖሩ “በምን ምክንያት ይሆን?” አሰኘኝ፡፡ ወሎ ሰፈር ስደርስ ጫፍ ላይ አንድ የሕዝብ ስልክ አገኘሁ፡፡ በዚህ ቦታ አራት የሕዝብ ስልኮች አሉ፡፡ ከአራቱ ሁለቱ በካርድ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ሁለቱ ደግሞ ሳንቲም ተጨምሮባቸው የሚደወልባቸው ቢሆኑም አይሰሩም፡፡ በካርድ የሚሰሩት ስልኮች ይስሩ አይስሩ ለማወቅ የግድ ካርድ ያስፈልግ ነበር፡፡ በአካባቢው ግን ይህንን የሕዝብ ስልክ ካርድ የሚሸጥ አልነበረም፡፡ ስለዚህ የግድ ወደ ቴሌ ሴንተር ወይም ወደ ሱቆች መሄድ ነበረብኝ፡፡ አንድ ሱቅ ጎራ ልኩና ስልክ እንደምፈልግ ነግሬ የምፈልገውን ቁጥር ነገርኩት፡፡ ገና 011434 ብዬ ስጀምር በ34 የሚጀምር ስልክ ከሆነ በደቂቃ የምትከፍለው አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ነው አለኝ፡፡ ለምን? 34 እኮ ቃሊቲ አካባቢ ነው አልኩት፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ክልል ውስጥ ስለሆነ የበለጠ አይቆጥርም ብዬ ተከራከርኩ፡፡ መልሱ ግን ካልፈለግክ ተወው የሚል ነው፡፡ ወደ ሌላ ሱቅም ሄድኩ ተመሳሳይ ነው፡፡ መደወሌ ግድ ነበርና ሁለት ደቂቃ አውርቼ 3 ብር ከፈልኩ፡፡ ነገሩ ግን በጣም አግባብ እንዳልሆነ በመረዳት ወደ ሰፈሬ ስጓዝም በ39 በ34 በ35 የሚጀምሩ ቁጥሮችን በመያዝ ለመደወል ስሞክር ባለ መደብሮቹ የሚጠይቁት ክፍያ በደቂቃ አንድ ብር ከሃምሣ ሳንቲም ነው፡፡ የምኖርበት አካባቢ ቃሊቲ ስለሆነ ከዛው ቃሊቲ ከሚገኝ አንድ ሱቅ ጎራ ብዬ ሁለት መቶ ሜትር ርቀት እንኳን ወደሌለው ዘመዶቼ ቤት ለመደወል 011439 ብዬ እንዲደውሉልኝ ስጠይቅ በአንድ ደቂቃ አንድ ብር ከሃምሳ መክፈል እንዳለብኝ ተነገረኝ፡፡ ነገሩ ከንክኖኝ ባደረግሁት ማጣራትም አዲስ አበባ ውስጥ (ቁጥራቸውን በጠቀስኩት የሚጀምሩ ስልኮችን ጨምሮ) የሚጠይቀው የቴሌ ዋጋ ታሪፍ አንድ ነው፡፡ የሚጨመርበትም ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሆኖም በሰበብ በአስባቡ የአገልግሎት ተጠቃሚው ያለአግባብ ክፍያ የሚጠየቅበት ምክንያት ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ያለአግባብ ሸማቹ ላይ የሚጣሉ ክፍያዎች ብዛትም የሚያመለክት ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽንም አገልግሎቱን ለማግኘት መብት ያለው ተገልጋዩን ፍላጎት ለማሟላት ማዕከላዊ በሆኑ ቦታዎች የሕዝብ ስልክ መትከል የማይችል ከሆነ ስልክ የሚያስደውሉ መደብሮች ከታሪፍ በላይ እንዳይጠይቁ ማድረግ ወይም ትክክለኛ መረጃ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ያለው በሞባይል ኔትዎርክ ዝርጋታና መደበኛ ስልኮችን ለማዳረስ እንደሆነ ከተለያዩ መግለጫዎቹ የምንገነዘብ ቢሆንም ብዙሃኑ ሊጠቀምባቸው በሚችሉ ለሕዝብ ስልክ አይነቶችም ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ አልፎ አልፎም ቢሆን የተተከሉት የህዝብ ስልኮች ብልሽትንም ማስተካከል ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በብዙ ቦታዎች የሕዝብ ስልኮች የሉም፡፡ ካሉት ውስጥም አንዳንዶቹ የተበላሹ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ሕዝብ እንዲገለገልባቸው የተተከሉት በካርድ የሚሰሩ የሕዝብ ስልኮች ባሉባቸው አካባቢዎች ካርዶቹ የሉም፡፡ ከሁሉም አቅጣጫ በዋጋ ንረት የተጨናነቀው የሕብረተሰብ ክፍል ቢያንስ በተመጣጣኝ ዋጋ ስልክ የሚደውልበት ቦታ አለማግኘቱ በራሱ ሌላ ራስ ምታት ይሆንበታል፡፡ ከመደበኛ ስልክ ወደ መደበኛ ስልክ ሊቆጥር የሚችለው በ3 ደቂቃ 0.20 ሳንቲም ብቻ እንደሆነ እየታወቀ በደቂቃ አንድ ብር ከሃምሳ መጠየቁ ነጋዴዎች የትርፍ መጠናቸውን ከልክ በላይ ማድረሳቸውን ያሳያል፡፡ ቀድሞ በሱቆች 40 ሳንቲም የሚከፈልባቸው የመደበኛ ስልክ ክፍያዎች አሁን 50 እና 75 ሳንቲም ድረስ መግባታቸውስ ምክንያቱ ምንድነው? ለዚህም አገልግሎት ነጃጅ ጨምሮ ይሆን? ቴሌም ምንም ትርፍ ጭማሪ ሳያደርግ የእነርሱ ጭማሪ ምን የሚሉት ነው? በእነዚህ የስልክ የማስደወል ስራ የሚገኘው ትርፍስ ግብር ይከፈልበት ይሆን? ብሎ መጠየቅም ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በናታን ዳዊት |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |