Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Sep 07th
Home arrow Sections arrow የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ለማጎልበት
የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ለማጎልበት Print E-mail
Sunday, 02 March 2008
Image
አቶ ኃይሉ ውድነህ
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን የሚያስችሉ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ለማጎልበት የሚረዳ የአምስት ዓመት የስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ በማከናወን ላይ መሆኑን የኤጀንሲው የሕግ፣ የኢንተርናሽናልና ሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊ አስታወቁ፡፡
በበልግ ወቅት በሀገሪቱ የሚጠበቀውን የአየር ጠባይ አዝማሚያን አስመልክቶ ኃላፊው አቶ ኃይሉ ውድነህ የካቲት 19 ቀን 2000 ዓ.ም ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንዳመለከቱት በስትራቴጂክ እቅዱ ላይ የተቀመጡትም የአየር ብክለት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ማቋቋም፣ አምስት የሚቲዎሮሎጂ ራዳሮችን መትከል፣ የኦዞን መሳሳትን የሚቆጣጠር ጣቢያ ማቋቋምና አሁን ያሉትን 903 የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን ወደ 1203 ከፍ ማድረግ ናቸው፡፡

በስትራቴጂክ እቅድ ውስጥ ከተካተቱት መካከል የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን ወደተጠቀሰው አሀዝ ከፍ ማድረግ የሚቻለው በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሲሆን ይህም እውን የሚሆነው በየዓመቱ 100 ጣቢያዎችን በማቋቋም መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አሁን ያሉት የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ጣቢያዎች በቂ አለመሆናቸውን ኃላፊው አመልክተው የሦስት ዓመቱ ተከላ እውን ሲሆን ግን የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ያስቀመጠውን መመዘኛ ለማሟላት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የትንቢያ ብቃትን ለማሻሻልና መረጃዎችን በተሻለ ሁኔታ ጠብቆ ለተጠቃሚዎች በቀላሉ ሊያደርሱ የሚችሉ ሁለት ፕሮጀክቶች ተቀርጸዋል፡፡ ለፕሮጀክቶቹም እውን መሆን በዓለም የሚቲዎሮሎጃ ድርጅት በኩል ከፊንላንድ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ተገኝቷል፡፡ ፕሮጀክቶቹም “ኒወሜሪካል ዌዘር ፕሪዲክሺን” እና “ዳታ ረስኪው” ይባላሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል ዳታ ረስኪው ፕሮጀክት ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠሩ መረጃዎችን በኤሌክትሮኒክ ፎርማት አድርጎ ለተጠቃሚዎች በቀላሉ እንዲደርስ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ሁለተኛው ፕሮጀክት ያተኮረው “ስታትስቲካል ሞዴል” በሚል መጠሪያ አሁን እየተሠራበት ባለው የአየር ትንቢያ ቴክኒክ ላይ “ኒወሜሪካል ዌዘር ፕሮዳክሽን” የሚል ተጨማሪ የቴክኒክ ዘዴ መጠቀም ነው፡፡ በዚህ ዘዴ የሚጠቀሙ አገሮች በርካታ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ወደዚሁ እንድትገባ በሚያስችላት መልኩ ነው ፕሮጀክቱ የተቀረፀው፡፡

ኃላፊው እንዳመለከቱት መቶ በመቶ የተሟላ የአየር ትንበያ የትም አገር አይሰጥም፡፡ ይህም ሆኖ ግን የአየር ሁኔታን ለመተንበይ የሚጠቅሙ ሁለት ግብአቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው መሬት ላይ የተተከሉት የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ሲሆኑ ሁለተኛው ግብዓት ደግሞ የከፍታ የአየር ሁኔታ የሚባለው ነው፡፡

መሬት ላይ ያሉት ጣቢያዎች እዛው መሬት ላይ ያሉትን ወይም እስከ ሰው ቁመት ያክል ያሉትን ቴምፕሬቸሩን፣ የትንነትና መሬት ውስጥ ያሉ የሙቀት መጠናቸውን፣ የፀሐይ የቆይታ ጊዜን ወዘተ. ፓራሜትር ይመዘግባሉ፡፡ የከፍታ የአየር ሁኔታ (አፐር ሄድ) በተመለከተ ግን ሬዲዩ ሶንድ የተባለ መሳሪያ የተገጠመለትና ሀይድሮጂን የተሞላበት ባሉን ወደ ላይ ይለቀቃል፡፡ ይህም ከመሬት ወለል እስከ 20 ኪሎ ሜትር ወደ ላይ የሚመዘግቡት ጣቢያዎች የመዘገቡትን ፓራሜትሮች በሲግናል ይሰጣል፡፡

ሌላው የትንበያ ዘዴ ደግሞ “የሚቲዎ ሳት ሰከንድ ጄኔሬሺን” የሚባል የሚቲዎሮሎጂ ሳተላይት መረጃ ሲሆን በዚህም በየአስራ አምስት ደቂቃዎች ሞኒተር ይደረጋል፡፡ ከዚህ አኳያ ኤጀንሲው ከሌሎች ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር ኔትወርክ ሆኖ የመረጃ ልውውጥ ያካሂዳል፡፡ ይህም ማለት አስፈላጊ መረጃዎችን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይወሰዳል፡፡ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ከኤጀንሲው ያገኛሉ፡፡ ምክንያቱም ደመና ድንበር የለውም፡፡

ኤጀንሲው በሀገሪቱ በሚታዩት የአየር ሁኔታ ገጽታዎች ላይ በየጊዜው የቅርብ ክትትል በማድረግ መግለጫዎች እንደሚያሰራጭ አቶ ኃይሉ ጠቁመው ከዚህ አኳያ ከየካቲት አጋማሽ እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ ያሉትን ወራት የሚያካትተው በልግ ለደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ዋነኛ የዝናብ ወቅት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለሰሜን ምሥራቅና ለምሥራቅ ኢትዮጵያ ግን ሁለተኛ የዝናብ ወቅት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የደቡብ ምዕራብና አንዳንድ የምዕራብ አካባቢዎች ከክረምት የአየር ሁኔታ ገጽታ ጋር በተያያዘ በበልግ በመጨረሻዎቹ ወራት ዝናብ ያገኛሉ፡፡

ለበልግ የተተነበዩት የአየር ሁኔታ ገጽታዎችና የውቅያኖሶች የሙቀት መጠን እንደሚጠቁሙት የበልግ ዝናብ በጊዜም ሆነ በቦታ ስርጭት ያልተስተካከለ ነው፡፡ በመጠንም ከመደበኛው ያነሰ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ይሁንና አንዳንድ አካባቢዎች በመጠን ከመደበኛው ጋር የሚቀራረብ ዝናብ ሊኖራቸው ይችላል፡፡

በመሆኑም የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑት የምሥራቅ ትግራይ፣ ምሥራቅ አማራ፣ አፋር፣ መካከለኛው ኢትዮጵያን ጨምሮ ምሥራቅና ደቡብ ኦሮሚያ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ደቡብና ሰሜናዊ ክልሎች እና አብዛኛው ሶማሌ ከመደበኛው ያነሰ ዝናብ የሚኖራቸው ቢሆንም ጥቂት ደጋ ቦታዎች መደበኛ ዝናብ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ምዕራብ ትግራይ፣ ምዕራብ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምዕራባዊ ክልል ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡

በበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ በአብዛኛው የሚጠበቀው ዝናብ ያልተስተካከለና ከመደበኛው በታች ይሆናል፡፡ ስለዚህም የዝናብ ውኃ በማሰባሰብ በደረቅ ሰሞን ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን አሉታዊ ገጽታ በመቀነስ የግብርናን እንቅስቃሴ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ በሰብል አመራረጥ ላይ በተገቢ ጥንቃቄ በማድረግ የእርጥበት እጥረትን መቋቋም በሚችሉ አዝርዕት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በግድቦች ያለውን ውኃ በቁጠባ ለመጠቀም ጥረት ማድረጉ ለተያያዝነው የኢኮኖሚ ዕድገት ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡

ይህ ዓይነቱ መረጃ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲሄድ ያስፈለገው ሊከሰቱ የሚችሉ ሁኔታዎች ላይ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ እንዲያስችል ነው፡፡ ይህም ማለት ብዙ እርጥበት የሚፈልጉ ሰብሎች ከተዘራ ጥሩ ውጤት እንደማይገኝ፣ ነገር ግን ከፍ ብሎ በዝርዝር የተጠቀሱትን ቴክኒኮች በመጠቀም ፕሮብሌሞችን መፍታት እንደሚቻል አቶ ኃይሉ አስረድተዋል፡፡
 
በታደሰ ገብረማርያም
 
< Prev   Next >