| ጡረተኛውና የኑሮ ውድነቱ |
|
|
| Sunday, 02 March 2008 | |
![]() አቶ ሽመልስ አዱኛ ![]() አቶ ኃይሌ ደንዱ ![]() ኰሎኔል ተስፋዬ አበበ የአዲስ አበባ ጡረተኞች ማህበር ለሚያሠራው ሁለገብ ሕንፃ ፕሬዚዳንቱ የካቲት 16 ቀን 2000 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ባኖሩበት ሥነስርዓት ላይ እንደገለጹት የማህበሩ ራዕይና ትልም ይፋ መሆንም ሀገሪቱ ለተያዘችው ፈጣን ልማትና ዕድገት ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ ሥራ የማንኛውም ዜጋ ዋስትናና የኑሮው መሠረት መሆኑን የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታም ሆነ ማህበራዊ ሳይንስ እሳቤ እንደሚያረጋግጡ ፕሬዚዳንት ግርማ ጠቁመው በዕድሜ መግፋትና በልዩ ልዩ ምክንያት በጡረታ ላይ የሚገኙ ወገኖች የዳበረ ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን በማቀናጀት ለተሻለ ሕይወት መንቀሳቀሳቸው በርካታ የሥራ ዕድሎችን ሊፈጥር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ አቶ ሽመልስ አዱኛ የአዲስ አበባ ጡረተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት በበኩላቸው “የጡረተኛ የእርከን ጭማሪ በየሁለት ዓመት እንዲሆን ላቀረብነው ጥያቄ ትኩረት ተነፍጎት በየአምስት ዓመቱ እንዲሆን የሚያደርግ ሕግ ወጥቷል፡፡ የኑሮ ውድነት እስከ 20 በመቶ እያሻቀበ በሚሄድበት ሁኔታ ለጡረተኛው እርከን ላይ መስተካከል ካልተደረገ የማያባራ የችግር ምንጭ ይሆናል፡፡ አሁንም አብዛኛው ጡረተኛ ችግር አስገድዶት በልመና ከመሠማራትና ለአገር ሕልውናና ልማት ያገለገለ ክንዱን ለልመና ከመዘርጋት አያመልጥም” ብለዋል፡፡ የጡረተኛ ችግር በጣም አሳሳቢና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ያሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጡረተኛው በሥራ ላይ ባለበት ጊዜ ለወታደሩ ክፍል የሙሉ ነጻ፣ ለሲቪል የግማሽ ዋጋ ሕክምና መብት እንደነበረው ጡረታ ሲወጣ ግን ይህ መብት እንዳልተከበረለት አስረድተዋል፡፡ ስለሆነም ይህ ዓይነቱ መብት በሕግ እንዲወጣ እንዲከበርም አሳስበዋል፡፡ ከአቶ ሽመልስ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው አዳራሾች አንዳንድ ጊዜ ለሌላ ሥራ ይፈልጋሉ በሚል ችግር እየተፈጠረ አበል ተቀባዩ ይጉላላል፡፡ ስለሆነም ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው ግድ ይለል፡፡ በየክፍለ ከተሞቹ የሚገኙ አንዳንድ የቀበሌ ጽሕፈት ቤቶችም ለጡረተኞች መሰብሰቢያና መጠቀሚያ በቋሚነት እንዲሰጡ ቢደረግ ጡረተኛው የዳበረ ልምድና የዕውቀት ክምችት ባለቤት ለመሆኑ ይህንኑ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ይችላል፡፡ ለማህበሩ ሁለገብ ሕንፃ ማሠሪያ የሚውል 2498 ካሬ ሜትር ቦታ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከሊዝ ነፃ ሰጥቷል፡፡ ለሕንፃው ማሰሪያም 26 ሚሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ ይህም በጡረተኛው አቅም ብቻ መሠራት ስለማይችል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲረዱ፣ የዋስትና ባለሥልጣን ቦርድና መሥሪያ ቤቱ ከወለድ ነፃ ብድር ቢያመቻች ለሥራው መቃናት እንደሚረዳ አቶ ሽመልስ አስትውቀዋል፡፡ አቶ ኃይሌ ደንዱ የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት በሰጡት አስተያየት የኑሮ ደረጃ እንዳሻቀበ፣ የጡረተኛው አበል ግን ከኑሮው ጋር ፍጹም እንደማይጣጣምና ከ1983 ወዲህ ለሠራተኛው ሦስት ጊዜ ጭማሪ ሲደረግ ለጡረተኛው ግን ሳይታሰብለት እንደቆየ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት አስታውሶ ቢጨምርም ችግሩን ይህን ያህል እንደማይቀረፍ አቶ ኃይሌ ገልጸው ይህንንም አነስተኛ አበል ለማግኘት የክፍያ ጣቢያ ችግር እንዳለ፣ ችግሩንም ለመቅረፍ ማህበሩ ጉዳዩ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል በደብዳቤ ጠይቆ መልስ በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ አሰታውቀዋል፡፡ ማህበሩ በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ 22 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ለሚያሠራው ሕንፃ የአፈር ምርመራ የተከናወነ ሲሆን ለሕንፃው ማሠሪያ የሚውል ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚረዳ ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ በመቋቋም ላይ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ኰሎኔል ተስፋዬ አበበ ጡረተኛና የማህበሩ አባል በበኩላቸው “ኑሮ ተወዷል፡፡ ገንዘብም የመግዛት ኃይሉ ወርዷል፡፡ ከዚህ ጋር ደግሞ በዕድሜ ምክንያት አቅምም ደክሟል፡፡ እነዚህ ክስተቶች ሁሉ ተደማምረው በሕይወት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል” ብለዋል፡፡ “የእኔ ጡረታ የጨመረው አስር ከመቶ ነው፡፡ ሕይወት ራሱ ቀድሞውንም ቢሆን ከማገኘው ጋር ፈጽሞ አይጣጣምም፡፡ ጭማሪው ለመብራትና ለውሀ ኪራይ እንኳን አይበቃም፡፡ እንዲያውም የመብራትን ኪራይ ብቻ ልትሸፍን የምትችል ናት የአሁኗ ጭማሪ፡፡ ከዚህ አኳያ የእኔን ሕይወት ሳየው ጭማሪው ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር የተመጣጠነ አንድም ነገር የለውም፡፡” ሲሉ ኰሎኔል ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ የሕንፃውን ዲዛይን የሠሩት አቶ ብርሃነ ሙሣ የሕንፃው የውጫዊ ገጽታ ይዞታው ጥንታዊነትን፣ አሁን ካለንበት የዘመናችን የከተማ ሁለንተናዊ አወቃቀር ጋር ተያያዥነትና ወጥነት እንዲኖረው ተደርጎ እንደተሠራ፣ ሕንፃው አልፎ አለፎ በኢትዮጵያዊነት የሕንፃ ጥበባዊ ተሞክሮ የሚታወቁ እሴቶችን እንዳካተተና የግምባታ ቁሳቁሶችም በአገሪቱ የሚገኙትን ታሳቢ እንዳደረገ አስረድተዋል፡፡ በውስጣዊ ይዞታውም ለማህበራዊና ባህላዊ ክንዋኔዎች የሚረዱ የመገናኛ፣ የመማሪያ፣ የጤናና የመዝናኛ አገልግሎቶች እንዲሁም አልፎ አልፎም ሱቆችም ይኖሩታል፡፡ በሱቆቹም ውስጥ ባህላዊ እሴቶችን የሚያንጸባርቁበት ሲሆን ቅርሳዊ ዕቃዎችም ይሸጡበታል፡፡ ገቢውም ለሕንፃው ማስጠገኛ አገልግሎት ይውላል፡፡ በታደሰ ገብረማርያም |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |